ማመልከቻ ለክቡራን ኢትዮጵያውያን ክፍል 2 የዲሞክራሲ ለውጥ ሽግግር ፍኖተ-ካርታ (Roadmap) ለውይይት የቀረበ – በዶ/ር አየለ ታደሰ

በዶ/ር አየለ ታደሰ
Aug 2019
የዲሞክራሲ ለውጥ ሽግግር ፍኖተ-ካርታ (Roadmap)

መግቢያ

ፍኖተ-ካርታ ማለት በጣም አስቸጋሪ የሚመስሉ ግን ሊተገበሩ የሚችሉ ድርጊቶችን ወይም ሥራዎችን በጊዜ ቀመር አስቀምጦ መተግበር ማለት ነው። በሌላ አገላለፅ ፍኖተ-ካርታ ማለት ሥራን በጊዜ፤ በዘዴና በዕቅድ ለመምራት የምንጠቀምበት ንድፍ ማለት ነው።

ለዲሞክራሲ የሚደረገው ትግል ግቡንና ውጤቱን በትክክል ካልተነደፈ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም። ብዙ የሕይወትም ሆነ የንብረት መስዋዕት ይገብራል። እንዲያውም አገርን ለፖለቲካ አምባገነኖች አሳልፎ ይሰጣል።

አንድ የተለየ ነገር በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ሲፈጠር ሰላማዊ ሰልፍ እንወጣለን፤ ወይም ልባችን ይደማል፤ አሊያም ደስ ይለናል። አንዴ ብቻ ሳይሆን ደጋግሞ ቆም ብሎ ማሰላሰል የሚያስፈልገው “ለምን ለዲሞክራሲ የሚደረገው ትግል ላለፉት 40 ዓመታት አልተሳካም? ምንድነው ችግሩ? የሚለውን ትንታኔ መፍታት ስንችል ነው።

ስለሆነም ይህ እንደ ምሳሌ ሆኖ ለውይይት የቀረበው የዲሞክራሲ ለውጥ ሂደት (Reform) በኢትዮጵያ የሽግግር ፍኖተ ካርታ (Roadmap) ለትግል እንዲረዳ በማለት ለኢትዮጵያ ህዝብ ለውይይት አቀርባለሁ። የዲሞክራሲ ለውጥ (Reform) እና አብዮት (Revolution) ሁለት የተለያዩ ፅንሰ ሃሳቦች መሆናቸውንና – የዲሞክራሲ ለውጥ (Reform) ፅንሰ ሃሳብ አሁን ያለው አስተዳደር ባለው ሕግ ላይ አዳዲስ ሕጎችን እያወጣ የአገሪቱን የአስተዳደር አቅጣጫ (በፖለቲካ፤ ምጣኔ ሃብትና ህገ-መንግሥት) መለወጥ ሲሆን ሌላው ደግሞ የአብዮት (Revolution) ፅንሰ ሃሳብ ደግሞ በአመፅ ላይ የተመሰረተ የአስተዳደር ለውጥ ማምጣት መሆኑን አንባቢያን እንዲረዱልኝም ከወዲሁ አሳስባለሁ።

መልካም ንባብ!

ፍኖተ-ካርታ ለምን ያስፈልጋል?

በአሁኑ ወቅት ትናንሽና ትላልቅ ድርጅቶች፤ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወዘተ ፍኖተ-ካርታን ይጠቀማሉ። የተለያዩ ድርጅቶች ስራቸው ምን ያህል በተነደፈው ንድፍ መሰረት ሥራውን አስኪደዋል? ለሚለው ጥያቄ ፍኖተ-ካርታው መልስ ይሰጣል። የፍኖተ ካርታ ንድፍ አንዴ ከልምድ በመነሳት ይነደፋል። የፍኖተ ካርታ ንድፉ የሚጠቀልለው የሚሰሩትን ስራዎች፤ የሚፈጀውን ጊዜ፤ በማን? ምን? እነደሚከናወን ነው። ንድፉ ከተነደፈ በኋላ ስራው በትክክል በጊዜው ተፈፅሟል? ወይስ ምን ብናደርግ ነው በጊዜው መጨረስ የምንችለው? በሚለው ዙሪያ ይገመገማል።

ለፖለቲካ ትግል ፍኖተ ካርታን መጠቀም አስፈላጊ ነው?

በፖለቲካ መስክም ሲታይ ፍኖተ-ካርታ እጅግ ጠቃሚና ሰላማዊ የመታገያ መሳሪያ ነው። በገፅ 4 ላይ የሽግግር መንግሥት ፍኖተ-ካርታ ቀርቧል። ይህ የሽግግር መንግሥት ፍኖተ-ካርታ የሚያስፈልገው በንድፉ መሰረት ስራው ተከናውኗል? ወይስ አልተከናወነም? የሚለውን ለመገምገም ነው። በሌላ በኩል የሥራው ኃላፊነትን ለማንና? ለምን? እንደሚሰጥ ለመመደብና ማንም ግለሰብ ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ ለማወቅ ይረዳል።

በተግባር የተፈተነ ፍኖተ-ካርታ[i]

የሽግግር መንግሥት ፍኖተ-ካርታ ለመንደፍና ተግባራዊ ለማድረግ መጀመሪያ በተግባር የተፈተነ ፍኖተ ካርታ መፈለግ ያስፈልጋል። ይህ የሽግግር መንግሥት ፍኖተ-ካርታ በ1990ዎቹ መጀመሪያዎቹ ላይ በምስራቅ አውሮፓ ውስጥ በተግባር ተፈትኖ የወጣ ነው። የምስራቅ አውሮፓ አገራት ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር ይህን የመሰለው ፍኖተ ካርታ ምሁራን ባወጡበት ወቅትም አፅናፍ በያዙ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ከፍተኛ ውግዘትን አስተናግዶ ነበር። ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር የፈጀባቸው ጊዜ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወራት ብቻ እንደነበር የምስራቅ አውሮፓውያን ታሪክ ያስተምረናል።

የምስራቅ አውሮፓ የሽግግር መንግሥት ፍኖተ-ካርታ በተለይም አሁን ላለችው ኢትዮጵያ እንዲስማማ አድርጎ ለማቅረብ ደግሞ የተለያዩ ሁኔታዎችን መጨመርና ለወቅቱና ተስማሚ እንዲሆን ማሻሻል አስፈላጊ ነው።

በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲ ሽግግር ፍኖተ ካርታ የሚፈጀው በጊዜ ሲተመን አጠረ ቢባል አንድ ዓመት ከሶስት ወር ሲሆን በጣም ረዘመ ቢባል ሁለት ዓመት ብቻ ነው።

ይህ ሽግግር በታለመለት ጊዜ እንዲሳካ ካስፈለገ ሁለት ነገሮች መሟላት አለባቸው።

1) ሕዝቡ ራሱ የፍኖተ ካርታ ንድፍ ይዞ የመሪነት ሚና ይዞ ሲጫወትና

2) አገር ወዳድ፤ ልበ-ቅን፤ ለራሱ የስልጣን ጥቅም ያልቆመ አመራር ሲኖር ነው።

ከላይ በገፅ 4 ላይ የሚገኘው ፍኖተ-ካርታ በተግባርና በጊዜ ሲተነተን፤

ሀ) ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን

ይህንን ተግባር ለማከናወን የሚፈጀው ሶስት ወራት (90 ቀናቶች) ነው። የሚከተሉት ስራዎችን ይጠቀልላል።

አሁን ያለው የኢህአዴግ ፓርላማ የተለያዩ ህጎችን እንዲያወጣ ማድረግ

 • በተለይም የክልል ወታደሮችን ማፍረስ፤
 • አንድ የኢትዮጵያ ሰራዊት መገንባት፤
 • የተፈናቀሉትን ኢትዮጵያውያን ወደቦታቸው እንዲመለሱ።

ለ) የዲሞክራሲ ለውጥ ጅማሮ

ይህንን ተግባር ለማከናወን የሚፈጀው ሁለት ወራት (60 ቀናቶች) ነው። የሚከተሉት ስራዎችን ይጠቀልላል።

አሁን ያለው የኢህአዴግ ፓርላማ

 • የዲሞክራሲ ጥቅል* ማሳለፍ ይጠበቅበታል።

* የዲሞክራሲ ጥቅል ሲባል በነፃነት የመሰብሰብን፤ የመደራጀት፤ የመፃፍ፤ የፖለቲካ ፓርቲን መስርቶ የመወዳደርን፤ በዘርና ቋንቋ ላይ የተመሰረተውን ክልልና ህገ-መንግስት የመለወጥ መብትን ይጠቀልላል።

 • ፓርላማው ራሱን ማክሰም ይጠበቅበታል።
 • በወረዳ፤ በአውራጃ እንዲሁም በክልል ደረጃ ያሉት ካድሬዎችም ስራቸው ያከስማል።

ሐ) የተወካዮች ምርጫ ማካሄድ

ይህንን ተግባር ለማከናወን የሚፈጀው ሁለት ወራት (60 ቀናቶች) ነው። የሚከተሉት ስራዎችን ይጠቀልላል።

አሁን ያለው የምርጫ ቦርድ በዲሞክራሲ ጥቅል ሕግ መሰረት

 • ሕዝቡ በነፃነት እንዲደራጅ ያበረታታል።
 • በነፃ ውድድር ተወካዮችን ያስመርጣል።
 • የምርጫ ቦርዱ ተወካዮችን ካስመረጠ በኋላ ራሱንም ያከስማል።

መ) የሕዝቡ ተወካዮች ስራውን ይጀምራል።

ይህንን ተግባር ለማከናወን የሚፈጀው አራት ወራት (120 ቀናቶች) ነው። የሚከተሉት ስራዎችን ይጠቀልላል።

የተመረጡት የሕዝቡ ተወካዮች በሶስት ወይም በአራት ንዑሳን ቡድኖች ለምሳሌ ፖለቲካውን፤ ምጣኔ ሃብቱን እንዲሁም ሕገ-መንግስቱን ወዘተ ንዑሳን ቡድኖች፤ በመከፋፈል ስራውን ይሰሩታል።

፩) የፖለቲካው ንዑስ ቡድን

የተለያዩ የውይይት መድረኮችን ያዘጋጃሉ። የፖለቲካው ንዑስ ቡድን የሚከተሉት ስራዎችን ያከናውናል።

 • አዲሱ የምርጫ ቦርድ አመሰራረት ሕግ ያረቅና ከሕገ መንግሥቱ አርቃቂ ንዑስ ቡድን ጋር በጋራ ይሰራል።
 • የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴት እንደሚመሰረቱ ሕግ ያረቅና ከሕገ መንግሥቱ አርቃቂ ንዑስ ቡድን ጋር በጋራ ይሰራል።
 • ከሕዝብ ጋር እየተመካከረ ሕጉን ያረቃል።
 • ወዘተ

፪) የምጣኔ ሃብት ንዑስ ቡድን

የምጣኔ ሃብት ንዑስ ቡድን የሚከተሉት ስራዎችን ያከናውናል።

 • የምግቡን ፍጆታና አቀራረብ በማመጣጠን ዋጋውን ያረጋጋል። የዋጋ ንረቱን ይቆጣጠራል። ወደ ውጪ የሚወጡትን የምግብ ሸቀጥ ላይ ቁጥጥር ያደርጋል።
 • የአገሪቱ ውጪ ብድር ዕዳ ምን ያህል ይሆናል? ምን ያህሉ ጥቅም ላይ ዋለ? ምን ያህል የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ብድሮች አገሪቱ አለባት? የጥናት ሰነድ በማዘጋጀት ለሕዝቡ ያቀርባል። ይህ የምጣኔ ሃብት የጥናት ሰነድ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ፕሮግራማቸው ውስጥ በማካተት እንደ አንደኛው የመወዳደሪያ ነጥብ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
 • ወዘተ

፫) ሕገ መንግሥት አርቃቂ ንዑስ ቡድን

የሕገ መንግሥቱ አርቃቂ ንዑስ ቡድን የሚከተሉት ስራዎችን ያከናውናል።

 • ሕገ መንግሥቱ እንዲረቀቅ ይደረጋል። ነገር ግን አንድ ወይም ሁለት የውሳኔ አንቀፆች በጊዜያዊነት ክፍት ይሆናል።
  • እነዚህ አንቀፆች ከመረቀቃቸው በፊት በሕዝቡ ውሳኔ ይሰጥበታል። ኢትዮጵያ የምትዳደርበት ሁኔታ ላይ ውይይት ይካሄዳል። በፕሬዝዳንት፤ በህገ-መንግሥታዊ ዘውዳዊ ንጉሥ፤ ፌደራሊዝም ወዘተ ሕዝቡ እንዲመርጥ ዕድል ይሰጠዋል።
  • የሕዝቡ ተወካዮች ባወጡት ህግ መሰረት የተቋቋመው የምርጫ ቦርድ የመጀመሪያው ስራው ይህ ይሆናል።
 • የሕዝቡ ተወካዮች ከሕዝቡም ሆነ ከሌሎቹ ንዑሳን ኮሚቴዎች ጋር እየተወያየ ሕገ – መንግሥቱን ያረቃል።
 • ሕዝባዊ መዋቅሮች እንዴት እንደሚዋቀሩ ህግ ያወጣል። ወዘተ

፬) ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ንዑሳን ክፍሎች ለምሳሌ እንደ ሕዝባዊ እርቅ ሆነ ሌላች ንዑሳን ኮሚቴዎች እንደ አስፈላጊነቱ ይቋቋማል።

 • ሕዝባዊ እርቅ በጅምላ ሳይሆን ጥፋተኞች በህጉ መሰረት እየተቀጡ እርቁ እንዲቀጥል ማድረግ ይቻላል።
 • ወዘተ

ሰ) ሕዝባዊ ምርጫ

ይህንን ተግባር ለማከናወን የሚፈጀው ሦስት ወራት (90 ቀናቶች) ነው። የሚከተሉት ስራዎችን ይጠቀልላል።

ምርጫው የሽግግር ጊዜ ስለሆነ በሦስት ደረጃ ይካሄዳል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝቡ ተወካዮች ባወጡት ህግ መሰረት ይመሰረታሉ፤ ይመዘገባሉ፤ በየደረጃው በሚያገኙት ነጥብ መሰረት ይዋሃዳሉ። ምርጫው በሦስት ደረጃ ይካሄዳል።

1) በወረዳ ደረጃ፤ አንድ ወር (30 ቀናቶች)

2) በአውራጃ ደረጃ፤ (30 ቀናቶች)

3) በአገራዊ ደረጃ፤ (30 ቀናቶች)

ረ) የዲሞክራሲ ሽግግር ወቅት ፍፃሜ

ይህ የመጨረሻው ደረጃ ሲሆን ፍፃሜው የሚጠቃለለው

 • የሕዝቡ ተወካዮች ስራቸውን ያጠናቅቃሉ። ወደ ቀደመው ስራቸው ይመለሳሉ።
 • አሸናፊዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፓርላሜንቱን ይረከባሉ።
 • ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ይመራል።

ማጠቃለያና ጥሪ

የዲሞክራሲ ለውጥ (Reform) ፅንሰ ሃሳብ አሁን ያለው የኢህዴግ አስተዳደር ባለው ሕግ ላይ አዳዲስ ሕጎችን እያወጣ የአገሪቱን የአስተዳደር አቅጣጫ (በፖለቲካ፤ ምጣኔ ሃብትና ህገ-መንግሥት) መለወጥ ነው። ፍኖተ ካርታም ነድፎ መንቀሳቀስ የሰላማዊ ትግል አንደኛው ስልት ነው። ከዚህ በኋላ ግን ሕዝቡ ፍኖተ ካርታ ነድፎ ለመንግሥት በማቅረብ ተጠያቂነትን ማጠናከር ይኖርበታል። ይህንንም በገፅ 4 ላይ የተነደፈው ፍኖተ ካርታን እንደ ምሳሌ በመውሰድ ሕዝቡ ባገኘው መንገድ ሁሉ ማለትም በስብሰባ፤ በቴሌ ኮንፍረንስ ወይም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እንዲወያይበትና አንድ ወጥ የሰላማዊ ትግል ፍኖተ ካርታ እንዲዘጋጅ ለኢትዮጵያውያን ጥሪዬን በማክበር አቀርባለሁ።

አስተያየት ወይም ጥያቄ ካሎት tayele@yahoo.com

[i] ማመልከቻ ለክቡራን ኢትዮጵያውያን – ክፍል 1ን www.ethiopia.org ድረ ገፅ ላይ ይመልከቱ

 

2 COMMENTS

 1. Ethiopia is unlucky country. Every Tultula tries to sell himself or herself as a brilliant mind and good political analyst on the Ethiopian political affairs.

  This guy is another Dawit Woldegiogies, Eskinder Nega or Ermias Legesse. It is better for him if he apply for a lucrative business by the Addis Ababa Balderas. Also he can keep on barking like a mad dog.

 2. Reply to Gamadaa

  ይገርማል! ዘ ሐበሻ ላይና ሳተናው ድረ ገፅ ላይ የሰጠኽው አስተያየት በነጥብም አይለያይም፡፡ ስለ አስተያየትህ አመሰግናለሁ፡፡
  Gamadaa “This guy is another Dawit Woldegiogies, Eskinder Nega or Ermias Legesse”

  በ”የዲሞከራሲ ለውጥ ሸግግር ፍኖተ ካርታ” ገፅ 3 ላይ ያለውን አሰተያየት ልብ ብለህ ያነበብከው አልመስለኝም፡፡ ካልሆነም ልጥቀስልሁ አንዲህ ይላል “የምስራቅ አውሮፓ አገራት ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር ይህን የመሰለው ፍኖተ ካርታ ምሁራን ባወጡበት ወቅትም አፅናፍ በያዙ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ከፍተኛ ውግዘትን አስተናግዶ ነበር።”
  ለማብራራት ያህል “አፅናፍ” በረገጡ ግለስቦች ይህን የመሰለ የስድብ ውርጅብኝን ደርሶባቸው ነበር፡፡ “አፅናፍ” ከረገጡ ግለስቦች መልካምና ገንቢ ቃላት አይጠበቅም፡፡ አሁንም በድጋሚ ”የዲሞክራሲ ለውጥ ሸግግር ፍኖተ ካርታ”ን ስላነበብከው አመሰግናለሁ፡፡
  አየለ ታደሰ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.