አዴፓን አውጋዡ! የአማራ ምሁርና አክቲቪስት ተግባር የለሽ ባዶ ጫጫታ (ኃይለገብርኤል አስረስ)

ደካማ መንግስት የደካማ ሕዝብ ውጤት ነው የሚል አባባል አለ:: ጠንካራ አመራርም የጠንካራ ሕዝብ ውጤት ነው:: ጠንካራ አመራር ለማዋለድ የምሁራንና የፖለቲካ አክቲቪስቶች ሚና ወሳኝ ነው:: ምሁሩ አልጫ አክቲቪስቱ ወሬኛ ከሆነ ግን ውጤቱ የተገላቢጦሽ ለመሆኑ የአማራ ክልል ፖለቲካ አይነተኛ ማሳያ ነው::
የአማራው ሕዝብ ባለፋት 28 አመታት የተካሄደበትን መጠነ ሰፊ ጥቃት ሊመክት የደፈረ የአማራ ምሁር ይጠቀስ ቢባል የአንድ እጅ ጣት አያክልም:: በተለይ በውጪ ያለው የአማራ ምሁር ከወሬ ያላለፈ ልፍስፍስ ሸርታታ ሃሳብ አልባና ደካማ ለመሆኑ ብዙ ማስረጃ አያስፈልገም:: መደራጀት የማይችል በኢጎ የተወጠረ ግለኛና ጥራዝነጠቅ በመሆኑ አንዲት ትንሽ ተቋም እንኳ ሳይፈጥር በወሬ እንደተጠመደ ዛሬ ላይ ደርሷል::
ይሄን የምለው እንዲሁ ከመሬት ተነስቼ አይደለም:: እዚህ ሰሜን አሜሪካ ከ1997 ጀምሮ አማራን ለማደራጀት በተደረጉት ሙከራዎች ሁሉ ካለማሰለስ ተሳትፌያለሁ:: በተለይ ሕዝባዊ ትግሉ በሃገር ቤት ከመቀጣጠሉ አመት አስቀድሞ በጎምቱ የአማራ ምሁራን አስተባባሪነት በአማራ ስም የተደራጁትን ሁሉንም ቡድኖች በአንድ መለስተኛ ፕሮግራም ስር አሰባስቦ አንድ ጠንካራ የአማራ ድምጽ የሚሆን ድርጅት ለመፈጠር የተደረገው ከፍተኛ ሙከራ ፈጽሞ ምክንያት ሊሆን በማይችል ጉዳይ ብዙ ቢደከሞበትም ሳይሳካ ቀርቷል::
ለዚህ ሁሉ ጥረት መክሸፍ ዋናውና መሰረታዊው ምክንያት ተራ ቡድነኝነት የዝና ጥማት አደባባይ እንደተቋም የመውጣት ፍርሃት አለመከባበር የአማራው ሕዝብን መከራ በቅጡ አለመረዳት ጥቅምን ማስቀደምና አሉባልታ ዋና ዋናዎቹ ናቸው::
በተለይ እንደ ንፍሮ ሶሻል ሚድያ ላይ ተጥዶ ወሬ ሲያቦካ የሚውለው ምሁር ተብዬ በዋናነት የተጠመደው ሕዝባዊና ተቋማዊ አስተሳሰቦችን በማበረስብ ውስጥ ማስረጽ አይደለም:: የግል ተከታይ ማብዛትና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚባል የዝና  ከፍታ ላይ መንጠላጠልን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ በጋራ መክሮ በጋራ ሊቆም አልቻለም::
አብዛኞቹ ምሁር ተብዬ የሳይበር ምድብተኞች ለተቋም ግንባታ በአማራነት ለማደራጀት ብሎም ትግሉን መሪ ሆነው እንዲይዙት ጭምር ከሚታወቁት ውስጥ ያልተጠየቀና ያልተጋበዘ አንድም ሰው የለም:: ሁሉም እዚህ የሶሻል ሚዲያ ፕላት ፎርም ላይ ያለ አላውቅም የሚል ወንድ ይምጣ :: ከወገን ስቃይ ይልቅ የራሱ ዝና ያሰከረው ከንቱ ስለመብዛቱ የየስብሰባዎቹ ቃለ ጉባኤና ሰነዶች በእጃችን አሉ::ወደፊት ይህንን ታሪክ ለሚጽፉት የምንጋራው ይሆናል::
በስደት ያለው የአማራ አቲቪስትና ምሁር ታሪክ ይህ ሆኖ እያለ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሃገር ውስጥ የሚካሄደውን ትግል በማወሳሰብና በመንደር በመከፉፈልም ቀላል የማይባል አደጋን እየሳበ መጥቷል:: በአዴፓ ውስጥ ቀውስ እንዲነግስና አመራሩ እርስ በዕርስ እንዲለያይና ፍጅት እንዲጸናም የራሱን እርኩስ አስተዋጽዖ አብርክቷል::
አሁንም ካለፈው ኪሳራ ሊማር ባለመፍቀዱ ተራ የሳይበር የዝና ሱሱን ለመወጣት በሚሰነዘሩ ሃላፊነት የጎደላቸው ገለጻና ማብራሪያዎች ሌላ ዙር አደጋን እንዳይጋብዝ መስጋት ተገቢ ነው ብዬ እገምታለሁ:: ሕዝባችንም ይህን እረብ የለሽ የፈሪዎች ሁካታ ከቁምነገር ሳይቆጥር ገንቢ ሚና ባለው መንገድ እንዲጏዝ መምከር ያስፈልጋል::
ላለፉት 28 አመታት ብአዴን/አዴፖን በጽናት ታግለነዋል:: ዛሬ ላይ አዴፖን ከነእንከኑም ቢሆን በመደገፍ  የአማራን ሕዝብ ጥይቄ እንዲመልስ ማገዙ ለሕዝባችን ሰላምና ጥቅም ያለውን አስተጽዖ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው:: እውነታው አሁን  ላይ ለአማራው ሕዝብ ከአብንና ከአዴፓ ውጪ ሌላ ተቋም የለም::
በተለይ አዴፓ መንግስታዊ መዋቅር የተቆጣጠረ በመሆኑ ድርጅቱ ለአማራው ሕዝብ የሚጠቅም እንዲሆን ማገዝ በገንቢ ሂስ ማረቅ አውቃለሁ ከሚል አማራ የሚጠበቅ ነው:: ተወደደም ተጠላ ዛሬ ላይ ከአዴፓ ውጪ የአማራውን ሕልውና እታደጋለሁ ማለት ዘበት ነው::
የአማራው የተደራጀ ሃይል ሃገር ውስጥ ካለው ውጪ ምንም ሌላ አማራጭ በሌለበት ሁኔታ ላይ ነው:: የጠላቶች ሴራ አንሶ ሌላ ተጨማሪ በታኝ አጀንዳ ማራገቡ ለማን ሊጠቅም እንደሚችል ያልተረዳው የወሬ ሃይል ጫፍና ጫፍ ቆሞ አዲስ የቅራኔ አዙሪት እንዳይቀስቅስ ያሰግል::
አዴፓ ባጣቸው መሪዎቹ ምትክ አዲስ ሰዎችን ሰይሟል:: አዲሶቹ ተሿሚዎች ያው የድርጅቱ ነባር አባላት ሆነው የቆዩ ካድሬዎች ናቸው:: ማንም ይሁን ምን አዴፓ የመረጠውን ተቀብሎ ማገዝ አለያም አማራጭ ሃይል ፈጥሮ የአማራውን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ መንቀሳቀስ: ሲቻል የተመረጠውን ሁሉ እየዘረጠጡ በክልሉ የአመራር ክፍተት ተፈጥሮ ወደለየለት ቀውስ እንዲያመራ መቀስቀስ አማራ ነኝ ከሚል አይጠበቅም::ያውም ስደት ካለ የአማራ ተወላጅ የሚጠበቅ አይደለም::
አዴፖ ማን እንደነበር ከየትኛው ምንጭ እንደተቀዳ የማያውቅ የለም:: አበበ ሆነ አየለ አዴፖ ውስጥ ያለ ሁሉም ሰው የአንድ ርዕዮት ውጤት ነው::የስራ ምደባው ምንም ይሁን ምን ግልሰቡ ያው አዴፓ ነው:: ይህ ሃቅ ተዘንግቶ በግለሰቦች ስብዕና ላይ የሚደረገው የስም ማጥፉት ርካሽ የባልቴት ፖለቲካ ሊቆም ይገባል:: እውነተኛ አማራ ካለ የሕዝብና የሃገር ጉዳይ የሚያሳስበው ምሁር ካለ ለአዴፓና ለተመራጭ መሪዎቹ አቅጣጫ ይጠቁም ሃሳብ ያዋጣ እስትራቴጂና ስልት ይንደፍ ይህ ነው የሚያስፈልገው:: አለያ እንደ ንፍሮ ሳይበር ላይ ተጥዶ ስድብን ማዝነብ አስነዋሪም በታሪክ የሚያስጠይቅ ነውር ነው::
ድል ለሕዝባችን!!!

3 COMMENTS

  1. ወንድሜ ሀሳብህን በሙሉ እጋራለሁ::ሆኖም አዴፓ ከሰኔ 15 ግድያ ቀጥታ እጃቸው የሌለበትን አማራ ሁሉ ማስፈታት ይኖርባቸዋል::በአዴፓና በጄኔራሉ መካከል ለአማራ መብትና ጥያቄ ዙሪያ ልዩነት የለም:: አማራውን በጅምላ ማፈስ ለኦነግና ህውሀት ስራ ሊያሳካ ይችል ይሆናል:: ነገር ግን አዴፓን የአማራ ህዝብ ድጋፍ ያዳክማል::በዚህ ህዝቡም ድርጅቱም ይጎዳል:: በአስቸኳይ ይፈቱ::የአማራ አንድነት ወቅቱ የሚፈልገው ነው::እያንዳንዱ አማራ በአዴፓ ላይ ጫና ማድረግ
    ይኖርብናል::ድጋፍና ጫና ይሰራል:: አዴፓ እውነተኛ አማራ ሆኖ ወጥቷል::

  2. ወንድሜ ጌታ ይባርክህ ! ለሁላችንም የሚበጀው መደጋገፉ ነው ለሀገራችን አንድነት በጋራ ከቆምን አዴፖ ም ይጠነክራል እባካችሁ አማሮች ከአማራ ነንባይ የጠላት ሴራ ተሸክሞ አራጋቢዎች እራሳችሁን ጠብቁ
    ድል ለኢትዮጵያውያን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.