የማጀት ሥር ወንጌል (ኅሊና ታደሠ)

የማጀት ሥር ወንጌል

ሙያተኛ ሀገሬ ከማጥገብ ጎደለ በረከት እራቀው የገበታሽ ለዛ፣
ተሻምቶ ለመጉረስ ከበላነው ይልቅ የደፋነው በዛ፡፡

ሙያሽ ባያስደፍር አጀብ ቢሰኙበት፣
ማዕዱ ቢሙላላ ዓይነቱ ቢያምርበት፣
አበዛዙ አይደለም አበላሉ ላይ ነው የገበታሽ ውበት፡፡

እየተማመንን! የፉክክር ቅሚያ በርሃብ እየናጥን፣
ከደፋነው ጠግቦ ውሻችን በለጠን፡፡

ከምርት አላነስን፣
ጎተራችን ሙሉ ጀግና አራሽ መች አጥተን፣
ማሰብ የጎደለው አያያዛችን ነው ገደል የከተተን፡፡

ይልቅ ግዴለሽም! ከምግባር ምጣድ ላይ ሳንበስል አንጋግተሸ ከማዕድ አትምሪን፣
ገበታሽ እንዲያምር ከእግዜር የሚያስታርቅ ፍቅር አስተምሪን፡፡

ገበታ ዕድሜ ነው ባለ ማሰብ መክነን፣
ሳንፀነስ ጃጀን፣
ሳንጣድ አረርን፣
ከዘመን ገበታ ከፊደል አቅድመን ዘር እየቆጠርን፡፡

ገበታ ሀቅ ነው በክፋት ሊጥ ጋግረው ያሻገቱት እውነት፣
በሆዳም እስክስታ ረግጠው ያፈኑት የምስኪናን ጩኀት፡፡

እስኪ ልጠይቅሽ በጥም ደዌ ደቆ የረሃብ ጠኔ ደፍቶት እልፍ ትውልድ ያልፋል፣
ቢራ ለመጥመቂያ ሚበተን ገብስ ግን ከሀገር መች ይጠፋል፡፡

ከሆድ በማይሻገር የማጀት ቤት ዕውቀት አጥብበሽ አትለኪን፣
እስቲ መኖር ይግባን ከማስተዋል መቅደስ ሰው መሆን ስበኪን፡፡

ዘመን ካልገበረው ከችጋር ተራራ ከሲኦል ዳር ኑሮ፣
እንዴት ነው መሻገር ከመርፌ ቀዳዳ በጠበበ አይምሮ፡፡

ከምስኪን ዘመን ላይ የማይኖሩበትን ዕድሜ መበዳደር፣
ለአንዲት ማምሻ ደስታ በአያት እስትንፋስ ላይ ቁማር መደራደር፣
ያሳፍራል አይደል?

እያደጉ ማነስ እያነሱ መዝቀጥ፣
አጎንብሶ ያፀናን የድሃ እናት ጉልበት በጭካኔ መርገጥ፣
ያሳምማል አይደል?

መንገስ ከሚያባላስ መጥገብ ከሚያቃቅር ማግኘት ከሚያጎለን፣
ማጣት ውሎ ይግባ ባርነት ይሰንብት ድህነት ይግደለን፡፡

ከረፈደ ፀፀት ደረት እየደቁ ከእግዜር ቢዋቀሱ፣
ትርጉሙ ምንድነው ሲኖር ተቃቅሮ ሲሞት መላቀሱ፡፡

በእናታችን አድባር በፍቅሯ ይሁንብን፣
መድመቅ ካጋደለን ቆሽሸን ይመርብን፡፡

በመጠማት ሲቃ እስትንፋስ እስኪያንቃት ነፍሳችን ትርበትበት፣
ብቻህን ከመጥገብ አብሮ መራብህ ነው ሰው የመሆን ውበት፡፡

በድፍን ግልብ እሚያጋድል ህዝብ የመሆን መንጋ አይንዳን፣
በማሰብ ስር እንፈወስ በሰውነት ፀበል እንዳን፡፡

አየህ! ሰው ስትሆን ከመንጋነት ሚያግድ እረኛ አያሻህም ከህሊናህ በላይ፣
ስታስብ መሪ ነህ በብስለት ከፍታ በማስተዋል ሰማይ፡፡

አየህ! ሰው ስትሆን የጎጥ አረም ነቅለህ በአንድነት መስክ ላይ ፍቅር ትዘራለህ፣
በወረወሩብህ የጥላቻ ድንጋይ ትውልድ የሚያፋቅር ድልድይ ታበጃለህ፡፡

አየህ! ሰው ስትሆን ዝምታህ ኃያል ነው ጀግና የሚያነበረክክ፣
ከፈሪ ቀረርቶ ከባዶ ሰው ጩኀት፣
ሀገር ላምስ ከሚል በመንደር አጀንዳ በአሽኮለሌ ተረት፡፡

አየህ! ሰው ስትሆን ነጻ ነህ እያሉህ መታሰር ያምርሃል፣
መቀመቅ መበስበስ፡፡

የኖርክለት እውነት ሀገር እስኪፈታ፣
በሀቁ እስኪመዘን ስለ በርባን ክብር የቆሸሸው ፍቅር የታሰረው ጌታ፣
ከድል ታሪክ ሰማይ ከሥልጣኔ ዳር ከጥበብ ከፍታ፣
እንሻገራለን ህዝብነትን ትተን ሰው የሆንን ለታ፡፡

በትረ ጥበበ ቢካን ዓለም ሊያንቀጠቅጥ ድል ሥልጣን ቢሰጠው፣
ጀግና መሪ አይደለም ብርቱ ተመሪ ነው ሀገር ሚለውጠው፡፡

አስተውል ወዳጄ ጠልተን ላንጣላ ችለን ላንጋደል ነደን ላንፋጀው፣
የኛው ትርምስ ነው በልቶ ለሚያባላ ጠላት ሚበጀው፡፡

ስጋና ደም እንጂ የአንድነታችን ውል የፍቅራችን ቀለም፣
ያሰመርነው ክልል የታጠርንበት ዘር ቋንቋችን አይደለም፡፡

ከመዋሃድ መቅደስ ትውልድ እናስተምር፣
ዘመን ይመርቀን ፍቅራችን ምን ጎድሎት ደማችን ያስታርቀን፡፡

በልጆቿ አጥንት በደም ኪዳን ምለን የገባንላት ቃል፣
ከጩኀት ያለፈ ዘመን የሚሻገር ተግባር ይጠይቃል፡፡

በአንድ ሃሳብ ተጋምደን በድል ድር እናብር ውድቀታችን ያንቃን፣
ሠርተን እናሳምን ሆነን ድል እንንሳ የአፍ ጀግንነት ይብቃን፡፡

ምስኪኒቷ እናቴ! በሞላ ጎዳና ባልጠበበ ድንበር በዘር ገመድ ታግዳ፣
ነጻ ነኝ ትላለች መንጋነት ያሰረው ባሪያ ትውልድ ወልዳ፡፡

የጀግንነት እብሪት ልባችንን ደፍኖት ማሰብ እየከዳን፣
እንዴት ነው ነጻነት እንዳበደ ፈረስ ስሜት እየነዳን፡፡

ገድሎ የመንገስ ጥማት ጩኀት ላገነነ አመጽ ላጀገነው፣
ለዚህ ምስኪን ትውልድ በጅምላ እየነዱት፣
በመንጋ እያሰበ ነጻነት እንዴት ነው?

ነጻነት ምርጫ ነው አምሮ ቢደላደል ጥፋት ያመነነው የመንጋዎች መንገድ፣
እንቅፋቱን ወዶ ለኖሩለት እውነት ለብቻ መራመድ፡፡

ነጻነት ማመን ነው ቀን ወዶ ቢያጀግን ቀን ጠልቶ ቢከዳም፣
ቢቆሽሹም ቢደምቁም እራስን መቀበል ራስን መምሰል ነው የነጻነት ገዳም፡፡

ነጻነት ማሰብ ነው በአንድነት መለምለም የኔነትን አረም ከህሊና ማጥፋት፣
ዘር ሆኖ ከማነስ ሀገር ሆኖ ማበብ ዓለም ሆኖ መስፋት፡፡

ንገሯት ለሀገሬ በጀግኖቿ ትግል ድንበር ባታስደፍር ከእጀ ገዥ ብትወጣ፣
ነጻ ነኝ እንዳትል በገዛ ልጆቿ በእጅ አዙር ተሸጣ ፡፡

ስሩን ካልሸመነው በመዋሃድ ጥለት በማስተዋል ሸማ፣
ታሪክ አናደምቅም በጭብጨባ ድግስ በሆይ ሆይታ ዜማ፡፡

ምን ብናቀነቅን በየሰልፉ ሜዳ ወኔ ብንደግስም፣
በፈረሰ አይምሮ በደቀቀ አንድነት ሀገር አናድስም፡፡

በጭፍን ከመሮጥ አስቦ ማዝገም ነው የመራመድ ውሉ፣
ሁሉም እንቅፋቶች እስኪጥሉን ድረስ ምርኩዝ ይመስላሉ፡፡

በድፍን ግልብ እሚያጋድል ህዝብ የመሆን መንጋ አይንዳን፣
በማሰብ ስር እንፈወስ በሰውነት ፀበል እንዳን፡፡

ከእግዜር ልንወዳጅ ለምህረቱ ጥላ እምባ ብንደግስም፣
ልብን ሳይመልሱ ለንስሃ መሮጥ ከጽድቅ አያደርስም፡፡

ውብ ነገን እናውርስ ትላንትን አክመን በይቅርታ ፀበል፣
ትውልድ ይጨርሳል ያረገዝነው እምባ የቋጠርነው በቀል፣
ከመስጠት አንጉደል ከቀማኞች ገደል ተረግጠን ብንጣል፣
ካሸከሙን በቀል ምናወርሰው ፍቅር ሀገር ይለውጣል፡፡

ከዕድሏ ጣሪያ ላይ ዘር የቀዳደው ሽንቁሯ ቢበዛም፣
ያ ከንቱ ፎካሪ ባፈጀ ቀረርቶ ሺህ ጉራ ቢነዛም፣
ሚሊዮን ዘር ቢሸጥ አንድ ሀገር አይገዛም፡፡

ኢዮጵያዊነት ነው የትርታችን ልክ የነፍሳችን ግጥም፣
መልስ ቤት በራቀው በከረመ ፀሎት ሰርክ ብታንጋጥም
አጎንብሳ ድሃ ባፀናችው ጉልበት ብትረጋገጥም
ነፍሷን አደህይታ ባሻረችው ቁስል ብትገሸለጥም፣
ሀገር ሆና ገዝፋ በየ ጎጣጎጡ አትርመጠመጥም፡፡

የዘመን እውነት ነን ከደግነት ሰማይ በጥበብ የኖርን፣
ትዕግስትም ልክ አለው ፈርተን እንዳይመስለው ስላቀረቀርን፡፡

ማተብ አስሮን እንጂ ተጣልተን እንዳንቀር በክፍፍል ገደል፣
ከሀገር ክብር በልጦ ሞት ብርቃችን አይደል፡፡

ንገሩት ለዛ ሰው ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ኃይል እንደ ተራራ ገዝፎ ቢከመርም፣
ክንዱን አፈርጥሞ እልፍ የሰገደለት ጀግና ቢሰድርም፣
ዓለም የሞተበት የጠላት ማርከሻ ጦር ቢደረድርም፣
በአንድ ዓይናችን ሰላም በኢትዮጵያችን ክብር አንደራደርም!!!

ኅሊና ታደሠ

2 COMMENTS

 1. አይ መመህር በቄ! ይህ ግጥም እኮ ሲያንስህ ነው። ግን አንተን እና መሠሎችህን እንደሚመለከት ማወቅህ ጥሩ ነው፡፡ ቀቀቀቀሺሺሺሺም!

 2. ይህች አማተር ልጅ በአንድም በሌላም እውቅና እንድታገኝ ሆኗል ፤ ግጥሟ መነጋገሪያ ከመሆንም አልፎ እውቅና እንዲቸረው ሆኗ፤ ሰው የድካሙ ውጤት በአድም በሌላም መንገድ መነጋገሪያ ሲሆንለትንሥ መልዕክቱን በሚገባ የማስተላለፍ ግቡን ሲመታለት ሃሳቡ ሰምሮለታል ማለት ነው ሕሊና በዚህ እድለኛ ናት ።

  በበኩሌ ለግጥም ያለኝ አመለካከት ሰፋ እና ላቅ ያለ ከመሆኑ አንጻር የልጅቷ ግጥም የተኮነነበትን ጥግ ለማየት ሞከርኩ በሀገራችን ያሉ ገጣሚያን እጅግ ጥቂት ከመሆናቸውም በላይ ጥሩ ስራዎቻቸውን ለህዝብ ካደረሱት ውስጥ ከታላቁ ሰው ፀጋዬ ገ/መድህን ጀምሮ አበባው መላኩ ፣ ኤፍሬም ስዩም ፣ ትዕግሥት ማሞ በእውቀቱ ስዩም ከማደንቃቸው እና ከማከብራቸው ለኔ አንጋፋዎች ናቸው “ቄሮን መንጋ አለች ” የሚል ጽንፍ የረገጠ አተያይን ብዙ ፖለቲካን ከሚተነትኑልን ሰዎቻችን ሁሉ ሰምቼ ነበርና ሙሉ ግጥሙን እስክሰማና ደጋግሜ እስካነብ ጓጉቼ ነበር ፤ የገረመኝ ግን “በግጥሙ የተንጸባረቀው ጉዳይ በይበልጥ የሚነካቸውና ከአማራነት ውጭ ሌላውን እንደ ርኩስ በድን የሚቆጥሩ ጭፍን እና መንጋ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች የተባሉ ሁሉ ዝም ባሉበት ሁኔታ እነ ኦቦ በቀለ ገርባን ያናደዳቸው ነገር አስገርሞኛል ፤ ገለጻውን እርሷ ካሰበችው ውጭ ለቄሮ ለመስጠት መሞከር በኔ እይታ ፍጹም ስህተት ነው ።

  ልጅቷ ያነሳችሁ ሀሳብ እንደ ሀገር ነው ፤ በመንጋ እየተነዳ ጥፋት ላደረሰው ትውልድ መልዕክት ይሆን ዘንድም ነው ።
  ወዳጆች ሆይ ቄሮ መንጋ አይደለም ፤ በነጻነቱ ለመጡበትና ለሚመጡበት ትዕግሥቱንም ለተፈታተኑት ወራሪ መንጎች ከብረት በጠነከረ ሕብረት ብረትን አቅልጦ ነጻነት ያቀዳጀን ፥ ከአንበሳም በጀገነ ጀግንነትና እና ከነብርም የበረታ ቁጡነት ነብር የሆነ ትንታግ የሀገር አለኝታ ድንቅ ኃይል ነው ፤ ቄሮ ሀገር አፍራሽ ሳይሆን ሀገር ለመገንባት የጨከነ ነው ቄሮ ለስልጣን ሲል ወገኑን አልበላም በልቶም አያውቅም። ስለዚህ ልጅቱ ቄሮን ያላለችውን ቄሮን እንዲህ አለች አትበሉ፤ ለፖለቲካ የማያልቅ ርዕስ አለና ።

  እስቲ ለግንዛቤ ከግጥሙ መሃል ይህችን ሀረግ እንምዘዝና ልጅት መልዕክቷን ለማን እንዳስተላለፈች እንረዳት :—–

  የጀግንነት እብሪት ልባችንን ደፍኖት ማሰብ እየከዳን ፣
  እንዴት ነው ነጻነት እንዳበደ ፈረስ ስሜት እየነዳን ።
  ገድሎ የመንገስ ጥማት ጩኸት ለገነነ –አመጽ ላጀገነው ፣
  ለዚህ ምሥኪን ትውልድ በጅምላ እየነዱት ፥ በመንጋ እያሰበ ነጻነት እንዴት ነው?

  ይህ በቅርቡ በአማራ ክልል የተደረገውን ገድሎ የመንገስ ጥማት የገለጠችበት መንገድ ድንቅ ነው ፤ እያንዳንዱን የክልሉን አክቲቪስት ህይወት ብታዩት በዚህ መንፈስ የተቃኘ ሆኖ ታገኙታላችሁ፤ ለሀገር አንድነት የሚያስቡትን እየበሉ በጎበዝ አለቃና በመንጋ እየተቧደኑ ተመራማሪ ዶክተሮችን ቀጥቅጠው ሲገድሉ ፣ የወሎ ሕብረት አባላት ላይ የፈላ ውሃ ሲደፉ ፣ የኢዜማ አባላትን በባህር ዳር ሲያሳድዱ ፣ አልፎም በስልጣን ጥማት ለራሳቸው ዋጋ የከፈሉ ምርጥ ጀግኖችን በጀግንነት እብሪት እና በስልጣን ጥማት እንዳበደ ፈረስ በጅምላ እሳቤ ብዙ ነገሮችን ሲያደርጉ ልጅት ገጣሚ ሆና ይህንን ሀቅ ባታወጣ ይገርም ነበር ፤ በበኩሌ የልጅቷን አገላለጽ አድንቄአለሁ ጎበዝ ገጣሚም ናትና ገና ብዙ ሀሳቦችን ይዛ ትቀርባለች ብዬ አስባለሁ ።

  በቸር ያቆየን!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.