የኢፌዴሪ  ሕገ-መንግሥት መቀየር ያለበት ምን ጉድለት ስላለበት ነው?

የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ለምን መቀየር እንዳለበት ተጨባጭ ምክንያቶችን ከመሰንዘራችን ፊት  የሕገ-መንግሥትን ትርጉምና ዋና ዓላማ ምን እንደሆነ ባጭሩ  መመልከቱ ለግንዛቤ ይረዳል::

ሕገ-መንግሥት ማለት የአንድ አገር የሕጎች ሁሉ እናት ወይም የሕጎች ሁሉ የበላይ ነው:: ዋና ዓላማውም በአንድ መልከዐ-ምድር  በአንድ መንግሥታዊ አስተዳደር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሰላማቸው እንዲጠበቅ  ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ  ጥቅማቸውና ነፃነታቸው እንዲረጋገጥ  የጋራ ደኅንነታቸው እንዳይናጋ  ተፈጥሮአዊ የሆነው ሀሳብን የመግለጽ የፈለጉትን ሃይማኖት የማምለክ ነፃነትና መብቶች ተከባሪ እንዲሆኑ የሚደነግግ የአገሪቱ ሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ነው::  ባጭሩ ፍትሕ ነፃነት ዕኩልነት  እና ወንድማማችነት የተሰኙት መርሆዎችን ያካተተ የዜጎችን መብቶችና ነፃነቶች የመንግሥትን ኃላፊነትና ግዴታዎች  የመንግሥቱን አደረጃጀት ዓይነትና ቅርጽ አገሪቱና ሕዝቡ የሚመሩበትን  የዕድገት ፈለግ  የሚከተሉትን የኢኮኖሚ ሥርዓትና የዓለም አመለካከት የሚወስን በምላተ ሕዝቡ ይሁንታ የሚጸድቅ በዜጎችና በመንግሥት መካከል የሚኖር ግንኙነት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው::

እነዚህን ጉዳዮች አካቶ ከ250 ዓመታት በላይ የዘለቀውና የዲሞክራሲይ አስተዳደር ምሳሌ በመሆን የሚጠቀሰው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ የሕገ-መንግሥት ዓላማ ምን እንደሆነ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል::”የተባበሩት የአሜሪካ ግዛቶች ፌደራላዊ መስተዳድር ሕገ-መንግሥት ዓላማዎች ፍትሕን ማስፈን  ውስጣዊ ሰላምንና የጋራ  መከላከያን  ማረጋገጥ  አጠቃላይ ማኅበራዊ ዋስትናን ማስፋፋት እና  የተፈጥሮ ሥጦታ የሆኑትን ነፃነቶችና  መብቶችን  ለራሳችንና ለሁላችን ብልጽግና ማስጠበቅ” እንደሆነ ይገልጻል::

በተመሳሳይ ሁኔታ የሕንድ ሕገ-መንግሥት ዓላማዎች የማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍትሕ መረጋገጥ  የሀሳብ የእምነት እና የሃይማኖት ነፃነት መከበርና የሁኔታዎች (opportunity) እና  ደረጃዎች (status) ዕኩልነት መረጋገጥ ዓይነተኛ ዓላማው እንደሆነ ያስረዳል::

ከነዚህ አጠቃላይ የሕገ-መንግሥት ትርጉምና ዓላም  ስንሳ  ሕገ-መንግሥት በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለ  በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው  የሁለቱ አካሎች ግንኙነት ግዴታና ኃላፊነቶችን የያዘ ውል ወይም ማኅበራዊ ስምምነት ነው:: ስምምነቱም ቀጣይና ዘላቂ የሚሆነውም ሁለቱም አካሎች ሰነዱ ለሰጣቸው ኃላፊነቶችና ግዴታዎች ሳያዛንፉ በሥራ ላይ ሲያውሉ ነው::  በታሪክ ተደጋግሞ እንደታየው ሕዝብ ቃሉን አክባሪ ግዴታውን ተወጭ ሲሆን  መንግሥታት በተለይም አምባገነን የሆኑ የገቡትን ውል ሲያከብሩ አይታዩም:: በመሆኑም በሕገ-መንግሥቱ የተገለጹትን መብቶችና ነፃነቶችን የሚገፈው መንግሥት (state)ወይም መስተዳድር (government)  እንደሆነ ይታወቃል:: መንግሥት የዜጎችን መብቶችና ነፃነቶች የሚገፍባቸው ምክንያቶች የተለያዩ እንደሆኑ ቢታወቅም  ዋና ዋና ምክንያቶቹ ግን የሚከተሉት ናቸው::

አንደኛ ሕዝብ ያልመከረባቸውን ያልተስማማባቸውን እና ያላመነባቸውን ሕጎች በልዩ ልዩ ጫና የሕገ መንግሥቱ አካሎች  ማድረግ::

ሁለተኛ በአስፋጻሚ አካሉ ጫና እና ተጽዕኖ ሕገ-መንግሥታዊ ባልሆነና የሕግን ሂደት ባልተከተለ መንገድ በሕግ ስም በዜጎች መብትና ነፃነቶች ላይ ጫና ሲፈጠር::

ሦስተኛ   ከማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ ዕድገት ጋር ተያይዞ ሕገ-መንግሥቱ አልሻሻል ሲል እና የዜጎችን ፍላጎቶች ማሙዋላት ሲሳነው:: ይህም በመሆኑ ሕገ-መንግሥቶች የሰላም የነፃነት የዕኩልነትና የተረጋጋ ማኅበራዊ ሕይዎት መሠረት መሆናቸው ይቀርና የብጥብጥ  የእገዛለሁ አልገዛም ምንጭ በመሆን የአገር እና የሕዝብ ሰላም ጠንቅ ይሆናሉ::

በዛሬው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የችግሮች ሁሉ ምንጭ ይኸው ሕገ-መንግሥት የሚባለው ነው:: ላለፉት 28 ዓመታት ሕዝቡ ምትክል የለሽ ሕይዎቱን መስዋዕት በማድረግ የአንድነቱ የሰላሙ የጥቅሙ የመብቶቹና የነፃነቶቹ ሁሉ ፀር የሆነው ሕገ-መንግሥት ይለወጥ ወይም ይሻሻል እያለ እየጮኸ ያለው ሕገ-መንግሥቱ  ከዜጎች መብቶች ነፃነቶች ጥቅሞችና ፍላጎቶች ተፃራሪ በመቆሙ ነው::

እንደ ዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት እምነት ሕገ-መንግሥቱ ይቀየር ወይም ይሻሻል የምንለው በሚከተሉት ተጨባጭ ምክንያቶች ነው::

 1. ሕገ-መንግሥቱ ሲረቀ ሲዘጋጅ እና እንዲጸድቅ ሲደረግ ከሚሊዮን በላይ የሆኑትን ስለሕገ-መንግሥት ምንነት ሠፊ ዕውቀት ያላቸውን የተካበተ ልምድና የአገር ምንነት በቅጡ የሚያውቁትን ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት መጠበቅ ከፍተኛ መሥዋዕትነት የከፈሉትን (ሀ) ከሰባት መቶ ሽ/700,000/ በላይ የሆኑትን የመከላከያ ሠራዊት አባሎችን (ለ) በሽዎች የሚቆጠሩትን የፖሊስ ሠራዊት አባላትን (ሐ) ከአንድ ሚሊዮን /1,000,000/ በላይ የሆኑ የኢሠፓ አባላትን (መ) በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ በአገሪቱ የሚገኙ የከተማ ቀበሌ ማኅበራት ከቀበሌ እስከ አጠቃላይ የከተሞች ማኅበራት ተመራጭ የነበሩትን (ሠ)በመላ አገሩቱ በሚገኙ ከገበሬ ቀበሌ ማኅበር እስከ አገር አቀፍ የተደራጁ ማኅበራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተመራጮችን (ረ) በገጠርና በከተማ ከቀበሌ እስከ አገር አቀፍ የተደራጁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የወጣትና የሴቶች ማኅበራትን አመራሮችን (ሰ) ከመሠረታዊ ማኅበር እስከ አገር አቀፍ የተደራጁ የሠራተኛ ማኅበር ተመራጬችን (ሸ) ቁጥራቸው በአሥር ሽዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱን የደኅንነት ሠራተኞች ወዘተ  በፖለቲካ አቁዋማቸው ብቻ ያለሕግ ሂደት  በሕገመንግሥቱ ቀረፃና ጸደቃ ሂደት በፖለቲካ ውሣኔ ድምፅ እንዳይሰጡ ተደርገዋል:: በመሆኑም እነዚህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች  እንዳይሳተፉ በመደረጉ ሕገ-መንግሥቱ በዜጎች መብትና ጥቅም ላይ የቆመ እንጂ የቆመላቸው ባለመሆኑ  የነዚህ ዜጎች ድምፅ ሊሰማ ይገባል::  ይህም ሕገ-መንግሥቱ እንዲሻሻል ግድ ያደርገዋል::  ሕገ-መንግሥቱ ሲጀመር ዜጎችን አግላይና ከፋፋይ በመሆኑ የአገሪቱ  ሰላምና አንድነት ፀር ሆኖ የቆመ ስለሆነ እውነተኛ ሰላምና አንድነት  በነበረ መልኩ እንዲቀጥል ለማስቻል የጥላቻና የመለያየት ግንብ የሆነው ይህ ሕገ-መንግሥት መለወጥ አለበት::
 2. ሕገ-መንግሥቱ የግለሰብን ነፃነት የሚፃረር ከመሆኑም በላይ ለግለሰብ ዜጎች መብት አይሰጥም:: መብት የሚሰጠው “ለብሔር/ ብሔረሰቦች/ ሕዝቦች” ለሚላቸው ትርጉማቸውና ማንነታቸው በግልጽ ለማይታወቁ አካላት ነው:: በሌላ በኩል ቁጥራቸው ከአንዳንድ ብሔረሰቦች እና ብሔሮች እጅግ የሚበልጥ መጠን ላላቸው ከሁለት እና ከዚያም በላይ ብሔር/ብሔረሰቦች/ሕዝቦች ለሚወለዱ ሰዎች የዜግነት መብታቸውን በመግፈፍ ያባት ወይም የእናት ማንነታቸውን ተገደው እንዲመርጡ በማድረግ ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዲጠፋ ያደረገ በመሆኑ  እነዚህ ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ዜጎችን መብትና ነፃነት ለማስከበር ሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ግድ ይለዋል::
 3. ሕገ-መንግሥቱ ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኩዋ የገነባቻቸውን የወል እሴቶችና የታሪክ ጉዞ በመካድ ከሦስት ሽ ዓመታት በላይ ጸንተው የቆዩትን መልካም ግንኙነቶች “የተዛቡ” ናቸው:: ያዛባውም ዐማራ ነው በማለት ዐማራው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ዓለም አቀፍ ወንጀል ሰለባ እንዲሆን በመሣሪያነት ያገለገለ በመሆኑ የነባሩ ኢትዮጵያዊነት የወልና የአብሮነት የግንኙነት እሴቶች የሆኑት ተገቢ ቦታቸውን እንዲይዙ ሕገ-መንግሥቱ መለወጥ ወይም መሻሻል ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው::
 4. በኢትዮጵያ ካሉት ነገዶች በቁጥሩ ከፍተኛ የሆነው የዐማራ ነገድ በጠላትነት ተፈርጆ በሕገ-መንግሥቱ ማርቀቅና ማጽደቅ ሂደት እንዲወከል አልተደረገም:: በመሆኑም በሕገ-መንግሥቱ የዐማራውን ጥቅምና መብት ያላካተተ ስለሆነ ሕገ መንግሥቱ መለወጥ አለበት::
 5. ሕገ-መንግሥቱ ልዩነትን የሚያራባ  መነጣጠልን የሚሰብክ በመሆኑ የአብሮነት የሰላም እና የልማት ፀር ነው:: በመሆኑም ለኢትዮጵያ አንድነት ጠንቅ ነው:: የልማትና የዕድገት ማነቆ ነው:: ይም በመሆኑ ዛሬ አገሪቱ ለገባችበት ሁለንተናዊ ችግር ምክንያቱ ሕገ-መንግሥቱ ስለሆነ ይህን መለወጥ ግዴታ ነው::
 6. ሕገ-መንግሥቱ የአገሪቱን ረጅም የአገርና የመንግሥትነት ታሪክ የሕዝቡን ውስብስብና ጥብቅ መስተጋብር ክዶ እና የነበረውን ንዶ በአዲስ ማንነት ላይ ለመመሥረት ያለመ በመሆኑ ይህም የሕዝቡ ማኅበራዊ ሰላም ዕድገትና ብልፅግና ፀር በመሆኑ የሕገ-መንግሥቱን መቀየር ግድ ያደርገዋል::
 7. የአገሪቱን ዓለማቀፋዊ ድንበር ዓለም በሚያውቃቸው ቁዋሚ ምልክቶች ሳይሆን ጠፊ እና ዕውቅና በሌላቸው የብሔር/ብሔረሰቦች/ሕዝቦች ክልል ደንበር ነው ማለቱ የአገሪቱን የምድርና የአየር ክልል በቁዋሚነት ለማስጠበቅ የማያስችል ስለሆነ ሕገ-መንግሥቱ ዳር ድንበሩ በቁዋሚ ምልክቶች መገለጽ ስላለበት ይህን ዕውን ለማድረግ የሕገ-መንግሥቱ መለወጥ የግድ አስፈላጊ ነው::
 8. ሕገመንግሥቱ በልዩነት ላይ የተመሠረተና ልዩነትን የሚያራባ ከመሆን ዘሎ የአገሪቱን የመንግሥት አደረጃጀት በቁዋንቁዋ ልዩነት ላይ ያዋቀረ ነው:: ይህም ለዘላቂ ሰላም ተከታታይ ዕድገት እና አብሮነትን አያጎናጽፍም:: ሰላምና ተከታታይ ዕድገትና አብሮነት ከሌሉ ኢትዮጵያ እንደአገር መቀጠል አትችልም:: እንደአገር እንድትቀጥል በዚህ  ከፋፋይ ሕገ-መንግሥት  መሣሪያነት የተደራጀው የፌደራል መንግሥት አሀዶች አደረጃጀት መለወጥ አለበት:: ይህም የሕገ-መንግሥቱን መለወጥ ግድ ያደርገዋል::
 9. ከፌደራሉ ሕገ-መንግሥት የመነጩት የየክልሉ ሕገ-መንግሥቶች የክልሉን ባለቤትነት የሚሰጡት ክልሎቹ ለተሰየሙባቸው ነገዶች ነው:: ለምሳሌ የትግራይ ክልል ባለቤቱ ትግሬ ነው:: የኦሮሚያ ክልል ባለባቱ ኦሮሞ ነው:: የአፋር ክልል ባለቤቱ አፋር ነው:: በነዚህ ክልሎች የሚኖሩ የሌሎች ነገድ አባሎች የክልሉ ባለቤትነት የላቸውም:: የነዚያ ክልሎች ባለቤቶች ሁለተኛ ዜጎች ናቸው:: የክልሉ ባለሥልጣኖች ባሻቸው ጊዜ መጤዎች ብለው ሊያባርሩዋቸው ይችላሉ:: ዐማራው በተለያዩ ክልሎች ለዘመናት ከኖረበት አካባቢዎች የተባረረው ሕገ-መንግሥቱ የባለቤትነት ዋስትና የከለከለው በመሆኑ ነው:: በሌላ በኩል ዐማራ የተባለው ነገድ በእርሱ ስም የተከለለው ክልል ባለቤት አይደለም:: ይህም በመሆኑ ዐማራው ዐማራው በስሙ በተሰየመው ክልልም ሆነ ከክልሉ ውጭ ባሉ የኢትዮጵያ የግዛት አካል የባለቤትነት መብት የለውም:: ለዚህም ነው ሕገ-መንግሥቱ ፀረ ዐማራ ነው የሚባለው:: ይህ በቁጥሩ ከፍተኛ ከሚባሉት ነገዶች ግንባር ቀደም የሆነን ነገድ የአገር ባለቤትነት የነፈገ ሕገ-መንግሥት  ባለበት መልኩ ይቀጥል ማለት በዐማራው ላይ የዘር ጥፋት ወንጀል ማወጅ ነው:: ይህ እንዲሆን ደግሞ ዐማራው አይፈቅድም:: በመሆኑም ሕገመንግሥቱ መሻሻል አለበት::
 10. ሕገ-መንግሥቱ የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነት ሰነድ ሆኖ በዘላቂነት እንዲያገለግል ተደርጎ የተቃኘ አይደለም:: ዘላቂ ሆኖ እንዲያገለግል ቢፈለግ ኖሮ በአገሪቱ የሚገኙ ብዙኃን ሰዎች ቀርቶ ግለሰቦች በሂደቱ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ይደረግ ነበር:: የሆነው ተቃራኒው ነው:: ሕገ-መንግሥቱ የትሕነግ/ወያኔ እና የኦነግ ኢትዮጵያን የማፈራረሻ ፕርግራም ነው:: የፖለቲካ ድርጅቶች ፕሮግራም በምንም ተዓምር የአገር ሕገ-መንግሥት ሊሆን አይችልም:: በመሆኑም ሕዝባችን በሁለት ፀረ ኢትዮጵያ ቡድኖች ፕሮግራም ሊገዛ አይገባምና መለወጥ ወይም መሻሻል  አለበት::
 11. ሕገ-መንግሥቱ የተቃኘው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የዓለም አመለካከት ነው:: ይህ አመለካከት ደግሞ ለገቢያ መር ኢኮኖሚና ለነፃ ውድድር ሥርዓት ተቃራኒ ከመሆኑም በላይ የዲሞክራሲ ዋልታ ለሆነው የሕዝብ ተሳትፎ በሩ ዝግ የሆነ ስለሆነ ለነፃ ገበያና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ በሆነው የሊበራል የዓለም አመለካከት መተካት አለበት:: ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ ሕገ-መንግሥቱ መለወጥ ወይም መሻሻልን ይጠይቃል::
 12. ሕገ-መንግሥቱ ከጥንስሱ እስከ ድምዳሜው ሕዝብ የመከረበትና የተወያየበት አይደለም:: በመሆኑም ሕገ-መንግሥቱ በሕዝብ ላይ የተጫነ በመሆኑ የኔ ብሎ የተቀበለው አይደለም::  ይህ ሕገ-መንግሥት ምላተ-ሕዝቡ ሊመክርበትና ሊስማማበት ቀርቶ ሕገ-መንግሥቱ እንዲረቀቅና እንዲጸድቅ ብሎም በፊርማቸው ያጸደቁት ዶር ነጋሦ ጊዳዳን ጨምሮ በማርቀቅ ሂደቱ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው አቶ ክፍሌ ወዳጆና ዶር ኃይሌ ወልደሚካኤል  ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም የማይበጅ ከፋፋይ እንደሆነ በሂደቱም ሆነ በፍጻሜው ተናግረዋል::  ስለሆነም ሕገ-መንግሥቱ  የሕዝቡን አንድነት ሰላምና  መረጋጋት እንዲሁም ተከታታይ ዕድገትና ብልጽግና የሚያረጋግጥ ስላልሆነ መለወጥ ወይም  መሻሻል  አለበት::
 13. ሕገ-መንግሥቱ ሰላም ፍትሕ ዕኩልነት ተከታታይ ዕድገትና ብልጽግና እንዲሰፍን ቁልፍ መሣሪያ እንደሆነ ይታመናል:: የዚህም መሣሪያ ማስፈጸሚያው የመንግሥት ቢሮክራሲ ቁጥጥርና ሚዛን(Check and Balance) መኖር ነው:: ይህም ሕግ አውጭ ሕግ ተርጉዋሚና አስፈጻሚ የሚባሉት ታላላቅ አካሎች ሕገ-መንግሥቱ በሚደነግገው መሠረት  ሥራዎች መከናዎናቸውን  ለማረጋገጥ  አንዱ ሌላውን ይቆጣጠራል:: ይጠብቃል:: ዝንፈት ሲከሰትም አስቸኩዋይ እርምት እንዲወሰድ አንዱ ሌላውን ያስገዳል::  በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እነዚህ አካሎች በራሳቸው ነፃ ሆነው የማይንቀሳቀሱ በመሆኑ ይህ አንዱ አካል ሌላው የመቆጣጠርና ሚዛን የመጠበቅ ሁኔታ የለም:: የአስፈጻሚ አካሉ ያሻውን በማድረግ ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን መብቶችና ነፃነቶች ይገፋል:: ይገድባል:: ይህም በመሆኑ ሕግና ሕጋዊነት ከሁሉም በላይ በሕግ የበላይነት ምትክ የግለሰቦች ወይም የድርጅቶች የበላይነት ሰፍኑዋል:: ይህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ፀረ ዲሞክራሲ አሠራርና አስተሳሰብ ስለሆነ የሕገ መንግሥቱን  መቀየር ወይም መሻሻል ግድ ያደርገዋል::
 14. የሕገ መንግሥት ጉዳዮች የትርጉም ችግር ሲነሳ እንዲተረጉም ሥልጣን የሰጠው በብሔር/ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ኮታ ላይ ተመሥርቶ ለተዋቀረ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው:: ይህ አካል የሕግ ዕውቀቱና ልምዱ ምን ያህል እንደሆነ በግልጽ ከመታወቁም በላይ ተመራጮቹ በፖለቲካ ድርጅት አባልነታቸውና በሚያራምዱት አመለካከት ታጭተው የተመደቡ እንጂ ስለሕግና ሕጋዊነት በቂ ዕውቀትአላቸው ተብለው የተሰየሙ አለመሆናቸው ግልጽ ነው:: በሌላ በኩልም የሕግ ዕውቀት አላቸው ወይም በሙያተኞች ያሠራሉ ከተባለም ሕግ የመተርጎም ኃላፊነት ሊሰጠው የሚገባው የፍርድ ሥርዓቱ አካል ወይም የተለየ ኮሚሽ እንጂ ይህ አካል ሊሆን አይገባውምና ለዚህም ሲባል ሕገ- መንግሥቱ መሻሻል ወይም መለወጥ አለበት እንላለን!
 15. ያሁኑ ሕገ መንግሥት የአገሪቱን ሥልጣን የሚቆጣጠረው በምርጫ አብላጫ ድምፅ ያገኘው ወይም ያገኙት ድርጅቶች በጥምረት እንደሆነ ይታወቃል:: ይህ በድርጅት ስም ባንድ ቀበሌ የተመረጠ ሰው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሁን ማለት ለሕዝቡም ሆነ ለተመራጩ የሞራል ልዕልዕናን የማያጎናጽፍ ስለሆነ ይህን ልዕልና መራጩ ሕዝብም ሆነ ተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመጎናጸፍ  ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የተለያዩ ሰዎች በፓርቲ ወይም በግል ተወዳድረው ሕዝቡ የኔ የሚለውን የመምረጥ እድል እንዲሰጠው ያስፈልጋል:: ይህ ደግሞ የሕገ-መንግሥቱን መለወጥ ወይም መሻሻል ይጠይቃል::
 16. በሕገ-መንግሥቱ ለጠቅላይ ሚኒስቴርነት የሚበቃው ኢሕአዴግ በሚል ስብስብ ትሕነግ በአምሳሉ የፈጠራቸው አራት ድርጅቶች ማለትም ትሕነግ/ሕወሓት ብአዴን/አዴፓ ኦሕዴድ/ኦዴፓ እና ደኢሕዴግ ብቻ ነው:: ሌሎች ቀርቶ አጋር ድርጅቶች የሚባሉት የሶማሊ የአፋር የጋምቤላ የቤንሻጉል እና የሐረሪ ክልል ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች ኢትዮጵያን እንዲመሩ ዕድል አይሰጥም :: ይህም ሕገመንግሥቱ ለአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን ቦታ ከአራት ክልሎች ወይም ድርጅቶች ውጪ ያሉት መያዝ ቀርቶ እንዳያስቡ ተደርጎ የተቃኘ ነው:: ባጭሩ ለተወሰኑ ክልሎች የነጋሢነት መብት ሲሰጥ ሌሎቹን ተገዥ አድርጎ የፈረጀ ነው:: ይህ መታረም ያለበት ጉዳይ ነው:: የፖለቲካ ሥልጣን ብቃት ችሎታና የሕዝብ አመኔታ ያላቸው ሰዎች ተወዳድረው በሕዝብ ምርጫ ለሥልጣን በውክልና የሚይዙበት ሥርዓት መዘርጋት ይኖርበታል:: ይህ እንዲሆን ደግሞ ሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ወይም መለውጥ ግድ ይላል::

4 COMMENTS

 1. HEGE MENEGESTU NE. YESAFUTE. SEWOCHE. ALAKEBERUTEME. .LEBOCHE, ZEREGHOCHE.,NEFSE GWDAYOCHE. HONU. HEZBUNE .BE EREHABE,. SERA BEMATATE. ASEKAYUTE. BE MESEDEDE. MENE TENEGERO .YALEKALE. . MEBERAT, WEHA , INTERNET ,BE MEZGATE. MATA MATA SEWE BE MAFENE, MENE YALADEREGACHEHUTE. ALE. ENANETE. TEGEREWOCH(WEYANEWOCHE ? 🤔 ASEBU. BEREGETE. YELUGHETA .YELACHEHUME. YEHE NEWE YE ENANETE HEGE MENEGESETE, MESEHAFUNE. KEWEDEDACHEHUTE. WEDE MEKELEYACHEHU. BE ERESA SATENE. WESETE ASEKEMETU ENA. KE ENE MELKU ENKWANE KE MEDEBEREWE. BANDERACHENE 🇪🇹 CHEHU. GARE. TESHEKEMACHEHU. HEDULENE .EGHA ADDIS HEGE MENEGESETE..KE USA ENDAYEMETA LEBE🇱🇷 LELA YEMENELEWE .YELENEME. ENANETE. YAWAREDACHEHUTENE.HEGE MENEGESETE. MANEME AYFELEGEWEME. AMEN.😇

 2. ለትግራይ ክልልም ሆነ ለሌሎች አንቀጽ 39 የመገንጠል መብት አይሰጣቸውም!

  የብዙዎች ስጋት በአንቀጽ 39 አገሪቱ ትበታተናለች የሚል ነው። ነገር ግን አንቀጹ መብት የሚሰጠው ለክልሎች (Federal states) ሳይሆን ለብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ወይም ሕዝብ ነው። ይህን በአንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 እንዲህ እናነበዋለን፦
  ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው፡፡

  የብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብን ምንነት በተመለከተ ሕገመንግስታዊ ድንጋጌው በንዑስ አንቀጽ 5 ላይ የሠፈረው እንደሚከተለው ነው፦
  በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ “ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ” ማለት ከዚህ ቀጥሎ የተገለጸውን ባህርይ የሚያሳይ ማኀብረሰብ ነው። ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንጸባርቅ ባሕል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች ያላቸው ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው፡፡

  በዚህ መሠረት የብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ወይም ሕዝብነት መስፈርቶች 5 ናቸው። የጋራ ባሕል/ልምድ፣ ቋንቋ፣ ሕልውና/ማንነት፣ ሥነ ልቦና፣ እና መልክዓ ምድር ናቸው። መልካም! አንድ ጥያቄ ይከተላል፦ ታዲያ ክልሎች(Federal States) ከዚህ ድንጋጌ ይለያሉ ወይ? የክልል መንግስታት ሲመሠረቱ በምን መስፈርት እንደሆነ ባስቀመጠው አንቀጽ 46 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ መልስ አለ፦
  ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው፡፡ ስለዚህ ክልል ለመመስረት 4 መስፈርቶች ተለይተዋል። እነርሱም አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት፣ እና የሕዝብ ፈቃድ ናቸው። ከብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ መለያ መስፈርቶች የጋራ ባሕል እና ስነልቦናን ሲያጎድል የሕዝብ ፈቃድን ጨምሯል። አንግዲህ ወሳኙ ጥያቄ የአንቀጽ 47 ክልሎች(States) 9 ሲሆኑ የተመሠረቱት በአንቀጽ 46 ንዑስ አንቀጽ 2 መስፈርቶች ነው ወይ የሚል ነው።

  መልሱ በፍፁም አይደለም የሚል ነው። ቢሆን ኖሮ 9 ክልሎች ከ80 በላይ ብሔረሰቦች በሚኖሩበት አገር እንዴት? 9 ፌደራል መንግሥታት ብቻ? ይህንን ስለሚያውቅ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 2 ገና ከ70 በላይ ክልላዊ መንግሥታት ከነዚህ 9 ክልሎች ውስጥ መወለድ እንደሚቀራቸው እንደሚከተለው ይጠቁመናል፦
  በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 የተመለከቱት ክልሎች ውስጥ የተካተቱት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው፡፡

  ስለዚህ የኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥታት የመፈልፈል የእድገት ደረጃቸውን(Metamorphosis) ገና አልጨረሱም። ሲጨርሱ ከ80 በላይ ፌደራል መንግሥታት ይኖሩናል።

  ያኔ የፌደራል አወቃቀራችን በእርግጠኛነት በአንቀጽ 46 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ነውና የአንቀጽ 39 የመገንጠል ጥያቄንም ማስተናገድ ይቻላል። ሂደቱም ቀላል የሚሆነው ብሔረሰቦች ሁሉ በወሰን ማለትም በአሠፋፈር፣ በማንነት፣ በቋንቋቸው እና በፈቃዳቸው ላይ የተመሠረተ ክልል ባለቤቶች ሆነዋል። አንቀጽ 39 መብትን የሚሰጠው ለብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ እንጂ አሁን ላሉት እና የብሔረሰቦች የጋራ መኖሪያ ለሆኑ የክልል መንግሥታት አይደለም።

  ለነጠላ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ እንጂ ለብሔረሰቦች ሕብረት እንኳን አንቀጽ 39 አይሠራም። ስለዚህ የትግራይ ክልል ስለፈለገ ብቻ ሀገር የመሆን መብት አይሰጠውም አንቀጽ 39። ይልቁንም መብቱ በውስጡ ለሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ነው። ለትግሬ፣ ለኢሮብ፣ ለኩናማ፣ ለራያ። የአማራ ማንነትና የአፋር ማንነት ጥያቄ እና ፈቃድ ባለበት ሁኔታ አንቀጽ 46 ንዑስ አንቀጽ 2 ተጨፍልቆ የሚመሠረት አገር አይፈቅድም ሕገመንግሥቱ። ገና የአገሪቱ ክልሎች ምሥረታ ዑደት አላለቀም። 80 ክልሎች እስከሚኖሩ መጠበቅ ባያስፈልግም ትግራይ ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦች ሁሉ ክልል እስከሚኖራቸውና የማንነት ጥያቄዎች ሁሉ እስኪፈቱ መጠበቅ ግድ ነው። ከዚያ እያንዳንዱ የትግራይ ብሔረሰብ በአንቀጽ 39 ተገንጥሎ በኋላ በመዋሐድ ትግራይን እንደ ሀገር ማቆም ይችላል። ከፈለገ።

  ደቡብ፣ ቤንሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ አማራም ልክ እንደ ትግራይ ነው። ኦሮምያም ፌደራል መንግሥት እንጂ ብሔረሰባዊ ክልል አይደለም። ብዙ ሚሊዮን የራሳቸው ቋንቋ፣ ማንነት፣ ሥነልቦና፣ እና ፈቃድ እንዲሁም አሠፋፈር ያላቸው ብሔረሰቦችን መብት ጨፍልቆ ሀገር የሚሆንበት ሕገመንግስታዊ መሠረት የለውም። ሐረሪም ያው ነው። በአንፃራዊነት ተመሳሳይ(homogeneous) ማንነት እና አሠፋፈር ያላቸው ሶማሌና አፋር አንኳ ከሌሎች ጋር ያላቸው የወሠን ጥያቄም ሆነ በውስጣቸው የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች እጣፈንታ ሳይለይ አንቀጽ 39 ላይ መንቀሳቀስ አይችሉም። እናም ሕገመንግሥቱ አንዱን በትኖ ሌላውን የሚምር አይደለም። በተለይ ደግሞ ፈጣሪዎቹንም ነው በመጨረሻ የሚበታትነው። ስለዚህ እልሁን ትተን ሀገራዊነትን በሚያጠናክር መንገድ ብናሻሽለው አይሻልም ወገኖች?

 3. እስከዚያው በዚሁ ሕገመንግስት የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ እና ራያ የትግል አቅጣጫዎች እንዴትነት!

  አንድነት ይልቃል

  በአማራ ክልላዊ መንግሥትና በነዚህ አካባቢዎች የማንነት አስመላሽ ኮሚቴዎች የትግል ድርሻዎች መካከል የጠራ መስመር ባለመቀመጡ ትግሉ ተቀዛቅዟል። ትሕነግ ከዳር ቆማ አገር እንዲፈርስ እሳቱን እያራገበች ነው። አማራ በየአቅጣጫው ተወጥሮ ለነዚህ አካባቢዎች ጊዜ እና አቅም እንዲያጣ ትሻለች። በአንቀጽ 39 ከመገንጠል ጣጣና ዳፋ በኢትዮጵያ መፍረስና በአማራ መዳከም ልትገላገል ናፍቃለች። የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻልና በኢትዮጵያ ሕዝብ የእርስበርስ ጦርነት መካከል የወሰደችውን ይዛ ለመጥፋት እና በእፎይታ ለመኖር ከጅላለች።
  ሕገመንግሥቱን ብትነኩ አገር ይፈርሳል ስትል ጠበቃው ሆናለች። ይሁን እስቲ። በፍቅር በወደቀችለት ሕገመንግሥቷ እንምጣባት። ታከብረው እንደሆን እና ጩኸቷ የምሯን እንደሆነ እንፈትናት። በወልቃይት፣ ጠገዴ፣ እና ራያ ትግል የኮሚቴዎችን እና የአማራን ክልላዊ መንግሥት የሠላማዊ ሕገመንግስታዊ የትግል አቅጣጫዎች ለይተን እናስቀምጥ።
  ኮሚቴዎች
  መነሻቸው አንቀጽ 46 ንዑስ አንቀጽ 2 ሲሆን እንዲህ ይነበባል፦
  ‘ ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው፡፡ ‘
  በዚህ መሠረት ትግርኛን ቋንቋ በመናገራችን ብቻ እኛ የአካባቢው ቀደምት ባለቤቶች ያለፈቃዳችን እና ያለ ማንነታችን በትግራይ ክልል ውስጥ ከታሪካዊ ወንድሞቻችን ተለይተን በመካለል ብዙ በደል እየደረሰብን ነው በማለት አቤቱታቸውን ለትግራይና ክልል አቅርበው ባለመሰማታቸው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጩኸታቸውን መቀጠል።
  የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
  የትግሉ ዋና መዘውር መሆን አለበት። የእርሱ ድርሻ በአንቀጽ 48 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የተመሠረተ ነው። እንዲህ ይነበባል፦
  ‘ የክልሎችን ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈጸማል። የሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይወሰናል፡፡ ‘
  በዚህ መብት መነሻነት የወሰን ጥያቄ በማንሳት የአቤቱታ ደብዳቤ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በማስገባት በግልባጭ ለትግራይ ክልልና ለሚመለከታቸው ክፍሎች ያሳውቃል።
  የፌዴሬሽን ምክር ቤት ድርሻ
  በአንቀጽ 48 በከፊል ንዑስ አንቀጽ 1 እና ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ እንደሚከተው ተመላክቷል፦
  ” 1 …የሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልቻሉ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የሕዝብን አሰፋፈርና ፍላጎት መሠረት በማድረግ ይወሰናል፡፡
  2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የቀረበ ጉዳይ ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በፌዴሬሽኑ ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ ‘ የቀደምት ነዋሪውን ፍላጎት ማስከበር ግዴታው ነው። ሐረሪ ክልል እንዴት የቀደምት ነዋሪ በመሆኑ እጅግ አናሳ የሆነው መብት እንደተከበረ ልብ ይበል። የሠፋሪው ቁጥር ምንም ያህል ብዙ ቢሆን ድምፅ እንደሌለው ከአርሲም ሆነ ከቤንሻንጉል አማራ መገንዘብ ይችላል።

 4. የአሜሪካው ሕገ-መንግስት ” የተፈጥሮ ስጦታ የሆኑትን ነፃነቶችና መብቶችን ለራሳችን ለሁለችን ብልፅግና ማስጠበቅ ይላል። ደግሞም ይተገብሩቲል። እኛ ጋር ግን ፍየል ወዲያ ቅዝምዝ ወዲህ ነው። የግለሰብ ወይም ብሔር ፍላጎት ሳይሆን የሚታየው ሌላ ነው።
  ወደደመ ተጠላ ሀገራዊነት ላይ ማተኮር ግድ ይላል ለዚች ደሃ አገር።
  ተቅዋሚ የተባሉ ፓርቲዎች እንደቅድመ መስፈርት/pre-requiste/ ህገ-መንግስቱ መቀየር እንዳለበት መታገል አለባቸዉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.