ሜቴክ የ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ኪሳራ እንደገጠመው ገለፀ

የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሜቴክ ቅድመ ክፍያቸው በባከኑ የምርት ትዕዛዞች ምክንያት የ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ኪሳራ እንደገጠመው አስታውቋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ካሉት 14 ኢንዱስትሪዎች በተሻለና በሙሉ አቅም በምርት ላይ የሚገኙት አራቱ መሆናቸውን የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል አህመድ አምዛ ለኤፍ ቢ ሲ ተናግረዋል፡፡

ሜቴክ በበርካታ ቀውስ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም ተቋሙ በ2011 በጀት ዓመት ከ9 ቢሊየን ብር በላይ ሽያጭ በመፈጸም 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ትርፍ ለማግኘት አቅዶ ነበር ብለዋል፤ ነገር ግን ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ከማትረፍ ይልቅ ኪሳራ ውስጥ እንደገባ ነው የተገለፀው፡፡

ለመክሰሩ ምክንያት ሁሉም ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት አለመግባታቸው አንዱ ቢሆንም በዋነኝነት ግን ቅድመ ክፍያ የተፈጸመባቸው ምርቶች ናቸው ተብሏል።

ውል ተፈፅሞ ገንዘቡ ገቢ ባልሆነበት ሁኔታ ምርቶቹን በውሉ መሠረት አምርቶ ማስረከብ ግድ ይለዋል። በዚህ ምክንያት ወጪ እንጂ ገቢ ባለመኖሩ ተቋም ትርፋማ እንዳልሆነ እና 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ኪሳራ እንደገጠመው ተጠቁሟል፡፡

ተቋሙ በ2012 በጀት ዓመት የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ግማሽ ቢሊየን ብር ትርፍ ለማሳካት አቅዷል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ሽያጭ ለመፈጸም የታቀደው ተጨባጭ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል አህመድ አምዛ አሁን ላይ ሁሉንም ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እየገቡ መሆኑን አንስተዋል። ኢንዱስትሪዎቹ የምርት መጠናቸውን እንዲጨምሩ የ24 ሰዓት ስራን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እንደተጀመረም ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ባለፈ ተቋሙ ዋነኛ ማነቆ የሆነበትን ቅድመ ክፍያቸው የተፈፀሙ ምርቶች እየተጠናቀቁ በመሆናቸው በቀጣይ ትርፋማ ለመሆን እንደሚያስችል ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ሽያጭ መፈጸሙ ለእቅዱ መሳካት ከወዲሁ በማሳያነት ተመላክቷል።

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 15/2011 ዓ.ም (አብመድ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.