‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬትም ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡›› አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቅ ኢትዮጵያ

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 22/2011 ዓ.ም (አብመድ) ይህ ሞት ካለፈውም ሆነ ከሚመጣው ፍፁም ይለያል፡፡ ይህ ሰማዕትነት ነፍስ ከስጋ የተለየችበት ተራ ሞት ብቻ አይደልም፤ ሐዋሪያዊ ተልዕኮም ጭምር እንጂ፡፡ ይህ ስለሀገርና ሕዝብ ሲባል ያለፈ የኢትዮጵያዊው አርበኛ የመንጋው እረኛ ሕይወት ትርጉም አለው፡፡ ‹ለምን?› ካለችሁ ሟች የሞታቸው ፍርድና ደብዳቤ ሲነበብ ከፊታቸው ላይ መረበሽም ሆነ መደናገጥ ፈፅሞ አይታይም ነበር፤ ነገር ግን የሞት ነጋሪት ጎሳሚው የፍርድ ደብዳቤውን አንባቢው ጣልያናዊ ዳኛ ይንቀጠቀጥና ታላቅ ፍርሃትም በፊቱ ላይ ይነበብ ነበርና ገዳይ እያፈረ ሟች እየደፈረ የተላለፈ ውሳኔ፡፡

ከ83 ዓመታት በፊት ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም የወራሪው ፋሽስት ጣልያን ኃይል የፍርሃት በትሩን ደጋግሞ ያሳረፈባቸው ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘ ምሥራቅ ኢትዮጵያ፡፡

የጣልያን ወረራን ለመከላከል በ1928 ዓ.ም አዋጅ በታወጀ ጊዜ በወቅቱ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ጴጥሮስም ንጉሠ ነገሥቱን ተከትለው ወደ ማይጨው ዘመቱ፡፡ ከኅልፈታቸው አንድ ቀን ቀድመውም ሐምሌ 21 ቀን 1928 ዓ.ም የተባበሩት የአርበኞች ግንባር አዲስ አበባ ላይ የሰፈረውን የጠላት ጦር ለመዋጋት ባደረገው ቀጠሮ መሠረት አቡነ ጴጥሮስም በነደጃዝማች አበራ ካሳ ይመራ ከነበረው የሰላሌ ጦር ጋር አብረው ወደ አዲስ አበባ ገቡ፡፡

ይህ ጦር ግን የሚፈለገውን ውጤትና ድል ማምጣት አለመቻሉን ተከትሎ ወደ መጣበት አቅጣጫ ለማፈግፈግ ሲገደድ አቡነ ጴጥሮስ የአዲስ አበባን ሕዝብ ለማስተባበር በማሰብ ከጦሩ ተለይተው አዲስ አበባ ቀሩ፡፡ ዳሩ ግን ብዙም ሳይውሉና ሳያድሩ በአንድ ቀን ውሎ ብቻ ተይዘው ከጣልያን የጦር አለቆች ፊት ቀረቡ፡፡

በሀገራቸው መሬት በጣልያናውያን ዳኞች ችሎት ፊት የቀረቡት አቡነ ጴጥሮስ ‹‹ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም አምፀዋል፣ ሌሎችም እንዲያምፁ አድርገዋል›› የሚል ክስ ቀረበባቸው፡፡ ጣልያናዊው የመሀል ዳኛም ‹‹ካህናቱም ሆኑ የቤተ ክህነቱ ባለስልጣናት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስም የጣልያንን መንግሥት ገዥነት አምነውና አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ተለይተው ለምን አመፁ? ለምንስ ብቻዎን ተለይተው አፈንጋጭ ሆኑ?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡

አቡነ ጴጥሮስም ሲመልሱ ‹‹አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገድዳቸው ነገር የለም፤ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኃላፊነት ያለብኝም የሃይማኖት አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለሀገሬ እቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ፡፡ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፤ ተከታዮቼን ግን አትንኩ›› በማለት መለሱላቸው፡፡

የፍርድ ውሳኔው በሞት እንዲቀጡ ከተወሰነ በኋላ ወደሚገደሉበት ቦታ እንደደረሱ ሞታቸውን ለመቀጣጫ እንዲያ በጣሊያን ወታደሮች ለተሰበሰበው ሕዝብ እንዲህ አሉ አቡነ ጴጥሮስ ‹‹ነፃነታችሁ ከሚረክስ ሞታችሁ ስማችሁ ሲቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡››

የሀገራቸው መደፈር የሕዝባቸው መታሰር እስከ ሞት ያደረሳቸው ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ በጥይት ሲደበደቡ ጥይቱ እርሳቸውን አልፎ ሌላ ሰው እንዳይጎዳ ቦታ ተፈልጎ ግንብ ተጠልለው እንዲመቱ ተደረገ፡፡ ወደሚገደሉበት ቦታ ከደረሱ በኋላ ከገዳዮቹ መካከል አንዱ ‹‹ፊትዎን መሸፈን ይፈልጋሉ?›› ሲል ላቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ይህ የአንተ ሥራ ነው›› የሚል ቆራጥ መልስ ሰጥተው ለሞት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠውለታል፡፡

ስምንት ወታደሮች ከአቡነ ጴጥሮስ በስተጀርባ 20 ርምጃ ርቀው በተጠንቀቅ ቆሙ፡፡ ወዲያውኑም አዛዡ ‹‹ተኩስ›› የሚል ትዕዛዝ እንዳስተላለፈ ስምንቱም ተኩሰው እና በስምንት ጥይት ተመትተው ሕይወታቸው ስላላለፈ ተጨማሪ ቦታ ላይ ተመትተው በዛሬዋ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ስለሀገራቸው እና ሕዝባቸው ክብር ሲሉ ይህችን ዓለም በክብር ተሰናበቱ፡፡

ጠላት ድል ሆኖ ከኢትዮጵያ ምድር ሁሉ ሲወጣ የብፁዕነታቸው ታሪክ ትውልድ ሲዘክረው ይኖር ዘንድ በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ዓፄ ኃይለሥላሴ አሳሳቢነት ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ እምብርት ላይ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡

ጳውሎስ ኞኞ እንደጻፈው

በታዘብ አራጋው

2 COMMENTS

  1. – “ዳኛው ይንቀጠቀጥና ታላቅ ፍርሃትም በፊቱ ላይ ይነበብ ነበርና ገዳይ እያፈረ ሟች እየደፈረ የተላለፈ ውሳኔ፡፡”
    – “አቡነ ጴጥሮስም ሲመልሱ ‹‹አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገድዳቸው ነገር የለም፤ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኃላፊነት ያለብኝም የሃይማኖት አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለሀገሬ እቆረቆራለሁ፡፡ ”
    Ohhhhhh, It is magnificence martyrdom. what about today’s spiritual and political leaders?

  2. This is self-sacrifice at its best. Abune Petros is a shining example of Ethiopiawinet. This is how our forefathers kept our independence from colonizers. Some ignorant Ethno-nationalist “scholars” now tell us “there is no Ethiopiawinet.” Abune Petros would turn over in his grave if he could see this treachery by these clowns.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.