በሌኒን ቱቦ ለማለፍ የጣረው መለስ ዜናዊ (ጌታቸው ሺፈራው)

(ይህ ፅሑፍ አቶ መለስ ዜናዊ በይፋ ሞቱ ከተባለ ከሁለት ቀን በኋላ ተፅፎ መሰናዘሪያ ጋዜጣ ላይ የታተመ ሲሆን በወቅቱ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ የነበረውና ጋዜጠኞችን በማዋከብ የታወቀው ሽመልስ ከማል ለጋዜጣው ባለቤት ደውሎ “መለስ በማንም ቱቦ አላለፈም። መለስ ራሱ ታላቅ መሪ ነው………” ብሎ ጮሆበታል። በዚሁ ጋዜጣ “መለስ ከቆየ አይቆረጠምም” የሚል ርዕስ ያለው ፅሁፍ ወጥቶ ስለነበር አቶ ሽመለስ “መለስ አይቆረጠምም የምትሉት አስከሬኑ ሳይቀበር ቆዬ፣ ደረቀ እያላችሁ ነው” ብሎ ብዙ ዝቷል። ዛሬ አቶ ሽመልስ ከማል ከሞተው መለስ ዜናዊ በባሰ ተረሳ መሰለኝ። ለማንኛውም ለማስታወስ ያህል እነ ሽመልስ በሌኒን ቱቦ አላለፈም ብለው እንዲቆጡ ያደረገቻቸው ፅሁፍ ከስር ተያይዛለች)

……………………

ቭላድሚር ኢሊች ሌኒን ከ1960 በኋላ ‹‹በሶስተኛው አለም›› ትልቅ ተከታይ ያገኘውን ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ከማርክሲዝም በራሱ መልክ በማሻሻል፣ በኋላ ለሌሎቹ ተምሳሌት የሆነውን የመጀመሪያውን ሶሽያሊስት ፓርቲ በማቋቋምና ታላቋን ሶቬት ህብረት በመመስረት በአለም ትልቅ ዝና ያተረፈ መሪ ሲሆን በአለማችን በእርሱ ፈለግ የተመሰረቱ ስርዓቶች አምባገነን ፓርቲና ግለሰብ በመፍጠር ከሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ይልቅ ለትልልቅ ጦርነቶች፣ ጭቆናዎችና አምባገነንነት መከሰት አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡

ሌኒን እኤኤ በ1917 የተደረገውን የሩሲያን የጥቅምት አብዮት በመምራት የተለያዩ “ብሄሮችን” ያጠቃለሉ 15 አገራትን አንድ በማድርግ ታላቋ ሶቬት ህብረት መስራች ሲሆን ከማርክስ መሰረታዊ መርህ ባፈነገጠ መልኩ የማንኛውም ግዛት ህዝቦች ተጨቁነናል ብለው ካመኑ የመገንጠል መብት አላቸው የሚል ህግን ስራ ላይ አዋለ፡፡ ምንም እንኳ የመሰረተው መንግስት ዲሞክርሲያዊ መሆኑን ቢያውጅም የሌኒንና የፓርቲውን ቦልሸቪክስን ስልጣን የሚገዳደሩ ውስጣዊና ውጫው ሀይሎች በመጠናከራቸው ከ1921 ጀምሮ ፓርቲውናና ራሱን ‹‹አውራ›› ለማድረግ ራሱ የፈቀዳቸውን መብቶችና ሁሉንም ተቀናቃኝ ሀይሎች አጥፍቷል፡፡ የተለየ አመለካከት ያሳዩትም የሪፖብሊኩ ጠላቶች፣ የምዕራባዊያን ተላላኪ፣ ፀረ-አብዮት በሚል በቀይ ሽብርም በአስር ሽህ ዎቹ የሚበልጡትን ተረሸኑ፣ ብዙዎቹ ታሰሩ፡፡

ምንም እንኳ ይህ እርምጃ ሌኒንንና ኮሚንስት ፓርቲውን ገንነው እንዲወጡ ቢያደርግም የጤንነቱ ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ተተኪ አመራሮችን መፈጠር እንዳለበት አመነ፡፡ ስታሊን፣ ትሮትስኪ፣ ቡክሃሪን፣ ዚኖቪቭና ካሜኔብ የተባሉ የፓርቲው አመራሮች ወደ መድረክ ብቅ እንዲሉም እድሉን ሰጣቸው፡፡ ሆኖም በሁሉም ላይ እምነት ስላልነበረው አንዱ በአንዱ ላይ ተቀናቃኝ እንዲሆኑ በማድረግ በእሱ ላይ ያደርሱብኛል ብሎ ያሰበውን ጫና ለመቀነስ እንዲሁም ስልጣን ለማግኘት አሊያም ስልጣን ላለማጣት ለእሱ ታማኝ እንዲሆኑ አደረገ፡፡ እኤአ በ1923 ህመሙ እየጠናበት በመምጣቱ የመተካካቱ ጉዳይ የማይቀርለት ቢሆንም የሌኒን ጥላ ያቀጨጫቸውና ሲፈልግም እርስ በእርሳቸው ሲያቦጫጭቃቸው የነበሩት አመራሮች ብቻቸውን እሱን ለመተካት አቅም እንደሌላቸው በማመኑ ስታሊንና ትሮትስካይ በጥምረት እንዲተኩት ወሰነ፤ ቀሪዎቹ በተለመደው መልኩ የሁለቱን ስልጣን እንዲቆጣጠሩ አደረገ፡፡ እነዚህ አመራሮች የሌኒን ፈለግ ተከትለው ስልጣን እንዴት ለእየራሳቸው መጠቅለል ወይንም ሌላውን መቆጣጠር እንዳለባቸው ከመሪያቸው ተምረዋል፣ የሌኒን ጥላ ለጊዜውም ቢሆን ቀለል ማለቱም ፉክክሩን ይበልጥ አጠናክሮታል፡፡ በጊዜው ስታሊን የፓርቲው ዋና ፀሃፊ የነበረ በመሆኑ የሚፈልጋቸውን ወደ ፓርቲው ለማምጣት፣ በማዕከላዊ ኮሚቴ የሚደረገውን ውይይት ለመቆጣተር፣ ወደ ፓርቲ የሚያድጉትንና የሚሾሙትንም መቆጣጠርና የፓርቲውን አጀንዳ ለመወሰን አስችሎታል፡፡ምንም እንኳ በ1917 የጥቅምት አብዮት የነበረው ሚና አነስተኝ ቢሆንም ከሌሎቹ የተሸለ ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች መፍትሄ ሰጭ፣ ተናጋሪና ታጋሽ በተለይም ለአርሶ አደሩ ልዩ ትኩረት ይሰጥ የነበረ በመሆኑ በፓርው አባላትና በአርሶ አደሩ ተቀባይነት አገኘ፡፡

በአንጻሩ ከስታሊን የተሻለ የተማረና ተናጋሪ እንዲሁም በግትርነቱ የሚታወቀው ትሮትስካይ የግዙፉ የቀዩ ጦር መሪ በመሆኑ የጦር ሃይሉንና በፓርቲው ውስጥ የሚገኙ የጦር አባላትን በመጠቀም የስልጣን እርከኑን ለመቆናጠጥ የስልጣን ሽኩቻው ውስጥ ሁለተኛው ወሳኝ ሰው ሆነ፡፡ ትሮትስካይ የጥቅምቱን አብዮት ከሊኒን ጋር የመራና ጀግና ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የተማረ፣ ተናጋሪ፣ ራዕይ ያለው ወጣት በመሆኑ በአብዛኛው ሶቬታዊ በተለይም በተማሪው፣ በወታደሩና በመንግሰት ሰራተኛው ተወዳጅ ቢሆንም የቀዩ ጦር መሪነቱና ወደ ምዕራባዊያና ያዘነበለ ግትር ሙህርነቱ በፖለቲከኞቹና በቀሪው ማህበረሰብ ከመፈራት አልፎ ያስጠላው ነበር፡፡

ሚዲያውን ተቆጣጥሮ የሁለቱን ስልጣን እንዲገዳደር በቀዳሚነት የተመደበው ወጣቱና ተናጋሪው ኒኮላይ ቡክሃሪን የሚዲያ ሀላፊ እንደመሆኑ የራሱን ሀሳብ በማስረጽና የሌሎቹን ሀሳብ በመተቸት ሶስተኛ ተቀናቃኝ ለመሆን በቃ፡፡ በአክራሪ ኮሚኒስትነታቸው የሚታወቁትና የየራሳቸውን ክልል ፓርቲዎች የሚመሩት ዚኖቪቭና ካሜኔብ የተባሉ ነባር የሌኒን ‹‹ጓዶች››ም በጥምረት ፓርቲውና አጠቃላይ የአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የራሳቸውን መዋቅር መዘርጋት ጀመሩ፡፡ ሌኒን በጠና በታመመበት ወቅት ሳይቀር እነዚህን አራት ቡድኖች አንዱን ከአንዱ ጋር በማጋጨት፣ በህዝቡ ፊት በመተቸት ወይም በማሞገስ ለራሱ በተመቸው መልኩ ለመጠምዘዝ ቢሞክርም እንዳሰበው አልተሳካለትም፡፡ በሌኒን አመራር ዘመን ፓርቲው ውስጥ የአንድ ግለሰብ ፖለቲካዊ ስብዕናና ተቀባይነት ጎልቶ በመውጣቱ በሌሎች ፖለቲከኞች መካከል የነበረው የስልጣን ሽኩቻ ወደ ውጭ አይውጣ እንጂ ሌኒን በዘየደው መሰሪ የማናቆር ስልት ከዋና ዋና የፖሊሲ ጉዳዮች እስከ ግለሰባው ስብዕና በመናቆር ላይ የተጠመዱ እንደነበሩ የታወቀው ሌሊን በመታመሙ በፓርቲው ያለው ሚና በቀነሰበት ወቅት ነው፡፡

ከሁሉም በተሻለ ተቀናቃኞቹን እንዴት ማጥቃት እንዳለበት ከሌኒን እንደተማረ የሚነገርለት ስታሊን ሌሎቹን በሚቃወምበት እያንዳንዱ እርምጃ ሁሉ ፖለቲካዊ፣ ርዮታዊና ወታደራዊ መሰረቱን እያጠናከረ ሲሄድ በአንጻሩ ሌሎቹ ስታሊንን እንደ ትልቅ ስጋት ከማየት ይልቅ እርስ በእርስ እየተፈራሩ ሀይላቸውን አባክነዋል፡፡ ሌኒን ከመሞቱ በፊት የታሰበውን የጥምረት አመራርና የመተካካት እቅዱ እንደፈለገው ሳይሳካ ሲቀር ብቻውን በፉክክሩ ገኖ የወጣው ስታሊንን ከፓርቲው እንዲባበር ቢናዘዝም ፓርቲው በነበረው መሰረታዊ ድብቅ ባህሪ ሚስጥሩን ከፖሊት ቢሮው ውጭ ለማውጣት ባለመቻሉና የስታሊን ፖለቲካዊ አቅም ከምናም በላይ መጠናከሩ የሌኒንና ሌሎች የስታሊን ተቀናቃኞች እቅድ እውን እንዳይሆን አድርጓል፡፡
ተናጋሪውና ፀሃፊው መሪ ቭላድሚር ኢሊች ሌኒን የፈለገውን ተተኪ ሳያፈራና የስልጣን ሽግግሩን በፈለገው መልኩ ሳይጨርስ እኤአ ጥር 21 1924 በ54 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡ አስከሬኑ ሙዚየም ውስጥ እስከተቀመጠበት ጊዜ ድረስ ለበርካታ ቀናት በዘለቀ አገር አቀፋዊ የሀዘን ቀንና ስነ-ስርዓት በተለያዩ የሶቬት ክፍሎች አስከሬኑ እየተዘዋወረ በህዝብ ተጎበኘ፡፡ የታላቋ ሶቬት ማህንዲስ፣ ቀዩን ጦርና ቦልሸቪክስን ያቋቋመና በቆራጥነት የመራ፣ አዋቂ፣ ሊቅ፣ የሶቬትን ህዝብ ከሰው በላው ኢምፕሪያሊዝምና ፊውዳሊዝም አገዛዝ ነጻ ያወጣ፣ ለሶቬት ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሰው ዘሮች ሲል በለጋ እድሜው ራሱን የሰዋ ልዩ ሰማዕት እየተባለ በሩሲያ ሚዲያና ልዩነታቸውን ለጊዜውም ቢሆን በደበቁት ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ተወደሰ፡፡ የፓርቲው ወጣት ሊግ ህዝቡን በማደራጀት በደመቀ ስነ ስርዓት በሩሲያ ከተማዎች ሁሉ አቀባበል ተደረገለት፣ የከተሞች፣ የድርጅቶች፣ የጎዳናዎችና የቦታዎች ስም እንደ አዲስ በሌኒን ስም ተሰየሙ፡፡

ህዝቡ አንዳንድ ፖለቲከኞችን የሚያውቃቸው ቢሆንም መሪው ሌኒን ወጣሁ ወጣሁ ሲሉ እርስ በእርሳቸውን በማጋጨት ስለሚያጠፋቸው ከእሱ ውጭ መሪ ያለ ስለማይመስለው መጨነቁ አልቀረም፡፡ የሌኒን ፖለቲካዊ ጥላ ገለል ያለላቸው ፖለቲከኞች የሚመሩትን ፓርቲ፣ ተቋም የተወለዱበትን አካባቢና የማህበረሰብ ክፍል ከጎናቸው ለማሰለፍ ከመቸውም ጊዜ በላይ ቢጥሩም መሪው ሌኒን ሳይሞት ጀምሮ የፓርቲውን መዋቅር የተጠቀመበትን ስታሊንን ለመገዳደር ግን አልተቻላቸውም፡፡ ከጥቃቅን የፖሊሲና ግለሰባዊ ችግሮች ባሻገር የኮሚኒስት ፓርቲው አካሄድ ላይ ክፍፍል ተጀመረ፡፡ ይህም ‹‹ታላቁ መሪያችን›› ሌኒን ያጠፋውን የፓርቲ ክፍፍል እንደገና ጀመሩት፣ ከሌኒን መርህ አፈነገጡ፣ ጸረ-ሶቬትና የምዕራባዊያን ቅጥረኛ ሆኑ በሚል ስታሊን ተቀናቃኞቹን ‹‹ታላቅ መሪያችን›› አጣን በሚለው በወታደሩ፣ በሰራተኛውና በሌላው ማህበረሰብ እንዲጠሉ አደረጋቸው፣ ራሱንም የሌኒን ቃል ጠባቂና ወራሽ አድርጎ ለማሳየት እድል አገኘ፡፡ 14ኛውን የፓርቲው ኮንግረንስ ተቀናቃኞቹን ለማስወገድ በተለይም ትሮትስካይን ከቀዩ ጦር አዛዥነት ለማሰናበት ተጠቀመበት፡፡ እርስ በእርሳቸው እየተፈራሩ ስታሊን ሳይታሰብ እንዲወጣ እድል የሰጡት ፖለቲከኞች በመጨረሻም ቢሆን ከትሮትስካይ ጋር ግንባር ፈጥረው ስታሊንን መቃወም ግድ ሆነባቸው፡፡ ሆኖም አዲስ ታማኝ ፖለቲከኞችን ወደ ፓርቲው ያመጣው ስታሊን ተቀናቃኞቹን በተለመደው ክስና ፓርቲንና አገርን በማዳን ስም ከፓርቲውም አባረራቸው፡፡ ከግትሩ ትሮትስካይ በስተቀር ሌሎቹ ይቅርታ ጠይቀው ቢመለሱም ስታሊን ከ1934-39 ባደረገው ‹‹ታልቁ ጭፍጨፋ›› ዋናዋናዎቹን ጨምሮ በሽዎች የሚቆጠሩ ተቀናቃኞቹን አስጨፍጭፎ ስልጣኑን አስተማማኝ አደረገ፡፡

አቶ መለስ፤ “ጠቅላይ ሚኒስተር ሌኒን”!
…………………

አቶ መለስ ዜናዊ የታላቋ ሶቬት ህብረት መስራችና ለ6 አመት ሩሲያንና ህብረቱን ያስተዳደረውንና ከማርክስ ቀጥሎ በዘርፉ ፍልስፍና ልዩ ቦታ የሚሰጠውን ሌኒንን የሄዱበትን መንገድ ከመኮረጅ አልፎ፣ ለሌሊን ካላቸው አድናቆት ለመመስል መድከማቸው ይነገራል። ለዚህ ሲባልም በሕይወት እያሉ ያደረጉት ብቻ ሳይሆን ከሞቱ በኋላም የለቅሶ ስርዓቶ የሌኒንን እንዲመስል ብዙ ጥረት መደረጉን ታዝበናል። ምንም እንኳ ሁለቱ ሰዎች ለአገራቸውና ለአለም ያበረከቱት፣ የነበሩበት ወቅትና አጠቃላይ ተፅዕኗቸው የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስተሩ የሚከተሉት ስልትና የገነቡት ፖለቲካዊ ተክለሰውነት የሌኒን ፈለግ የተከተለ በመሆኑ እንዲሁም በሁለቱ የስልጣን መጨረሻ የተከሰተው የተተኪ አመራር ክፍተትና ከሞቱ በኋላ የሚከሰተው ክፍፍል በእጅጉ የሚያመሳስላቸው ይሆናል፡፡

አቶ መለስ በበላይነት የሚመሩት ህወሃት መሰረቱ ሌኒን ከማርክሲዝም ጋር የቀየጠው ‹‹ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም›› የተባለ ርዮት አለም ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የሌኒንን ‹‹የብሄር ብሄረሰቦችን መብት›› መርሆች እኤአ 1976 ትግራይን ለመገንጠል ባወጣው ማንፌስቶ፤ በኋላም በዚሁ ርዮት አለም የተመሰረተችው ሶቬት ህብረት ፈራርሳ ርዮት አለሙ አበቃለበት በተባለለት ወቅት የአቶ መለስ ህውሃት የኢህአዴግን መንግስት በበላይነት ሲመሰርት በኢፌደሪ ህገ መንግሰቱ አንቀጽ 39 ላይ ይኸውን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለአሁኑ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ዳረገን ብለው የሚያስቡትን የሌኒን የመገንጠል መብት የማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታ ሳያጠና እንደወረደ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ሌኒን 15 አገራትን አንድ ሲያደርግ የሌኒንን መርህ የሚከተሉት አቶ መለስ ግዛት አንድ በማድርግ ጉዳይ ከሌኒን በተለየ ከነባር የአገሪቱ ክፍል ኤርትራን የባህር በር እንዳይቀር በሚመስል የወሰን አከላለል ካስቆረጡ በኋላ ቀሪውን የአገሪቱን ክፍል ለዘመናት ታይቶ በማይታወቅና ለብዙ ግጭት በዳረገው የብሄርና የጎሳ ወሰን ሸንሽነው የራሳቸውን አዲስ ‹‹አገር ግንባታ›› ወጥነው አልፈዋል፡፡
የሌኒኑ ቮልሸቪክስ በመጀመሪያዎቹ አመታት አንጻራዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ከፈቀደ በኋላ ዲሞክራሲያዊ ተቋማትንና ተቀናቃኝ ፖለቲከኞችን በማጥፋት ቮልሸክስንና የሌኒንን ‹‹አውራነት›› እንዳረጋገጠው ሁሉ ነባራዊ ሁኔታው ከሚፈቅደው አዲስ ፖለቲካው ስርዓት ይልቅ ዘጠኝ አስርት አመታት ወደ ኋላ ተመልሶ ልክ እንደ ቮልሸቪኪስና ሌኒን አቶ መለስም ዲሞክርሲያዊ ተቋማትን በማቀጨጭ የራሳቸውንና የኢህአዴግን የበላይነትን ያረጋገጠ ሌኒናዊ ስርዓት ዘርግተዋል፡፡ እንደ ሌኒን ሁሉ አቶ መለስም በጫካ እያሉም ሆነ ስልጣን ከወጡ በኋላ ራሳቸውን አግንነው ከማውጣት ባለፈ አንገታቸውን ቀና ለማድረግ የሞከሩ ፖለቲከኖችን በሌኒናዊ ስልት አዳዲስ ታማኞችን ተጠቅመው እርስ በእርሳቸው ወይንም ፓርቲን በማዳን መልክ ለፓርቲ አባላት አለፍ ሲልም በሙስና ስም ለህዝብ ‹ይፋ›› በማድረግ ከፓርቲው ሲያርቁ በተደጋጋሚ ተስተውለዋል፡፡ እንደ ሌኒን ሁሉ ተናጋሪነታቸውን በመጠቀም፣ ከፓርቲው አባላት ሁሉ የተሻለ እውቀት እንዳላቸው በማሳየት ፖለቲካዊ ተክለ ሰውነታቸውን አፈርጥመዋል፡፡ እንደ ሌኒን ‹‹ጓዶች›› ሁሉ የመለስን ፖለቲካዊ አቅም የተረዱ የአቶ መለስ ‹ጓዶች››ም ታማኝ ከመሆን ውጭ አማራጭ እንዳልነበራቸው ባለፉት አመታት አቶ መለስ ፓርቲው ውስጥ የነበራቸውን ፍፁም የበላይነት ማየት በቂ ነው፡፡

ፓርቲውና አገራዊ ፖለቲካ ውስጥ የራሱን የማይነቃነቅ ፖለቲካዊ ተክለሰውነት ለመገንባት በቀን እስከ አስራ አራት ሰዓት ሲሰራ የነበረው ሌኒን ከመሞቱ ሁለት አመት ቀደም ብሎ በተከሰተበት የጤና እክል የሚወደውን ስልጣን የሚተካ መሪ እንደሚያስፈልግ በማመኑ ‹‹የመተካካት ፖሊሲ›› ለፓርቲው ሲያስተዋውቅ በተመሳሳይ አቶ መለስ በቀዳሚነት እንዳመነጩት የሚነገርለት ‹‹የመተካካት ፖሊሲ››ም እንደ ሌኒን ሁሉ በጤናቸው ባለመተማመናቸው ከመሞታቸው ሁለት አመት ቀደም ብለው የወጠኑት የችኮል ፖሊሲ ነው፡፡ (አቶ መለስን ህመም የጀመራቸው ከ2 አመት በፊት መሆኑን “መንግስት” አምኗል)፡፡

አቶ መለስም መሞታቸው በይፋ ከተነገረ በኋላ የተደረገው አቀባበል፣ ለቀናት የታወጀው የሀዘን ቀንና ከስራቸው ከነበሩ ፖለቲከኞቹና ደጋፊዎቻቸው የሚሰማው የኢትዮጵያን ህዝብ ከጭቆና ያወጣ፣ ለአገሪቱ ፍትህና ዲሞክራሲን በተደላደለ መሰረት አስቀምጦ ያለፈ፣ የልማት መህንዲስ፣ አባይን የደፈረ፣ ሙሉ ጊዜውን ለህዝብ አውሎ የተሰዋ ፍጹምአገር ወዳድ፣ የክፍለ ዘመኑ መሪ፣ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አፍሪካና አለም ያጡት ‹‹ሞት›› የማይገባው መሪ አይነት ሙገሳ ከሌኒን ስር የነበሩና በስልጣን ይገባኛል የተከፋፈሉት የቮልሸቪክስ ፓርቲ ፖለቲከኖችና ወጣት ሊግ አባላትን በሚያስታውስ መልኩ ቀጥሏል፡፡ የሌኒን አስከሬን በህዝብ እንደተጎበነው ሁሉ የአቶ መለስ አስከሬንም ቤተ መንግስት ውስጥ እየተጎበኘ ይገኛል፡፡ ከጅጅጋው ሆስፒታል እስከ ጎንደሩ ቴክኒክና ሙያ በመላው አገሪቱ ቀጥሎ ተቋማት፣ መንገዶችና ሌሎች ቦታዎች በአቶ መለስ ስም እየተሰየሙ ነው፡፡ እስካሁን ያልታወቀው ‹‹አልሞተም›› የተባሉት የአቶ መለስን አስከሬን ደጋፊዎቻቸውና ታማኝ ፖለቲከኞቻቸው ልክ እንደ ሌኒን፣ ማኦ፣ሁችሚኒና የመሳሰሉት መሪዎች ሁሉ ‹‹ሙዚየም ውስጥ ይቀምጥ›› የሚል ሀሳብ ማቅረብ አለማቅረባቸው ነው፡፡

በመሆኑም በፓርቲውና አገሪቱ ላይ የነበራቸው ሚና፣ በጓዶቻቸው የሚወስዱት የማግለል ፖሊሲ፣ መተካካቱን የጀመሩበት ወቅት፣ የመታካካቱ ውጤት አልባነት፣ ከሞቱ በኋላ የታየው ድባብና ሙገሳ አቶ መለስ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ የኖሩት ቭላድሚር ኢሊች ሌኒን፣ ፓርቲውንም የቮልሸቪክስ ያስመስለዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በእርግጥ ከሚያደንቁት ሌኒን ከ3 እጥፍ በላይ አመታትን ስልጣን ላይ ቆይተው ከአጤ ምኒሊክ በኋላ መሪ አልቅሳ ባልቀበረች አገር፣ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ከመሰረቱ ከአቶ መለስ የተሻለ ተቀባይነት ኖሯቸው እንኳ በጊዜያዊ አመፅ ከስልጣናቸው ክብራቸው ተገፎ በሚወርዱበት ወቅት በክብር ተቀብረው የሰሩት አወንታዊም ሆነ አሉታዊ ታሪክ እንዲታወስ አጋጣሚውን ማግኘታቸው እድለኛው መሪ ሊያሰኛቸው የሚችል ይመስላል፡፡

ኢትዮጵያዊ ስታሊን፣ትሮትስካይ……………?

ከ6 አመት በላይ አገሩን ለመምራት እድል ካላገኘው የሶቬቱ ሌኒን ጋር ሲነጻጸሩ አቶ መለስ ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ከ3 እጥፍ በላይ ጊዜ አግንተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ባለፉት ጥቂት አመታት በተለይም ከ2002 ዓ/ም ምርጫ በኋላ ፓርቲውንና እርሳቸውን ወደውም ሆነ በግድ የተቀላቀሉ ካድሬውች ከማፍራታቸው በፊት ከመፍራትና ከመወቀስ አልፈው ብዛት ያለው ተከታይ ነበራቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ህዝብ መሪው የማክበር የቆየ ባህል ያለው ቢሆንም እረፍታቸው ከተሰማ በኋላም ታየ የተባለው ‹‹ህዝባዊ ሀዘን›› እና አቀባበል ኢህአዴግ በእየቀበሌው ካለው የካድሬ መዋቅርና የሥርዓቱ ተጠቃሚ አንጻር ሚያዚያ 29 1997 ኢህአዴግ የከተማው ህዝብ በሙሉ እንደወጣ ካወጀ በኋላ በማግስቱ በተደረገው የቅንጅት ሰልፍ ጋር ሲነጻጸር እንደገና ከተገመገመው ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡

የሶቬት መሪዎች እንደተጠቀሙበት ሁሉ የኢህአዴግ መሪዎችም የጠቅላይ ሚኒስተሩን ሚና በማግዘፍ በፖለቲከኞቹ መካከል ተከሰተ የተባለውን ክፍፍል ለመሸፈን፣ አባላቶቻቸውን ለማበረታት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም፡፡ በተጨማሪም የአቶ መለስ ሚና ጎልቶ መውጣት በፖለቲከኞቹ መካከል በሚፈጠር አለምግባባት የአቶ መለስን ፈለግ እንከተላለን የሚሉት ሌሎቹን ‹‹ታሪካዊ መሪያቸው›› የጣሉባቸውን አደራ የማይወጡ አስመስሎ ለመክሰስ ያመቻቸዋል፡፡ በተቃራኒው እስካሁን በአቶ መለስ ጥላ ተሸፍኖ መኖራቸው ሳይበቃ አሁን ለአቶ መለስ የሚደረገው ሙገሳ ወደፊት የሚመጣው መሪ ላይ ትልቅ ጫና ይኖረዋል፡፡ የአስከሬን አቀባቡ ወቅት አድናቂዎቻቸው ‹‹መለስ አይሞትም››፣ ‹‹ለማን ጥለኸን››፣ ‹‹አገሪቱ ማን አላት›› እና የመሳሰሉ ቁጭቶች ከዚሁ የመነጩ ናቸው፡፡
ሌኒን ወደ ፓርቲው ያመጧቸው ሰዎች እስከታመሙበት ጊዜ ጎልተው ያልወጡ ቢሆንም ለህዝብ እንዲታወቁ ግን ተደርገዋል፡፡ አቶ መለስ ‹‹መተካካቱ››ን ካፈለቁ በኋላ ወደ ፓርቲው እንደ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ያሉ መሪዎች ብቅ ቢሉም ወደመድረክ ከመጡት ይልቅ አንዳንዶቹ ከህዝብ ፊት እንዲርቁ ተደርገዋል። በእንዚህ ፖለቲከኞች መካከል በሶቬት ህብረት ፖለቲከኞች በተለየ በብሄር፣ በአባል ፓርቲ፣ በነባር ታጋይና በሲቪልነት አለመግብብት የሚፈጥሩ ሲሆኑ እስካሁን የአቶ ሀይለማሪያም ስታሊንነት፣ የአቶ በረከትና ኩማ ደመቅሳ ቡክሃሪን ወይም ስትሮትስካይነት፣ የአቶ አባዱላ፣ አርከበር እቁባይና ስዩም መስፍን ዚኖቪቭና ካሜኔብነት ወይንም እንደራሴነታቸው በፓርቲው ቮልሸቪክሳዊ መሰረታዊ ባህሪ እስካሁን ለመገመት ባይቻልም የ‹‹ሽግግሩ›› ጊዜ አጓጊና አስጊ እንደሚሆን ግን የሚጠበቅ ነው፡፡ በተለይ እነዚህ ፖለቲከኞች እስካሁን በነበረው መተማመን ያልሰፈነበት ስርዓት ውስጥ በተለያ ጎራዎች ተሰልፈው የየሚተዋወቁ በመሆናቸው በመካከላቸው የሚኖረው መጠራጠር በጥምረት ለመምራትም ሆነ ጎልቶ የሚወጣውን ለመገዳደር እንቅፋት የሚፈጠርባቸው መሆኑን መገመት ይቻላል አንዳቸውም በህዝብ ተቀባይነት የሚያስገኝ ልዩ ተሰጥኦ እንዳለቸው ለህዝብ ለማሳየት ጊዜ አለማግኘታቸው የስልጣን ሽግግሩንን አጓጊ የሚያደርገው ተጨማሪ ምክንያት ይሆናል፡፡

1 COMMENT

  1. ኢትዮጵያውያን ቶሎ ብለን በሌሎች ላይ መንጠላጠል ለምን እንደምናበዛ ይገርመኛል። መለስ ዜናዊን ከሌኒን፣ ከትሮትስኪ፣ ከስታሊን ጋር ማመሳሰል ድንቊርና እንጂ እውቀት አይደለም። የትግራይ ምሑራን (እነ አረጋዊ በርሀ፣ ብርሃነመስቀል ረዳ፣ ተስፋዬ ደበሳይ፣ ወዘተ) ይህንን ሊሉ አልደፈሩም። መለስ ጒብዝናው ማድባት፣ ተቀናቃኞችን ቶሎ መለየትና ማጥቃት ነው፤ እንደ መንግሥቱ ኃ/ማርያም። የዶክትሬት ማሟያ ጥናት እያካሄደ ነው ተባለ፣ እነ አሌክስ ዲ ዋል እና ሌሎች እየመከሩትና እየረዱት እንኳ መልክ ማስያዝ አልቻለም። በጅምር ቀረ። እነ ገላውዴዎስ አርአያ፣ ደስታ አሳየኸኝ ቢያገንኑት ምን ብሉ ጥናቱን አደባባይ ማውጣት አልተቻለም። አደባባይ ከወጣ የኮረጃቸው ሁሉ ሊጋለጥ ነው። ባለው ጥናት ላይ የሚጨምረው አዲስ ነገር አለመኖሩ ሌላው ጉዳይ ነው። ከእርሱ ቀደም ብሎ የጋናው መሪ የተመራመሩበት ስለነበር መለስ ያንኑ በሌላ መልክ ከመድገም ውጭ የማይችለው ሆነ። መለስ ጎበዝ አይደለም ክርክሬ። መለስ ጎበዝ ነው። መለስ ደግሞ ጥራዝ ነጠቅም ነው! አንዳንዶች “ሞት ቀደመው እንጂ” ይሉናል። የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንዲሉ ኢትዮጵያ ላይ የፈጸማቸው የኢኮኖሚ በደሎች ግልጽ ሆኖ እያለ ለአፍሪካ ልማት መቆርቆሩ ራሱን ከማተለቅ በስተቀር ፋይዳ አልነበረውም። ቀድሞ በቅልጥፍና የማረካቸው ምሑራን አሜሪካኖች (ስትግሊትዝ፣ ሳክስ) የእንግሊዝ ፖለቲከኞች (ብሌር፣ ጌልዶፍ) ነቅተውበት ገሸሽ አርገውት ነበር። በነገራችን ላይ መለስ ከሞተ ሰባት ኣመት ሊሞላው ነው፤ የሚያስታውሰው ቢኖር ሚስቱና ልጆቹ ናቸው። በኦሮምያ ተረስቶአል። በአማራ ክልልም። በደቡብም። በአዲስ አበባ መሳቂያ መሳለቂያ ሆኗል። ምን ቀረ? ትግራይም እንኳ ኃፍረት ይዞአቸው ነው!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.