መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ጥቃት ጉዳይ እንዲወያይ ከቅዱስ ሲኖዶስ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ የሚሊዮን ወጣቶችና አገልጋዮች ማኅበራት ኅብረት አሳሰበ

• በቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ፣መፈናቀልና ግድያ ጉዳይ እንወያይ ቢባል ዝምታን መርጧል፤
• ዝምታውን እንቃወማለን፤ ለለውጥና ነፃነት ቆሜያለኹ ከሚል መንግሥት አይጠበቅም፤
• ለቅ/ሲኖዶሱ፣የእንወያይ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥና እኛንም እንዲያነጋግረን እንጠይቃለን፤
• ከ7ሚ. በላይ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና የ240 ማኅበራት አእላፋት አባላት ጥያቄ ነው፤
***

• ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ያበረከተችው አስተዋፅኦና የከፈለችው መሥዋዕት የማይካድ ነው፤
• ውለታዋ ተዘንግቶ በሐሰተኛ ትርክት ተተክቶ በየቦታው እየተወነጀለችና እየተጠቃች ነው፤
• በተደራጀ መንገድ ታቅዶ የሚፈጸምና በደለበ ሀብት ጭምር የተደገፈ ጥላቻና ጥቃት ነው፤
• ከመንግሥት የፈረጠምን ነን ባይ ኀይሎች ኾነው ሳለ፣ ያለተጠያቂነት ዐደባባይ ይፏልላሉ፤
• መንግሥት በሓላፊነት ስሜት ማስቆም ሲገባው፣ የሚያሳየውን ለዘብተኝነት እንቃወማለን፤
‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ይቁም!!!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት እና ምሩቃን እንዲሁም የመንፈሳዊ ማኅበራት ተወካዮች በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፡-

ከአገራችን ኢትዮጵያ የደመቀ ገጽታ እና ከተዋበ ታሪክ ጀርባ የበርካታ አካላት ማለትም የተለያዩ እምነቶች፣ ባህሎች እና የማኅበረሰብ አደረጃጀቶች አስተዋፅኦ መኖሩ ተጨባጭ እውነታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ረገድ ትታው ያለፈችውን አሻራ፣ መዝግባ ያለፈችው ወርቃማ ታሪክ እና የከፈለችው መሥዋዕት ደግሞ ሰዎች ሊክዱት ቢነሡ እንኳን የኢትዮጵያ ሰማይ እና ምድር አፍ አውጥተው የሚመሰክሩት ሊደበዝዝ የማይችል ሐቅ ነው፡፡

ይኹን እንጂ ዛሬ ዛሬ ግን፣ ይህ ኹሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውለታ እውቅና ተነፍጎት በርካታ አካላት ሐሰተኛ ትርክትን በመፍጠር ለአገሪቱ ጥፋት ወንጀለኛ አድርገው ሊኮንኗት ሲሞክሩ መመልከት፣ ለአማኙ ቀርቶ በቅን ልብ ለእውነት ለቆመ ለማንኛውም ሚዛናዊ ኅሊና ላለው የሰው ልጅ ጭምር ብርቱ ሕመምን የሚፈጥር ክሥተት ነው፡፡ በመኾኑም እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ አገልጋዮችን ያቀፍን፦ የሰንበት ትምህርት ቤት አንድነት፣ የመንፈሳውያን ኮሌጆች ምሩቃንና ደቀ መዛሙርት እና የመንፈሳዊ ማኅበራት ተወካዮች በቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በመምከር የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡-

1. የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ውለታ እና እያደረገችው ያለችው አስተዋፅኦ ተረስቶ ለአገራዊ ጥፋት ባለቤት ተደርጋ መኮነኗን በጽኑ እንቃወማለን፡፡

2. አገራችን አንዱ እንዳያኮርፍ አገራዊ ሕግ ጭምር ተጥሶ ለጥያቄው ሁሉ ምላሽ የሚያገኝበት፣ ሌላው ግን መብቱን ተነፍጎ የሚሳደድባት አገር እየኾነች መምጣቷ እንደ ኦርቶዶክሳዊያን ኅብረት በጽኑ ያሳዝነናል፤ በዚሁ ከቀጠለ፣ መጪው ጊዜ በጣም አሳሳቢ በመኾኑ በአስቸኳይ የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

3. መንግሥት በታቀደ እና በተደራጀ፣ ምንጩ የት እንደኾነ በማይታወቅ የደለበ ሀብት ጭምር እንደሚደገፍ የምናምንበትን በአገራችን በርካታ ቦታዎች ላይ እምነትን መሠረት ባደረገ ጥላቻ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተቃጣውን ይህን ዘመቻ በተቻለ ፍጥነት እና ትኩረት እንዲያስቆምልን እንጠይቃለን፡፡

4. እስከ ዛሬ ሲፈጸሙ በኖሩ ጥቃቶች ላይ ከጥንስሱ ጀምሮ እጃቸውን የከተቱ፣ ያለአንዳች ፍርሃት በዐደባባይ ጭምር በክርስቲያኑ ሕዝብ ላይ ሲሳለቁ እና በል ሲላቸውም እልቂትን ሲያውጁ በከረሙና እያወጁ ባሉ «ከመንግሥት ጭምር የፈረጠምን ነን» ባይ ግለሰቦች እና ተቋማትን መንግሥት ለፍርድ እንዲያቀርብልን እንጠይቃለን፡፡

5. አገርና እና ሕዝብን ለመምራት የተቀመጠው መንግሥት በየአካባቢው እየደረሰ ባለው፥ የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎ፣ የኦርቶዶክሳውያንን መፈናቀል፣ ድብደባ፣ ከዚያም ሲያልፍ አሠቃቂ ግድያ ላይ ያሳየው ከቸልተኝነት የዘለለ የሓላፊነት ማጣት መንፈስ የበርካታ ሚሊየን አባላቶቻንን ልብ በእጅጉ የሰበረ ወደፊትም ቢኾን ለደኅንነታችን መጠበቅ ምንም ዓይነት ዋስትና እንደሌለን እንዲሰማን ያደረገን በመኾኑ የመንግሥትን ለዘብተኝነትን በእጅጉ እንቃወማለን፡፡

6. በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ቤተ ክርስቲያናችንን ከሚመራው የመጨረሻ አካል-የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በ2011 ዓ.ም. የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባ ወቅት የጋራ መፍትሔ ፍለጋ የቀረበለትን «የእንወያይ» ጥያቄ መንግሥት ከምንም ሳይቆጥር በዝምታ የመመልከቱን መልእክት «በለውጥ ላይ ነኝ ከምትል» አገር እና «ለኹለንተናዊ ነፃነት ቆሜያለኹ» ከሚል መንግሥት የማይጠበቅ ተግባር እንደኾነ እናምናለን፤ ድርጊቱም እንቃወማለን፡፡

7. «ፖሊቲካ ከሃይማኖት ጋራ ያለው ኅብረት ተቀብሯል» ብላ ከሕጎች ኹሉ በላይ በኾነው ሕጓ የደነገገች አገር ላይ፣ ሕዝብን ለማገልገል ተሹመው ከሕዝብ ሕዝብ ከእምነት እምነት እየመረጡ ለማስተዳደደር የሚሞክሩ፣ ሥልጣናቸውን ለሃይማኖታቸው ጥልቅ መሠረት መጣያ አድርገው እየቆጠሩ ያሉ የመንግሥት አካላትን አደገኛ መስመር እንዲፈተሸልንና በጥፋተኞች ላይም ርምጃ እንዲወሰድልን እንጠይቃለን፡፡

8. በኦርቶዶክሳውያን ላይ የሚፈጸሙትን ግፎች፣ ድርጊቱ በሚፈጸሙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የሌሎች እምነት ተቋማት መሪዎች፣ የባህል አባቶችና ሽማግሌዎች፣ የኅበረተሰብ አደረጃጀቶች ይህን ድርጊት እንደሚቃወሙ እናምናለን፤ ከቤተ ክርስቲያን ጎን በመቆም ጥቃት አድራሾችን እንዲያወግዙ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

9. በመጨረሻም፣ በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ የሚመለከተው የመንግሥት አካል፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ላቀረበው ጥያቄ ተገቢውን መልስ እንዲሰጥልንና እኛንም በግልጽ አግኝቶ እንዲያወያየን እንጠይቃለን፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር አገራችንን እና ሕዝቦቿን ይባርክልን!!

• በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት
• በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅ/ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት
• በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰዋሰው ብርሃን ቅ/ጳውሎስ መ/ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት
• በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር
• በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰ/ት/ቤ/ማ/መ/ማኅበረ ቅዱሳን
• በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወጣቶች እና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት
• በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሠለስቱ ምእት ማኅበራት ኅብረት
• በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአእላፋት ድምፅ የካህናት እና ምእመናን ተናሥኦት ኅብረት

ፎቶ፡- አእላፋት ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችንና ምእመናንን ያቀፈው የማኅበራት ኅብረቱ አመራሮች፣ ትላንት ኀሙስ፣ ሰኔ 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በዮድ አቢሲኒያ ሆቴል መግለጫውን በሰጡበት ወቅት

ሰኔ 6/2011 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

ሐራ ተዋሕዶ

1 COMMENT

  1. Golden rule from the Bible: “In everything, therefore, treat people the same way you want them to treat you, for this is the Law and the Prophets.” 

    All wickedness in the Ethiopian politics spring from the Ethiopian orthodox churches all the times till now. But no more! Everyone is aware  of its wickedness. Now it is better, if you stop your malicious tactics and empty crying. It will not help you anymore. You have been imposing the Amaharic language and the Amahara culture on other peoples in Ethiopia. The Ethiopian orthodox churches controlled one third of the Oromia and the the Sutherland during Menlik and Haile Seilase. The churches clergy used to behave as lords over the peoples, but not as servants of the Almighty God.

    The main source of racism, discrimination, economic and political corruption in Ethiopia is the Ethiopian orthodox churches. Since the era of Menilik it is the right hand of the government. It is and was used as tools, in orderto to discriminate other languages and cultures. One thirds of the Oromo land were controlled by such evil doers. Now they make delibretly noises.  But there will never comeback to the old era. Enough is enough. Brig what ever you have in your corrupted stores. We will see who will be affected more.

    No more disgusting and discriminating others (especially the Oromo) in the name of christianity and the almighty God. Now it is better, if you stop your malicious tactics and empty crying. It will not help you anymore.

    Cheap propoganda  is not helpful  for you and for the orthodox churches. No power on earth will stop the Oromo people from fulfilling its aspirations as a freedom loving nation to regain its human dignity and rights. It is up to you to respect this great nation for the sake of your own benefits. For durable solutions use your mind as a rational thinker, but don’t use your belly like a big.   

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.