ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሸገር ሬዲዮ (ጠገናው ጎሹ)

የሬዲዮውን ቃለ ምልልስ  እኔም እንደ አንድ የአገሩን ጉዳይ እንደሚከታተል ኢትዮጵያዊ አዳመጥኩት  ።  እውቋና የማደንቃት ፀሐፊ መስከረም አበራ  የፃፈችውን አጭር አስተያየትም በጥሞና አነበብኩት ።

የእኔን እነሆ !

በጥሩ አገላለፅ ተገልጿል የምንለው የአስተዳደግና የቤተሰባዊ ግንኙነት ትረካው  መጨመሩ ካልሆነ በስተቀር የቃለ ምልልሱ አጠቃላይ ይዘት ከሥልጣን እርክክቡ ጀምሮ ከአንድ ዓመት በላይ ስንሰማው ከነበረው ለስሜት ቅርብ ከሆነ የህዝበኝነት (ተግባራዊ ይሆናል ወይ ሳይሆን ህዝብን ደስ ያሰኝልኛል ወይ ? )   ዲስኩር ጨርሶ የተለየ ሆኖ አላገኘሁትም ።  አዎ! የትህትና ቅላፄ ያለው መሆኑ እውነት ነው። የገሃዱ ዓለም ፖለቲካ ግን በትህትና ቅላፄና በሞራላዊ ዲስኩር ብቻ የሚቀመስ ፈተና አይደለም። መሥራት የሚችሉትን ተናግሮና አድርጎ በመገኘት ነው የገሃዱን ዓለም ፈተና መጋፈጥ የሚቻለው።

የቃለ መጠይቁ አቅራቢ የወ/ሮ መዓዛ ብሩ ጥያቄዎችም አንድ ዓመት ሙሉ አገርን ማረጋጋት የተሳነውን  መንግሥት መሪ ምን ያህል  የሚፈትኑ (challenging) እንደ ነበሩ በኩራት መመለስ የሚቻል አይመስለኝም ። ጥያቄዎችን በመሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው ምስቅልቅልና አስከፊ ሁኔታ አንፃር እያሰቡና እራስንም በነዚያ ሚሊዮን ንፁሃን ዜጎች መከራና ስቃይ ውስጥ እያስገቡ ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት የመጀመሪያው ረድፍ ላይ የሚገኘውን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ተጠየቅ! ከማለት ይልቅ ገብስ ገብሱን (ቀና ቀናውን) እየጠየቁ በጥሩ ቃላትና አንደበት በሚመለሱ መልሶች “ተአምረኛው ፖለቲከኛ”  በሚል አይነት አድናቆት አይንን አፍጥጦ ማዳመጥ የተዋጣለት ጋዜጠኝነት ነው  ማለት የሙያውን ሃያልነት ዝቅ ማድረግ ነው የሚሆነው።

የመስከረም አበራ አስተያየትም በተለመደው የጠቅላይ ሚኒስትሩ  የአቀራረብ ትህትና እና የቃላት አደራደር ወይም አንደበተ ርእቱነት የተማረከ በመሆኑ ደካማ ነው የሚል አስተያየት አለኝ ።

ልቀጥል

ለመሆኑ የአንዲት ደሃ አገር ባለሥልጣን እንደማነኛውም ኢትዮጵያዊ ህፃንና ወጣት ሆኘ ነው ያደግሁ ማለቱን   እንዴት በተለየ ሁኔታ  ሰው ሰው ሸተተኝ ወይም አልሸተተኝም የሚያሰኝ አድናቆትን ይፈጥርብናል ?

በአገር መሪነት  ወይም በሌላ ከፍተኛ ሥልጣን እርከን ላይ የምናገኛቸውን ፖለቲከኞች ትርክት በእንዲህ አይነት ሁኔታ የምናይበት ሥነ ልቦና ትክክል አይመስለኝም። መደብ ላይ ተኝቶ ያደገ ሰው በታሪክ አጋጣሚም ይሁን በግሉ ጥረት ወይም እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ   ከኢህአዴግ ወጥቶ ኢህአዴግን በማደስ  የመሪነትን ቦታ ሊይዝ መቻሉ ተአምር ነው እንዴ? ነው ወይስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ ብቻ የተሰጠ ልዩ ስጦታ ነው? ምነው እያደር አስተሳሰባችን ይኮሰምናል ?

“ጠቅላይ ሚኒስትር ስለሆንኩ የምሠራው ለሁሉም ነው።” ሲል አረጋገጠ አይነት አግራሞትን ወይም አድናቆትን ምን  ይሉታል ? አንድ ፖለቲከኛ  ከዚህ ሌላ ምን እንዲል ነበር (ነው) የተጠበቀው ወይም የምጠበቀው? አንገርምም?

 

“ሃገራቸውን እንደሚወዱ የገለፁበት ልቤን ነካኝ” የሚል  አይነት  ስሜታዊነትንስ ከገሃዱ ዓለም ወይም ከተግባር ሰውነታችን አንፃር ከምር ካላስተያየነው የት ያደርሰናል ?

” ነገ ጧት ሌላ ጥፋት ሊያጠፉ ይችላሉ  ፤ ኢትዮጵያን ከመውደድ ከፍታ እስከ አልወረዱ ድረስ ከነቃርሚያው ተስፋ እንዳደርግ ይረዳኛል ።” ምን ማለት ነው?  የተስፋ ቃርሚያስ ምን ማለት ነው? ያውም ለቃርሚያ ተስፋ ነው እንዴ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ ምልልስ ልብ ያላወሰ ?   ኢትዮጵያን የመውደድ ከፍታ መለኪያው ምንድንና የት ድረስ ነው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳን ከፍ የሚያደርግ በቅጡ እንድትቆይ የሚያደርግ ሃላፊነት እየተወጡ ነው እንዴ ? መቸነው ከፍ ብለው አገርን ከፍ ያደርጋሉ የምንለው? እየዳከሩ ያሉት እኮ   ኢትዮጵያን ዝቅ   በሚያደርጋት የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጥራ ፖለቲካ አዙሪት ውሰጥ ነው ። ለውጥ አመጣለሁ የሚሉን እኮ የመከራው ሁሉ ምንጭ የሆነው ህገ መንግሥት እና ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓተ ኢህአዴግን እያስቀጠሉ  ነው። ለውጥ የሚሉን እኮ እርሳቸውና በወንጀል የተዘፈቀው ገዥ ቡድናቸው የሚሉትን (የሚፈልጉትን)  እንጅ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚለውን (የሚፈልገውን) መሠረታዊ ለውጥ አይደለም።

የመጣንበትና የምንገኝበት አስከፊ ፈተና እኮ  በሞራልና “ልቤን አላወሰው” በሚል የምንወጣው አይደለም።

ገና ከለውጥ ብልጭታው ጀምሮ  “ስንወለድም ኢትዮጵያውያን ፥ ስንሞትም ኢትዮጵያውያን ፥ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው”  የሚል እፁብ ድንቅ አባባል ሲያስተጋቡ ከነበሩ ፖለቲከኞች  “አገራችን ስንውድ እስከ ነፍሳችን ነው” ቢሉ ምን አዲስ ነገር ሆነና ነው ልቤን ነካኝ የሚያሰኘን  ?

የፖለቲከኛን ፖለቲከዊ ሰብእናስ እውን በእንዲህ   አይነት ግልብ  “እንስፍስፍነት” ነው እንዴ የምንለካው?

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርንና የእኒህን ክፋት ወይም ደግነት  በዋናነት የምናነፃፅረው በየነበሩበት ወይም በያሉበት ወቅትና ተጨባጭ ሁኔታ እና  በድርጊት ካደረጉት ወይም ከሚያደርጉት ጋር   እንጅ  ልብ የሚበላ አንደበት ነበራቸው ወይም የላቸውም ከሚል ነው   እንዴ

“ኢትዮጵያን በተወሰኑ ዓመታት ካደጉ አገሮች ተርታ እናደርሳታለን” የሚለው ዲስኩር በተጨባጩ ሁኔታችን ላይ ሳይሆን ፖለቲካና ሥልጣን ወለድ (political and authoritative) የሆነ አገላለፅ ነው። እውነት ቢሆን እንዴት ሸጋ ነበር!

ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ያለምንም ተጨባጭና ትንሽ እንኳ እንዲመስል የሚያስመስል ጥናታዊ ዋቢ ሳይኖር እንዲህ አይነት ከስሜት የማያልፍ ተስፋ “ማብሰር” ቢያንስ ባለሙያን መናቅ ነው። መሃይሙ ወገኔስ በለውጥ ስም ሥልጣን ላይ የወጣ ሁሉ የህልም እንጀራ እየጋገረ ሲያስጎመዠው መኖሩን ተለማምዶታል ።አንድ ቀን በቃኝ እስኪል ድረስ ተተኪዎችም በዚያው መቀጠላቸውን እየነገሩን ነው ።

የኢህአዴግ ፖለቲከኞችን ” ተአምረኞችና ሙሴዎች” እያልን የተቀበልንበት መንገድ ወደ የት እየወሰደን እንደሆነ እያየን መሆኑ ትምህርት አልሆነን ብሎ አሁንም በሚዲያ የሚሰጡትን ድንቅ ዲስኩር ለምን? እንዴት? ከየት ወደየት? መቸ? ወዘተ ሳንል ተቀብለን እፁብ ድንቅ እንላለን ።  ክፉ አባዜ ! ለዚህ ነውና ከተዘፈቅንበት መውጣት ያቃተን አሁንም ልብ እያልን ከመራመድ ሌላ የተሻለ አማራጭ ከቶ የለንም። ልብ ይስጠን አልልም ። አሳመሮ ሰጥቶናልና። ሳይመሽብን ልብ እንድንል ግን ይርዳን እያልኩ አበቃሁ ! 

 

 

4 COMMENTS

  1. The herd mentality and behavior of some Oromo activists and elites have made it difficult for prime minister Abiy Ahmed to go ahead with his reformist politics. The herd mentality and behavior are also visible in the TPLF and their members and followers. I think the sources of the herd mentality and behavior is the wrong and misguided approach to group or ethnic rights. Humans should not act and behave like herds to defend and promote their group rights.

  2. ትክክል አልክ ወንድም ጠገናው፡፡ ጠቅላዮ እኮ ይችን ሀገር የሚመሯት በዙሪያቸው በሚውሉ ነበይ (ፓስተር) ነን በሚሉ ሀሳዊያን ራዕይ ለይ ተመርኩዘው ነው፡፡፡

  3. ትክክል አልክ ወንድም ጠገናው፡፡ ጠቅላዮ እኮ ይችን ሀገር የሚመሯት በዙሪያቸው በሚውሉ ነበይ (ፓስተር) ነን በሚሉ ሀሳዊያን ራዕይ ለይ ተመርኩዘው ነው፡፡፡

  4. አለቃ ጠገናው እኔም ግርም ያለኝ ነገር በእርግጥ በእሷ ነው የተጻፈው የሚል ጥርጣሬ ገብቶን ነበር ።እስከ አሁን ማስተባበያ ባለመስጠቷ የእሷ ጽሁፍ ነው ብለን በማሰብ የተጓዘችበት እርቀትና ያሞገሰችበት ልክ ሚዛኑን ስቷል እንላነል።
    ለነገሩ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም ቀደም ባለው ጊዜም እንዲሁ አንዳርጋቸው ጽጌን ከመላእክት ጎን አስቀምጣ ከአዋቂዎች በላይ አግዝፋ የላከችውንም ጽሁፍ ተመልክተናል በመሰረቱ በዛ ጽሁፍ እሱም ሳይገረም አልቀረም።
    አንዳርጋቸው ህወአት ሲደናበር ጣቱን ይዞ ተንኮልና አዲስ አበባን ያለማመደው የህወአት የክፉ ቀን ወዳጁ ነው ብሗላም ቀስተደመና ግንቦት ፯ የሚባል መላ የሌለው ቡድን መስርቻለሁ ብሎ በኢሳት አማካይነት እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆችን ያሸማቀቀ ትግሉ ወደፊት ሂዶ የትግሬ ፋሽስቶችን እንዴይጥል ደንቃራ የሆነ ግለሰብ ነው። አሁንም ኢዜማ የሚል ድርጅት መስርቶ እነ አንዱ አለም አራጌን ገልብጦ ብርሀኑ የተባለውን የእርሱን መንታ ያስቀመጠና የሌሎችን ሀሳብ ቀድሞ ሰርቆ የነገድ ድርጅትን ኮትኩቶብአሳድጎ አሁን ደግሞ ወቅት አይቶ የገበያውን መድመቅ ትመልክቶ የዜግነት ፖለቲካ ብሎ ብቅ ያለ ግለሰብ ነው a bad actorvis always a bad actor የሚለውን ብሂል ማስታወስም ይጠቅማል።
    ብዙ ጽፈሻል ይኽኛው አልተመቸንም ማለታችን ለእርምት ይረዳሻል የሚል ግምት አለን። በተረፈ በይሉኝታ ማለፍ ብዙ ጎድቶናል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.