ፖሊስ ጋዜጠኛውን ለምን እንዳሰረውና እንደማይፈታው ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ተሰጠ

ኤልያስ ገብሩ

ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡40 ሰዓት ላይ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ውሎ በእስር ላይ የሚገኘውን ጋዜጠኛና የባላደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) ተብሎ የሚጠራው ምክር ቤት ጸሐፊ ኤልያስ ገብሩን፣ ፖሊስ ለምን እንዳሰረውና ከእስር እንደማይለቀው ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

ትዕዛዙን የሰጠው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ሲሆን፣ ለትዕዛዙ መሰጠት ምክንያት የሆነው የታሳሪው ጠበቃ አቶ ተማም አባቡልጉ አካልን ነፃ የማውጣት (Habeas Corpus) አቤቱታ በማቅረባቸው ነው፡፡

ጠበቃው የፍትሐ ብሔር ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 177 እና 205  ድንጋጌ መሠረት አድርገው ባቀረቡት አካልን ነፃ የማውጣት አቤቱታ እንዳብራሩት፣ ማንንም ሰው አስሮ ምርመራ የማድረግ ሥልጣን ለማንኛውም አካል የሚሰጠው በግልጽና በሕግ ብቻ ነው፡፡

ጋዜጠኛው ታስሮ የሚገኘውና ምርመራ እየተደረገበት ያለው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሲሆን፣ የተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊት ደግሞ የሽብር ወንጀል ነው፡፡ ይህንን የወንጀል ድርጊት ለማጣራት ኮሚሽኑ በሕግ የተሰጠው ሥልጣን ስለሌለ፣ ድርጊቱ ሕገወጥ መሆኑን ጠበቃው ገልጸዋል፡፡ ከፖሊስና ከደኅንነት የተውጣጣና በሕግ ተቋቁሞ ሰው አስሮ የመመርመርና የማጣራት ሥልጣን የተሰጠው አካል እንደሌለ የተናገሩት ጠበቃው፣ ጋዜጠኛው የታሰረው ያለ ሕግ ድግፍ በተደራጀው ግብረ ኃይል በመሆኑ ድርጊቱ ሕገወጥ  መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጋዜጠኛውን በቁጥጥር ሥር ያዋለው በሕግ ያልተቋቋመው ግብረ ኃይል፣ ጋዜጠኛው ወንጀል ሲሠራ እጅ ከፍንጅ ሳይዘውና የፍርድ ቤት መጥሪያ ሳይያዝ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ አንድን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ማዋል የሚቻለው ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ 12፡00 ሰዓት ባሉት ሰዓታት ብቻ ሆኖ የተደነገገውን ሕግ በመተላለፍ፣ ከምሽቱ 2፡40 ሰዓት ላይ መሆኑም ሕገወጥ እንደሆነ ጠበቃው አመልክተዋል፡፡

ጋዜጠኛው የተያዘው ከጓደኛው ቤት ቆይቶ ወደ ቤቱ በመሄድ ላይ እያለ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆነው ሲጠብቁት በነበሩና ማንነታቸው በማይታወቁ ስድስት ግለሰቦች መሆኑን ጠበቃው ጠቁመው፣ ማንም ሰው በሕገወጥ መንገድ ከተያዘ በኋላ ፍርድ ቤት ቢቀርብ እንኳን የእስራቱን ሕገወጥነት እንደማያስቀረው ገልጸዋል፡፡

ጋዜጠኛው አደረገ ተብሎ በሽብርተኝነት ቢጠረጠርም፣ ድርጊቱ በሽብርተኝነት አዋጅ ሥር የሚወድቅ ሳይሆን በወንጀል ሕግ ድንጋጌ ሥር የሚወድቅ ቢሆን እንኳ የማይመለከተውን አዋጅ ጠቅሶ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ ሕገወጥ ስለሆነ እስራቱ በሕግ ያልተደገፈ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጋዜጠኛው ቋሚ አድራሻ ያለው መሆኑንና ወንጀል ስለመሥራቱም ጠቋሚ ነገር እንዳልቀረበበት ተናግረው፣ ከእስር ውጪ እንዳይሆን የሚከለክለው ሕጋዊ ምክንያት ሳይኖር መታሰሩ ሕገወጥ መሆኑንን አክለዋል፡፡

የጋዜጠኛው መኖሪያ ቤት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመበርበር ሞባይሎችን፣ ላፕቶፖችንና የተለያዩ ጽሑፎችን መውሰድም፣ ሕገወጥ መሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዲገነዘብላቸው አሳስበዋል፡፡

ጋዜጠኛው የሳይነስ ሕመምተኛ መሆኑን እየተናገረና እየታወቀ የታሰረው በቂ ሕክምና እንዳያገኝ ተደርጎ በመፀዳጃ ቤት አጠገብ፣ በጨለማ ቤት ውስጥ ለብቻው መሆኑም ተገቢ አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ጨካኝነትን፣ ነውርንና ኢሰብዓዊ ድርጊት እንደሆነ አክለዋል፡፡ አያያዙና እስራቱ ሕገወጥ መሆኑን ደጋግመው አስረድተው፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋዜጠኛው ፍርድ ቤት ይዞ ቀርቦ ከእስር እንዲፈታው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠበቃው ጠይቀዋል፡፡

አቤቱታውን የተመለከተው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እስረኛውን ለምን እንዳሰረውና እንደማይፈታው ከእስረኛው ጋር ቀርቦ እንዲያስረዳ ለሐምሌ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

2 COMMENTS

  1. it is the same old corrupt system. every cadre of opdo is now empowered to jail, torture, or even kill anyone whom they hate.

  2. This shows the old times are not a past. The OPDO Idiots want to make their Opposition suffer because they have no argument against Baldars’s agenda. we will kick their asses out of office come election day

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.