ከሐረር በራስ መኮንን የተመራው ቀዳሚው የአድዋ ዘማች ሠራዊት ማንነት (አቻምየለህ ታምሩ)

ዶክተር መረራ ጉዲና ከሰሞኑ በዋልታ ቴሌቭዥን ቀርበው በሰጡት አንድ ቃለ ምልልስ የኦነጋውያንን ያልተመረመረ ትርክት በመድገም ከጎጃም፣ ከወሎ፣ ከሐረር፣ ከሸዋ፣ ወዘተ ወደ አድዋ የዘመተውን ጦር ሁሉ ኦሮሞ ሠራዊት አድርገው አቅርበውታል። ምንም እንኳ ያገራችን የግራ ፖለቲከኞች ሁሉ ደጋሚዎችና አፍ ነጠቆች እንደሆኑ ባውቅም ዶክተር መረራ ግን ይህን ያህል ዘመን በማስተማርና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ኖሮ ኦነጋውያን የሚያስተጋቡት ትርክት ሳይመረምሩ መሰልቀጣቸው ሳያስገርመኝ አልቀረም።

ከጎጃም፣ ከወሎና ከሸዋ ወደ አድዋ ስለዘመተው ጦርና መሪዎቹ በተደጋጋሚ ስለጻፍሁ የኦነግ ፕሮፓጋንዳ በተደጋገመ ቁጥር የጻፍሁትን ደግሞ በማተም የአንባቢን ጊዜ አልሻማም። ዶክተር መረራ የፈጠሩትን አጋጣሚው ተጠቅሜ ዛሬ መጻፍ የምፈልገው ታሪክ ማንነታቸው ላልተነገረላቸውና ጀግንነታቸው ስላልተጻፈላቸው በራስ መኮንን እየተመሩ ከሐረር ተነስተው ወደ አድዋ ስለዘመቱት ቀዳሚ የአድዋ ድል ጀግኖች ታሪክና ማንነት ነው።

በራስ መኮንን እየተመራ ወደ አድዋ የዘመተው የሐረር ጦር ዶክተር መረራ የኦነጋውያንን ትርክት ደግመው እንደነገሩን የኦሮሞ ጦር ሳይሆን የጎንደር ተወላጆች ጦር ነበር። አምባላጌ ላይ መሽጎ የነበረውን የጀኔራል ባራቴሪ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ ሰራዊት አፈር ድሜ አስግጠው ቀዳሚውን የአድዋ ድል አምባላጌ ላይ በደማቸው ያስመዘገቡት እነዚህ በራስ መኮንን መሪነት ከሐረር የዘመቱት የጎንደር ተወላጆች ናቸው።

እነዚህ የአድዋ ድል ቀዳሚ ጀግኖች የሆኑት ጎንደሬዎች ታሪካቸው እስከዛሬ ድረስ አልተነገረላቸውም። እነ ታከለ ኡማም ሊያቆሙት ባሰቡት የአድዋ ድል መታሰቢያ ላይ የነዚህን የጎንደር ተወላጅነት ያላቸው የአድዋ ጀግኖች ታሪክ ቀምተው ከሐረር የዘመተውን የራስ መኮንን ጦር «ከሐረር የዘመተው የኦሮሞ ሰራዊት» የሚል ስያሜ እንደሰጡት ሊያቆሙት ካሰቡት የመታሰቢያ ሐውልድ ንድፍ ለማወቅ ችያለሁ።

በራስ መኮንን እየተመራ ከሐረር ወደ አድዋ የዘመተው ቀዳሚው ጦር ጎንደሬ ስለመሆኑ ታሪኩን የሚነግሩን ሁለት በዘመኑ የነበሩ የዐይን ምስክሮች ናቸው። ቀዳሚው የታሪክ ምስክር የራሳቸው የራስ መኮንን ዜና መዋዕል ጸሐፊ ግራጌታ ኃይለጊዮርጊስ በለጠ ዘሐረር ናቸው።

ግራጌታ ኃይለጊዮርጊስ በለጠ የራስ መኮንን ጦር ጎንደሬ እንደነበር ያስተዋወቁን በግዕዝ ቋንቋ በጻፉት የራስ መኮንን ዜና መዋዕል ውስጥ ነው። በግራጌታ ኃይለ ጊዮርጊስ የተጻፈው ዜና መዋዕሉ የተዘጋጀው ራስ መኮንን በሕይወቱ በነበሩበት ወቅት ሲሆን የዜና መዋዕሉ ርዕስ «ዜናሁ፡ ለልዑል፡ራስ መኮንን» ይላል። ዜና መዋዕሉ የጸሐፊውን ማንነት ሲገልጽ ደግሞ «ዘጸሐፎ፡ ግራጌታ፡ ኃይለ፡ ጊዮርጊስ፡ ዘሐረር» ይላል።

ግራጌታ ኃይለጊዮርጊስ በለጠ የራስ መኮንን ጦር ጎንደሬ እንደነበር የሚነግሩን ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ቀድሞ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረውን ሐረርን ካስገበሩ በኋላ ባላምባራስ መኮንንን «ደጃዝማች» ብለው የሐረርጌ አውራጃ አስተዳዳሪ አድርገው ከሾሙ በኋላ ወደሸዋ ከመመለሳቸው በፊት ወደ ሐረር ከዘመተው ጦር መካከል ለራስ መኮንን ትተውላቸው ስለመጡት ጦር ማንነት በሚገልጹበት የዜና መዋዕል አምዳቸው ነው። ግራጌታ ኃይለጊዮርጊስ ይህን ታሪክ ከገጽ 24-25 ባለው የዜናመዋዕሉ ክፍል እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል፤
______
«ወእምዝ፡ ይቤሎሙ፡ለሠራዊተ ዘምድረ፡ ጎንደር፡ እለ፡ኀደጎሙ፡ ምስሌሁ፡ ንበሩ፡ በተፍቅሮ፡ ምስለ፡ ወልድየ፡ ደጃዝማች፡ መኮንን ወጽንዑ፡ ከመ፡ እብን፡መንፈሳዊ፡ ወታቦት፡ ለንጉሥ፡ እስመ፡ ተኅረይክሙ፡ እምብዙኃን፡ ሠራዊት፡ ዘመንግሥትየ። ወለውእቱኒ፡ ይቤሎ፡ አንተኒ፡ ዕቀቦሙ፡ ከመ፡ ብንተ ዓይን፡ ወእሙንቱሂ፡ ይኩኑከ፡ ከመ፡ እድ ወእግር። ወዝንተ፡ ብሂሎ፡ ንጉሥነ፡ ምኒልክ፡ ተይመጠ፡ ውስተ፡ ብሔሩ፡ ምድረ፡ ሸዋ፡ ወአስተፋነውዎ፡ በዳኅና፡ ወበሰላም።»

ትርጉም፡

«. . . ከዚያም ዳግማዊ ምኒልክ ከደጃዝማች መኮንን ጋር የተዋቸውን የጎንደርን ወታደሮች “ከልጄ ከደጃዝማች መኮንን ጋር በፍቅር ተቀመጡ፡ እንደመንፈሳዊ ድንጋይና እንደ ንጉሥ ታቦት ጽኑ፡ ከብዙዎቹ የመንግሥቴ ሰራዊት [ሐረር እንድትቀሩ] እናንተ ተመርጣችኋልና” አላቸውም። ደጃዝማች መኮንንም “አንተም [እነዚህ የጎንደር ወታደሮች] እንደ ዓይን ብሌን ጠብቃቸው፤ እነሱ እንደ እጅና እነ እግር ይሁኑህ” አሏቸው። ንጉሠችን ምኒልክን ይህንን ተናግረው [ከሐረር] ወደ ሸዋ ተመለሱ፤ [ራስ መኮንንም] በሰላም በደኅና ሸኙዋቸው»
______

ከዚህ የራስ መኮንን ዜና መዋዕል የዘመን ትውስታ እንደምንገነዘበው የራስ መኮንን ጦር የጎንደር ወታደሮች እንደሆኑ በግልጽ እንመለከታለን። ራስ መኮንን ከስድስት ዓመታት በኋላ ከሐረር ተነስተው ወደ አድዋ የዘመቱት ይህንን የጎንደር ተወላጆች ሠራዊት አሰልፈው ነው።

የሐረር ሠራዊት ቀንደኛው ጎንደሬ እንደነበር የሚነግሩን ሌላኛው የዘመን የታሪክ ምስክር ደግሞ ሐረር ራስ መኮንን ቤተ መንግሥት በራስ መኮንን እጅ ያደጉትና በልጅ እያሱና በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ዘመን የጅጅጋ እና የጨርጨር [ ምስራቅ ሐረርጌ] አውራጃዎች አስተዳዳሪ የነበሩት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ናቸው።

ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት «ኦቶባዮግራፊ (የሕይወቴ ታሪክ)» በሚል በጻፉት የዘመን ታሪክ ትዝታቸው ውስጥ የሐረር ሠራዊት ቀዳሚው ጎንደሬ መሆኑን የዘመን ምስክርነታቸውን የሰጡን «ባለጉ» ያሏቸውን ልጅ ኢያሱን እዚያው ሐረር ውስጥ ለመግጠም በተነሱበት ወቅት ካደረጓቸው ዝግጅቶች መካከል ቀዳሚው የሐረርን ሠራዊት ማሳመንና ከጎናቸው እንዲሰለፍ ማግባባት መሆኑን በነገሩበት የሕይወት ታሪካቸው ክፍል ነው።

ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም ይህንን ታሪክና ልጅ ኢያሱን ለመግጠም ሲነሱ ያደረጉትን ቅድመ ዝግጅት በጻፉበት የዘመን ታሪክ ትዝታቸው ውስጥ ከገጽ 284-85 በጻፉት ታሪክ የሚከተለውን አትተዋል፤
______

«የሐረር ሠራዊት ቀዳሚው ጎንደሬ ነው። ጎንደሬን ካሳበርነው የቀረው አያስቸግርም። የጎንደሬዎች [ጦር] እንደራሴ ግራዝማች ጋሹ ያቶ ንጋቱ ወዳጅ ነውና እንተዋወቃለን። ከደጃዝማች ተፈሪም ጋር ወዳጅነት እንደነበረው አውቃለሁ፤ ያቶ ንጋቱን አሽከር አቶ ዓለሙን አስጠራሁና [ወደ ጎንደሬዎች ሠራዊት እንደራሴ] ወደ ግራዝማች ጋሹ ላክሁት። “ከደጃዝማች ተፈሪ አሽከር መልዕክት መጥቶልሀል፤ አፍላፍ ተነጋገሩ ብለውናል። ድሬዳዋ ድረስ በፍጥነት መጥተህ እንገናኝ። የሞት ቀጠሮ ነው፤ አትቅር” ብዬ ላክሁበት።

[ለመልዕክተኛው] ለአቶ ዓለሙ አስቀድሜ መቶ ብር ጉርሻ ሰጠሁት፤ ሲሄድ ነገርኩት፣ ጋሹን በፍጥነት ያመጣህልኝ እንደሆን ደግሞ መቶ ብር እሰጥሃለሁ አልኩት። አቶ ዓለሙ ያቶ ንጋቱ አብሮ አደግ ነው። በደጃዝማች መኩሪያ ቤት ከልጅነት ጀምሮ በባልንጀራነት አድገዋል።

አቶ ዓለሙ ግራዝማች ጋሹን አገሥግሦ አመጣው። እቤቴ አሰነበትኩት። ወደ ሱቅ እየወሰድኩ የሚወደውን እቃ እያስመረጥሁ ገዛሁለት። በመጨረሻም ሐሳቤን ገለጥሁለት። ወደደው። “ጎንደሬ ለተፈሪ መክቶ ይሞታል። ለዚህ እኔ አለሁ” እያለ በተጋጋለ አንደበት አረጋገጠልኝ። “እንማማል” አልኩት፤ “ብከዳ ምድር ትክዳኝ” ብሎ ማለ።»
________

ይህ የፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም የዘመንና የዓይን ምስክርነት እንደሚያስረዳን የሐረር ሠራዊት ቀዳሚው ጎንደሬ እንደነበር ነው። ይህ ጦር ነው በራስ መኮንን መሪነት ወደ አድዋ ዘምቶ መጀመሪያ አምባላጌ ላይ፤ ቀጥሎ መቀሌ ላይ፤ ከዚያም አድዋ ላይ በተካሄደው ከፍተኛ ውጊያ ቀዳሚውን መስዕዋትነት የተቀበለውና በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም የሆነውን የአድዋን ክስተት በደሙና በአጥንቱ ያስመዘገበው።

ይህ የሐረር የጎንደሬ ሠራዊት ግን ታሪኩ እስካሁን ድረስ አልተጻፈለትም፤ አልተነገረለትም። እነ ታከለ ኡማም በኦነግ የፈጠራ ታሪክ እየተመሩ «የአድዋ ጀግኖች መታሰቢያ» በማለት ለማቆም እያሰሩት ባለው መታሰቢያም ከሐረር ተነስቶ የአድዋ ድል ቀዳሚ ባለቤት ለመሆን የበቃውን የሐረር ጎንደሬ ሠራዊት ታሪክ በመዝረፍ ከሕዝብ በሚሰበሰብ ግብር በሚገነባ ሐውልት ላይ የፈጠራ ታሪካቸውን ለመፃፍ እየተጉ ናቸው።

ፍትሕ በራስ መኮንን መሪነት ከሐረር ተነተው መጀመሪያ አምባላጌ ላይ፣ ቀጥሎ መቀሌ ላይ፣ በመጨረሻም አድዋ ላይ ለተገኝው የጥቁር ሕዝቦች ድል ግንባር ቀደም ተሰላፊ ለነበሩት የሐረር ጎንደሬ ሠራዊት! በቅኝ ገዢዎች ፊት የጥቁሮችን እኩል ሰው መሆን ያረጋገጠውን ደማቅ ድል በደማቸው የጻፉት የነዚህ የአድዋ ድል ግንባር ቀደም ተሰላፊ ጀግኖች አባቶቻን ታሪክ ከፍ ብሎ ሊነገር ይገባል!

እውነተኛ ኢትዮጵያውያንና ብአዴን የሚባለው ድርጅት ነፍሱ ካለ እነ ታከ ኡማ ታሪካቸውን ቀምተው መስዕዋትነታቸውን ከንቱ የሚያደርግ ሐውልት ለማቆም እያሰሩ ያሉትን የታሪክ ቅሚያ በመቃወም በራስ መኮንን መሪነት ከሐረር የዘመተው ቀዳሚው የአድዋ ጀግኖች ጦር «የጎንደሬ ሠራዊት» ተብሎ ታሪካቸው እንዲጻፍና ሐውልት እንዲቆምላቸው ሊያደርጉ ይገባል።

አቻምየለህ ታምሩ

10 COMMENTS

 1. ወንድሜ አቻሜለህ – ታሪክ የሚጀምረው ከትላንት ነው ብሎ ከሚያምን ትውልድ ጋር ሰለ እውነት መከራከር እብዶችን መምሰል ነው። አዎን ዶ/ር መራራ በሃገራችን ተመንጥረው ከቀሩን ጥቂት ሚዛናዊ ምሁራን መካከል አንድ ናቸው። ያላቸውም እይታ ሁለንተናዊ እና ሃገር አቀፍ ለመሆኑ በየጊዜው የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች አመላካች ናቸው። ምን አልባት አሁን አሉ ብለህ ባቀረብከው ጉዳይ የተሳሳቱት ነገር ካለ አመላክቶ ማስተካከሉ ማለፊያ ነው። ግን ለዘመናት በግፈኞች እጅ የከፈሉትን ሃበሳ የአንድ ቀን የቃል ልውውጥ ሊያፈርሰው አችይልም። ሳውቃቸውም እሳቸው የኦነግ የሃሳብ ተካፋይ አይደሉም:: የሃገራችን ህዝቦች የጠላትን ወረራ የተጋፈጡት በጋራ ነው። ስንቅ ተካፍለው፤ አንድ ሲወድቅ ሌላው ደግፎት፤ በበረሃና በሽንተረር ተፋልመው ሲችሉ ሙታናቸውን ቀብረው፤ ሳይሆንላቸው ለራሳቸው ነፍሴ አውጪኝ ብለው ነው ዛሬ ላለንበት ቀን ያደረሱን።
  በ60ዎቹ አመታት ተጸንሶ አሁን እኛን በማሳነስ ላይ ያለው የሽሙጥ ፓለቲካን አመድ አልብሶ ማለፍ ነው። ለማንም አይበጅም። ኦሮሞ ይህን ሰራ፤ አማራ ይህን አደረገ፤ ትግሬው በዚያ ነበር የሚባለው የስሪት ፓለቲካ ሃገር አፍርሶ የመሳፍንት ዘመንን ለማምጣት የቀኑ ገዢዎቻችን ከውጭ ሃይሎች ጋር አብረው የጫኑብን እዳ ነው። መተው ነገሬን ከተተው ይላል የሃገሬ ሰው። እርሳቸው … ሙታን ሙታናቸውን ይቅበሩ። ከእጣት እጣት ይበልጣል እያሉ ህዝባችንን የሚያውኩ ወልጋዳና ሽምድምድ የዘር ፓለቲካ ተከታዮች በጊዜአቸው ይመክናሉ። የአድዋ ድል አድራጊዎች ገድላቸው ያልተጻፈላቸው፤ በየጫካው የቀሩ ከሁሉም የኢትዮጵያ ዳር ድንበር የተሰባሰቡ ወገኖች ናቸው። ብንደምራቸው፤ ብንቀንሰው፤ ብናባዛው፤ የአንድ ወገን አጉልተን የሌላውን ብናደበዝዝ እኛን ሞኝ ያደርጋል እንጂ የሚታመን ነገር የለውም። ለአንዲት ሃገር በጋራ ነው የተፋለሙት። ግን ፓለቲካ ሰውን መሳሪያው አድርጎ ሌላውን መጎንተል ከጀመረ ወዲህ ታሪካችን የሁሉም እንዳይሆን ሆን ተብሎ ደባ እየተሰራ ነው። ያው ከእኔ የበለጠ የአሁኑን የሃገራችንን የፓለቲካ ትኩሳት አንተ (አቻምየለህ ታምሩ) ታውቀዋለህ። የወረፋ ፓለቲካ እየሆነ ነው። ይህም ደግሞ የቂሎች የፓለቲካ ፈሊጥ ነው። ሃገር በወረፋ አትመራም። በህብረት እንጂ! እንደ እነ ጀዋር ያለው የጠባብ ብሄርተኞች አቀንቃኝ “የጋራ ታሪክ የለንም” ቢሉንም ሴራቸው ሁሉ ፉርሽ ነው። መማር እንደ ጀዋር ከሆነ ሳልማር ብኖር እመርጣለሁ። እግዚኦ ያሰኛል። አንድ ገጣሚ ግን ነገራችንን በተወሰነ ስንኝ አሳምሮ ገልጦታል

  ዘቅዝቀን ሰቅለነው የተፈጥሮን ካርታ
  እግራችን ይታያል በራሳችን ቦታ። (ምንጭ ፌስታሌ – እያዪ ፈንገስ ትርኢት)
  ይብቃኝ።

 2. አቻምየለህ፣
  ከምኞትህና ከጥላቻ ተነሥተህ መጻፍ እስካላቆምክ ድረስ ከምትነቅፋቸው አንሰህ ትገኛለህ።
  ያልተገነዘብከው ነገር ቢኖር ግራጌታ ኃይለ ጊዮርጊስ ሆኑ ሌሎች ታሪክ ሲጽፉ ለማወደስም
  ጭምር ነው፤ በማወደስ ነው ኑሮአቸው! ትክክሉንማ ቢጽፉ አይሰነብቷትም። የምንሊክን፣
  የአፄ ኃ/ሥላሴን የሕይወት ታሪክ አንብብ፤ ታሪካቸውና የሚታየው ተመጣጣኝ አይደለም!
  “የታሪክ ተመራማሪ” ነኝ ማለትህ ትዝ ይለኛል። ምን ዓይነት ትምህርት ቤት ይሆን ያስተማረህ?

 3. አንበሳው ብእርህ አይድረቅ እናት አንተን ወለደች ይሄ ሁሉ አውቃለሁ ባይ ሆዱ በልጦበት አፉ ተለጉሞ ጀግናው አቻምየለህ በምሁር ብእር ይህን እበላ ባይ ሙጃ ይሸነቁጠዋል። እንግዲህ ተመልከቱት እሱ እራሱ ጎጃሜ ሁኖ ሳለ ታሪክን ከባለ ታሪክ ቀምቶ ለጎጃሜ አልሰጠም ለጎንደሮች እንጅ እነዚህ እንከፎች ከዚህ አንበሳ ምን ይማሩ ይሆን? መቼም ለመማር አልታደሉም። አንበሳው ዘር ይውጣልህ።

 4. No more stealing Oromo’s history. You and your likes have been snatching someone’s history to look only people you represent are more good Ethiopians than other ethnic groups in the country. this makes some societies more important than others. that is why our perspective for Ethiopia is so diverse. Blame no one but you and your likes who has been engaging to make Ethiopian history is only Amharas’ history. For you other societies are simply people without history.

 5. ተስፋ ነህ ማነህ? ስለ መራራ የሰጠኸው ግንዛቤ ከሰው የሰማኸው ሊሆን ይችላል መራራ ህይወቱን ለኦሮሞ የታገለ ለንግድ ህገ አራዊት አንገቴን እሰየፋለሁ ያለ የስርአቱ ተጠቃሚ በዚህ ላይ መጽሐፉን ብታነብ ተጨማሪ እውቀት ይሰጥሀል። እሱን ነጋሶ ጊዳዳን መሰል የኦሮሞ ብሄረተኞችን የሆኑትን ትተን እኛ የምንፈልገውን ኢትዮጵያዊነትን ባንጭንባቸው ጥሩ ነው ዘረኝነት ተስማምቶናል ብለዋል።
  Aleme እና Roba ደግሞ አቻምየለህን በመምክር፣በመሳደብ፣በመለማመጥ ካለበት አንቀሳቅሰዋለሁ ማለት ዘበት ነው። ግለሰቡ የ60ዎቹ ተረት ማርከሻ የተረተኞቹ ማምከኛ ሁኖ በክፉ ቀን የተገኘ የኢትዮጵያ መድኃኒት ስለሆነ በቀላ አይናችሁ አትዩብን።

  ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው እንደ ስስት እህል አይን አይኑን ያያል እንጅ እንዲህ ይዳፈራል? ያለማወቅ ደጉ አቻም ጀመረ እንጅ አልጨረሰም ጽሁፍ ሲለቅ ብልህ ከሆንክ ቴሎ ካፉ መልካም ነው ከተዳፈርክ ግን ብዙ የቆጠበው ስላለ ውርድ ከራሴ ነው።

  በተጨማሪ የሚያስዝን ነገር የኦሮሞ ታሪክና እንቅስቃሴ የሚመራው ዳውድ ኢብሳ(ኡርትርና ትግሬ) እስመሮም ለገሰ፣ተስፋዬ ገ/አብ (ሻቢያ) በቀለ ገርባ (ትግሬ) ጸጋዬ አራርሳ (አማራ) ሌሎቹም ገበሮዎች ሁነው ተገኝተዋል የኦሮሞ ነገድ እነዚህን እበላ ባይ ገለል አድርጎ የሚያዋጣውን ኢትዮጵያዊነት ቢይዝ መልካም ይሆናል።

 6. ሰመረ፣ ስም እንጂ ተረትህ አለሰመረልህ።
  “[አቻምየለህ] የ60ዎቹ ተረት ማርከሻ የተረተኞቹ ማምከኛ ሁኖ በክፉ ቀን የተገኘ የኢትዮጵያ መድኃኒት ስለሆነ በቀላ አይናችሁ አትዩብን” ዘራፍ
  ጊዜ ያለፈበት ነው። አቻምየለህ (ሥራ ፈት) የታሪክ ተመራማሪነት ሽታውም የለበትም ላልኩት ምላሽ እንደ መስጠት “ዘራፍ!” ምን ተደርጎ ትላለህ።
  ደግነቱ ሩቅ ሳትሄድ ተገለጥክ፣ “ዳውድ ኢብሳ(ኤርትርና ትግሬ)” ነው ስትል ሰው ሁሉ እንዳንተ መሃይም ይመስልሃል።
  “የኦሮሞ ነገድ እነዚህን እበላ ባይ ገለል አድርጎ የሚያዋጣውን ኢትዮጵያዊነት ቢይዝ መልካም ይሆናል።” ለኢትዮጵያዊነት ካንተና ከአቻምየለህ
  ፈቃድ ማግኘት ያስፈልጋል ነው የምትለው? ያማ ኢትዮጵያዊነትን ማዋረድ ነው።

 7. አለም ይገባኛል በአቻምየለህ ተጎድተሀል ለእንዳንተ አይነቱ ክፉ ሰው ነው። እንዳንተ መሳደቡ ይከብደኛል ስለ አቻምየለህ አላዋቂነት ካንተው ህዝቅኡል ጋቢሳ ካንተው አቤ ቶክቻና ከሌሎች ኢትዮጵያን ጋር የሰጠውን ምልልስ ሙግት ማዳመጥ ማንበብ ጥሩ ነው።
  በተርፈ ለእኔ ልኬና የእውቀት ምንጮቼ ጁዋር መሀመድ፣ህዝቅኤል ጋቢስ፣ነጋሶ ጊዳዳ፣ ተስፋዬ ገ/አብ፣ አስመሮም ለገሰ ናቸው ካልክም መብትህ ነው።
  የሰውን ፍላጎት መገደብ አለማቀፍ መብት ነው። ቆም ብለህ አስብ ማለት ይቻላል ወስኛለሁ ገደል ልግባ ካልክ መብትን አከብራለሁ ያንተ ገደል መግባት እኔንም የሚጨምረኝ ከሆነ ይህ ነገር አይሆንም ብዬ የመቃወም ተፈጥሯዊ ምላሽ መሰለኝ።
  በተረፈ አትጥፋ ሲመችህ ስደበን።

 8. ዐቻምየለህ ሲመቸው የሃረር ጦር የጎንደሬዎች ነው ይለናል። ሌላ ጊዜ በሌላ ክርክሩ ደግሞ ሃረርን ያስገበሩት ኦሮሞዎች ናቸው ይለናል! Typical Amhara hypocrite! For him 1+1 can be 3 or 4 if it serves him good! በኦሮሞ ጥላቻ ስለተለከፈ በየጊዜው የሚጽፋቸውን እንኳ አያገናዝብም!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.