የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት የሚያስችል አዲስ መመሪያ ማዘጋጀቱን የአማራ ክልል ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 15/2011 ዓ.ም (አብመድ) ማኅበራት በጋራ ሆነው ህንጻ የሚገነቡ ከሆነ ቅድሚያ ቦታ እንሚያገኙም ተገልጿል፡፡

የአማራ ክልል የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት የሚያስችል የተሻሉ ስልቶችን በመቀየስ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቋል፡፡ በሥራ ላይ ያለው መመሪያ ቁጥር 28/2009 ኅብረተሰቡ በማኅበር ተደራጅቶ የራሱን ቤት ሊገነባ የሚችልበትን ቦታ እንዲያገኝ ያስችላል፡፡ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ምስራቅ ተፈራ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የክልሉ መንግስት መመሪያውን በመጠቀም ለተደራጁ ማኅበራት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ ሲሰጥ ቆይቷል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም በስፋት የመኖሪያ ቤት እጥረት መኖሩን አመላክተዋል፡፡

ቢሮው የመኖሪያ ቤት ችግሩን ለመፍታት የተሻሉ ስልቶችን በመቀየስ ወደ ሥራ መገባቱንም አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ክልሉ ማኅበራት የጋራ ህንጻ የሚገነቡ ከሆነ ቅድሚያ ቦታ የሚያገኙበትን አዲስ መመሪያ አውጥቷል፡፡ ከተሞች ወደ ጎን እየተለጠጡ የእርሻ ቦታቸዎችን ለግንባታ እንዲውሉ ከማድረግ ባለፈ መንግሥት ጥራት ያላቸው መሠረተ ልማቶችን በተሟላ መንገድ እንዳይሰጥ አድርጎታል ብሏል ቢሮው፡፡ በመሆኑም ከተሞችን ወደ ጎን ሳይሆን ወደ ላይ በማሳደግ የተሟላ ጥራት ያለው እና ለኑሮ ተስማሚ መሠረተ ልማት እንዲሟላ ማስቻል የመመሪያው ዓላማ ነው ተብሏል፡፡

አዲስ የወጣው መመሪያ ቁጥር 4/2011 ማኅበራት በጋራ ሆነው ህንጻ ሲገነቡ እንዴት ቅድሚያ ማግኘት እንደሚችሉ፣ የዋጋ ተመኑን፣ የማስያስያዣ ገንዘቡን ምጣኔ፣ ገንዘቡ የሚለቀቅበትን መንገድ፣ የግንባታ ዋጋ ግምቱን እና የግንባታ መስሪያ ዲዛይን ጭምር እንደሚተነትን እና አሠራሩን የተሟላ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡ በመመሪያው እውቅና ለማግኘት የሚያዘው የገንዘብ መጠንም ወደ 20 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉን አቶ ምስራቅ በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡ ማኅበራት የግንባታ ቁፋሮ ሲጀምሩ 50 በመቶው፣ መሠረት ካወጡ በኋላ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ያስያዙት ገንዘብ የሚለቀቅ ይሆናል፡፡

የአንድ ማኅበር የህንጻ ዲዛይን ተመሳሳይነት ያለው እና እስከ መጨረሻ ድረስ በጋራ የሚሰራ እንደሚሆንም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡ የሚሰራው ህንጻ ከፍታም ከባለ አራት ፎቅ በታች አይሆንም፡፡ ግንባታው ሲጠናቀቅ የታችኛው የቤት ክፍል በጨረታ እንዲሸጥ እና ለንግድ አገልግሎት እንዲውል የሚፈቅድ አሠራርም እንዳለው በመግለጽ ግንባታው ሲጠናቀቅ የማኅበሩ አባላት እንዴት ይከፋፈላሉ ለሚለው አሰራር እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡
በቅርቡ የወጣው የማስፈጸሚያ መመሪያ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኃላፊው ከአሁን በፊት በነበሩት መመሪያዎች ላይ ተደምሮ የተሻለ ውጤት ሊያመጣ የሚችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አሠራሩን የተለየ የሚያደርገው በማኀበር ሕንጻ እንዲገነቡ ማድረጉ ነው፤ ከዚህ ቀደም የነበረው መመሪያ ቁጥር 28/2009 በሥራ እንደ ሚቀጥልም ታውቋል፡፡ ትዳርን ፈትቶ መደራጀትንም ይከለክላል፡፡ ባለትዳሮች በህጋዊ መንገድ ትዳር ፈትተው ቀደም ብሎ ቦታ ያልደረሳቸው ከሆነ ለመደራጀት አራት ዓመት መቆየት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በአንዳንድ ከተሞች ላይ ኅብረተሰቡ ተደናግሮ ያልተገባ ወጭ እያወጣ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል፡፡

ኮንዶሚኒየም ሊሰጥ ነው በሚል ሰበብ በዚህ መንገድ መደራጀት ለሚፈልጉ በልዩ ሁኔታ በተከለከለባቸው አካባቢዎች ላይ ኅብረተሰቡን የሚያደናግሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የተደራጁ ማኅበራትም ወደዚህ አሠራር ቀድመው የሚገቡ ከሆነ በከተሞች ፈቃድ እና ይሁኝታ በነበራቸው አደረጃጃት መሠረት የሚተገበርላቸው ይሆናል፡፡ ተጨማሪ አዲስ ማደራጀትን በሚመለከት ከተሞች ካላቸው የከተማ ቦታ ምጣኔ እና ከኅብረተሰቡ የመኖሪያ ቤት ችግር ጋር አጣጥመው መስጠት በከተሞች የሚወሰን ይሆናል ተብሏል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.