ብሔራዊ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን አምስት ቋሚ ኮሚቴዎችን አቋቁሜ እየሠራሁ ነው አለ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡ ማግሥት የቆዩ ቁርሾዎችን ለማከም የተቋቋመው ብሔራዊ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን፣ ባለፉት ሦስት ወራት አምስት ቋሚ ኮሚቴዎችን አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ነሐሴ 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ለሪፖርተር በላከው መግለጫ የሦስት ወራት የሥራ ክንውኑን ያሳወቀው ኮሚሽኑ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫና የሕዝብ ግንኙነት፣ የመረጃ ማሰባሰብና ማጠናቀር፣ የእውነት ፈላጊና ቅሬታ ሰሚ፣ የፍትሕና ዕርቅ፣ እንዲሁም የሀብትና ግብዓት ማሰባሰብ ቋሚ ኮሚቴዎችን ማቋቋሙን አስታውቋል፡፡

ከሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በቢሾፍቱ ከተማ ባደረገው ስብሰባ ዕቅድ አውጥቶ የኮሚሽኑን የወደፊት ትልም ማስቀመጡን ገልጿል፡፡ ‹‹የሽግግር ፍትሕ አካል›› እንደመሆኑም፣ ከመደበኛ የፍትሕ አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ከፍትሕ ዓብይ ኮሚቴ ጋር በመተባበር ሐምሌ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል ስብሰባ ማካሄዱን አስረድቷል፡፡

የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት በማድረግ ዝርዝር ሕጎችን በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ፣ ኮሚሽኑ በሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴው አማካይነት የላከው መግለጫ ያስረዳል፡፡

በቀጣዮቹ ሁለት ወራት የዕርቀ ሰላም የሚዲያ ፎረም ለማቋቋም እንደሚሠራ የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ከልዩ ልዩ በሕዝብ ተነሳሽነት እየተካሄዱ ካሉ ባህላዊና ዘመናዊ የዕርቅ ሒደቶች ጋር በቅርበት በመሥራት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየጣረ እንደሆነም ገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት ነሐሴ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱን፣ ነሐሴ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በአገሪቱ ከሚገኙ ረጂ አካላትና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ጋር የመረጃ ልውውጥ መድረክ ማዘጋጀቱን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የዕርቅ መንፈስ እንዲመጣ ለማስቻል ጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ጉባዔ ጋር በመተባበር የፀሎት ቀን ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑን ሥራ በሰፊው የማስተዋወቅና የተለያዩ ልምዶችን ከተለያዩ አካላት ለመቅሰም ዕቅድ እንደያዘ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

1 COMMENT

  1. The Commission is good for nothing except one and only one thing. And that only thing is to serve as a political game card .
    . It was formed not for the purpose of solving a problem in a real sense of term but to neutralize peoples’ outrage and let them calm down and take politics as usual . That is what those old guards of TLPF /eprdf and now ODP/eprdf are busy with . We like it or not, there will not be any genuine democratic transition under a ruling party of political crime !!!! Absolutely no!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.