ጠ/ሚ/ር አብይ አስመራ ላይ ሾፈሩ ፣ሲዳማ እና ዲሲ ሞት እና እስራትን አስተናገዱ (ህብር ራዲኦ)

የሲዳማ የክልል እንሁን ጥያቄን ተከትሎ በደቡብ ኢትዬጵያ በተፈጠረው ውጥረት የሰዎች ህይወትን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።ጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድ በኤርትራ ቆይታቸው ኢሳያስ አፈወርቅን በመኪና አንሸራሸሯቸው፣ዋሽንግተን ዲሲ ለሰልፍ የወጡ ኢትዬጵያኖች መታሰራቸው የተለያዩ ዘገባዎች ገለጹ።

በአዋሳ እና በአካባቢው በተቀሰቀሰው ውጥረት የጸጥታ ሀይሎችን ክልከላን በተቃወሙ ወጣቶች እና በጸጥታ ሀይሎች መካከል ጋር በተደረገው ግጭት ከሶስት በላይ ሰዎች መሞታቸው የተለያዩ ዘገባዎች እየገለጹ ይገኛሉ።
የሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ዝናው ሰርኒሶ ለዜና ሰዎች እንደገለጹት በትላንትናው ሐሙስ አራት ሰዎች:- በጥይት ተመተው ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ ሶስት ወንዶች በትላንትናው እለት የሞቱ ሲሆን አንዲት ሴትም ዛሬ (አርብ)መሞቷን ገልጸዋል።

የክልሉ የፖሊስ ሹም የሆኑት ቴዎድሮስ ወ/ሚካኤል በበኩላቸው ሀዋሳ ላይ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና አምፕጻ ከከተማው ውጪ መዛመቱን ጠቅሰው”በቁጥጥር ስር ለማድረግ “በእንቅስቃሴ ላይ ነን ብለዋል።

በምርጫ ቦርድ በኩል የሀዋሳ ጉዳይ ለአምስት ወራት ይራዘም ምላሽ በተቃዋሚው የሲዳማ ነጻ አውጪ ግንባር በኩል ይሁንታ ቢያገኝም አንዳንድ ተቃዋሚዎች እና አቀንቃኞች ” የዘገየ ፍትህ ለፍትህ ማጉደል ይቆጠራል”በማለት ቅሬታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

የተቃውሞ እና የድጋፍ ጉዳይ ከተነሳ ከዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት በሁዋላ ላለፈው አንድ አመት በባህር ማዶ ጋብ ብሎ የነበረው የጸረ መንግስት እና የአፍቃሪ መንግስት ሰልፎች ሰሞኑን ወደ ቀደመ ቦታቸው ተመልሷል።
በትላንትናው እለት በአሜሪካ መናገሻ ከተማ ዋሽንግተን ዲሲ አቅራቢያ ለድጋፍ እና ለተቃውሞ የወጡ ኢትዬጵያኖች የዛሬ አመት ሁሉም በአንድነት እንዳልወጡ እና ለዶ/ር አብይ አስተዳደር ይሁንታ እንዳልሰጡ ገሚሱ “የዶ/ር አብይ አስተዳደር የዛሬ አመት የገባውን ሰላም እና ዲሞክራሲ የማስፈን ቃል ኪዳኑን አልተገበረም ፣ዘረኝነት ፣መፈናቀል፣ መሞት እና በተለይ አማራውን ማሸማቀቅ እና በገፍ ማሰሩ ዛሬም ተባብሷል” ሲሉ የተቀሩት የለውጥ ሂደቱን የሚደግፉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ታይተዋል።

ለድጋፍ እና ለተቃውሞ ከወጡት ኢትዬጵያኖች ውስጥ የተወሰኑ የእስራት ሰለባ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።ቀደም ባሉት ሳምንታት በምእራብ አውሮፓዎቹ በፓሪስ፣በሎንዶን እና በበርሊን ለድጋፍ እና ለተቃውሞ የወጡ ኢትዬጵያኖችም ተመሳሳይ መንፈስ ያለው እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውለዋል።

ለብዙዎች የወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት የሆነው የሲዳማን ጉዳይ በቅርበት ከሚከታተሉት እና በጉዳዩ ዙሪያ ቀደም ሲል “ቀጭን ትእዛዝ ያስተላለፉት” ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ አሕመድ በሲዳማ የክልል እንሁን እወጃ ሙከራ እለት(ሐሙስ ዓለት) ወደ አስመራ ፣ ኤርትራ ለሁለት ቀናት የስራ ጉብኝት ለማድረግ ተጉዘውል። በአመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አስመራ ያቀኑት ዶ/ር አብይ አህመድ ፕ/ት ኢሳያስን ከጎን በማድረግ አንድ ነጭ ቶዬታ ላንድ ክሩዘርን ሲሾፍሩ እና በአስመራ ጎዳና ላይ ሲዘዋወሩ የሚያሳይ ምስል በኤርትራኖች ማህበራዊ ድህረ ገጾች ላይ በስፋት ተሰራጭቷል። ጠ/ሚ/ሩ በዚህ ቀውጢ ወቅት ወደ ኤርትራ የመሄዳቸው ጉዳይ በኦፊሲላዊ ቻናሎች ረገድ የሁለት እዬሽ ትብብር ለማጠንከር ነው ቢባልም አንዳንድ ወገኖች” ትንሽ አየር ለመሳብ እና ከአቶ ኢሳያስም ምክር ለመቀበል ሳይሆን አይቀርም “ሲሉ ተደምጠዋል።

ጠ/ሚ/ር አብይ የአገር መሪዋችን በሹፌርነት በማንሸራሸር የአስመራ ከተማው ሹፍርናቸው ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ባለፈው አመት እንዲሁ ወደ አ/አ ኢትዬጵያ ለጉብኝት የመጡት የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ልኡል መሃመድ ቢን ዛይድን ከጎናቸው በማስቀመጥ መኪና እያሽከረከሩ ሲያስጎበኟቸው እንደነበር አይዘነጋም ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.