ይዋል ይደር መባል የሌለበት የብሔራዊ ዕርቅ ጉዳይና መንገዱ (ደግፌ ደባልቄ)

  • የብሄራዊ ዕርቅ ሂደት በረዥም የጊዜ ርቀት ጉዞ ውስጥ የሚከናወን እንጂ በጥቂት ቀናት ሰብሰባ ተጀምሮ በጭብጨባ የሚጠናቀቅ የቀናት ክንውን አይደለም፡፡ 
  • የሂደቱ ዋነኛ መርህ ጣት መጠቋቆም ሳይሆን በየጊዜው እያመረቀዘ ያገሪቱን ጤና የሚያውከውን ቁስል በጋራ ከፍቶ የማየትና ፈውሱንም አብሮ ባንድነት የመፈለግ ጥረት ነው፡፡
  • ማንኛውም ለአገራዊ ዕርቅ የተቋቋመ አካል ለስራው ስኬት የሚያስፈለጉት በርካታ የአስተዳደር የባጀትና የሰው ኃይል ግብአቶች አሉ፡፡ከሁሉም በላይ በዋናነት ለተልዕኮው መሳካት አስፈላጊው ግን ከቀና ልቦናና ንፁህ አገራዊ ስሜት የሚመነጭ ህዝባዊ ተሳትፎና ድጋፍ ናቸው፡፡    

ኢትዮጵያ ባንድ ወቅት ከደረሰባት ህመም በወጉ ሳታገግም ሌላ ደዌ በላይ በላዩ ተነባብሮ( layers of injustice) እያጎሳቆላት በህመም ላይ ህመም ተሸክማ ከዚህ አሁን ካለንበት የትኩሳቱ መጠኑ እጅግ ባጣም ካሻቀበ የጤና መታወክ ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡‘አገርም እንደ ሰው’ እንዲሉ ሆነና አገር በህመም ላይ ነች፡፡በክፉ ደዌ እንደ ሚሰቃይ ሰው ሁሉ የአገርም ደዌ በጊዜው ታውቆ መድኃኒት ካልተጨመቀለት ውሎ ሲያደር እየበረታ ይሄድና መፈወሻው ከጤናአዳምና ከዳማከሴ አቅም በላይ ወደ ሚሆንበት ጥግ ሊዘልቅ ይችላል፡፡በመሆኑም‘ ሳይቃጠል በቅጠል’ እንዲሉ ተማክሮ ተነጋግሮና ተደማምጦ መፍትሄ መሻት ወቅቱ ከሚጠይቀው አገራዊ ኃላፊነቶች ውስጥ ዋነኛው ነው፡፡

እንደዚህ ያለ አገራዊ ውጥንቅጥና ፈተና በአገራችን ኢትዮጵያ ላይ ብቻ የሚታይ ወይንም የታየ ጉዳይ አይደለም፡፡ በርካታ አገሮች ዛሬ በእኛ ላይ ከተጋረጠው ፈተና ጋር የሚመሳሰል አንዳንዴም የሚበልጥ ከባድ አደጋ ተጋርጦባቸው ነበር፡፡ባህላዊ እሴቶቻቸውን እውቀታቸውን ሆደ ሰፊነታቸውን ታጋሽነታቸውንና አስተዋይነታቸውን አሰባስበው በጋራ ለችግሩ መፍትሄ መፈለግ የቻሉት አገሮች ፈተናውን ተቋቁመው መሰናክሉን ተሻግረው በአገራዊና ህዝባዊ አንድነት ላይ የተመሰረተ የዲሞክራሲ ስርዓትና ዘላቂ ሰላም መገንባት ችለዋል፡፡ይህንን ማድረግ የተሳናቸው ደግሞ እንደ አገር ህልውናቸውን አጥተው መበታተን ብቻ ሳይሆን ወደ እዚህ መበታተን ለመድረስም ክፉ እልቂት ደርሶባቸዋል፡፡ያልተሳካለቸውን እንተውና ተሳክቶላቸው ወደ ዘላቂ ሰላምና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ያመሩትን ስንቃኝ ደቡብ አፍሪካ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፋ እናገኛታለን፡፡ከዚህም የተነሳ ዛሬ ከራስዋ አልፋ አፍሪካውያን(ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ)ስደተኞችን ታስተናግዳለች፡፡ለሃያ ሰባት አመታት በእስር የቆዩት የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ከተፈቱ በኃላ ደቡብ አፍሪካ በርካታ አስፈሪና አስጊ የሚባሉ ሁኔታዎች ተጋርጠውባት ነበር፡፡ይሁን እንጂ ይህንን ያጠላባትን አደገኛ የመተላላቅ ዳመና ገፍፋ አሁን ካለችበት አገራዊ ሰላም ለመድረስ በቅታለች፡፡ ታዲያን እንዴት ብታደርግ ነው ደቡብ አፍሪካ ከዚህ ስኬት ልትደርስ የቻለቸው? ኢትዮጵያስ ከዚህ ምን ትማራለች?ለሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ ናቸው የምላቸውን ሃሳቦች አጋራለሁ፡፡

የተጋረጠውን ስጋት በተመለከተ የደቡባዊቷ የኬፕ ከተማ የአንግሊካን ቤተ ክርስትያን ጳጳስ የነበሩትና በኃላም ፕሬዝደንት ኔልሰን ማንዴላ የእውነትና የእርቅ ኮሚሺኑ ሊቀ መንበር አድርገው የሾሙዋቸው አቡነ ዴዝመንድ ምፒሎ ቱቱ ሲናገሩበወቅቱ ማንኛውንም በደቡብ አፍሪካ ጉዳይ ሰከን ያለ አመለካከት ያለውን ሰው እንኳን ‘የደቡብ አፍሪካ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?’ ብለህ ከጥቂት አመታት በፊት ብትጠይቅ የሁለም መልስ ተመሳስይ ነበር የሚሆነው፡፡ይኸውም እልቂት በአገራችን ይከሰታል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በደም ጎርፍ ትታጠባለች የሚል ነበር የሚሆነው፡፡እውነቱ ግን ይህ አልሆነም፡፡ ይልቁንም የደቡብ አፍሪካ ህዝብ በመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለመሳተፍ በተጠማዘዘ ረዥም ሰልፍ ለሰአታት ያለመታከት ቆመ፡፡ይህንንም ምርጫ ተከትሎ ፕሬዝደንት ኔልሰን ማንዴላ የመጀመሪያው በዲሞክራሲያዊ ስርአት የተመረጡ ፕሬዝዳንት ሁነው ሜይ 10 1994 ( እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር) ቃለ ምህላ ፈፀሙ፡፡” እንደ ሚታወቀው ደቡብ አፍሪካም ይከሰታል ከተባለው አደጋ ተርፋ ዛሬ መንግስት ዲሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ብቻ የሚተካካባትና ሁሉን የሚያሳትፍ የዲሞክራሲ ስርዓት የሚተገበርባት አገር ሁናለች፡፡ይህ በአጋጣሚ ወይንም የተአምራዊ ክስተት ውጤት አይደለም፡፡ ይልቁንም መሪዎችዋና ያገሪቱ ህዝብ ወደ እርቅ ሰላምና የዲሞክራሲ ጎዳና ለመሸጋገር ባሳዩት ቁርጠኛ ተሳትፎ የተገኘ ነው፡፡

የመሪዎች ምሳሌነት በእርቅ ፤ ሰላምና አብሮ መኖር ላይ

ማርቲን ሉተር ኪንግና ዕርቀ ሰላም  

 “ይቅር ባይነትና ዕርቅ ሲያስፈልገን የምናደርገው በሌላ ጊዜ ደግሞ የምንተወው ሳይሆን ሁሌም አብሮን መኖር ያለበት   የአስተሰሳብ ባህርይ ነው”

    “Forgiveness (Reconciliation) is not an occasional act, it is a constant attitude.”

— ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ

በአለማችን ታሪክ ውስጥ የአንድ አገር መሪ “ ታላቅነት” የሚመተረውና ብቃትም የሚለካው በተለምዶው በጦር አመራር  በውጊያ ውሎ ስኬትና ከጦር አውድማ ጋር በተቆራኘ ጀግንነት ነው፡፡“ታላቁ አሌክሳንደር” “ታላቁ ናፖልዮን”  ጋንግስ ከሃን ወዘተ ታላቅነታቸውን የተጎናፀፉት በጦር ሜዳ ውሎአቸው ባስመዘገቡት ገድል በፈጁት ሰው ብዛት ባቃጠሏቸው መንደሮችና ቅዬዎች ስፋት ነው፡፡ይህ እስከ ዛሬም የምንታዘበው በአለማችን የሚታይ “ጀግንነትን” ጦር ከመምራት ህይወት ከማጥፋትና ንብረት ከማውደም ጋር አያያዞ የመመዘን ባህል ነው፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ለሰላም ላብሮ መኖር ለመቻቻልና ለእርቅ ራሳቸውን ያስገዙ መሪዎች ደግሞ  እንደ“ ደካማ” “ፅናት የሌለው” ወዘተ እየተባሉ ባንዳንዶች ይተቻሉ ይከሰሳሉ፡፡ ለምሳሌ ዛሬ በምድረ አሜሪካ ትልቅ ቦታ የተሰጣቸውና በየአመቱ ጃንዋሪ 20 የመታሰቢያ ቀን የሚከበርላቸው የጥቁሮችን የነፃነት ትግል ያስተባበሩትና ያቀናጁት ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር በሰላሳ ዘጠኝ አመት እድሜአቸው በነጭ አሸባሪ ጥይት ህይወታቸው ከማለፉ በፊት “ ደካማ” ናቸው “ ከነጮቹ ወግነው የጥቁሮቹን ትግል ከድተዋል” የሚሉ በርካታ ክሶች ይሰነዘሩባቸው ነበር፡፡ ይህም የሆነበት አንዱ ምክንያት እርሳቸው በፅናት የቆሙለት የሰላማዊ ትግል መንገድ ( non violent struggle) በተወሰኑት ጥቁሮች በተለይም በማልኮም ኤክስና በወቅቱ(Black Panthers – ጥቁር ግስላ) በመባል በሚታወቀው ቡድን በኩል ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነው፡፡

እነኚህ ወገኖች ነፃነት በሰላማዊ ትግልና በማስታመም ብቻ ሳይሆን ማልኮም ኤክስ ባንድ ወቅት እንዳሉት “ሁሉንም የትግል ስልቶች ያካተተ (by all means necessary)” ሲሆን ነው ውጤት የሚያስገኘው ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ ለሰላም ባላቸው ፅኑ አቋም ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ አሜሪካ በቪየትናም ላይ በወቅቱ የምታካሂደውን ጦርነት በመቃወም April 4 1967 ( April 4, 1968 ተገደሉ ) አቋማቸውን ይፋ ካደረጉ በኃላ ከፍ ያለ ቁጥር ያላቸው ከጥቁሮቹም ከነጮቹም በኩል ይደግፏቸውና ያወድስዋቸው የነበሩ ሸሹዋቸው፡፡ ይህንን ንግግር ሁሌም ተገኝተው በሚሰብኩበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባደረጉ በአንድ አመት ውስጥ ከነጭ አሸባሪ በተተኮሰ ጥይት በአሜሪካ ደቡብ ምዕራዊ ከተማ ሜምፍስ ህይወታቸው አለፈች፡፡እኚህ ሰው የህይወት ዘመናቸውን ሁሉ ዘር የቆዳ ቀለም ኃይማኖት ሳይለይ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት በእርቅ መንፈስና በሰላም እንዲኖሩ ታግለዋል፡፡ በመሆኑም ባንድ ወታደራዊ ገድል አንድ የጦር መሪ ከሚያስመዘግበው ድል የበለጠና ታሪክ የማይዘነጋው በሁሉም ሰላም ወዳድ የሰው ልጆች ህሊና ውስጥ ለዘልአለም የሚታወስና የሚዘከረ ቅርስ ትተው አልፈዋል፡፡ ለዚህም ስራቸው በ1964  በሰላሳ አምስት አመት ዕድሜአቸው የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡

ኔልሰን ማንዴላና ዕርቀ ሰላም

የዚህ ስኬት ምንጩ ባንድ በኩል ደቡብ አፍሪካ አስተዋይነትን ይቅርባይነትን ሆደ ሰፊነትን ከሁሉም በላይ ለአገር አሳቢነትንና ለሁሉም ዜጎች እኩልነት መቆምን መርህ ያደረጉ እንደ ኔልሰን ማንዴላ ያሉ መሪዎችን በመታደልዋ ነው፡፡ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ በአገር መሪነታቸው ደቡብ አፍሪካ ወደ በቀልና ጥፋት ጉዳና እንዳትሄድ የሰጡት አመራር በመላው አለም የተመሰከረላቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከመሪነት ኃላፊነታቸው ባሻገር በግል ምሳሌነታቸው ደቡብ አፍሪካ ከታሪክ ቁስልዋ እንድታገግምና ወደ ተሻለና ሁሉን ዜጎችዋን ወደ አቀፍ ጎዳና እንድታመራ ያደረጉት አስተዋፅኦ በመላው አለም በምሳሌነት ከፍ ብሎ የሚጠቀስና የሚወደስ ነው፡፡በእርግጥ በወቅቱ ደቡብ አፍሪካን ሊያጋጥማት ከሚችለው ፈተና ጥልቀትና ስፋት አኳያ ስናስብ በአንድ ግለሰብ አዕምሮአዊ ስነ ልቦናዊና መንፈሳዊ ብቃትና ጥንካሬ ብቻ ፈውስ የሚያገኝ አይደለም፡፡ይሁን እንጂ የፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ትከለ ሰውነት ከቂም በቀል  መንፈስ ራሳቸውን ነፃ አድርገው ራሳቸውባንድ ወቅት እንደተናገሩት “ለረዥም አመታት ከቆየሁበት እስር ቤት ወጥቼ ነፃነቴን ለመጀመር ወደ እስር ቤቱ በር ሳመራ አንድ ከራሴ ጋር የተስማማሁበት ጉዳይ ጥላቻንና ምሬትን እዛው እስር ቤቱ ውስጥ ትቻቸው ካልወጣሁ ሁሌም በእስር እንደምኖር ተገነዘብኩ፡፡” እንዳሉት ለጥላቻና ለበቅል በሩን ቢከፍቱ ኖሮ ደቡብ አፍሪካ ሊደርስባት የሚችለው ደም መፋሰስና እልቂት ዘግናኝ ሊሆን እንደሚችል መገመት ብዙም አያስቸግርም፡፡

ከኔልሰን ማንዴላ የነጠላ አመራር ባሻገርም በፀረ አፓርታይድ ትግል ወቅት ትግሉን በግንባር ቀደምትነት የመራው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ(African National Congress) ሌሎች ብቃትና ራእይ ያላቸው አንጋፋና ላገር አሳቢ መሪዎች ማፍራት መቻሉም ፕሬዝዳንቱን ማገዝ ብቻ ሳይሆን አገሪቱን ከጥፋት በማዳኑ ረገድ ጉሉህ ድርሻ አለው፡፡ በመሆኑም ከፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ባሻገር  ታዲያን ከመዲናችን አዲስ አበባ በ5396 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው አገረ ደቡብ አፍሪካ አገራችን ምን ትማራላች? እርግጥ ነው የደቡብ አፍሪካ የፖለቲካና ማህበራዊ ስብጥር በብዙ መልኩ ከአገራችን የተለየ ነው፡፡ በመሆኑም የምንቀይሰው የመፍትሄ አውራ መንገድም በአገራችን ታሪካዊ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ባህላዊ እውነታ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፡፡ ይህ ማለት ግን ከኛ በመጠኑም ቢሆን ራቅ ብላ ከምትገኘው እህት አገር ከደቡብ አፍሪካ የምንቀሰመው ልምድ የምንማረው ስልት የለም ማለት ግን  አይደለም፡፡

የእርቅ ጎዳና በአገራችን ለምን?   ባገራችን “ይቅር ለእግዜአብሄር” መባባል የተለምደ ነው፡፡ የተለያዩ ያገራችን ማህበረሰቦች የየራሳቸው የሆኑ የእርቅ ስነ ባህሎች አሉዋቸው፡፡ ይሁን እንጂ “ ይቅር ለእግዜአብሄር” ከመባባል በፊት ይቅር ባዩና ይቅርታ ጠያቂው ከዚህ ሰላምን ካሳጣቸው ሁኒታ ያደረሱዋቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አውጥተው መነጋገርና መደማመጥ ይኖርባቸዋል፡፡ በጭፍን ጉዳዩ በግልፅ ሳይታወቅ “ ይቅር” መባባል ውጤቱ ‘ አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ’ ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህ ነው በተለያዩ አገሮች የዕርቅ ኮሚሽኖች ሲስየሙ በስማቸው ላይ እውነት (Truth) የሚጨመረው Truth and Reconciliation Commission- የእውነትና የዕርቅ ኮሚሽን፡፡ የአገራዊ እርቅ ዋነኛ ሂደት እውነቱን መናገር ነው፡፡ይህም ማለት ግፍ የተፈፀመበትም ሆነ ግፉን የፈፀመው ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ እውነቱን መናገር ለግልና ለአገራዊው ቁስል መሻር መሰረት ስለ ሆነ ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በብዙ የፖለቲካ ትርምስ ውስጥ ያለፉና ደም ያፋሰሱና ደም ያቃቡ ግጭቶችና ጦርነቶች በተካሄዱበት አገር የዕርቅና የሰላም ጎዳና አማራጭ መንገድ ሳይሆን ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ በየጊዜው ብቅ ያሉ ኢፍትሃዊ ስርዓቶች ጥለውት ያለፉት   የተነባባረ በደል ለረዥም ጊዜ ሲንከባለል በመቆየቱና ስር ሳይሰድና አገራዊ ታዛችንን ሳይቦረቡር መፍትሄ ባለማግኘቱ ይኸው ዛሬ በመሰሶው ላይ ተጠምጥሞ ብቸኛ ቤታችንን እየገዘገዘና እያወላዳ ይገኛል፡፡ የአገራዊ እርቅ ጎዳና ማለት የተፈፀመውን በደል መርሳት ወይንም ከታሪክ ማህደር ፍቆ ማጥፋት ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ተቃራኒው ነው እውነቱ፡፡ እርቀ ሰላም ማለት ያለፈውን በትክክል ነቅሶ ማወቅና ትውልድም በሚገባ እንዲገነዘበውና ከማድረግ ባሻገር አገራዊ እርቅ ማለት የተፈፀሙትን በደሎች በእውነት ላይ ተመስርቶ እውነቱንና ተረቱን በለየ መንገድ ማውጣትና በአግባቡ ለማሰብና ለማስታወስ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ማለት ነው፡፡  ይህ ሲደረግ ነው እንዲህ አይነቱ ድርጊት ዳግም እንዳይከሰት ትውልድን ማስተማርና የሚያደረሰውን በቶሎ የማይሽር ጠባሳ ተገንዝቦ ጥንቃቄን አስተዋይነትን መከባበርንና ልዩነቶች ከሃሳብ ግጭት አልፈው ወደ ደም መፋሰስ እንዳያመሩ ማስተማርና ትወልድንም በዚህ አይነቱ አስተምህሮ መቅረፅ የሚቻለው፡፡

ምን አይነት የአገራዊ ዕርቅ ሂደት? 

አንዳንድ ወገኖች ስለ እርቅ የተዛባ እውቀት ከመያዛቸው የተነሳ የዕርቅ ሂደትን በሁለት ወይንም በሶስት ቀን ከሚካሄድ ስብሰባ ጋር ያያይዙታል፡፡የእርቅ ሂደትና ስብሰባ መሰረታዊ ልዩነት ያላቸው ከመሆኑም ባሻገር አገራዊ እርቅ በሁለትና በሶስት ቀናት ስብሰባ መደምደሚያ ላይ በሚደረግ ጭብጨባ የሚረጋገጥ ሳይሆን ረዥም ጊዜ ሲያስፈልግም እስከ አንድ ትውልድ ዘመን ወይንም ከዚያም በላይ ሊዘልቅ የሚችል ሂደት ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ይህ ሂደት የሁሉም የአገሪቱን ዜጎች ቀና ተሳትፎና አስተዋፅኦ በከፍተኛ ደረጃ የሚሻ አገራዊ ኃላፊነት ነው፡፡ብሄራዊ እርቅ አንድ አገርና ህዝቦችዋ እስከ ዛሬ መፍትሄና መድኃኒት ሳይፈልጉለት የኖሩትን ደዌ በጋራ  የሚጋፈጡበት ሂደት ነው፡፡ የሂደቱ ዋነኛ መርህ ጣት መጠቋቆም ሳይሆን በየጊዜው እያመረቀዘ ያገሪቱን ጤና የሚያውከውን ቁስል በጋራ ከፍቶ የማየትና ፈውሱንም አብሮ ባንድነት የመፈለግ ሂደት ነው፡፡ እዚህ ላይ ሊታወቅ የሚገባው ዋነኛ ጉዳይ ይህ ሂደት ቀላልና በያዝ ለቀቅ የሚካሄድ ሳይሆን ሙሉ ትኩረትንና አቅምን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህን በሚገባ ያገናዘበና ከግምት ውስጥ ያስገባ ሂደት ቁስሉን ከፍቶ ማየት ብቻ ሳይሆን ቁስሉ በሚገባ እንዲሽር አቅምና ብቃት ይኖረዋል፡፡ ከዚህ ስንነሳ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት አይነት ማለትም የአጭር ጊዜና የረዥም ጊዜ የዕርቅ ሂደት ያስፈልጋል፡፡ የአጭር ጊዜ የእርቅ ሂደቱ ማተኮር ያለበት በፖለቲከኞና በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ሲሆን የረዥም ጊዜ ሂደቱ በሰፊው አገራዊ በሆነና ረዘም ላለ ጊዜ ከብሄራዊ የእርቅ ኮሚሽኑ የሶስት አመት የስራ ኃላፊነት ዘመን ካበቃም በኃላ በሰላም ሚኒስቴር ስር አንድ አካል ተቋቁሞለት መቀጠል የሚገባው ነው፡፡

መግባባትና ስምምነት በፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎች መካከል

ኢትዮጵያ ውስጥ በቅርብ ጊዜ በተፈጠሩትም ሆነ እድሜን ካስቆጠሩት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ከሃሳብ ያለመስማማት የተነሳ ሰላማዊ ፍትጊያ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ያለፈና ደም ያፋሰሱ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ ይህ ጎራና ወገን በለዩ የአንድ አገር ልጆች መካከል የተፈጠረው ሰላማዊ ያልሆነ አምባ ጓሮና ደም መፋሰስ ከፖለቲከኞቹ አልፎ ቤተሰብንና ሲዘልቅም ማህበረሰብን የጨመረ ሲሆን አገራዊ እንድምታም ያለው ነው፡፡በመሆኑም ቂም በቀልንና  ቁርሾን የቋጠሩ ጨው የማይበዳደሩና እሳት የማይጫጫሩ ቤተሰቦች ማህበረሰቦች የፖለቲካ መሪዎችና ተኮራረፈውና የየራሳቸውን ጥግ ይዘው ባሉበት ሁኔታ ውስጥ የረዥም ጊዜ እቅድ ያለውን ብሔራዊ የዕርቅ ሂደት ማስጀምርና ወደ ታቀደለት ውጥን እንዲጓዝ ማድረግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ይህም በመሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎቻቸውለአገር ሲባል በአገራዊ የእርቅ ጎዳና ለመጓዝ መመረጣቸውን በግልም ሆነ በድርጅት ደረጃ ይፋ ማሳየትና ለዚህም ምስክር ሊሆኑ የሚችሉ ተምሳሌታዊ ( symbolic act) ተግባሮችን ለተከታዮቻቸውና ለኢትዮጵያ ህዝብ በግልፅ ማሳየት ቢፈቅዱ ለረዥም ጊዜው የአገራዊ እርቅ ሂደት ከፍ ያለ በጎ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡  መግባባትና ስምምነት ሲባል ግን የፖለቲካ ድርጅቶች በመካከላቸው ያሉትን የርዕዮተ አለምና የአስተሳሰብ መስመሮች አክስመው ሲያበቁ ልሙጥና አንድ ወጥ ድርጅት ይሁኑ ማለት አይደለም፡፡ማድረግ ቢችሉ እሰየው ነው፡፡ ይህ እዚህ የቀረበው ሃሳብ ግን ለረዥም ሂደቱ የአገራዊ ዕርቅ ጉዞ አመቺ ሁኔታ ከመፍጠር ጋር የተያያዘ እንጂ የፖለቲካ ልዩነትን አጥብቦ በጋራ መስራትን የሚመለከት አይደለም፡፡ በጋራ የመስራትን ሂደት የሚመርጡ ድርጅቶች በራሳቸው ጊዜ ተገናኝተው በሚያስማሙዋቸው ጉዳዮች ላይ መነጋገርና የሚሄዱበትን መንገድ መቀየስ የራሳቸው ምርጫ ነው፡፡

የረዥም ጊዜ የብሔራዊ ዕርቅ ሂደት

ከፍ ሲል የተቀመጠው በፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎች መካከል መፈፀም ያለበት የአጭር ጊዜ የዕርቅ ሂደት በተሳካ ሁኔታ ከተፈፀመና የፖለቲካ ድርጅቶችም በማያወላዳ ሁኔታ ለዚህ በፅናት መቆማቸውን ካሳዩ የሚኖረው እንድምታ ትልቅ ተሰፋ ሰጪና በብሄራዊ እርቅ ላይ የተመሰረተ ዘላቂ አገራዊ ሰላም ለመገንባት ለሚደረገው ስራ ስኬት የሚኖረው ድርሻ ትንሽ አይደለም፡፡በዚህ በተከፈተው በር ገብቶ የረዥም ጊዜ የእርቅ ሂደቱን ለማሳካት  ግን ሂደቱን የሚያሰፈፅመው አካል የሚከተሉት አበይት አቅሞችና ሊኖሩትና የኮምሽኑ አቅምና ኃላፊነትም በግልፅ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ኮሚሽኑ በተገደበለት የስራ ዘመን የሚያተኩረው በየትኞቹ የኢትዮጵያ ታሪክ ዘመናት ነው? የሚለው ጥያቄ በግልፅ ሊመለስ ይገባዋል፡፡ከዚህ ተነስተን የአገሪቱን ታሪክ በሶስት የጊዜ ምዕራፎች ማለትም ቅድመ 1974 እኤአ ከ1974- 1991 በመጨረሻም ከ1991- እስከ አሁን ብንከፍል የትኛው የታሪክ ምዕራፍ የኮሚሽኑ ትኩረት እንደሚሆን በማያሻማ ሁኔታ መቀመጥ አለበት፡፡ይህ ከተወሰነና መልስ ካገኘ በኃላ ነው የኮሚሽኑን የስራ ሸክም መገመትና ይህንንም የስራ መጠን ለመወጣት ምን ያክል  የገንዘብ የሰው ኃይልና ጊዜ እንደሚያስፈልግ መወሰን የሚቻለው፡፡የረዥም ጊዜ የአገራዊ ዕርቅ ሂደቱ በርካታ አስተዳደራዊና ሎጅስትካዊ ብቃቶች ከሚያስፈልጉት አቅሞች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን ሂደቱን የሚመሩት ግለሰቦች መንፈሳዊ ስነ ልቦናዊና አእምሮአዊ ዝግጅትና ብቃት በጥብቅ የሚያስፈለግ ነው፡፡የአገር ቁስልን ገልጦ ለማየትና ጠረን የማሽተትና ይህንን የአገር ቁስል ከፖለቲካ ስሌት ውጪ ተገንዝቦ ህመሙን ለመታመም ፈውሱንም ለመሻት ፅናትና የማይናወጥ እምነት አስፈላጊ መለኪያ ነው፡፡

ባህላዊ የእርቅና የሰላም እሴቶችን ለአገራዊ የዕርቅ ሂደት ማዋል

ኢትዮጵያ በርካታ ዘመናትን የተሻገሩ ባህላዊ የእርቅና ግጭትን የመፍታት  እሴቶች ያላት አገር ናት፡፡ እነኚህን እሴቶች በዚህ አገራዊ የእርቅ ሂደት ውስጥ መጠቀም ለሂደቱ አገራዊ መፍትሄን በተግባር ላይ ከማዋል ባሻገር ያንዱን ማህበረሰብ እሴት ለሌላው ለማስተዋወቅና ከተለያዩ ማህበረሰቦች የተውጣጡ እሴቶች በጋራ ቅኝት ተባበረው በተግባር ላይ የሚውሉበትን መንገድ ያመቻቻል።በተጨማሪም ይህ ያገር ሃብት በአዲሱ ትውልድ መንፈስ ውስጥ እንዲሰርፅና ለመጪው ትውልድም በሚገባ ተፅፎና ተጠርዞ እንዲተላለፍ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡

ማጠቃለያ 

ጁላይ 18፣ 1918 እኤአ ማለትም ልክ የዛሬ 101 አመት በደቡብ አፍሪካ የትራንስካይ ግዛት የተወለዱት ኔልሰን ማንዴላ በህይወት ዘመናቸው ውስጥ ሁለት ታላላቅ ቅርሶችን ጥለው አልፈዋል፡፡አንደኛው ለነፃነት ባሳለፉት የትግል ዘመን ውስጥ ትግላቸው ለራሳቸው የግል ነፃነት ወይንም ዝና ሳይሆን በአፓርታይድ ሰንሰለት ታስሮ ለሚማቅቀው የደቡብ አፍሪካ ህዝብ መሆኑን በግልፅ አስመስክረዋል፡፡ ሁለተኛው ለአገር ዘላቂ ሰላምና ለአብሮ መኖር ከአገራዊ እርቅ ባሻገር የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ የሚያስችል መንገድ እንደሌለ አስምረዋል፡፡ ይህ ለታሪክ ያስተላለፉት አሻራ ነው ዛሬ በመላው  አለም በምሳሌነቱ የሚጠቀሰውና በሞዴልነቱም አገራት የሚጠቀሙበጥት፡፡ እኛም በትግል ዘመናቸው ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር የማይዘነጋው ቁርኝት ያላቸው ኔልሰን ማንዴላ ትተውት ካለፉት የተወደሰ ቅርስ የምንማራቸው በርካታ ፍሬ ነገሮች አሉ፡፡ ከእነኚህም አንዱና ዋነኛው የይቀር ባይነትና ለእርቅ የተገዛ መንፈስ ማጎልበትን ነው፡፡

እስከ ዛሬ ባለው ታሪካችን ውስጥ እርስ በእርስ በመጠፋፋትና አንዱ ሌላውን“በማሸነፍ”ላይ የተመስረተ ጀግንነትን ስናወድስ ኑረናል፡፡ወንድም ወንድሙን በመግደሉ አንዱ በሌላው ላይ ግርፍያና ሰቆቃን በመፈፀሙ በ”ጀግንነት”ና  በ “አይበገሬነት” ሲፎክር ኑሯል፡፡ይህ ለረዥም ዘመናት የተጠናወተን ባንድ ቤት እየኖርን የመሸናነፍና አንዱ ሌላውን በማንበርከክ የሚሸልልበትን ባህል የምንለውጥበትና ለሰላም ለይቅርታና ለዕርቅ ጊዜአቸውንና እውቀታቸውን ለሰጡና ለዚህ የተቀደሰ ስራ መንፈስና ልቡናቸውን ያስገዙትን መሪዎችና ዜጎች በሰላማዊ ጀግንነታቸው የምናወድስበትና የምናሞግሳቸው ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡ይህ የዕርቅ ሂደትም እንደ አገርና እንደ ህዝብ ለዚህ ብቃት እንዳለንና እንደሌለን የምንፈትሽበት መድረክ ነው። በጦር ሜዳ ገደል አገራችን በርካታ ጀግኖች አፍርታለች።አሁን ደግሞ የሰላም ጀግኖችን ከምታፈራበት ልዩና አመቺ ሁኔታ ላይ ትገኛለች።ማንኛውም ለአገራዊ ዕርቅ የተቋቋመ አካል ለስራው ስኬት የሚያስፈለጉት በርካታ የአስተዳደር የባጀትና የሰው ኃይል ግብአቶች አሉ፡፡ከሁሉም በላይ በዋናነት ለተልዕኮው መሳካት አስፈላጊው ከቀና ልቦናና ከብርቱ አገራዊ ስሜት የሚመነጭ ህዝባዊ ተሳትፎና ነው፡፡

የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ደም መፋሳስ ሊያስከትሉ የሚችሉ ወይንም በማስከተል ላይ ያሉ ግጭቶች መከላከልና አፈታት ባለ ሙያ ነው፡፡

ገንቢ ሃሳብ አስተያየት ወይንም ጥያቄ ካልዎት በሚቀጥለው የኢሜይል አድራሻ ይላኩ፡፡

ደግፌ ደባልቄ

Digafie.debalke@gmail.com

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.