የዓለም ባንክና ዓለም አቀፍ የገንዘብ አቅርቦት ተቋም በታዳጊ አገሮች ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ (በገ/ክርስቶስ ዓባይ)

በገ/ክርስቶስ ዓባይ                                                  ነ
ሐሴ 5 ቀን 2019 ዓ/ም

ስለ ዓለም ባንክና የዓለም አቀፉ የገንዘብ አቅርቦት ተቋም ከአሁን ቀደም “ትንቢት ይፈጸም ዘንድ የግድ ነው፤ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” በሚለው ጽሑፌ በይበልጥ ለማብራራት ቃል በገባሁት መሠረት ‘የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ’ እንዲሉ ይኸው ተከስቻለሁ።

እነዚህ ሁለት ተቋማት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሲሆኑ በይበልጥ ጠንክረው የሚሠሩት የአሜሪካንን ፖሊሲና ጥቅም ለማስጠበቅ ነው። እንግዲህ እግዚአብሔር ያሳያችሁ! ፖሊሲ የሚለውን ብቻ ብንመለከት እንኳ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ ለማሰብ ከአእምሮ በላይ ነው። በአጭሩ ለመግለጽ ያህል ከአሜሪካ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፤ ከአሜሪካ የቴክኖሎጂ ፖሊሲ፤ ከአሜሪካ የፖለቲካ ፖሊሲ፤ ከአሜሪካ የማኅበራዊ ፖሊሲ……. ምን አለፋችሁ ኅልቆ መሳፍርት የለውም።

ስለሆነም በማንኛውም ዘርፍ የአሜሪካ ተቀናቃኝ የሆነ ማንኛውም አገር በእነዚህ ሁለቱ ግዙፍ ተቋማት ትብብር ድባቅ ይመታና መንግሥቱ ይሽመደመዳል፤ አስተዳደሩ ይናጋል። ሁኔታው የሕዝብን አመጽ በመቀስቀስ የዚያን አገር መሪ ለመለወጥ እስከማሴር ይሄድና ከፍተኛ ለሆነ ደም መፋሰስና ዕልቂት ምክንያት እስከመሆን ይደርሳል። እጅግ በጣም የሚገርመው ደግሞ የዚህ ሤራ ዋና ተዋናኝ በመሆን አገራቸውንና ሕዝባቸውን ለከፍተኛ ችግር እንዲዳረግ በተባባሪት ግምባር ቀደም ቅጥረኛ ሆነው የሚሠሩት አውቀናል የሚሉት ምሁራን መሆናቸው ነው።

ይህን አስተሳሰብ ግልጽ ለማድረግ አንዳንዶቹን እያነሳን በምሳሌ መመልከቱ ይበጃል። በቅድሚያ እስኪ የኢኮኖሚ ፖሊሲውን እንይ። አንድ ሀገር የአሚሪካን ሠራሽ ዕቃ ወደ ሀገሯ እንዳይገባ ብታደርግ የሚደርስባትን በምሳሌ እንመልከት።

ታይላንድ በሕግ ደረጃ ሲጋራ ማጨስን ከማይደግፉ የዓለም አገሮች አንዷ ናት። በዚህም ምክንያት ምንም አንኳ ሲጋራ ለሚፈልገው ሰው የማግኘት ችግር ባያጋጥምም፤ሲጋራ እንደ ማንኛውም ሸቀጣ ሸቀጥ በመደርደሪያ ተቀምጦ ለሕዝብ እየታዬ አይሸጥም። በጣም ትላልቅ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች፤ ሲጋራ የመሸጥ ፈቃድ ይሰጣቸዋል። እንዲህም ሆኖ ወጣቱ ትውልድ ወደ ሲጋራ ማጨስ ክፉ ልማድ እንዳይሳብ፤ የአገሪቱም ኤኮኖሚ ለገንዘብም ሆነ ለጤና ጠንቅ በሆነው ትምባሆ እንዳይባክን፤ ከውጭም እንዳይገባ፤ በሕግ ተደንግጓል።

በተለይ እኤአ በ1992 በተደነገገው መሠረት የታይላንድ ሕዝብ የሲጋራን አደገኛነት እንዲያውቅ ከፍተኛ ትምህርትና ቅስቀሳ ሲደረግ ቆይቷል። ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ወደ ታይላንድ ሲገቡ የተወሰነ ፓኮ ይዘው የመግባት ፈቃድ ቢኖራቸውም ከተወሰነው በላይ ይዞ የተገኘ ሰው ግን በየአንዳንዱ ተርፍ ፓኮ የ15 ዶላር መቀጫ እንዲከፍል ተደርጎ፤ በትርፍነት የተገኘው ሲጋራም ውርስ ይሆናል። በተጨማሪም የሲጋራ ፈቃድ ያላቸው ትላልቅ ሆቴሎች የውጭ ብራንድ የሚያስገቡ ከሆነ 71.5% ቀረጥ እንዲከፍሉ ያዛል።

ይሁን እንጂ አገሪቱ ካላት 65 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 13 ሚሊዮን የሚሆኑ አጫሾች ስለአሉ የእነርሱን ፍላጎት ለማርካት ሲባል ብቻ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጃፓን ወረራ ወቅት፤  እንግሊዝና አሜሪካ በሽርክና ያቋቋሙት BAT (British and America Tobaco) የተባለ የሲጋራ ፋብሪካ ስለነበር ከጦርነቱ በኋላ ሲወጡ ጥለውት ስለሔዱ፤ ያንን በመጠቀም ለአገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ የሚያመርት TTM (Thailand Tobaco Monopoly) የታይላንድ ትምባሆ ሞኖፖሊ የተባለ ኩባንያ አቋቁማ ስትጠቀም ቆይታለች።

ነገር ግን በዓለም የታወቀው የአሜሪካ የሲጋራ ሞኖፖል ፊሊፕ ሞሪስ (Philip Moris) ወደ ታይላንድ በመግባት ዓለማችን እየተከተለችው ባለው የነፃ ገባያ አማካይነት በተወዳዳሪነት እንዲነግድ እኤአ በ2013 ዓ/ም ለታይላንድ መንግሥት ጥያቄ ያቀርባል። የታይላንድ መንግሥትም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያደረገውን ጥናት መነሻ በማድረግ፤ በታይላንድ ከሲጋራ ማጨስ ጋር በተያያዘ በሽታ በየዓመቱ 50,700 ሰዎች እንደሚሞቱ በመግለጽ እንዲህ ያለውን ጥያቄ ተቀብሎ ለማስተናገድ እንደሚቸገር ያስረዳል።

ጉዳዩ ለዓለም ንግድ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለፊሊፕ ሞሪስ ይፈረድለታል። የታይላንድ መንግሥት ግን ውሳኔውን አልቀበልም በማለት ይግባኝ ይላል። በዚህ ጊዜ ፊሊፕ ሞሪስ ሁኔታውን ለአሜሪካ መንግሥት ያሳውቃል። የሜሪካ መንግሥትም ወዲያው የፖለቲካ ትርጉም በመስጠት “እንዴት ታይላንድ የአሜሪካንን ምርት አልቀበልም ትላለች? በዚሁ አቋማችሁ የምትጸኑ ከሆነ አሜሪካ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ከማድረግ አትመለስም በማለት በኢምባሲያቸው አማካይነት አቋሟን ለታይላንድ መንግሥት ታስተላልፋለች።

በዚህ ጊዜ የታይላንድ መንግሥት እያለቀሰም፤ እየተናደደም ቢሆን ውጤቱን ያውቃልና ሳይወድ በግድ ተቀበለው። አሁን የፊሊፕ ሞሪስ ሲጋራ በታይላንድ ውስጥ በየነፃ ገበያው ተጠቃሚ እየሆነ ነው። እዚህ ላይ አንድ ነገር ማንሳት ይገባናል። የዓለም ጤና ድርጅት የሲጋራን አስከፊነት አስመልክቶ እንኳን ገበያ ማስፋፋት ይቅርና ሕዝብ በተሰበሰበበት አካባቢ ሲጋራ ማጨስ እንዲከለከል እኤአ በ1991 ዓ/ም መመሪያ ማስተላለፉ ያታወቃል። ነገር ግን እንደ ፊሊፕ ሞሪስ ያለ ግዙፍ የሲጋራ ኩባንያ ጋር ሰፋጣ ቢገጥም፤ ዳይሬክተር ጄኔራሉን ጨምሮ ሌሎችም ኃላፊዎች በአጭር ጊዜ ይበወዛሉ። ስለዚህ ያላቸው አማራጭ ዓይኔን ግምባር ያድርገው ብቻ ሳይሆን የዝሆን ጆሮም ይጨምርብኝ በማለት ጭጭ ብለዋል።

እኤአ በታህሣሥ 1997 ዓ/ም አካባቢ የአሜሪካ የረዥም ጊዜ ወዳጅ የነበሩት የኢንዶኔዥያው ፕሬዚዳንት ሱሀርቶ በአገሪቱ ላይ እየተከሰተ የነበረውን የሩፕያ (የኢንዶኔዥያ ገንዘብ) እና ዶላር ሕጋዊና የጥቁር ገባያ ምንዛሬ በየጊዜው እየዋዠቀ ስለነበር ለዚህ ጉዳይ አስማሚ የሆነ መፍትሔ ለመስጠት ያስባሉ። በወቅቱ መደበኛው ዋጋ አንድ የአሜሪካ ዶላር በአምስት ሺህ ሩፒያ ይመነዘር ነበር። የእርሳቸው የመፍትሔ ዕቅድ ግን አንድ የአሜሪካ ዶላር በስምንት ሺህ ሩፒያ እንዲመነዘር ሲሆን ይህንኑ ዕቅዳቸውንም ለዓለም ባንክ እና ለዓለም አቀፉ የገንዘብ አቅርቦት ተቋም ያሳውቃሉ።

ሁለቱም ተቋማት እንደተነጋገሩ ሁሉ የለም አይሆንም፤ ገበያው ይወስን እንጂ አንተ በዚህ መልክ መወሰን የለብህምና አርፈህ ተቀመጥ የሚል ምክር አይሉት ማስጠንቀቂያ ይሰጧቸዋል። ፕሬዚዳንት ሱሀርቶ ግን ኮሚቴ ሰይመው ረዥም ጥናት የተደረገበት ጉዳይ ስለነበር ሊተውት አልፈለጉም። ምክንያቱም የጥቁር ገበያው የኢንዶኔዥያን ኢኮኖሚ እየጎዳው ከመሆኑም በላይ መንግሥታቸውን በከፋ ሁኔታ እየተፈታተነው መሆኑን ስለተረዱ፤ በዕቅዳቸው መሠረት አንድ የአሜሪካ ዶላር በስምንት ሺህ ሩፒያ እንዲመነዘር እኤአ. በጥር ወር መጨረሻ 1998 ዓ/ም በይፋ አጸደቁ።

ይህ ውሳኔ በተላለፈ በበነጋታው በኢንዶኔዥያ የነበሩ የአሜሪካ ኩባንያዎች በአስቸኳይ ከኢንዶኔዥያ ለቀው እንዲወጡ በኢምባሲው በኩል መመሪያ ተሰጣቸው። የዚህን እንቅስቃሴ የተመለከቱ ሌሎች ምዕራባዊ አገሮችም ይሠሩባቸው ከነበሩት የሚሲዮን አገልግሎት፤ እና የከፈቷቸውን የግል ክሊኒኮች፤ሆስፒታሎች፤ እንዲሁም ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች፤ በድንገት ዘግተው ከአገር ለመውጣት ይራኮቱ ጀመር። እነዚህ የውጭ አገር ዜጎች በባንክ የነበራቸውን የሩፒያ ገንዘብ በማውጣት ወደ ዶላር ለመቀየር ሲሻሙ፤ አንድ ዶላር ለማግኘት እስከ አሥራ ስደስት ሺህ ሩፒያ መስጠት ነበረባቸው። ከዚህም የተነሳ የልዩ ልዩ ድርጅቶች በድንገት መዘጋት በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ግርግርና ብዥታ በመፈጠሩ ሰው ሁሉ የመንፈስ መረበሽ አደረበት።

በማከታተልም የምዕራባዊያን የሜዲያ አውታሮች ቢቢሲን ጨምሮ ስለ ሱሀርቶ የአምባገነንነት አገዛዝ ታሪክ ትንታኔ በመስጠት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ማራገብ ጀመሩ። ፕሬዚዳንት ሱሀርቶ የፕሬዚዳንት ሱካሮን መንግሥት እኤአ በ1966 ዓ/ም በመፈንቅለ መንግሥት አስወግደው ሥልጣን ከወሰዱ በኋላ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር ጥሩ ወዳጅ በመሆን ለ32 ዓመታት ኢንዶኔዥያን በፕሬዚዳንትነት መርተዋል።

ፕሬዚዳንቱ ምንም እንኳ ከድሀ ቤተሰብ የተገኙ ቢሆኑም አብዛኛውን ዘመናቸውን ያሳለፉት በዓለም ከፍተኛ  የሙስሊም ሕዝብ መኖሪያ የሆነቸውን ኢንዶኔዥያን ለማዘመን በትጋት በመሥራት ነበር። በዚህም እጅግ በጣም እንደተሳካላቸው ይነገራል። ነገር ግን ቀስ በቀስ በተፈጠረው ዓለም አቀፍ የኑሮ ውድነትና የዕድገት ለውጥ ሳቢያ የሠራተኛው ደመወዝ ባለመጨመሩ፤ የእርሳቸው ባለሥልጣናትም ከላይ እስከ ታች ድረስ አንዳንድ ጉዳዮችን ለመፈጸም የደመወዛቸውን እጥረት ለማካካስ ከተገልጋዩ ሕዝብ የእጅ መንሻን መቀበል በመጀመራቸው፤ ኢንዶኔዥያን ሙስና እንደ ምስጥ ቁርጥም አድርጎ ጨረሳት።

እዚህ ላይ የህወሀት መራሹ ጠ/ሚንስትር የነበሩት ሟቹ መለስ ዜናዊ በ2001 ዓ/ም የወሰዱትን  BPR (Business Processing Re-engineering) በመባል የሚታወቀውን ይፋ የሙስና አሠራር ማስታወሱ ተገቢ ነው። በዚህ ዓይነቱ አዲስ አሠራር የአንድ ክፍል ሠራተኞች በመስማማት ጉዳይን ለማስፈጸም ከተገልጋዩ ሕዝብ በይፋ የእጅ መንሻ (ሙስና) እንዲቀበሉ የሚያደፋፍር ዘዴ እንደነበረ አይዘነጋም።

ከዚህም የተነሣ የ333 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ የሆነችውን ኢንዶኔዥያን ለማስተዳደር አንዳንድ የፖሊሲ ለውጦች ማድረግ ተገቢ ስለነበር፤ ይህንኑ ያስተካክላል ብለው የወሰዱት እርምጃ ከሠላስ ዓመታት በላይ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር የገነቡትን ወዳጅነት አደጋ ውስጥ ከተተው። የፕሮፓጋንዳው ዘመቻ ግዙፍ የነበረውን የሱሀርቶን ዝና ጎርፍ እንደወሰደው መሬት በየቀኑ ይሸረሽረው ገባ።

ከእነዚህም ውስጥ ፕሬዚዳንት ሱሀርቶ በሥልጣን ላይ በቆዩባቸው 32 ዓመታት ውስጥ የኢንዶኔዥያን ሕዝብ ሀብት በመበዝበር በስዊዝ ባንክ 28 ቢሊዮን ዶላር አስቀምጠዋል፤ በቅጽል ስሙ ቶሚ እየተባለ የሚጠራው Hutomo Mandala Putra ቁማርተኛ ልጃው፤ ቻርተር አውሮፕላን በመከራየት ቁማር ለመጫወት ወደ ላስቬጋዝ አሜሪካ መሔዱ፤ እንዲሁም በቅጽል ስሟ ቱቱት በመባል የምትታወቀዋ ሌላዋ ሴት ልጃቸው Siti Hardijanti Rukmana የ2 ቢሊዮን ኩባንያ በአውስትራሊያ አላት የሚሉት ይገኝበታል።

እንዲህ ያለው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ‘ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው’ እንዲሉ የእንዶኔዢያ አክቲቪስቶች፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የሃይማኖት መሪዎች ሁኔታውን በስፋት በማውገዝ ሕዝብ ለአመጽ እንዲነሳሳ መቀስቀሳቸውን ተያያዙት። ቀደም ሲል ትንፍሽ የማይል የነበረው ሁሉ ለትችት አፉን አሞጠሞጠ፤ ምላሱንም ማውለብለብ ጀመረ። በአጭር ጊዜ አገሪቱ በአለመረጋጋት ተሸበረች። የሕዝቡ ኅልውና ጥያቄ ውስጥ ገባ። ወዲያውም ሱሀርቶ ይውረድ፤ሱሀርቶ ገዳይ ነው፤ሱሀርቶ ዘራፊ ነው የሚሉት መፈክሮች በየቦታው መስተጋባት ያዙ።

በመጨረሻም ‘ብርሌ ከነቃ አይሆንም ዕቃ’ እንዲሉ አስተዋዩ እና ጥበበኛው ሱሀርቶ ምንም አልተፈራገጡም፤ መዘዙን አውቀውታልና። እንደ ሳዳም ሁሴን ወይም እንደ ጋዳፊ ቢያንገራግሩ ኖሮ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለ32 ዓመታት የደከሙባቸው የልማት ሥራዎች ሁሉ የአሸዋ ቁልል እንደሚሆኑ በመረዳት፤ ከታማኝ ባለሥልጣኖቻቸው መካከል አንዱ የሆኑትን ሐቢቢን ለእርሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ኅልውና መከበር ቃል አስገብተው የፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑን አስረክቧቸው።

ይህ እርምጃ ለኢንዶኔዢያዊያን ታላቅ የምሥራች ሆኖ ተወሰደ። ጭፈራዎች በየመንገዱ ቀለጡ፤ በአገሪቱ ላይ ያጠላው ታላቅ ዕልቂት በዚህ አኳኋን እንዲረግብ ተደረገ። የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ አቅርቦት ተቋም ሴራ በዚህ ዓይነት ከሸፈ። ነገር ግን ጦሱ በዚህ አላበቃም ምሥራቅ ቲሞር የተሰኘችው የኢንዶኔዥያ አካል እንድትገነጠልና ነፃነቷን እንድታውጅ ምክንያት ሆኗል።

እዚህ ላይ የዚምባብዌንም ጉዳይ ማንሳቱ ጥሩ ግንዛቤ ሊያጨብጥ ይችላል የሚል እምነት አለ። እኤአ በ2002 ዓ/ም ዚምባብዌ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣችበት ከ1980 ዓ/ም ጊዜ ጀምሮ ሲንከባለል የቆየውን የመሬት ጥያቄ ለማደላደል የሕግ ማዕቀፍ በመጠቀም አዲስ የመሬት ፖሊሲ አዋጅ ማወጇ ይታወሳል። የፕሬዚዳንት ሙጋቤ መንግሥት ይህንን አዋጅ ማወጅ ያስፈለገው አብዛኛው መሬት የተያዘው በነጮች ስለነበር ያንንን ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ለነባር ዜጎችም ጭምር እንዲሆን ለማስቻል ነበር። በወቅቱ ከፍተኛውን መሬት በባለቤትነት ከያዙት ነጮች ጋር ረዝም ላለ ጊዜ ሲደራደሩ ቆይተው ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ፤ ነጮቹ ሐሳባቸውን በመቀየር በመሬት የመጣ ነገር ፈጽሞ አንቀበልም በማለት አሻፈረኝ አሉ።

በመጨረሻ ሮበርት ሙጋቤ ጉዳዩን ሕጋዊ በሆነ አዋጅ ለመፍታት ወሰኑ። አዋጁ እንደታወጀ  የዘመናዊ እርሻ ባለቤት የነበሩት ብዙዎች ነጮች ስላኮረፉ፤ በአሜሪካ፤ በካናዳ እና በአውስትራሊያ መንግሥታት ተመሳሳይ የሆነ የእርሻ መሬት እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸው የሠፈራ ጥያቄ ቀረበላቸው። በዚህ ጊዜ እጅግ የተናደዱት ባለሀብቶች ሊንቀሳቀስ የሚችል ሀብታቸውን እየሸጡ፤ የማይንቀሳቀሰውን እያቃጠሉ፤ እንዲሁም አንዳንዶቹ ቀጥረው ሲያሠሩዋቸው የነበሩትን የዚምባብዌ ዜጎች ‘እኔ ስሄድ አንተ ልትወርሰኝ ነው?’ በማለት አሠቃቂ የሆነ ግድያ በመፈጸም አገሪቱን መልቀቃቸው ተዘግቧል።

ይህ በሆነ በዓመቱ የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት እየተባለች ትጠራ የነበረችው ዚምባብዌ፤ ገበሬዎቹ ጥለው በመጥፋታቸው ሳቢያ መሬት ጦም በማደሯ በቂ ምርት ሊገኝ አልቻለም። በዚህም ምክንያት የዚምባብዌ ሕዝብ ርሃብ ላይ በመውደቁ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሰደድ ተገዷል። ነገር ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለችግር ጊዜ ደራሽ ነውና አንዳንድ የዕርዳታ ድርጅቶች የዚምባብዌን ሕዝብ ከረሃብ ለመታደግ እርዳታ ለማሰባሰብ ተሯሯጡ። ከዚያም በብዙ ሺህ ቶን የሚገመት ስንዴ ወደ ዚምባብዌ በገፍ ይገባ ጀመር።

አስተዋዩ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ግን  ስንዴው ለሕዝብ ከመታደሉ በፊት በላቦራቶሪ እንዲመረመር ያዛሉ። የምርመራውም ውጤት እንደሚያመለክተው እህሉ በዘረመል የተዳቀለ GM (Genetically Modified) መሆኑ ይረጋገጣል። ፕሬዚዳንቱ ውጤቱን እንደተረዱ ‘ይህንንማ እንኳን ሕዝቤ የዚምባብዌ መሬት እንኳ አትቀበለውም፤  የምትረዱን ከሆነ እናንተ የምትመገቡትን ዓይነት እንጂ ይህንንስ አንፈልግም’ በማለት ወዲያውኑ በመጣበት አኳኋን እንዲመለስ ያደርጋሉ።

እርዳታ ለጋሽ የተባሉት አገሮች ደግሞ በሁኔታው በጣም ይናደዱና፤ በአካባቢው ካሉ አገሮች ስንዴውን ለመውሰድ የሚፈልጉ መንግሥታት ካሉ በማለት ሲያጠያይቁ፤ የእኛው ጉድ ሟቹ ጠ/ሚንስተር መለስ ‘ረሃብ ጊዜ አይሰጥም’ እኛ እንወስደዋለን በማለት ከተቀበሉ በኋላ ያ ስንዴ በክልል አንድ እንዳይታደል መመሪያ መስጠታቸው ይነገራል። የዚያ ጦስ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከስቱ ያሉት አዳዲስ በሽታዎች እንደ ምክንያት መሆናቸውን ምሁራን ያብራራሉ።

ሮበርት ሙጋቤ ግን የለጋሽ ሀገሮችን የናሙና ጥናት እህል ተቀብለው ለሕዝባቸው እንዲታደል ባለማድረጋቸው የቴክኖሎጂ ምርምር ፀር፤ እንደሆኑ ተቆጥሮ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ተጣለባቸው። በወቅቱ አንድ የአሚሪካን ዶላር $10.00 የዚምባብዌ ዶላር ነበር። የኢኮኖሚ ማዕቀቡ ከተጣለ በኋላ ግን በየጊዜው እየወረደ ሄዶ አሁን $1.00 የአሚሪካን ዶላር $362.00 የዚምባብዌ ዶላር ደርሷል። እንግዲህ እንዲህ ያለው ስውር ሴራ የሚታቀደው እና የሚተገበረው በእነዚሁ ሁለት ተቋማት ሲሆን የተጎጅውን ሀብት እንዴት አድርገው እንደሚዘርፉ መገንዘብ አያዳግትም።

ሌላው አንዳንድ ሀገሮች አዋጭ የሆነ ፕሮጀክት ከአላቸው፤ እነዚህ ሁለቱ ተቋማት ገንዘብ እንሰጣለን በማለት  እጃቸውን ያስገባሉ። የሚጠይቁትም የወለድ መጠን ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ የሕንድ መንግሥት የናርማዳን ወንዝ ተከትሎ  3000 ትንንሽ፤ 136 መካከለኛ እና 30 እጅግ ግዙፍ የሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን ለመገንባት ያቅዳል። ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የሕንድን ሦስት ትላልቅ ግዛቶች ለቀጣዩ ሃምሳ ዓመታት ምንም ዓይነት የኤሌክትሪክ አቅርቦት እጥረት ሳይኖርባቸው ማንኛውንም ኢንዱስትሪ ያለምንም ስጋት ማንቀሳቀስ እንደሚያስችላቸው ይታመናል። ታዲያ የዚህ ግድብ ግንባታ ጠቅላላ ወጭ 19 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ሁሉንም ለመሸፈን የዓለም ባንክ ተፈራርሟል።

ይሁን እንጂ ግድቡ በሚገነባባቸው አካባቢዎች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እንደሚፈናቀሉና፤ ለአዕዋፋትና ለዱር እንስሳት መጠለያ የሆነው የአካባቢው ደን በውሀ እንደሚዋጥ፤ በተጨማሪም የከባቢ አየር ንብረት መዛባት ሊያስከትል እንደሚችል በመግለጽ፤ የአካባቢ ዱር አራዊትና ደን ጥበቃ ምሑራንና፤ የሰብአዊ መብት አክቲቪስቶች በመከራከር ላይ ናቸው።

ሆኖም የዓለም ባንክና የዓለም አቀፉ የገንዘብ አቅርቦት ተቋም የሕዝቡን አቤቱታ ከግምት ውስጥ ባለማስገባት ግንባታው እንዲካሄድ እያደረጉ ይገኛሉ። የግምባታው ወጭ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ገንዘብ አቅራቢዎቹ ሊያገኙት ያቀዱት ወለድ በጣም አቋምጧቸዋል። ይህ ብቻም አይደለም እነዚህ ተቋማት ለአንድ ሀገር ገንዘብ ለማበደር ሲዋዋሉ ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሟሉ ይጠይቃሉ። ይህንንም SAP (Structural Adjustment Program) የመዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራም በማለት ይጠሩታል።

የመዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራም በራሱ የታዳጊን አገሮችን ዕድገት በማቀጨጭና በማናጋት ይታወቃል። ይኸውም የመጀመሪያው ጥያቄያቸው የአገሪቱን ገንዘብ ከዶላር ምንዛሬ ጋር ያላትን መጠን በመቀነስ የውጭ ዕቃዎችን የመግዛት አቅም ማሳነስ አንደኛው ሲሆን፤ በአንፃሩም ሚዛኑን ለመጠበቅ ተበዳሪው ሀገር ወደ ውጭ የሚልከውን ዕቃ እንዲያሳድግ ይገደዳል።

በዚህም የአገር ውስጥ ነጋዴዎች በተለይ ደግሞ አርሦ አደሩ እጅግ በጣም ይጎዳል። ለምሳሌ የኢትዮጵያን ጉዳይ ብንመለከት የቡና፤ የቅባት እህሎች እና የቆዳ ዋጋ ይቀንስና መጠኑ (አቅርቦቱ) ግን እንዲጨምር ይሆናል። እንግዲህ እነዚህ ገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ጥቅማቸው እጥፍ ይሆናል ማለት ነው። በዚህ አኳኋን ከአሚሪካ የሚገባ ዕቃ ደግሞ ቀድሞ ከነበረው ዋጋ ይጨምራል ማለት ነው። እዚህ ላይ ማየት ያለብን ዋጋው የጨመረው የዶላሩ ቁጥር ሳይሆን ዶላሩን ለማግኘት የሚመነዘረው የብር ቁጥር በመጨመሩ መሆኑን ልብ ይሏል። ለምሳሌ አንድ ዶላር 20 የኢትዮጵያ ብር የሚመነዘር ቢሆን 20 ሺህ ዶላር የሚያወጣ መኪና ለመግዛት የሚያስፈልገው 400 ሺህ ብር ነበር እንበል። የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ አቅርቦት ተቋም በጠየቁት ማስተካካያ መሠረት አንድ የአሜሪካ ዶላር 25 ብር መሆን አለበት ቢሉ የዚህ መኪና ዋጋ 500 ሺህ ብር ሆነ ማለት ነው።

ሌላው ደግሞ መንግሥት ያለውን ሠራተኛ በ10% መቀነስ አለበት በማለት ጫና ያሳድሩና ብዙ ሠራተኞች ከሥራ እንዲሰናበቱ ያደርጋሉ። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ ገንዘቡን አንለቅም በማለት መንግሥትን   ያስጨንቃሉ። መንግሥት ደግሞ የታቀደውን ፕሮጀክት ቶሎ ለማከናዎን ብድሩን ማግኘት ስለሚፈልግ ያለው አማራጭ በጥያቄው መሠረት መፈጸም ይሆናል።

ሟቹ ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊም ሲያደርጉት የቆዩት ይህንኑ ነበር። በ1983 ዓ/ም ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር የአንድ ዶላር የምንዛሬ ዋጋ ከአምስት እስከ ስምንት የኢትዮጵያ ብር ነበር። አሁን ግን አገራችን የአለችበትን ሁኔታ መገመት አይከብድም። ከዚህም የተነሳ አሥር ብር የነበረው የአንድ ኪሎ ሥጋ ዋጋ በአሁኑ ወቅት ምን ያህል እንደሆነ ይታወቃል። ሃምሳ ብር የነበረው የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ አሁን ግን እንዴት እንደናረ ለሰሚው ግራ ነው።

ይህ ማለት የምርት አቅርቦት ቀንሦ ሳይሆን የብር የመግዛት አቅሙ ስለተሸረሸረ ዋጋ ቢስ ሆኗል ማለት ነው። እንግዲህ ከዚህ አኳያ ሲታይ የዶላር አቅም እየገዘፈ እና እየጎለበተ ስለሚሄድ አንዳንድ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ከውጭ የሚገቡትን ቁሳቁሶች ለመግዛት የሚወጣው ወጭ በእጥፍ ይጨምራል ማለት ነው። ምክንያቱም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገሮች አብዛኛው የውጭ ንግዳቸው በግብርና ምርት ላይ ያተኮረ ስለሆነ ዶላሩን ለማግኘት የግብርና ምርታቸውን በገፍ ማቅረብ ይገዳዳሉ።

በዚህ አኳኋን እነዚህ ግዙፍ የገንዘብ ተቋማት የድሀ አገሮችን ንብረት በምንዛሬ አሳበው ሲመዘብሩ ታዳጊ አገሮች በሚፈልጉት መጠን ዕድገታቸውን ለማሳለጥ አይችሉም። ስለሆነም የአገራቸው የሥራ አጥ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ስለሚሄድ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት ሁሌም በጥርጣሬና በአለመተማመን ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ከዚያም አንድ ቦታ ኮሽ ባለ ቁጥር መንግሥት የጅምላ አፈሳ በማድረግ ውጥረቱን ለማስተንፈስ በፍርሃት በሚወስዳው የከረረ እርምጃ፤ ከሕዝብ ጋር በየጊዜው ይጋጫል። የሚገርመው ደግሞ በእነዚሁ ታዳጊ አገሮች የምርምር ጥናት እናደርጋለን በማለት ትንሽም ቢሆን በየዓመቱ የተገኘውን ዕድገት በመካድና የሥራ አጡን ቁጥር ደግሞ በማግዘፍ ትችታቸውን ያቀርባሉ። ይህም አካሄድ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ውጥረት የበለጠ እንዲባባስ የሚያደርግ ነው።

በአጠቃላይ ግን ሁለቱም ተቋማት በዓለም ዙሪያ የአሜሪካንን ጥቅም ለማስጠበቅ ቅድሚያና ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ ድርጅቶች መሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ይሆናል። እንዲህ ያለው አካሄድ አካሄድ ያሳሰባቸው 5 ሀገሮች በቻይና ጎትጓችነት ብሪክስ (BRICS) የተባለውን ተቀናቃኝ ድርጅት አቋቁመዋል። እነዚህ ሀገሮች ብራዚል፤ሩሲያ፤ሕንድ፤ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው።

-//-

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.