ሰጎች (ሰዎች + በጎች)

በመስኪን መስከረም አበራ አስታዋሽነት ነው ወደፊት ያመጣነው። አሁን ይሄ ቤተ መንግስት ቢቀርብ ጓድ በቀለ ገርባ እረኛ እና ሰግ ብሎ ሰደበን ሊል ኖሯል?

ሰዎችም በጎችም ይመስሉኛል። ምንነታቸውን በውል ለመለየት ይከብዳል።

በቡድን ነው የሚኖሩት። በቡድንን ይንቀሳቀሳሉ። አንዳቸውን ከአንዳቸው ለመለየት ከባድ ነው። ብቻ እነሱ በምን ጥበብ እንደሚለያዩ እንጃ ተጣልተው እርስ በእርስ የሚወጋጉበት ጊዜ አለ።

ጠጋ ብዬ በአቅራቢያቸው ቆሞ የሚቃኛቸውን ጠየኩት።
«ምናቸው ነህ?»
«በበጎች ቋንቋ ስናወራ እረኛቸው ነኝ፤ በሰው ቋንቋ ስናወራ ደግሞ አክቲቪስታቸው ወይ መሪያቸው ልትለኝ ትችላለህ»

“አልገባኝም ሳያቸው ሰው ይመስላሉ፤ አኗኗራቸው እና ያንተም እንክብካቤ ግን እንደ በግ ነው። ምንድነው? ” አልኩት።
ፈገግ ብሎ መለሰልኝ፤

“በግ ለመሆን የተስማሙ ሰዎች ናቸው።”
እንዲያብራራልኝ ጠየኩት።
_
“አየህ የሰው ልጅ ሰው የመሆንንም፣ በግ የመሆንንም አቅም በውስጡ ይዟል። የሰው ልጅ ከምክንያት ወዲያ ወይም ወዲህ በመሻገር ይህ እጣውን ይወስናል። ጆርጅ ሳንታያና የተባለ የማድሪድ ተወላጅ የሆነ አሜሪካዊ ፈላስፋ ምን ይላል መሰለህ፣ ” Reason is ‘man’s imitation of divinity” ይላል። ከምክንያት ውጪ መሆን ደግሞ የሰው ልጅ ከበግ መምሰያ መንገዱ ነው።»
.
«…እኚህ ያየሃቸው ሰጎች ምክንያትን የጣሉ ናቸው። ያኔ ገና ንፁህ ሰው መሆን ሊያቆሙ ሲሉ እኔ እረኛቸው እንድሆን መርጠውኛል። አሁን ግን ወደ «ሰግነት» ስለተለወጡ፣ የተመረጠላቸውን እንጂ የመረጡትን አይኖሩም። ሰው መሆኑን በፍቃዳቸው ስለጣሉ ያን የማድረግ ህሊናዊ መብት የላቸውም»

“አንተ የነሱ እረኛ በመሆን ምን ትጠቀማለህ? ”

“የፈለኩትን አገኛለህ። አንደኛ ሰዋዊ የሆነ የበላይነት ስሜቴን አረካለሁ። ከዛ ባለፈ፣ ሰጎቹ የበግና የሰው ባህሪ ስላላቸው እንደ ሰው መስዋዕት ያቀርቡልኛል፣ እንደ በግ ደግሞ ራሳቸውን መስዋዕት ሆነው ይቀርቡልኛል።» በገዛ ንግግሩ የተደነቀ ይመስል ሳቀ!
_
“ከሰጎቹ መሃል ይህንን አውቆ የሚያምፅ የለም?”

“ይሄ የሚጠበቅ ነው። ግን አንዱን ባንዱ ላይ ታሰነሳበታለህ። ሰውነት ይቅደም ሲል ሰግነት ይለምልም ብለህ ታስጮህበታለህ። ሰግነቱን የካደ አቃቂረኛ ታስብለዋለህ። ታስወግዘዋለህ! የጥንት የተኩላዎች ስርዓት ሊያመጣባችሁ ነው አስብለህ ታስወግዘዋለህ…የሰግነት ደም ኖሮት ሰግነት የማይሰማው በማንነቱ የሚያፍር ነው ታስብልበታለህ። ሃሃሃ ሰግነት ብሎ ደም እኮ የለም። ትንሽ የሚበዛው ከውጪ ያለ ቅስቀሳ ነው እንጂ የውስጡ ቀላል ነው።»

«የውጪ ቅስቀሳው ሲበዛ አንተ ምን ታደርጋለህ?»

«እሱም ብዙ አይከብድም! የሰግነትን ውበት ደጋግሜ እነግራቸዋለሁ። ሰግነት አይበጃችሁም እያሉ ለምለም ሳራችሁን ሊነጥቋችሁ ነው እላቸዋለሁ። በጋዊ ባህሪ ስላላቸው ለግጦሽ መሬታቸ ሲሉ ባዕድ ያሉትን አሳደው ይወጉታል። ውጊያው ባስ ሲል ተዉ በቃ። በቂ ሳር አለ እኮ እያልኩ በድብቅ እስቃለሁ»

«ለህሊና አይከብድህም? »
.
“ስለለመድኩት አይከብድም። እንደውም ያዝናናኝ ጀምሯል። እኔ ብተው እንኳም ሌሎች የራሳቸው ሰጎች ያሏቸው አክትቪስቶች እና እረኞች አሉ። ሰጎችህ ሰው እንዳይሆኑብህ ዋናው መንገድ ከሌሎች እረኞች ሰጎች ጋር እንዲጣሉ ማድረግ ነው። ይበልጥ በተጣሉ ቁጥር አንተን እንደ አዳኝ ያዩሀል። ተጠቃን ብለው ስለሚያስቡ በሰግነት በረት ውስጥ ተጠጋግተው በአንድነት ይኖራሉ። ግጭቶቹን አንተ እና ማዶ ያለው እረኛ ለግላችሁ የመንፈስ ከፍታ እንደፈጠራችሁት አያውቁብህም!… “ብሎኝ ማዶ ላይ እርስ በእርስ የሚዋጉ ሰጎችን አሳየኝ።
.
«ይህንን በተለያዩ መንገዶች ማሳካት ቀላል ነው። ብዙዎቹን በቀለም አጣላቸዋለሁ። እገሌ የተባለው ሰግ ያሾፍብሃል ይንቅሃልም እላቸዋለሁ። በሰው ቋንቋ እየሰሙኝ በበግ አዕምሮ ይረዱኛል። እነሱ ደጅ ብጥብጥ፣ እኔ ሰፈር ሰላም ይወለዳል። ሌሎቹን ደግሞ በውል በማያውቁት ታሪክ አጣላቸዋለሁ። «ድሮ ያንተን ዘመዶች ወግቶብሃል» እለዋለሁ።በነገርህ ላይ መዋጋት የሰው ልጅ ሳይሆን የበግ ነው። የሰው ልጅ ግን “መዋጋት ” የሚለውን ቃል ለጦርነት ሲያውለው ታያለህ። ይህ እንግዲህ ልቡሰ ጥላው፣ በግ መሆኑን ስታውቅ ሰውን ለመግለፅ ከበጎች ድርጊት የወሰደችው ቃል ነው። ”
.
.
ቀጥሎ የምጠይቀው አልነበረኝም። መንገዴን ቀጠልኩ። ወዴት እንደምሄድ አላውቅም። የሰግነት ባህሪ ሊጋባብኝ ነው መሰል።ከሰጎች ባህሪ አንዱ ወዴት እንደሚሄዱ አለማወቅ ነው። ወዴት እንደምሄድ ለመወሰን ቆም አልኩ…

 

3 COMMENTS

 1. I think the so called herd political terminology used nowadays to describe the political discourse and activism of Oromo politicians and activists is interesting. I would not speculate on the cause but think that the writer and journalist Tesfaye Gebreab or the Gadaa who is also known as a specialist in Oromo psychology and mentality can have his own answers to it. I say this because I my self have come to know a lot about the Oromos from him.

 2. ሰዎችና በጎችን መለየት ካቃተህ ምን ያህል ጊዜ ሆነህ? የአእምሮ ሐኪም የሚባል አለ (የእንስሣ ሳይሆን)። እሱ ጋ ሰዎች እንዲወስዱህ ብትጠይቃቸው እርዳታ ልታገኝ ትችላለህ።

 3. ደሳለኝ
  ____\የመንጋ ፍርድ ውጤት/_____
  ተሳሳትሽ አትበለኝ የቱ ነው ስተቴ
  ጥበብ ነው ማርከሻ የብዕር ጥይቴ
  አዎ መንጋማ አለ ከጥንት መሰረቱ
  እየሱስን አስረው በርባንን ሲያስፈቱ
  ዛሬም በኔ ዘመን
  የመንጋ ፍርድ ነው ሀገሬን የፈታት
  አዋቂ ዝም ብሎ መንጋ እየፈተታት
  በድንጋይ በርሚል ውስጥ ሽ ድንጋይ ቢቀቀል
  ሽ ዘመን ተጥዶ እልፍ አመት አይበስል
  አገር ተረክቦ በሰፈረ የኮራ
  የመንጋ ፍርድ አይደል ያበቃን ለተራ
  የቱ ጋ ነው የሳትኩ አርመኝ መምህሩ
  ምላስክን አጥፈኽው ሞክር በብዕሩ
  ዘመን የሰጠው ቅል ድንጋይ ቢሰብር ጣሪያ
  ማዕዘን ተደርጎ አይሆን ለቤት መስሪያ
  ሰውነት ነው ልኩ የሰው ሚዛን ፍርዱ
  አዋቂ እንዲበይን መንጋዎች ይውረዱ
  አሁንም እላለው
  በመንጋ ተፈጭቶ በመንጋ ተጋግሮ
  እልፍ ጾም አዳሪ ወና ነው ጉረሮ
  ቤት መምታት ቤት መድፋት ስንኝ መቋጠሩ
  ጥበቡ ቢያቅተው
  ቤት እያፈረሰ ህዝብ እያስደደ
  አገሩን አመሰው
  እኔ ይሄንን ሰው
  ሌላ ምን ልበለው
  መንጋነትም ሲያንሰው
  በባዶነት ሙሌት በዘር እብሪት ታስሮ
  ከጥበብ ጓዳ ውስጥ ከሰውነት አጥሮ
  አበውን ሲያሰደድ ሲያርድ ሲያጎሳቁል
  አንተም መንጋ ካልሆንክ መቼም ሰው ነው አትል
  እና ምኑ ላይ ነው ብዕሬ የሳተች
  ብሔር የነቀፈች ህዝብን ያዋረደች
  “ንገረኝ በሞቴ የመንጋው ጠበቃ
  አንተም ሰው ሁንና መንጋነትህ ይብቃ”

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.