የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ማን ነው? (ምሕረት ዘገዬ)

እኔን መሰሉ ጅል ሰው ግልጽ ጥያቄ በመጠየቅ የራሱንና የሌሎች ሰዎችን ጊዜ በከንቱ ያባክናል፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለዜጎች ቀርቶ ለሣር ቅጠሉ በማያሻማ ሁኔታ ግልጥ ሆኖ ሣለ ይህን ጥያቄ መጠየቅ በርግጥም ሞኝነት ነው፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሀገራችን ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሳትር ዶክተር አቢይ አህመድ ይመስለኝ ነበር፡፡ በቅርብ በተላለፈ የኤል ቲቪ አንድ የቃለ መጠይቅ ፕሮግራም መሠረት ግን ተሳስቼ እንደነበር ተረዳሁ፡፡ እናም በዚያ የጃዋር መሀመድና የቤተልሄም ታፈሰ የቃለ መጠይቅ ዝግጅት መገንዘብ የቻልኩት አቢይ አህመድ የጃዋር አሽከርና ጉዳይ አስፈጻሚ እንጂ ምንም ዓይነት እዚህ ግባ የሚባል ሥልጣን የሌለው መሆኑን ነው፡፡ ሲጀመር አቢይ ለሚጠየቀው የጥፋትና ውድመት ጥያቄ ሁሉ መልሱ “አልሰማሁም፤ አላወቅሁም፤ አጣራለሁ…” እንጂ ኃላፊነት ሲወስድም ሆነ በሥሩ የሚገኙ ባለሥልጣናቱን ሲቆጣጠር አይታይም፡፡ ደግሞም እርሱ የተመሰጣረበት ይሁንም አይሁንም ብቻ አንድ ችግር ሊፈጠር ሲል ወደ ውጭ ሀገር ሹልክ የሚልበትና አንድ ሚሊዮን ሰው በሀገር ውስጥ አፈናቅሎ መቶ እስረኞችን ከውጭ ይዞ የሚመጣበት በዓይነቱ አዲስ የሆነ የማፍዘዣ ሥልት አለው፡፡ ይህ እጅግ ይገርመኛል፡፡ ልዩ አፍዝ አደንግዝ ነው፡፡ ይህ የአቢይ በሀገር ጉዳይ ባይተዋር የመሆን ነገር በራሱ የሚያሳየን ኢትዮጵያ ከዶክተር አቢይ ቁጥጥር መውጣቷንና እርሱ ጠ/ሚኒስትር መባሉ ለላንቲካ መሆኑን ነው፡፡

በበቀደሙ ቃለ መጠየቅ ጃዋር ከጠ/ሚኒስትርነትም ባለፈ የፈጣሪን ቦታ የተካ ያህል የሚሰማው ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ የኛ የኢትዮጵያውያን ፈጣሪ (አላህም እንበለው እግዚአብሔር ወይም ዋቃ) እርሱ የሆነ ያህል እንደሚሰማው መገመት አላቃተኝም፡፡ ያለው የራስ መተማመንና የአድራጊ ፈጣሪነት ስሜት እጅግ የሚገርም ነው፡፡ ሀገራችን በሥውር ኃይሎች እየተገዛች እስከመቼ እንደምትቆይ አንድዬ ይወቅ፡፡

“አዎ፣ በዚህ ጉዳይም በጆሯቸው ሹክ ብለናቸዋል፤ ግን አልሰሙንም፡፡ ባለመስማታቸውም የሚደርስባቸውን ያውቃሉ፡፡ … ስለዚህም ጉዳይ ከጀርባ ሆነን ነግረናቸዋል፡፡ … ስለምትይውም ነገር አስጠንቅቀናቸዋል፡፡… የሲዳማን ነገር ተይው ያለቀለት ነው፡፡… ፈተናውን አሰርቀን ለሁሉም ክልሎች የበተንነው ለትግል ሥልት ነው … ለኦሮምያ ብቻ ማድረግም እንችል ነበር፡፡… ትምህርት ሚኒስቴር ብልሹ ነው፡፡ ደኢህዲን የሞተ ነው፡፡ ስለሱም ጉዳይ ማስጠንቀቂያ ልከንላቸዋል፡፡ … ዝም ያልናቸው የትም እንደማይደርሱ ስለምናውቅ ነው፡፡”

ንጉሠ ነገሥት ወጠቅላይ ሚኒስትር ዘኢትዮጵያ ወኦሮምያ፣ ፊልድ ማርሻል ሃጂ ወፓትርያርክ ዘምድረ ሀበሻ ወዕጨጌ ዘአክሱም … አቤቶሁን ጃዋር መሀመድ እንደዚያ ሊንቀባረር የቻለው በጌታዋ የተማመነችዋን በግ ሆኖ እንጂ አንድ “አክቲቪስት ነኝ” ባይ በምን ሥልጣንና ችሎታው እንዲያ እንደሚዘባነን ለማንም ግልጽ አይደለም፡፡ የሆኖ ሆኖ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ ሰው እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡

ቀጣዮቹን ፎቶዎች እየፈታታችሁ ግጠሟቸው፡፡ ብዙ ትረዳላችሁ፡፡

ሦስቱ በሚታዩበት የመጀመሪያው ፎቶ አቢይ የገባው ለማን ግን ያልገባው ነገር እንዳለና ያንን ነገር ጃዋር እያስረዳው እንደሆነ እንረዳለን፡፡ አቢይም ለራሱ የገባው ነገር ለማም እንዲገባው የፈለገ ይመስላል፡፡ እነዚህ ሦስት ሰዎች ምን እየተመሳጠሩ እንደሆነ በፎቶው ባይገባንም በተግባር ግን አሁን የተዘፈቅንበት ችግር እየገለጠልን ይገኛል፡፡ የነዚህን ሰዎች ፀረ ኢትዮጵያዊነት ለመገንዘብ  ጤናማ ሰው መሆንን ብቻ ይጠይቃል፡፡ ማንም አንፋሽ አከንፋሽና የሥልጣንና የፍርፋሪ ተስፈኛ እስኪነግረን አንጠብቅም፡፡ ዘመን ሲያልቅ ብዙ ጉድ ይወጣል፡፡ አሁን አሁን ሽሉም ገፍቷል፤ ቂጣውም ጠፍቷል፡፡ በየሚዲያው የተሰገሰገው ሆዳምና አድርባይ ሁሉ እየለየለት ስለመጣ ታሪካዊው ዕንቆቆና መተሬ ሥራውን በሚገባ እየሠራ ነው፡፡ ወደፊትና በቅርቡ ደግሞ ቋንቋ ከናካቴው የሚደበቅበትና ተግባር ብቻውን የሚናገርበት ጊዜ ይመጣል፡፡

ሁለተኛው ፎቶ ላይ የሚታየው የአቢይ ምስል የልጁን ትክክለኛ ተፈጥሮ ይገልጻል፡፡ አስመሳዮችና የትያትር ሰዎች እንደዚህ ናቸው፡፡ ይህን ፎቶ ያነሳውና ያሰራጨው ሰው ልጅ ይውጣለት፡፡ ሾካኮችና አጭቤዎች በሚነሱዋቸው ፎቶግራፎችም በሚገባ ይታወቃሉ፡፡ የለማን ገርነትና ጨዋ ባሕርይ ከፎቶው መገመት ይቻላል፡፡ ለማ ለዓላማው ሲል ከዘረኞቹ ጋር ቢዶልትም ተፈጥሮው ግን ቀና መሆኑን ፎቶዎቹ በግልጽ ይጠቁማሉ፡፡ወርቅነህ ሞኝ ቢጤ ነው ለጊዜው እንተወው፡፡ ማኪያቬሊ(ጃዋር) ግን ያለውን የእባብና የሸለምጥማጥ ጠባይ በሚገባ መረዳት ይቻላል፡፡ ለማንኛውም ድግሱ ተደግሷል፡፡ ጥሪውም ለሁሉም ተላልፏል፡፡ ሰማንያ ሰባት ፈረሶችን የሚያስጋልበው ድንኳኑና ዳሱም ተጥሏል፡፡ የሚቀረው ብፌውን የሚያስነሳው የፊሽካው መነፋት ብቻ ነው፡፡ በየአቅጣጫው ቀዳዳ እየተፈለገ ሀገር እንደ ዶሮ የምትበለትበት የቅርጫ ሥርዓቱ ተዘርግቶ አሁን በወረቀትና በሚዲያ ላይ ነገ ደግሞ ከ… ተጀምሮ መሀል … በሚጠናቀቅ የጦርነት ዐውድማ የሀገራችን መፃዒ ዕድል ሊበየን ዝግጅቱ ሁሉ በየፊናው ተጠናቋል፡፡ ሦርያና ሩዋንዳም ጓዛቸውን ጠቅልለው የኢትዮጵያን ድምበር በመሻገር አዲስ አበባ ላይ መሽገዋል፡፡ ዕድሜ ለነጃዋርና እነሱን ለላኩ የግብጽና የምዕራቡ ኃያላን ድግሱ ይህ ቀረሽ በማይባልበት ሁኔታ ተደግሶ እንግዶቹን እየጠበቀ ነው፡፡ ሁሉም ቢላዎውን ስሎ ቁርጡን ሊበላ አሰፍስፏል፡፡ መልካም ዕልቂት ከወዲሁ፡፡ ከአድማስ ማዶ ካልተገናኘን ቻው፡፡

(በውጭ የምትኖሩ ዜጎች ላልተወሰነ ጊዜ በያላችሁበት ብትቆዩ መልካም ነው፡፡ ሃይማኖት ያላችሁ በየሃይማኖታችሁ ተግታችሁ ጸልዩ፡፡ ክፉ ዘመን ማለፉ ባይቀርም ጉዳቱ የሚናቅ አይደለምና ሀገራችንን በጥሞና እናስባት፡፡ ዶፉን እንዲያቀልልን በሱባኤና በምህላ ፈጣሪን እንለምነው፡፡ ዕድል ብርቁዎቹ ኦነጎችና ኦህዲዶች ከሀገራችን መሠሪ ጠላቶች ጋር በግልጽም በኅቡዕም በመመሳጠር ሀገራችንን በየቀኑ በሚባል ደረጃ ወደ ስቅለቷ እያዳፏት ነው፡፡ የትንሣኤዋን እውን መሆን ማንም ባያስቀረውም ሰሙነ ህማማቷና ስቃይዋ እንዲቀልላት ለሀገራችን ሁላችንም በየእምነታችን እንጸልይ፡፡ ያም የሚሆነው ዛሬ እንጂ ነገ አይደለም – ነገ ዕድሉ አይኖረንምና፡፡   …)

2 COMMENTS

  1. ሣቅ አምሮኝ ነበር በነፍስ ደረስክልኝ ዓለም። መቼም ልታሾፍብኝ ባልሆነ። እንጂ የኢትዮጵያ ሹመት ሺ-ሞት እንጂ ሹመት ባለመሆኑ ለኔ ለወንድምህ እንዲህ ያለ ምድራዊ ሲዖል ትመኝልኛለህ ብዬ አላምንም። “ሥልጣን ይፈልጋል” ብለህ አስበህም ከሆነ እጅግ ተሣስተሃል። ብፈልግም ደግሞ መብቴ መሆኑ ይታወቅልኝ ፦ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነኝና። “ሆኖልኝ ነው! አርጎት ነው ጃንሆይ!” ብላለች አሉ አንዷ ምሥኪን ዜጋ ቀ.ኃ.ሥን ዛሬ የማንም ወንበዴ ከሃዲ መጫወቻ የሆነውን ክቡር ባንዲራ መንገዳቸው ላይ አንጥፋ በማስቆም “ባሌ አምሥት ልጆች አሥታቅፎኝ ሲያበቃ ሞቶብኝ…” እያለች ብሶቷን ስታሥሰማቸው ወደአጃቢዎቻቸው ዘወር ብለውና በለሆሣስ “አግባኝ ነው እምትለኝ?” ሲሉ ሰምታ። እኔም አልመኝም እንጂ ምኞት አይከለከልም።
    ለሥልጣኑማ ይሄውና ጃዋርስ ባልተወለደ አንጀት በሚባል ሁኔታ እየቀጠቀጠን አይደል?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.