ምን ልታዘዝ ሳምንታዊ የቴሌቭዥን ድራማ ተቋረጠ

በፋና ቴሌቭዥን ሲቀርብ የነበረውና በይዘቱ ፖለቲካዊ ሽሙጥ ላይ ያተኮረው ምን ልታዘዝ ሳምንታዊ ድራማ “በተደረገበት የተቀነባበረ ዘመቻ” ለመቋረጥ መገደዱን የድራማው አዘጋጆች ተናገሩ።

ከድራማው ፀሃፊዎች አንዱ የሆነውና የፊልም ባለሙያ በኋይሉ ዋሴ (ዋጀ) እንደነገረን ያለፉትን ወራት የገጠሟቸው ፈተናዎች በተቀነባበረ መልክ ወደ ህዝብ ተመልሰው እንዳይቀርቡ እንዳደረጋቸው ይገልፃል።

ድራማውን በፋይናንስ ሲደግፍ የነበረውና የድራማው ተባባሪ አዘጋጅ የሆነው አያልነህ ተሾመ ለ17 ቀናት ያህል በፖሊስ ተይዞ መታሰሩንና በዋስ መለቀቁን ዋዜማ ከፖሊስ ከምንጮቿ ሰምታለች። አያልነህ የታሰረው ለምን እንደሆነ ያልተገለፀለት ሲሆን ፍርድ ቤትም ሳይቀርብ ቆይቶ በዋስ መለቀቁንና በምርመራ ወቅት ምን ልታዘዝ ድራማን ማን በፋይናንስ እንደሚረዳው ጥያቄ ቀርቦለት እንደነበር ስምተናል።

ምን ልታዘዝ በነፃ በተገኘ የግለሰብ መጋዘን ውስጥ ቀረፃው ይካሄድ የነበረ ሲሆን ሁለት ስፖንስሮችም ይደግፉት ነበር፣ አዋሽ ባንክና ኖህ ሪል ስቴት። ድርጅቶቹ በሳምንት ልዩነት ድጋፋቸውን ያቋረጡ ሲሆን ሌሎች ስፖንሰሮችም ድጋፍ ለማድረግ ከመጡ በኋላ በድንገት ሀሳባቸውን ቀይረው ይመለሱ ነበር።

“ለሀገር የሚጠቅም፣ የመናገር ነፃነትን የሚያበረታታ የተሻለ ስራ ሰርተን ለተመልካቹ ማሳየት እንፈልጋለን። አሁን ባለው ሁኔታ በፋና ተመልሰን እንደማንመጣ ግልፅ ሆኗል። ሌሎች የግል ሚዲያዎችም ምን ልታዘዝን ለመቀበል የሚደፍሩ አይደሉም። ስለዚህ በድረ ገፅ ወደ ተመልካች ለመድረስ ሀሳብ አለን” ይላል በኋይሉ።

ምን ልታዘዝ ድራማ የሀገሪቱ የሚዲያ ነፃነት ትኩሳት መለኪያ ተደርጎ ሲታይ ቆይቷል፣ በተለያዩ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀንም ሽፋን አግኝቷል።

ምንጭ ዋዜማ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.