ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር ዶክተር አብይ አህመድ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠ/ሚንስትር

ለክቡር ዶክተር አብይ አህመድ
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠ/ሚንስትር
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

ሰኔ 15 2011 ዓ/ም

ጉዳዩ፦ ስለ ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ታጋይ እስክንድር ነጋ።

ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤

በቅድሚያ የማክበር ሰላምታችንን እያቀረብን በመጀመሪያ ይህችን ድንቅ አገራችን ኢትዮጵያን በሃላፊነት ለመምራት ከተመረጡበት ጊዜ ጀምሮ ስላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከልብ እናመሰግንዎታለን። በሃገራችን የዲሞክራሲ ባህልን ለመገንባት በሚያደርጉት እርብርቦሽም፣ ከጎንዎ ተሰልፈን ድርሻችንን እየተወጣን እንገኛለን::

የዴሞክራሲ ዋነኛ መርሆ ማንኛወንም ከግለሰብም ሆነ ከሕዝብ የሚመነጭ ሀሳብ በሃይልም ሆነ በስልጣን ሳይገታ በሰከነ መንገድ ተወያይቶና ተደራድሮ በሰላም ሁሉንም ባካተተ ሁኔታ እልባት ላይ እንዲደርስ ማድረግ ነው። ይህንኑ ዴሞክራሲያዊ እሴት በመጠቀም ከዚህ በታች ያለውን ስሞታችንን ስናቀርብ በቀጥታ እርስዎን እንደ ግለሰብ ለመቃወም ሳይሆን፣ እርስዎ በሚመሩት መንግሥት ሥር እየተፈፀመ ያለውን ድርጊት በመቃወም ነው።

ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤

ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በሕወሃት (ኢህአዲግ) መሪነት ተመስርቶ በዘረኝነት የፖለቲካ ዓላማ ሥር የኢትዮጵያን ህዝብ ሲገል፤ ሲያስር፤ ሲያፈናቅልና ሲዘርፍ የቆየውን የአገዛዝ ሥርዓት ለመለወጥ በቆራጥነት ከታገሉት ጋዜጠኞችና አክቲቭስቶች መካከል እስክንድር ነጋ ተቀዳሚውን ቦታ ይይዛል።

እርስዎም ሆኑ አሁን ያለው የእርስዎ አመራር ወደ ሥልጣን እንዲወጣ ያደረጉት እንደ እስክንድር ነጋ ያሉ ቆራጥ፣ ሕይወታቸውን ለፍትህና ለነፃነት ያበረከቱ፣ የማያወላውል አቋም ያላቸው ፅኑ ኢትዮጵያዉያን ናቸው። ታድያ ይህ የሰፊው ሕዝብ ባለውለተኛ እንዴት እሱና ጭቁኑ ሕዝብ ባሰቀመጣቸው የዛሬው መሪዎች ለዓመታት የታገለለት መብቱ ይጣሳል?

እስክንድር ነጋ ጨርቄን ማቄን ሳይል ቤተሰቡን ለፈጣሪ ትቶ ለፍትህና ለሕዝብ ነፃነት የታገለ ቆራጥና ደፋር ጋዜጠኛና የሰብዐዊ መብት ተሟጋች እንጂ ዝናን ፈላጊ ጀብደኛ ሰዉ አለመሆኑ ለብዙዎች የተሠወረ አይደለም::

እኛም በውጭ ሃገር የምንኖር ትውልደ ኢትዮጵያንም ሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በፊትም፣ አሁንም ከወንድማችን የነፃነት መብት ተሟጋች ጎን ቆመናል ወደፊትም እንቆማለን። ቆራጡ እስክንድር ነጋ የፃፈው የትግል ምዕራፍ ከቶ እንዴት ባንድ ጀምበር ይረሳል?

ክቡር ጠ/ሚንስትር

የእርስዎ መንግሥት፣ አክቲቪስት ነን የሚሉና የዘር ፖለቲካን የሚዘምሩ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጫርስ ሰበካ ለሚነዙና ለሚረጩ ግለሰቦች ያልተገደበ ነፃነትና አስተማማኝ የደህንነት ጥበቃ እየሰጠ፤ በአንፃሩ ደግሞ በጨዋነቱና በሕግ አክባሪነቱ አለም የመሰከረለትን እውነተኛ ጋዜጠኛ መብት መንፈግ፣ ማስፈራራትና ሃይልን የመጠቀም ዛቻ ማድረግ እጅግ በጣም አሳዝኖናል።

ትላንትና በዓለም ዙሪያ ባሉ ከተሞች ከርስዎና ከመንግስትዎ ጋር ለመደመር ግልብጥ ብለን የወጣነው፤ በማግስቱ ይህን የሚመስል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማየት አልነበረም። የርስዎም ሆነ የሚመሩት መንግስት መግለጫና ድርጊት ለሁሉም ዜጋ እኩልና ተመሳሳይ እንዲሆንም አጥብቀን እናሳስባለን። ስልጣን ሰፊውን ሕዝብ እንዲያገለግሉ የተሰጠ ሀላፊነት እንጂ የቂም መወጣጫ በትር አይደለም። እርስዎ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ “በሃሳብ እንከራከር” እንዳሉትና ቃል እንደገቡት፣ የእስክንድር ነጋን በሃሳብ የመከራከር መብት እርስዎም ሆኑ የሚመሩት መንግሥት የማክበር ሃለፊነት አለባችሁ። እስክንድር ነጋ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ የተከለከለበትን ምክንያት ከፖሊስ ኮሚሽን የቀረበዉን ዘገባ ስንሰማና ስናይ ላለፉት 27 ዓመታት ያስተናገድነዉን የአፈና ሥርዓት እንድናስታዉስ አድርጎናል:: እንዲያወም “ሌላ ያልታወቀ መንግሥት ከጀርባ አለ እንዴ?” ወደሚል ብዥታ ጥሎናል ።

ክቡር ጠ/ሚንስትር

እኛ በለንደን ኦንታርዮ ካናዳ የምንኖር ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች፣ የማንኛውም ዜጋ ሰብዓዊ መብትና ነፃነት እንዲረገጥ አንፈልግም። እስክንድር ነጋ፣ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ በሰላማዊ መንገድ የመሟገት መብቱ በመንግሥት ሳይገታ፣ ያለ ማስፈራሪያና ዛቻ በነፃነት ለሚወዳትና ለተሰቃየላት ኢትዮጵያ ዛሬም የድርሻዉን እንዲያበረክት ሊበረታታ እንጂ ሊገፋና ሊወገዝ አይገባም በማለት በማክበር አጥብቀን እናሳስበለን።

በለንደን ኦንታሪዮ ካናዳ የኢትዮጵያ ሲቪክ ማሕበር

ግልባጭ፦

ለኢፌዲሪ ም/ጠ/ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን
ለኦዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ
ለአዲስአበባ ከተማ ም/ ከንቲባ ኢንጂኒር ታከለ ኡማ
ለአቶ እስክንድር ነጋ
ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ድርጅት አ/አበባ

1 COMMENT

  1. “ቆራጥና ደፋር ጋዜጠኛና የሰብዐዊ መብት ተሟጋች እንጂ ዝናን ፈላጊ ጀብደኛ ሰዉ አለመሆኑ ..” ጀብደኛም ዝናን ፈላጊም ነው! ባይሆንማ ኖሮ፣ እሱ ዉጪ ሃገር ተወልዶ እና አድጎ መጥቶ ቢጤዎቹን በመሰብሰብ፣ መንግስት ባለበት ሃገር “ባለአደራ መንግስት” ከማቋቋም አልፎ ቢጤዎቹ አፈናቅለውት ቪላ የሰሩበት ሃገር ነባር ነዋሪዎችን እንደዉጩ ሃገር ዜጎች አይመለከትም ነበር! ጀብደኛም ብቻ ሳይሆን ባለጌም ነው!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.