ሜሮን አለማየሁና ዳዊት አስራደ 14 ቀን ተቀጠረባቸው

ነገረ ኢትዮጵያ

Dawit Asrade
ዳዊት አስራደ
Meron
ሜሮን አለማየሁ

መንግስት ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም የአይ ኤስ አይ ኤስን ድርጊት ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ በተነሳበት ተቃውሞ ሰበብ ግንቦት 4/2007 ዓ.ም ተይዛ የታሰረችው የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሜሮን አለማየሁ እንዲሁም በሰልፉ ወቅት ከተያዘ በኋላ በ25 ሺህ ብር ዋስ ወጥቶ እንደገና የታሰረው የቀድሞው አንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የነበረው ዳዊት አስራደ ዛሬ ግንቦት 7/2007 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት ቀርበው ለግንቦት 21 ቀን ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ሜሮንና አቶ ዳዊት ሚያዝያ 5/2007 ዓ.ም ንፋስ ስልክ ላፍቶ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቀርበው በዋስት እንዲወጡ ተፈቅዶላቸው የነበር ቢሆንም ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመጣስ ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በማዛወር በእስር ላይ እንዲቆዩ አድርጓል፡፡ በዛሬው ፍርድ ቤት ፖሊስ ሜሮንና አቶ ዳዊት ከአሁን ቀደም ተከሰውበት ዋስትና ከተፈቀደላቸውና ዋስትና ከማያስከለክለው ‹‹ሁከትና ብጥብጥ መፍጠር›› ያልተለየ ክስ ያቀረበ ቢሆንም የጠየቀው 14 ቀን ተፈቅዶለታል፡፡
ሜሮንና አቶ ዳዊት አስራደ የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው እንደነበርና ይህም በህገ ወጥ መንገድ መጣሱን፣ ያለ አግባብ ወደ ሌላ እስር ቤት መዛወራቸውን፣ ክሱ ዋስትና የማያስከለክል መሆኑንና እነሱም ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ቢጠይቁም ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያደርግ በመግለጽ ዋስትና እንዳይሰጥበት ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱም ፖሊስ ያቀረበውን በመቀበል 14 ቀን ቀጥሮባቸዋል፡፡