ኢህአዴግ በዜጎች ላይ ፍርሃት በመልቀቅ እንዲመረጥ እያግባባ ነው ሲሉ የባህርዳር ነዋሪዎች ተናገሩ

ዘጋቢያችን በላከችው ሪፖርት የገዢው መንግስት ካድሬዎች በየመንደሩ በመዞር የሚደርጉት የምርጫ እንቅስቃሴ የነዋሪዎችን ነጻነት ከማሳጣቱ በተጨማሪ፣ ኢህአዴግ በሚጠራው የመንደር ስብሰባዎች የሚቀር ሰው የተቃዋሚ ድርጅት ደጋፊ ተብሎ ይመዘገባል።

የገዢው ፓርቲ አባላትና የቀበሌ አመራሮች በየሰፈሩ በሚያደርጉት ስብሰባ በአካባቢው የሚኖሩ ባለሃብቶችን ያለ ፈቃዳቸው ለዕለቱ የሚስፈልገውን ለቡና፤ዳቦ እና ቆሎ ዝግጅት የሚውል ገንዘብ በመቀበል በሰፈሩ በመዘዋወር እንዲሰባሰቡ የሚያደርጉ
ሲሆን፣ የሚዘገዩ ሰዎችን ስልክ በመደወል ‹‹ ለምን አልመጣችሁም?›› ፣ ‹‹ ጸረ ህዝብ ስራችሁን አቁሙ!›› በሚሉ ማስፈራሪያዎች ገዢውን መንግስት እንዲመርጡ ለማድረግ እየጣሩ ነው።

በየመንደሩ የሚካሄዱት ስብሰባዎች በየሶስት ቀኑ የሚቀጥሉ መሆኑን ያስታወቁት የገዢው መንግስት ካድሬዎች በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ጫና በመፍጠር ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ ዜና ደግሞ አምስቱ የኢህአዴግ አጋር ተብለው የሚታወቁ ክልሎች ማለትም ሶማሌ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና ሃረሪ ቅዳሜ በአዲስአበባ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የስብሰባ ማዕከል በመገኘት ለኢህአዴግ ያላቸውን አጋርነት ከማረጋገጥ አልፈው በመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደሰማያዊ ፓርቲ ያሉትን ፓርቲዎች ያወግዛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም ኢህአዴግ በወጣት ሊጉ አማካይነት በአዲስአበባ በየክፍለከተማው ወጣቱ ኢህአዴግን እንዲመርጥ የተለያዩ ቅስቀሳዎችን ሲያደርግ የሰነበተ ሲሆን፣ በብዙ አካባቢዎች ወጣቶች ኢህአዴግን እንደማይመርጡ ፊት ለፊት ከመናገር ጀምሮ ተቃውሞአቸውን በተለያየ መንገድ እየገለጹ መሆናቸው ታውቆአል፡፡

ሰሞኑን በየካ ክፍለከተማ በተደረገ አንድ ስብሰባ ላይ ወጣቶች “ኢህአዴግ ምን ስላደረገልን እንመርጠዋለን» በማለት ጥያቄ ከማቅረብ ጀምረው ሥራአጥነትና የኑሮ ውድነት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር የመሳሰሉ ችግሮችን በማንሳት እንደማይመርጡት በግልጽ ተናግረዋል።

Source:: Ethsat