አገራችንን ከጥፋት፤ ሕዝባችንን ከመከራ ለመሰወር፤ በጌታ ፍቃድ (ከዶ/ር በቀለ ገሠሠ)

መንደርደሪያ፤

ሁላችንም የወጣነዉ ከየእናቶቻችን ማህፀን ዉስጥ ነዉ፤ ለ9 ወራት በማህፀን ተሸከሙን፤ ወለዱን፤ አጠቡን፤ አበሉን፤ ሳሙን፤ አቅፈዉ አሳደጉን። በዚህም ምክንያት እናቶቻችንን ከማንም አስበልጠን እንወዳቸዋለን። እንደዚሁም አገር እናት ናት። ዕትብታችን የተቀበረዉ በርስዋ ዉስጥ ነዉ። ከመሬትዋ እህሎች በቀሉልን፤ በልተን አደግን። ከከርሰ ምድርዋ የሚወጣዉን ዉሃ ጠጥተን አደግን። ወተትና ምግብ የሚሰጡን ከብቶቻችን የሚግጡትና የሚጠጡት ዉሃ የሚገኘዉ ከዚያችዉ ምድር ነዉ። የምንተነፍሰዉ ጥሩ አየር የሚነፍሰዉ በርስዋ ላይ ነዉ። ስንሞት የምንቀበረዉ በርስዋ ዉስጥ ነዉ። ስለዚህ ዉድ አገራችንን የእናቶቻችን ያህል እንወዳታለን። አገር ደግሞ የጋራ ናት። ቸሩ አምላካችን ሲፈጥረን የዚያችን ፍሬ እኩል እንድንካፈል ነዉ። እንደፈለግን በነፃ ተዘዋዉረን ሠርተን እንድንኖርባት ነዉ። ይሄ ሁሉ በጣም ግልፅ ይመስለኛል። ከፋም ለማ፤ የብዙ ሺህ ዓመታት የጋራ ታሪክ ያለን ሕዝብ ነን። ዛሬ ግን በተግባር የምናየዉ ሌላ እየሆነ አስቸገረን፤ ብዙ የአፍሪቃ አገሮች ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቶች እየገነቡ በሰላም ሲኖሩ እኛ ለምን ወደኋላ እንደምንቀር ስመለከት እጅጉን አዝናለሁ፤ መንፈሣዊ ቅናት ያድርብኛል። ሃሳብና ጭንቀት ዉስጥ ይከተናል። ተያይዘን ከምንጠፋ ተያይዘን ብንነሳ ይቀላል። ስለዚህ ዉድ አገራችንን ከጥፋትና ሕዝባችንን ከመከራ ለመሰወር እያንዳንዳችን የምንችለዉን ያህል አስተዋጽኦ እንድናደርግ በፈጣሪያችንና በልጆቻችን ስም አደራ እላለሁ፤ እግዜር ይታረቀን፤ የጌታችን በረከት አይለየን፤ አሜን።

፩ኛ/        ኢትዮጵያ የማን ናት?

መጠየቁስ? እንዳትሉኝ። ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጎችዋ እኩል አገር ናት። እንኳን ለዜጎችዋና በፖሊቲካም ሆነ በሃይማኖት ምክንያት ከየአገሮቻቸዉ ተሰድደዉ የመጡትን በሙሉ እጇን ዘርግታ በመቀበልና በማስተናገድ የታወቀች ቅድስት አገር ናት። በመጽሐፍ ቅዱስ፤ በቅዱስ ቁራንና በታሪክ መዘክሮች በግልጽ የተቀመጠ ሃቅ ነዉ። ዛሬ ግን ፌደራላዊዉ ሥርዓት የተዘረጋዉ ጎሣንና ቋንቋን ብቻ መሠረት በማድረጉ ምክንያት ብዙ ግጭቶች እየተፈጠሩ ይገኛሉ። ከ80 በላይ ጎሣዎች በሚኖሩባት አገር ለሁሉም ዜጋ ተስማሚ የሆነ ሥርዓት መዘርጋት የግድ ይላል። ይሄን አስፈላጊና አንገብጋቢ ጉዳይ በተመለከተ እንደብዙዎቹ ግልፅ ስምምነት ላይ መድረስ እጅግ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ።

፪ኛ/        ምን ዓይነት ኢትዮጵያን እንፈልጋለን?

 • ሰላም የሰፈነባትና ዜጎችዋ በነፃ እየተዘዋወሩ የሚኖሩባት፤ የሚነግዱባት፤ ወዘተ አገር
 • ፍትሕ ያልተዛባባት
 • ድህነትና በሺታ የማይፈራረቁባት
 • የሁሉንም ዜጋ እኩልነት የምታረጋግጥ ዲሞክራሲያዊት አገር።

፫ኛ/        ከመሪዎች ምን እንጠብቃለን?

በመጀመሪያ ከዬት ተነስተን ዬት እንዳለን አለመርሳት ያስፈልጋል። አምባገነናዊ አገዛዞችን አስወግዶ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ዜጎች ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉባት አገር ናት። አሁን ደግሞ የለዉጥ ጮራ ፈነጠቀ ተብሎ ታላቅ ተስፋ በተጣለበት ወቅት ሁኔታዎች እየተባባሱ የመጡበትን ምክንያቶች በግልፅ መረዳት ያስፈልጋል። ሕገ መንግሥቱም ሆነ መንግሥት ገና በትክክለኛዉ የሕዝብ ተሳትፎ (በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት) አለመቋቋማቸዉን መርሳት ከባድ ችግር ዉስጥ ይከተናል። አሁን ያለዉ መንግሥት ጊዜያዊ ባለአደራ እንደመሆኑ መጠን ነፃ የሆነ አገራዊ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ በተለይ በሚከተሉት ሀሳቦች ዙሪያ ከፍተኛ ትኩረት ቢያደረግ የሚጠቅም ይመስለኛል፤

 • የዜጎች ደህንነትና እኩል መብት መጠበቁን ማረጋገጥ፤
 • የሺማግሌዎችን፤ የኃይማኖት አባቶችንና የምሁራንን ምክር መስማት፤
 • አገርና ሕዝብ ማረጋጋት፤
 • የሽግግሩን ሂደት ማስተካከልና ተሳትፎ መጨመር፤
 • አስፈላጊ ተቋማትን ማቋቋምና ማጠናከር፤
 • ርትዐዊና ፍትሐዊ የሆነ ነፃ አገራዊ ምርጫ ማመቻቸት።

፬ኛ/        ከሺማግሌዎችና ከመንፈስ አባቶች ምን እንጠብቃለን?

አገሪቷ ለስንት ሺህ ዓመታት በሰላምና በነፃነት የኖረችዉ በአረጋዉያንና በኃይማኖት አባቶች ምክርና ፀሎት ነዉ። ፅዉቀት፤ ፀጋና የሕይወት ልምድ ያለዉ በነርሱ ዘንድ ነዉና። አሁንም ዉድ ሺማግሌዎችንና የኃይማኖት አባቶችን አጥብቄ የምለምነዉ፤

 • የአገሪቷ ታሪክ እንዳይዛባ ሃቁን እንዲመሰክሩ፤
 • ‘ድር ቢያብር አንበሳ ያስር’ የሚለዉን መርህ እንዲያስታዉሱ፤
 • በጭቁን ሕዝባችን መሃል ምንም ዓይነት ጥል እንዳልነበረ እንዲመሰክሩ፤
 • በከንቱ ፖሊቲከኞች ቅስቀሳ በተጋጩ ወገኖች መሃል እርቀሰላም እንዲያወርዱ፤
 • ሰላም፤ እርጋታና ዕድገት ይሰፍን ዘንድ ለመንግሥት አስፈላጊዉን ምክር እንዲለግሱ፤
 • ለአገራችን አንድነትና ለሕዝባችን ደህንነት ፀሎታቸዉ እንዳይለየን።

፭ኛ/        ከምሁራንና ባለሙያዎች ምን እንጠብቃለን?

ዕድሜ ለተፈራረቁት አምባገነን መንግሥታት፤ ኢትዮጵያ ያሳድጉኛል በማለት በሌላት ዐቅም ለፍታ ያስተማረቻቸዉ  ብርቅ ልጆችዋ በጥይቶች ረገፉ፤ ከተረፉት መሃል ደግሞ ብዙዎቹ እንደባህር አሸዋ በዓለም ተበትነዉ በስደት ላይ ይገኛሉ። አሁንም ተስፋ መቁረጥ አይኖርብንም። ከያለንበት ሆነን ለአገራችን ሰላምና ዕድገት የምንችለዉን ሁሉ አስተዋጽኦ ከማድረግ መቆጠብ አይኖርብንም።  ‘የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ’ ተብሎ የሌ?

በእህል ማምረቻ፤ በአካባቢዉ አየር ብክለት መከላከያና መቋቋሚያ አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎች ማሳደግ፤ በወንዞቻችንና ሃይቆቻችን ጥበቃ፤ በሰዎችና እንስሳት ጤናዎች አጠባበቅ፤ ወዘተ ላይ በቶሎ ካልተባበርን አገራችን ምድረበዳና ሕዝባችን ጉዳተኞች ሆነዉ እንዳይቀሩ እጅግ በጣም ያሳስበኛል። የተማረ ሰዉ ቃልኪዳኑን መጠበቅ ይኖርበታል፤ አለመዋሸት፤ ሃቁን መመስከርና ሣይንሱን ማስተማር ይጠበቅበታል። በሙያዉ ሠርቶ ማደር ስለሚችል ሕዝባችንን መታደግ እንጂ በክፉ ነገር ላይ መጣል ከቶ አይጠበቅበትም። አገሪቷ ለፍታ ያስተማረቻቸዉ ልጆችዋን እንዲከፋፍሉና እንዲያናክሱ ሳይሆን በእዉነተኛዉ መንገድ እንዲሄዱና እንዲታደጓቸዉ ነዉ።

፮ኛ/        ከወጣቶችስ ምን እንጠብቃለን?

ከሁሉም በላይ የሚያሳስበኝ የአሁኑ ወጣቶችና የመጪዉ ትዉልድ ዕጣ ፈንታ ነዉ። ግጭቶች እየተበራከቱ ናቸዉ። በሰላም ወጥቶ መግባት አጠራጣሪ እየሆነ ነዉ። አየሩ እየተበከለ ነዉ። መሬቶቻችን ጠፍና ምድረበዳ እየሆኑ ናቸዉ። ስለዚህ ለወጣቱ ትዉልድ የሚከተሉትን ቅን ምክሮች ስለግስ ትህትና በተሞላበት መንፈስ ነዉ፤

 • ተስፋ አትቁረጡ፤
 • ራሳችሁን ጠብቁ፤
 • በባልንጀሮቻችሁ ላይ አትጨክኑ፤
 • ራስ ወዳድነት እንዳያሸንፋችሁ፤
 • የአገራችሁን ትክክለኛ ታሪክ ጠንቅቃችሁ ለማወቅ ሞክሩ። አገር መገንባት፤ አንድነት ማጠናከርና ድንበራችንን ከዉጪ ጠላቶች መከላከል ቀላል ትግል አልነበረም፤ አባቶቻችን፤ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን አጥንታቸዉን ከስክሰዉና ደማቸዉን አፍስሰዉ ነዉ ነፃ አገር ያስረከቡን።
 • ለእኩልነት መታገል እጅግ ያስፈልጋል፤ ለዚህም ነበር እልፍ አእላፍ ወጣቶች ለመሬት ላራሹና ለመደብ እኩልነት ከፍተኛ የሕይወት መስዋእትነት የከፈሉት።
 • ዘርና ጎሣ አትለዩ። አምላካችን በአምሳሉ የፈጠረን አንድ ሕዝብ ነን። እኛ ልጆች በነበርንበት ወቅት ሆነ በትግሉ ውስጥ እያለን ዘርና ጎሣን ለይተን አናዉቅም ነበር። እያንዳንዱ ግለሰብ መታት ያለበት በማንነቱ ብቻ ነዉ።
 • ትግላችሁ ለሁሉም ዜጋ ዲሞክራሲና እኩልነት እንጂ ለጭቆናና ለመጠፋፊያ እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባችኋል።
 • ከሁሉም የሚቀድመዉ ሰላም ነዉና ሰላም ፈጣሪዎች ሁኑ፤
 • ዋናዉ ጠላታችን ርሃብና ችጋር ስለሆነ እርሱን ለማጥፋት እንነሳሳ፤ በሥራ ፈጠራና አገራዊ ዕድገት ላይ እንረባረብ።
 • የምትኖሩባትን ምድርና አየሯን ተንከባከቡ፤ ይህን ካደረግን ምድራችን እንኳን ለኛና ለሌሎችም ትተርፋለች።
 • ቸሩ አምላካችን ከመከራ ይሰዉራችሁ።

፰ኛ/       ከሁሉም በላይ ግን ሕዝባችንና አምላካችን አለ

ሕዝቤ ሆይ፤ ሁላችሁንም እጅግ አድርጌ እወዳችኋለሁ፤ አከብራችኋለሁ። በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ዞሬ ዐይቻለሁ፤ በሙያዬ ትንሽም አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ። ደግ ሕዝብ፤ እንግዳ ተቀባይ፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር (በየአምልኮቱ) ያደረበት ነዉ። በየቦታዉ (ከሰሜን እስከደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከምዕራብ) ያለዉም የሕዝባችን ችግር ተመሳሳይ ነዉ። ዋናዉ የዲሞክራሲ አስተዳደርና ሰላም መጥፋት ነዉ። ምድራችን በጠፍነት እየተጠቃ ከመሆኑ በስተቀር ሰፊ ነዉ፤ ለሁሉም የሚሆን፤ ከዚያም የሚተርፍ ነዉ። ሰላም ካለ የአየሩን ብክለትና የመሬቱንም ጠፍነት ልንከላከል እንችላለን።

ደጉ ሕዝቤ ሆይ፤ ለብዙ ሺህ ዓመታት የምትታወቀዉ በደግነትህና በአንድነትህ ነዉ። አሁንም በማንም በማንም እንዳትታለል፤ በዘር፤ በጎሣና በሃይማኖት እየተከፋፈልክ እርስ በርስ አትባላ። ባንድ ላይ ሆነህ ኑሮህን አሸንፍ። በህብረት ቆመህ ድንበርህን ከዉጪ ጠላት ተከላከል። ከክፍፍላችንና ከጥፋታችን የሚያተርፈዉ ሴይጣንና የዉጪ ወራሪ ጠላት ብቻ ነዉ። እስካሁን ድረስ በአንድነትህና በእግዚአብሔር ኃይል ነፃነትህን ጠብቀህ ቆይተሃል። አሁንም በዚያዉ ቀና መንፈሣዊ መንገድ ቀጥል። ለልጆችህና ለልጅ ልጆችህ ሰላም የሰፈነባት አገር አዉርስ።

የቸሩ ፈጣሪያችን በረከት ሳይለየን የዉድ አገራችንን አንድነትና የሕዝባችንን ደህንነት ይጠብቅለን ዘንድ ባንድ ላይ እንፀልይ፤ ንሥሐ እንግባ፤ ጌታ ይታረቀን።

 

3 COMMENTS

 1. ዶ/ር በቀለ ገሠሠ እንዲህ አይነት ሚዛኑን የጠበቀ ቀና አስተሳሰብ አጥተን ነው የተቸገርነው ።

 2. ተሰባጥሮና ተዘንቆ የኖርን ህዝብ ሆን ተብሎ በክልል ፓለቲካ በመከፋፈል የተሰራው ሴራ ጣሊያን በሃገራችን ላይ ካደረሰው ሰቆቃ የበለጠ አድርሷል በማድረስም ላይ ነው። ወያኔና ሻቢያ በሸረቡት የጋራ ገመድ ታንቃ አንገቷ የተቆረጠው ተራፊ ሃገር ከእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ ሆኖባት ዛሬም ህዝቦቿ እናውቅልሃለን በሚሉ የ 50 ዎቹና የ 60 ዎቹ ትውልድ ትራፊዎችና የዚሁ ስብስብ ደቀመዝሙሮች ታክለው ያውኳታል። ተምሬአለሁ ያለው ዘመኑን ሁሉ የሚያሳልፈው በጥለፈው ፓለቲካ ነው። ለመኖር የፓለቲካ ባላንጣ ግድ አስፈላጊ ነውና ዛሬም የምንታዘበው ያንኑ የያዘው ጥለፈው ፓለቲካ ነው። መሬት ላራሹ የምትሉ ተዋጉለት አትሽሹ ሲል የነበረው ትውልድ አሁን መሬት ለባለሃብት ይለናል። ሲከፋም በዘርና በጎሳው ተጠልሎ ይደነፋል። እንደ እንጉዳይ የፈሉት ብሄርተኞች ህብረ ብሄር ፓለቲካ አይዋጥላቸውም። ይህ ዝግመታዊ ጉዞ ከሽያጭና ከክፋይ የቀረቸውን ሃገር እንደ ሶሪያና ኢራቅ ወይም እንደ የመንና ሶማሊያ እንደሚያደርጋት መገመት አዳጋች አይሆንም። በቅርቡ በዶ/ር አብይ አመራር ትንሽ ተስፋ ሰጪ ነገሮች ቢታዪም በዘር ፓለቲካ ተቀፍድዶ የተያዘው የሃገሪቱ ላዕላይና ታህታይ መዋቅር በቀላሉ ለለውጥ እጅን የሚሰጥ ሆኖ አልተገኘም። እንደ እሳት አደጋ ሰራተኛ አንድ ጋ እሳቱ ሲጠፋ ሌላ ጋ በየሰበቡ ቦግ ብሎ እየነደደ ህዝባችንን የሜዳ አዳሪ እያደረገው ነው። እንደልቡ የሚያልበው ጥገት ከእጅ በጥቂቱም ቢሆን ያፈተለከው ወያኔ ሃርነት ትግራይ መቀሌ ላይ መሽጎ ማን ሊነካኝ ይለናል። አሁን ሃገሪቷ ያለችበት ሁኔታ አስፈሪ ነው።
  ታዲያ እንዲህ ቅጥ አምባሩ የጠፋውን የሃበሻው የፓለቲካ አሸንክታብ እንዴት አሳምሮ ሁሉም በሰላምና በደስታ እንዲኖር ማድረግ ይቻላል? በእኔ እምነት ስብራቱ ጥልቀት ስላለው ነገሩን መበየድ ሳይሆን ከሥር መሰረቱ አፍርሶ አዲስ መሰረት መጣልና አዲሱን ትውልድ በህብረ ብሄር አሳምኖ ለአንዲት ሃገር ተሰላፊ ማድረግ ነው። የሃገሪቱ ችግር ሽርብ ነው። የውስጥና የውጭ ሴራ ዛሬም አለ በፊትም ነበረ። የሃገሪቱ መጻኤ እድል በየስፍራው የነደደን እሳት በማጥፋትና ሌላ እሳት እስኪነሳ ለመጠበቅ ጊዜ አይሰጥም። የዶ/ሩ ጠለቅ ያለ አስተሳሰብና እይታ እጋራለሁ። ግን እኮ የሃገራችን የመከራ ምንጭ ተምሬአለሁ የሚለውና ጠበንጃ አንጋቹ ነው። ከዘመናት በፊት ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) እንዲህ ብሎን ነበር።
  ዲግሪማ ነበረን፣ ሁሉም በያይነቱ
  ከቶ አልቻልንም እንጂ፣ ቁንጫን ማጥፋቱ።
  ኢትዮጵያዊነትን አስመልክቶ ደግሞ ከግማሽ ምዕተ አመት በፊት ኢብሳ ጉተማ “ኢትዮጵያዊ ማን ነው” ከተሰኘው ግጥሙ በጭልፋ እንሆ።
  ኢትዮጵያዊው ማን ነው?
  ያገር ፍቅር መንፈስ ያደረበት ሁሉ
  ማንነቱን ሳያውቅ በመንቀዋለሉ
  ማነኝ ብሏችኋል መልሱን ቶሎ በሉ፣
  እናንተ ወጣቶች ኢትዮጵያዊ ማን ነው?
  ከሆዱ ያበጠ ቦርጫም መኰንን ነው?
  ወይስ ኰሰስ ያለው መናጢ ድሃ ነው?
  ላቡን አንጠፍጥፎ ከመሬት ተታግሎ
  ካገኘውም ሰብል ለጌቶች አካፍሎ
  ለራሱ ከእጅ ወደ አፍ የሚያስቀረው ነው?
  በሉ እስቲ ንገሩኝ ኢትዮጵያዊ ማን ነው?

  እስቲ ይብቃኝ። ለሃገራችን ሰላም ይሁን!

 3. ዶ/ር ነህ መሰለኝ። ግና የምትጽፈው የግብዞች ምኞታዊ ፖለቲካን ነው ወይስ የትምህርት ደረጃህን የጠበቀ፣ ነባራዊዉን ሁነታ ያገናዘበ፣ ላልተማሩት ምክር የሚሆን ሳይንሳዊ ትንተና ማቅረብ ነበረብህ??
  “ምን ዓይነት ኢትዮጵያን እንፈልጋለን?” ሲባል መልሱ ፣ ምን ዐይነት መንግስታዊ ስርዐት እና ፖለቲካ መሆን አለበት ነው።
  “ከመሪዎች ምን እንጠብቃለን?” > በህዝብ የተመረጠ፣ የህዝቡን አደራ ተቀብሎ ህግ እና ህገ መንግስቱን አክብሮ የሚያስከብር መሪ ሳይኖር፣ ራሱን ከሾመ መሪ ምንም አይጠበቅም! ስልጣን ለህዝብ ከመመለስ በስተቀር።
  “ከምሁራንና ባለሙያዎች ምን እንጠብቃለን?” > ከላይ ያቀረብኩልህን ጥያቄ ስትመልስ ለጥያቄህም መልስ ይሆናል!
  “ከሺማግሌዎችና ከመንፈስ አባቶች ምን እንጠብቃለን?” > በ21ኛው ክ ዘመን ታቦት ከሰማይ ወረደ፣ ሌላም ሌላም እያሉ ከሚያጭበረብሩ ‘መንፈሳዊ’ ሰዎች ምን እንደሚጠበቅ አይገባኝም! ሃይማኖትም እንደፖለቲካው ለሆድ ከሆነ ቆይቶአል እኮ፣ ድሮስ ምን ነበር እንዳትለኝ እንጂ!
  “ከወጣቶችስ ምን እንጠብቃለን?” > the future is theirs. They have to demand and pressure for a better future. ተስፈኞች ብቻ አደርግሃቸው!
  “ከሁሉም በላይ ግን ሕዝባችንና አምላካችን አለ” > አምላክ ፖለቲካ ዉስጥ አይገባም። ህዝብ ግን የሃገሩም የፖለቲካ ስልጣኑም ባለቤት ነው። ሃገሩን እና ስልጣኑን ለህዝብ መልሱ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.