ሀበሻ ጉድህን ስማ! የጭካኔ ደረጃዎችን ልጠቁምህ አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)

የአሁኑ የሀገራችን ጉዳይ ዕረፍት እንደሚነሣ ለማንኛውም ወገን ግልጽ ሆኗል፡፡ እርግጥ ነው – ወቅቱ ብዙ የሚወራበት አይደለም፡፡ በሩጫ ከኢትዮጵያ የሚወጡበትና ሕይወትን የሚያተርፉበት ወይም በሩጫ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበትና የሀገርንና የሕዝብን ኅልውና የሚታደጉበት የሁለት አስቸጋሪና ጠባብ አማራጮች ጊዜ ነው፡፡ ምርጫው የኛው ነው፡፡ መተኛት ግን ፈጽሞ አያዋጣም፡፡

በሀገራችን ብዙ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ከ100 በላይ ናቸው ይባላል፡፡ ሁሉም ግን ከእንጀራ ገመድ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ከሀገር ዕድገትና ከጤናማ የሃሳብ ልዩነት ጋር የተያያዙ አይደሉም፡፡ እንደምንሰማው ከጥቂት ዘመድ አዝማድ ጀምሮ እስከ ቅርብ ጓደኛማቾች የሚመሠርቷቸው ፓርቲዎች አሉ፡፡ ወያኔ ራሱ ከዱርየዎችና ከሥራ አጥ ቦዘኔዎች በመምረጥ ሳልቫጅ ኮትና ጃኬት እያለበሰ በፓርቲ አመራርነት የሚሰይማቸው መቀለጃ ዜጎችም ነበሩ –  የአእምሮ ዘገምተኞችን ሳይቀር በከፍተኛና መካከለኛ የሥራ አመራር እርከኖች ከመመደቡ በተጓዳኝ፡፡ ወያኔ እኮ አሮጌ ኮት፣ የነተበ ጂንስ ሱሪና አሮጌ እስኒከር አስለብሶ “‹እንዲህ የሚባል› ፓርቲ ሊቀ መንበር ስለምርጫው ዛሬ መግለጫ ሰጡ” እያስባለ በኢቲቪ የሚቀልድ የፍየል ዐይን በጨው አጥቦ የበላ ወመኔ ነው፡፡ አሁንም ያ አሠራር ስለመቆሙ አናውቅም፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ብለው የሚመሠረቱ ፓርቲዎች ከአንድ እጅ ጣቶች አይበልጡም፤ እነሱም በብዙ ችግር የተተበተቡ ናቸው፡፡ ሰዎች ሥራ ሲያጡ፣ ሰዎች ሥራ ሠርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ማኖር ሲያቅቸው ቀላሉ አማራጭ ፖለቲካ ውስጥ ገብተው ሕዝብንና ሀገርን በማደናበር የዕለት ዳቦን ማሸነፍ ነው፡፡ አብዛኛው የፓርቲ መሥራች ዜጋ የኋላ ታሪክ ቢታይ ከቀማኛና ከአውቶቡስ ውስጥ የኪስ ሌባ አያልፍም፡፡ የፖሊስ ሠራዊት ለፖሊስነት ሥራ ሌቦችን መልምሎና አሰልጥኖ ከቀጠረ፣ ፖለቲከኞችም አጭበርባሪዎችንና በትምህርት ያልገፉ ቅን ታዛዦችን መልምለው በፓርቲዎች ቢያደራጇቸው ሁለቱም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ሰው ሲቸግረው አንድም ሃይማኖቱን በመቀያየርና በየሥርቻው “ቸርች” በመመሥረት ከቀጣፊ ባልደረቦቹ ጋር የሕዝብን ማጅራት ይመታል – እነታምራት ላይኔንና በየመንደሩ እንደ አሸን የፈላውን “ፈዋሽ” ፓስተር ያስታውሷል፡፡ አለበለዚያም ፓርቲ መሥርቶ ሕዝብን እየቀፈለና እያምታታ በሚያገኘው ገንዘብ ይኖራል – ሆድ እኮ ዕዳ ነው፤ የኅሊናን ሚዛን የሚያዛባ አዋራጅ ዕዳ፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ያለች የመሠሪዎች መጫወቻ ሆና ቀረች፡፡ እጅግ ያሳዝናል፡፡ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ እንዳለመሆን ትልቅ ፀጋና በረከት የለም፡፡ እውነቴን ነው፡፡

ከነዚህ ትላልቅ ከሚባሉት ፓርቲዎች እጅግ ብዙዎቹ አረመኔዎች ናቸው፡፡ ከአባላቱና ከአመራሮቹ ብዙዎቹ ሃይማኖትና ባህል፣ ሞራልና ዲስፕሊን ስለሌላቸው ጭካኔያቸው ወደር የለውም፡፡ የእናታቸውን ልጅ እንኳን አይምሩም፡፡ የዝናና የገንዘብ ፍቅር ስለሚያናውዛቸው ከፊታቸው የሚቆምን ሁሉ እያጨዱ ወደፊት ይገሰግሳሉ፡፡ በዚህ መልክ ከሚኖሩት ውስጥ በጭካኔ ደረጃ ቀጥለን የተወሰኑትን እንይ፡፡

  1. ኦነግ – ይህ ድርጅት በዐረመኔነቱ ተስተካካይ የለውም፡፡ ብዙ ምሣሌዎችን መጥቀስ ቢቻልም አንዲቷን ብቻ ልናገርና ወደቀጣዩ ዐረመኔ ልለፍ፡፡ ባለፈው ሰሞን ወለጋ ውስጥ አንድ የኦህዲድ ስብሰባ ነበር፡፡ በዚያ ስብሰባ አንድ የበርካታ ልጆች አባት “ኦነግን ለኔ ተውት፡፡ እናንተ ብቻ ጥይት ስጡኝ፡፡ ቢያንስ በኛ ወረዳ መግቢያ መውጫ አሳጥተን እናባርረዋለን›፡፡…” በማለት ይናገራል፡፡ አንድ ባላገር ማይም ሰው እንዲህ ማለቱ ብቻውን እንደኅልውና ሥጋት ሊቆጠር አይገባውም ነበር፡፡ ይህን የሰማው ኦነግ “ጀግንነቱ”ን እንዴት እንዳሳየ ብትሰሙ ትገረማላችሁ፡፡ ሁለት ወታደሮቹን ወደዚያ ሰውዬ ቤት በመላክ የዚያኑ ቀን ማታ በቤተሰቡ መሀል ያን ምሥኪን ሰውዬ ግምባሩን በታትኖ ገደለው፡፡ ይህ ጀግንነት አይደለም፡፡ አለቃቸው ለይስሙላና ለንግግር ጥፍጥናም ቢሆን  “መግደል መሸነፍ ነው” ያለውን አልተረዱትም፡፡ በመሠረቱ መግደል በጣም ቀላል ነው፡፡ ማስተማርና አእምሮን መለወጥ ግን ከባድ ነው፡፡ ለኦነግ ዓይነት ጭራቃዊ ስብስብ አእምሮን ከመለወጥ ይልቅ ሰውን ወደትቢያነት መለወጥ ቀላሉ “የማስተማሪያ” መንገድ ነው፡፡ ይህ አለመታደል ነው፡፡ አእምሮ የሌለው እንስሳ ብቻ ነው በግድያ የሚያምን፡፡ እንዲያውም አንዳንድ እንስሳት ከኦነግና ከሌሎች እርባና ቢስ ድርጅቶች በእጅጉ ይሻላሉ፡፡ ውሾች ለአብነት የጓደኛቸውን መሸነፍ እግሩን በማንሳቱ በደመነፍሳዊ ልማዳቸው ከተገነዘቡ በኋላ አይነኩትም፡፡ ከውሻ ማነስ ደግሞ የሰው ልጅ ተፈጥሮን እንድንመረምር ያስገድደናል፡፡ ስለሰደበህ መግደል? ስለዛተብህ መግደል? ሃሳቡን በነፃነት ስለገለጸ መግደል? ስላልደገፈህ መግደል? ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ይህ ዓይነት ቡድን አገር ቢገዛ አንድም ሰው አይተርፍም፡፡ ታሪኩ ብዙ ነው ወገኖቼ፡፡ ኢትዮጵያን ከዚህ ዓይነቱ ዐውሬ ይጠብቃት፡፡ ከቀጣዮቹም!
  2. ሕወሓት – ይህ ድርጅት ከመነሻው ራሱን በራሱ ሳይቀር እየበላ ነው ለትልቅ ሀገራዊ ጥፋት የደረሰው፡፡ ለመግደልና ለማሰቃየት ወደኋላ አይልም፡፡ የማሰቃያ መንገዶቹን ደግሞ አንዳንዶቹን ሰይጣን ራሱም አያውቃቸውም፡፡ እጅግ ሲበዛ ዐረመኔ ውድብ ነው፡፡ አለቃው “ጓሓፍ ጽረጉለይ” በሚለው “ቆሻሻን አስወግዱልኝ” ንግግሩ ይታወቃል – “የሚቃወሙኝን ግደሉልኝ” ማለቱ ነው በግልጽ አማርኛ፡፡ ከዕኩይ ዓላማው የሚያናጥበው መስሎ የታየውን ግለሰብም ይሁን ድርጅትና ፓርቲ አፈር ከመሬት ካልደባለቀ ዕረፍት የሚባል ነገር የለውም፡፡ በተለይ አማራውን ሕዝብ ቁጥሩ በሚሊዮኖች በሚቆጠር ደረጃ ከምድረ ገጽ እንዳጠፋ መዛግብት ይመሰክራሉ፡፡ ወያኔ ወይም ሕወሓት በጭካኔው ከኦነግ ጋር ቢስተካከል እንጂ ብዙም አያንስም፡፡ ከኦነግ በመጠኑ የሚለየው በል ሲለው በትንሹም ቢሆን ማሰብ መቻሉና አንዳንዴ ለራሱ ጥቅም ሲል ይሉኝታን ማስታወሱ ነው፡፡ ኦነግ ጭንቅላት የሚባል ነገር ጨርሶውን የለውም፡፡ በ“ዘራፍ” ብቻ የታወረ በመሆኑ ለሁሉም ችግሩ መፍትሔ መግደልና መደምሰስ ብቻ ነው፡፡ በዘረፋና በቅሚያም ከወያኔ አይተናነስም፡፡ አንድ ዓመት እንኳን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ 23 የሚደርሱ ባንኮችን እንደዘረፈ ታሪክ መዝግቦለታል – ዕድሜ ለኦህዲድ፡፡ በጌታዋ የተማመነች በግ ገና ብዙ ጅራቶችን ማነው ባንኮችን ትዘርፋለች፡፡ ታዲያን የኢትዮጵያ ሕዝብ በደምብ ተኛ! ተኩላና ጅብ ሲተኙላቸው ይወበራሉ፤ ጉልበታቸው አይቻልም፡፡ እናም ቶሎ ለመጥፋት በደምብ እንተኛ፡፡
  3. ግንቦት ሰባት – ይህ ድርጅት አንዱ የኢሕአፓ ቅሪት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ኢሕአፓ ደግሞ በተለይ የዱሮው በግድያ የሚያምን ድርጅት ነው፡፡ ግንቦት ሰባትም ከወያኔ በማይናነስ መልኩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን በማጥፋት ረገድ እጅግ ጨካኝ ነው፤ በብዙ የደምና የአጥንት ደለል ላይ የቆመ ድርጅት እንደሆነ ከሚያማምሩ መግለጫዎቹና የጋዜጣ መጣጥፎቹ በተጓዳኝ በሚከፈት የሕይወት ስንክሳሩ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ የአመራር አባላቱም ከእግዜር ቀርቶ ከፈሳቸው የተጣሉ ናቸው ይባላል፡፡ የተሞሉት ልክ እንደላይኞቹ ሁሉ በአሉታዊ ኃይል (Negative Energy) ነው፡፡ ይህን አፍራሽ ኃይል ወደ ገምቢ ኃይልነት ቢለውጡት (Positive Energy ቢሆን) ብዙዎቹ ካላቸው የዕድሜ ተሞክሮም ሆነ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ አኳያ ለሀገርና ለወገን ብዙ ጥቅም ሊሰጡ ይችሉ ነበር፡፡ እንደመጥፎ ዕድል ሆኖ ግን ከቀደምት የደርግና የሕወሓት አጥፊ መስመር የቀሰሙት መጥፎ ትምህርት አመዝኖባቸው የነሱም መመርያ “ውቃው”ና “በለው” ከመሆን አልዘለለም፤ ይህ ደግሞ ለነሱም ለሀገርም አጥፊ ነው፡፡ እንደትምህርታቸውና እንዳነጋገራቸው ቢሆን ኖሮ ሀገራችንን በብዙው ሊጠቅሙ የሚችሉበት ዕድል ነበራቸው፡፡ ይሁንና ሙሌታቸው ክፋትና ተንኮል፣ ንባባቸው “The Prince” እንዲሁም አስተዳደጋቸው ሸፋፋ በመሆኑ ይመስላል መጠፋፋትንና መገዳደልን ባህል አድርገው በዚህ ሰለጠነ በሚባል ዘመን ሳይቀር የሙጥኝ ይዘውታል፡፡ አመለካከታቸውና ፍልስፍናቸው በአብዛኛው ሸውራራ ነው፡፡ አንድን ነገር በበጎ ጎኑ ለመቀበል ይቸግራቸዋል፡፡ የዚህ ባሕርያቸው መነሻ ምናልባት ከልጅነታቸው ጀምሮ የተጎዳ ሥነ ልቦና ስላላቸውም ሊሆን ይችላል፡፡ የሁሉን ዐዋቂነት አባዜም ሳያስቸግራው የሚቀር አይመስልም፡፡ መጥፎ ችግር ነው ይሄ፡፡ መድኃኒትም በቀላሉ አይገኝለትም፡፡ “በትምህርትም፣ በዕውቀትም፣ በልምድና ተሞክሮም፣ በአደረጃጀትም፣ በተሰሚነትም፣ በብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ድጋፍም፣ በሙያዊ ብቃትም… ከኛ በላይ ላሣር ነው” ብሎ ስለራሱ ጣርያ የነካ ግምት ያዳበረ ሰው ወይም ቡድን ከእውነታው ጋር እንደተቃረነና እንደተላተመም ያረጃል እንጂ አንዳችም አወንታዊ ነገር ያበረክታል ተብሎ ደግሞ አይገመትም፡፡ ለዚህም ይመስላል እነዚህን መሰል ድርጅቶች ለፖለቲካው ይጠጌ አይነኬ (asymptote) እንደሆኑ ግማሽ ክፍለ ዘመንን ያህል ረጂም ጊዜ ፉት ሲሉት የሚስተዋሉት፡፡ “ሸርሙጣ ስታረጅ አቃጣሪ ትሆናለች” እንደሚባለው አሁን አሁን ደግሞ በአንዳንድ የዋሃን ዘንድ የት ይደርሳሉ የተባሉ ግንቦት ሰባትን መሰል ንቅናቄዎች ለይቶላቸው ፀረ-ዴሞክራሲ መሆኑ በአደባባይ ከተመሰከረለት የዶክተር አቢይ ዘረኛና ዕኩይ “መንግሥት” ጋር በማበር ሚዲያዎቻቸውን ጨምሮ ሁለመናቸውን ለዚህ መንግሥት ገብረዋል፤ አንዳንዶቹ ዘልለው እንደገቡ ዘልለው መውጣት አፍረው በስማም እንደተባለበት ሰይጣን ፀጥ ረጭ ብለዋል፡፡ ይህም አሳዛኙ መጨረሻቸው ነው፡፡ ሁሉም የሚያልፍ መሆኑ ደግሞ ጥሩ ነው፡፡

እነዚህ በሚገኙበት የፖለቲካ መድረክ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲና ፍትህ ይመጣል ብሎ ማሰብ ቂልነት ነው፡፡ ሁሉም ፊደሎች እስኪያልቁ የፓርቲ ስሞች ቢመሠረቱና መልከ ጥፉዎችም በስም መለዋወጥ እየተደገፉ ሀገራዊ ምስሉ በዚህ ሁኔታ ቢቀጥል ዴሞክራሲ የገደል ላይ ወይን እንደሆነች ትቀራለች እንጂ አንድም ለውጥ አይኖርም፡፡ ሰዎች “ስንተዋወቅ አንተናነቅ” የሚሉት ወደው አይደለም፡፡ እርግጥ ነው – ሌባን ሌባነቱን ማሳመን አይቻልም፡፡ ውሸታምን ስለውሸታምነቱ መከራከር ጉንጭን ማልፋት ነው – አያምንምና፡፡ በግትርነት የተዘጋን አእምሮ መክፈት የሚቻለው አንድም ምድራዊ ኃይል የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰይጣን ራሱ እንኳን በእግዚአብሔር እንዲያምንና ወደ ገነት እንዲመለስ ቢሰበክ እሽ አይልም፤ እነዚህ ኢትዮጵያውያን አጋንንትም ልክ እንደባሕርይ አባታቸው እንደ ሊቀ ሣጥናኤል በድርቅናቸው ጸንተው የመጨረሻ ዕድላቸውን ይጠባበቃሉ እንጂ እመኑኝ ሀገርና ሕዝብ ወደሚፈልጉት የጋራ መድረክ አይመጡም፡፡ ከጅብ ጅማትና ቁርበት የተሠራ ከበሮ ሲመቱት እንብላው እንጂ እንተወው አይልም፡፡ ስለዚህም…

ስለዚህም ሕወሓትም ሆነ ግንቦት ሰባት ወይም ኦነግ የዴሞክራሲ ምሠሦዎቻችን ናቸውና እንንከባከባቸው፤ እናፍቅራቸው …. ከዚያም ተጋግዘን እንሣቅ …. ቂቂቂቂቂ፡፡

እግዚአብሔር ሀገረ ኢትዮጵያን በምሕረት እጆቹ ይዳብሳት፤ ከተደገሰላት የዕልቂት ዐዋጅም በአፋጣኝ ይታደጋት፤ አሜን፡፡

3 COMMENTS

  1. ወዳጄ ጽሁፉ ጥሩ ነበር በአብኖች ባይጻፍ፡፡

    ኦነግ= ወያኔ = አብን

    ዋናዎቹ የኢትዮጵያ ጠላቶች!!!!!!!!!!!!

  2. በጣም ጎበዝ ! በቀላልና በሚገባ ቋንቋ ያለውን የፖለቲካ ሂደት ገልጸሀዋል። በርታ !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.