ባለተራው እና ባለግዜው እኛ ዴሞክራሲ ስንክ እና ዘረኞች ዴሞክራሲ ሲሉ – መንግስቱ ሙሴ/ዳላስ

ዘረኝነት የሚለው ይሰመርበት እና እኔ የምለው ዘረኝነት ቤተመንግስት ከገቡት ተቃዋሚ ነን ባይ አድርባዮች ይለያል። ብዚህ ጉዳይ ብዙ አልሄድበትም ግን ዘረኛውን ሕገመንግስት ደግፈው እና በስልጣን ላይ ያለውን ዘረኛ ስርአት እያወደሱ ሌሎችን ዘረኛ ሲሉ ስናይ ምጸት ስለሚሆንብን ማለቴ ነው። ለሁሉም ወደሀሳቤ ልሂድ።

የሀገር ችግርን ለመፍታት “የሽግግር መንግስት” ማለት ሁሉንም ባለጉዳዮች (stakeholders) ያሉበት ችግሩን ከስር ሊፈታ አድላዊነት የሌለው፣ አካል ይመስረት ማለት ነው። ይህም የመነሻ እርእሴ ስላይደለ ወደዛሬው ሀሳቤ ልሂድ።

ዴሞክራሲ ስንል እኛ በጸረ ህወሓት/ኢሕአዴግ ግንባር ለዘመናት የታገልን እና ህወሓታውያኑ (የዘረኛው ክፍል በመላ)  ዴሞክራሲ ሲሉ የተለያየ ነው። ለምሳሌ እነርሱ ፌደራሊዝም ሲሉ ከዚህ በፊት እንዳሳየሁት የውሸት እንደሆነ ሁሉ። ዴሞክራሲ ሲሉን ከወረቀት የዘለለ እንዳልሆነ ሁሉም ሊያውቅ ይገባል። የጸረ አንድነት እና የጸረ ዴሞክራሲ ኃይሎች ዋና አላማ ሀገር ማፍረስ እና “አማራ ሰራሽ” የሚሏትን ኢትዮጵያ ማጥፋት ስለሆነ ስለዴሞክራሲ አስበውም ተጨንቀውም ወይንም መሰረታዊ የዴሞክራሲን አላማወች ለማሟላት ሰርተው አያውቁም። በእርግጥ “ሲሞቅ በጭልፋ፣ ሲበርድ በእጅ” እንዲሉ የሕዝብ ትግል አይሎ እና ጠንክሮ ሲገፋቸው ሁለት እርምጃ ወደኋላ አፈግፍገው ለስልሰው እና ዴሞክራት መስለው እንደሚቀርቡን ከትናንት እስከ ዛሬ የተጓዝንበት ታሪክ ያስተምረናል። ለምሳሌ ከ1984 እስከ ምርጫ 1997 ድረስ ቁጥረ ብዙ የግል ጋዜጦች እና መጽሄቶች ይታተሙ እንደነበር ትዝታችን ነው። እነዚያም ጋዜጦች እና መጽሄቶች ዜጎች ያሻቸውን ተናግረው ጽፈው፣ ሀሳብ አቅርበው፣ ዘረኝነትን አውግዘውም እንደነበር የምናስታውሰው ነው። የኋላ ኋላ የዘረኛው ኃይል መሰሪነቱ እንደታወቀበት ሲያውቅ እና ሲረዳ የወሰደንን የሴኦል ጎዳና የምናስታውሰው ይመስለኛል። በእርግጥም ነጻ መጽሄት ፈቀድሁ፣ ተቃዋሚ ድምጽን አስተናገድሁ፣ ባሻው መደራጀትን ፈቅደናል ያለችው ህወሓት እና ስብስቧ ኢሕአዴግ የአይናቸው ቀለም አላማረንም ብለው ካገር ከማባረር እስከ ግብረ ሶዶማዊነት በእብነበለ ፍርድ ባሰሯቸው ኢትዮጵያውያን ላይ ፈጽመዋል። ዴሞክራሲ ካልነው ያም ዴሞክራሲ ነው ማለት ነው። ዴሞክራሲ ሲሉን ህወሓታውያኑ (ኢሕአዴጎች) ስለ ብሄር ነጻነት ማውራት ነው። ዴሞክራሲ ሲሉን ስለ አብዛኛው የፈቀደው እንዲመራ የሚሰጥ መብት ሳይሆን ወይንም በዴሞክራሲያዊ ስርአት የግለሰብ መብት እና ነጻነት እስከየት እንደሆን የሚያግዝ ሳይሆን ስለ ሉአላዊ እና እራሳቸውን ስለቻሉ “ብሄሮች” እና “ሕዝቦች” መብት የሚቆም ማለት ነው። በየ “ብሄሮች “ ውስጥ ስለሚኖሩ ግለሰብ ዜጎች መብትም ሆነ ያሻቸውን የመምረጥ፣ ሀሳብ የማቅረብ፣ የማስፈጸም ደንብ በዘረኛው ስርአት ውስጥ ሊተገበር ቀርቶ ከግምት የሚገባ አይደለም። ለምሳሌ በታላላቅ የክልል ከተሞች እና አንዳንድ ቀበሌወች የሚኖሩ የተለየ ቋንቋ የሚናገሩ፣ የተለየ እምነት የሚከተሉ ዜጎች መብታቸው ሳይሆን ግዴታቸው የመፈጸም ብቻ ተልእኮ ያለው ስርአት ነው  ማለት ነው። ለምሳሌ ብዙ አማርኛ ተናጋሪ ባለባት ጅማም ሆነ ሀረር ወይንም አሰላ ሆነ ይርጋአለም የእነዚህ ዜጎች ተግባር በክልል የሚተላለፍን ህግ የማክበር እንጅ እነርሱ የህጉ አካል ሆነው ተቆጥረው ድምጻቸው የሚከበርበት መብትን የመጠየቅ ጉዳይ የሚታሰብ አለመሆኑ ነው። ወይንም ልጆቻቸው በእናት ቋንቋ የሚማሩበት ትምህርት ቤት መፍቀድ የሚታሰብ አለመሆኑ ነው። ይህ ዴሞክራሲ የጠባብ ብሄርተኞች የቂም እና የበቀል ስርአት ብንለው የተሻል ትርጉም የሚሰጥ ይሆናል።

ለምሳሌ በአንድ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የፌደራል መንግስት የበላይነት እና በሀገሪቱ ሕግ የማስከበር ህገመንግስታዊ ስልጣን ይኖረዋል። በሀገራችን የዘረኞች ፌደራሊዝምም ሆነ የሚሉት ዴሞክራሲ ይህ የሚሰራ አለመሆኑን በትግራይ ዋና ከተማ መቀሌ የከተሙ ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብ መብትም ሆነ ስልጣን የፌደራል መንግስቱ እንዳልቻለ አሳይቶናል። በሌላ በኩል ግን በሰኔ 15 2011 በባህርዳር በታየው የዘረኞች ተግባራት የፌደራሉ ጦር በመግባት ቁጥረ ብዙ የሆኑ ዜጎችን በስልጣኑ ማሰር እና እስካሁን ለፍርድ ሳያበቃ የመቆየት ስልጣን አሳይቶናል።

ዴሞክራሲ የሚለው መንፈስ እና የአስተዳደር ስርአት ከ 2400 አመታት በፊት በጥንታዊት ግሪክ የተጀመረ መሆኑ ይታወቃል። ዴሞክራሲ የሚለውም ቃል  “ሕዝባዊ መንግሥት” ማለት ነው ይላል። ይህ ማለት የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ማለት የ’እያንዳንዱ ዜጋ መብት፣ ጥቅም፣ እና ደህንነት የሚከበርበት ማለትም ነው። ይህ አባባል በሀገራችን ከመተግበር ይልቅ ከአንድ አንባ ገነን መንግስት የዜጎችን መብት ከሚጥስ ወደሌላ ዘረኛ እና አንባ ገነን መንግስት የዜጎችን መብት ከመጣስ አልፎ መኖራቸውን ወደሚክድ መተላለፋችን ሊሰመርበት ይገባል። ዛሬ ከአንድ ክልል ወጥቶ ወደሌላ የሄደ እና የተለየ ቋንቋ ተናጋሪ ከሆነ ባእድ እና መኖር የሌለበት ወይንም እንዳለ ከቁጥር የማይገባ መሆኑ ነው። እናም ዘረኞች ዴሞክራሲ ሲሉ ዜጎች በኢትዮጵያ ውስጥ ባሻቸው ተንቀሳቅሰው እንዲኖሩ የማይፈቅድ እና ከተሰጣቸው የቋንቋ ክልላቸው ከወጡ መኖር ቢችሉም ስለመኖራቸው ግምት የማይሰጠው ሆነው የፈለገ የዘረኛ የቀበሌ አስተዳደር ባሻው ግዜ ውጡ ብሎ የሚያንጋጋቸው ማለት ነው። ይህ ነው የእኛ እና የእነርሱ የዴሞክራሲ ትርጓሜው እና ልዩነታችን።

ይህን የዘረኞችን የዴሞክራሲ ትርጓሜ ደግሞ ላለፉት 28 አመታት ያየነው ቢሆንም ዛሬ ለውጥ መጣ ካልን በሁላ እና የለውጥ መንግስት ነን ያለው ያው ኢሕአዴጉ ላለፉት 12 ወራት መጠነ ሰፊ ማፈናቀል እንድናይ አድርጎናል። “የለውጥ ኃይሉ” ኢሕአዴግ (በዶክተር ብርሀኑ) ቃል ማለት ነው ካስተማረን እና ዜጎች ካሳደረባቸው ቅጥቃጤ አንዱ የአውሮፓ ቅኝ ግዛትን አቸንፈው በድል የተመለሱባት እና ለአፍሪካ አህጉር የነጻነት ጮራ የሆነችው። ለሀገራችን አንድነት እና ለሕዝብ አብሮነት ታላቅ ተምሳሌያችን ዋና ከተማችንን የአንድ ዘር የማድረግ ስልታዊ የመንጠቅ ጎዳና ነው ዴሞክራሲ የምንለው ማለት ነው። ባጭሩ የለውጥ ኃይል ነኝ ያለው ግን በሕዝብ ትግል ተንገዳግዶ የቀረው ኢሕአዴግ የአምና ታች አምናው ሕዝባዊ አመጽ የረሳው እና ላዲስ ዙር እና ለሌላ ባለጊዜ የስልጣን ዘመን ቦታውን እያሸራሸ መሆኑን በመካሄድ ላይ ያለው ጉዞ እያስተማረን መሆኑ ነው።

ዴሞክራሲ እና ህገመንግስት

እንደሚታወቀው ህገመንግስት የህገ አዋቂወች ሕዝብን ወክለው ሊያረቁ ይችላሉ። ሆኖም የተረቀቀውን ህግ ተግባራዊ ሆኖ በስራ እንዲውል ሕዝብ ይሁንታውን ማስፈር ይኖርበታል። ይህ ይሁንታ ደግሞ በ Simple majority ወይንም በ 51 ፐርሰንት ህዝበ ውሳኔ የሚጸድቅ ሳይሆን ቢቻል ሙሉ ሕዝባዊ ይሁንታ አለያም ¾ ኛውን የሕዝብ ይሁን ባይነት ሊኖረው ይገባል። እናም ይህ ሲሆን ሕዝብ ስልጣን በእርሱ ላይ እንዲጫን የሚሰጥ ሳይሆን ለሕዝብ ከግለሰብ እስከ ማህበረሰብ ግልጋሎት እንዲሰጥ የሚደረግ ህግ ነው። በሀገራችን የዘረኞች ህገመንግስት ግን የምናየው የትቂት የፖለቲካ ድርጅቶች የፖለቲካ ፕሮግራምን ለሀገር ሕዝብ ህገ ሰጠን በሚል በማስፈራራት የተጣለ ሕግ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የመገነጣጠልን ሕግ አልደገፈም፣ ወይንም የኢትዮጵያ ሕዝብ በየቋንቋ መንደራችን ተወስነን ሌላው ባእድ ነው ብሎ አልወሰነው፣ አለበለዚያም ለዚህ አይነት ህግ ድምጽ አልሰጠም። አሁን ተቀበሉ ካልተቀበላችሁ ግን ወግዱ የሚባልበት ህገመንግስት ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን የዘረኛ አንባ ገነኖች ምርጫ እና ፍላጎትን ካላከበራችሁ ከዚ ጥፉ እንደማለት መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል።

ህገመንግስት ስንል በዴሞክራሲያዊ ስርአት ሕዝብ ስልጣን ሲሰጥ እንዲያገለግሉት፣ ጥቅሙን እንዲጠበቅለት፣ መብቱ እና ሀገሩ እንዲከበርለት በህዝብ ይሁንታ የሚሰጥ አስፈጻሚ ደንብ ማለት እንጅ እንዳሻቸው እንዲገዙት፣ ሲያሻቸው እንዲያስሩት እንዲያሰድዱት የሚደነግግ ህግ ማለት አይደለም። እናም ህገመንግስት የመንግስትን ሃይል የሚቀንስ እና ለሕዝብ ሆኖ የሚያገለግል ደንብ እና ስርአት ማለት ነው።

ዴሞክራሲ አምስት ዋነኛ መሰረቶች አሉት እነርሱም፦
ማሕበራዊ እኩልነት (Social equality)
የብዙሀን ሀላፊነት መውሰድ (Majority Rule)
የአናሳ መብት መከበር (Minority right)
ፍጹም ከማነኛውም ተጽእኖ ነጻ መሆን (Freedom)

የሞራል ጣራ መኖር፣ ፍጹም እውነታኛነት፣ አንድነት እና ያልተበታተነ ህብረተሰብ መፍጠር፣ ናቸው-(Integrity)

ከላይ ለማሳየት ከሞከርኋቸው መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱም በሀገራችን ተሟልቷል ማለት ያስቸግራል። ዴሞክራሲ ሲሉ ዘረኞች ታክቲክ ማለታቸው ነው። ይህ ማለት የሕዝብ ትግል ሲያይልባቸው ዴሞክራት ሆኖ እና መስሎ መገኘት። ትግሉ ሲቀዘቅዝ ማንም ሰው ሆነ ቡድን የህገመንግስት ጥያቄ ማንሳት እንደማይችል፣ ህግ እንዳይተላለፍ ማስፈራራት ማለት ነው። የዚህ የዴሞክራሲን ሕዝባዊ ጥያቄነት ለማሳነስ ዘረኞች የዘር ግጭትንም ይሰብካሉ፣ ዜጎችን ያፈናቅላሉ ወይንም የቋንቋ ውድድር እንዲፈጠር ይገፋፋሉ ይህ ሁሉ ለሀገር እና ለሕዝብ እያሰቡ ሳይሆን በእንዴት አይነት ቴክኒክ ዘረኝነት ማስቀጠል እንችላለን ወይንም የዘረኛውን ሕገመንስት ዘላለማዊ ማድረግ እንችላለን ከሚል ስሌት በመነሳት ነው። ባጠቃላይ ዴሞክራሲ ማለት የግለሰብ ምርጫን እና ነጻነትን በመርህ የሚያከብር ማለት እንጅ፤ የእደግን እና የቶሎሳን አክብሮ የገብረ እግዚያብሔርን እና ገመዳን የሚያቃልል ማለት አይደለም። ከዘረኝነት ስንላቀቅ የግለሰብ ነጻነትን ማህከል ያደረገ የዴሞክራሲ ስርአት እንመስርት ማለት ሲሆን። ዘረኞች ሁሉንም ጉዳይ ወደ ቡድን ነጻነት ይወስዱት እና ክልል አንድ ተጨቁኖ ስለኖረ ክልል አምስ ተነስቶ በክልል አንድ ይተካ የሚል መርህ ነው። እኛ ዘረኞችን የምንቃወመው መጀመሪያ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከልሎ ይህ ያንተ ያ የኔ የሚለው እራሱን የቻለ ችግር ያለበት እና ከክልሉ ውጭ የሚኖርን ሚሊዮኖች ነጻነት፣ እና የዜግነት መብትን የነፈገ ኢዴሞክራሲያዊ ነው እንላለን።፡በመሆኑም ስለ ቡድን ነጻነት ማስቀደም ውጤቱ ዘረኝነት እንጅ ዴሞክራሲ ስላልሆነ በኢትዮጵያ ዴሞክራቶች እምነት እና በአለም ዴሞክራሲያዊ ስርአትን መስርተው በተገበሩ ሀገራት ተመክሮ ዴሞክራሲ የግለሰብ ነጻነት የሚከበርበት ስርአት መመስረት በዋናነትም አንድ ሰው አንድ ድምጽን ያከበረ ነው እንላለን።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.