ሜቴክ ከ108 ሚሊየን ብር በላይ ያወጣበትን የኢምፔሪያል ሆቴል ህንፃን እንዲለቅ ሊደረግ ነው

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከ108 ሚሊየን ብር በላይ ያወጣበትን ህንጻ ከ2 ወር በኋላ እንዲለቅ ሊደረግ መሆኑን ገለጸ።

በተለምዶ ኢምፔሪያል ሆቴል ተብሎ የሚጠራውን ህንጻ በሽያጭ ሂደቱ ወቅት 32 ሚሊየን ብር የገቢዎች ክፍያ ባለመፈጸሙ ነው ሜቴክ ህንጻውን እንዲለቅ እግድ የወጣበት።

በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ የሚገኘውና በተለምዶ ኢምፔሪያል ሆቴል ተብሎ የሚጠራው ህንጻ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከዓመታት በፊት ከገዛቸው ህንጻዎች ውስጥ ተጠቃሹ ነው።

ሜቴክ ህንጻውን ከገዛ በኋላ ባለቤት መሆን የሚችልበት የህግ ሂደትን ያላጠናቀቀ ቢሆንም፤ ከግዢው በኋላ አሁን ድረስ ተቋሙ ህንጻውን በቢሮነት እየተጠቀመበት ይገኛል።

ሆኖም ግን ሜቴክ የህንፃውን ግዢ ከፍያ ከፈጸመ በኋላ የስም ማዞር ሂደቱን ማስኬድ ያልተቻለ ሲሆን፥ ምክንያቱ ደግሞ ህንፃውን ለሜቴክ የሸጠው አካል ቀድሞ ግዢውን ከፈፀመው የህንጻው ባለመብት ስም አዙሮ ስላልጨረሰ ነው።

የዚህ ምክኒያት ተብሎ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከሜቴክ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፥ ከቀድሞ የህንፃው ከባለቤት ገዝቶ ለሜቴክ የሸጠው ተቋም ቀድሞውኑ 20 ሚሊየን ብር ብቻ ነው የከፈለው።

በዚህ ምክኒያት ስሙን አዙሮ ባለቤት መሆን ስላልቻለ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከዚህ በኋላ የራሱን አማራጭ የወሰደ ቢሆንም፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን የገቢዎች ሚኒስቴር በግዢና ሸሽያጭ ወቅት ሊያገኝ የሚገባው ገቢ አላገኘም።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የገቢዎች ሚኒስቴር ከመጀመሪያው ሽያጭ ሊከፈለው የሚገባውን 12 ሚሊየን ብር ጨምሮ በድምሩ ከ32 ሚሊየን ብር በላይ አልሰበሰበም።

ገቢዎች ሚኒስቴር አሁን ላይ በኦዲት የተደረሰበትን ክፍያ የህንጻው ባለቤት ወይም ገዢው አካል እንዲከፍለው ቢጠይቅም ከፋይ አልተገኘም።

የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ፥ በሽያጭ ወቅቱ መረጃ ማግኘት ስለማይቻል ሚኒስቴሩ ገንዘቡን መጠየቅ የሚችለው አሁን ላይ የህንፃው ባለቤት የሆነውን አካል ነው ብለዋል።

ሜቴክ በበኩሉ ክፍያውን ፈጽሜ ህንጻውን ወደራሴ የማዞርበት ሂደትን ጀምሬ ቲን ነበሩ በባለ ይዞታው በመሆኑ አልቻልኩም ብሏል።

ባለመብት የተባሉትን አካል በዚህ የዜና ዘገባ ላይ ሀሳባቸውን እንዲያካፍሉን ጠይቀን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ መስጠት እንደማይፈልጉ ምላሻቸውን ሰጥተውናል።

በዚህ ሂደት ውስጥ የሚገኘው የኢምፔሪያል ሆቴል ህንጻን ከገቢዎች ሚኒስቴር ለሜቴክ እንዲለቅ የሚል ደብዳቤ እንደደረሰው አስረድቷል።

የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል አህመድ ሀምዛ፥ ሜቴክ በዚህ ህንጻ ላይ ከ108 ሚሊየን ብር በላይ እንዳወጣበት በመግለጽ፤ የገቢዎችን ክፍያ ፈጽሞ ህንጻውን በራሱ ስም ለማድረግ ደግሞ ከባለቤቱ ከ100 ሚሊየን ብር መጠየቁን አንስተዋል።

ሜተዬክ ይህን ማድረግ ስለማይችል ህንጻውን ለመቀቅ እንደገተደድም ነው የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል አህመድ ሀምዛ ያስታወቁት።

በቅርብ በወጣው መረጃ የገቢዎች ድርሻ ከነበረው 32 ሚሊየን ብር በጊዜ ገደብ ማለፍ ምክኒያት 150 በመቶ ወለድን ጨምሯል።

ህንጻው በግዚና ሽያጭ ሂደት ውስጥ አጠቃላይ ወጪው 200 ሚሊየን ብር መድረሱን ነው ድምር ውጤቱ የሚያሳየው።

የገቢዎች ሚኒስትር ደኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ፥ ገቢዎች ሚኒስቴር ገንዘቡን ህጉን ተከትሎ እንደሚሰበስብ ገልፀዋል።

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ በበኩሉ ከሁለት ወር በኋላ ህንጻውን ለገቢዎች ሚኒስቴር አስረክባለሁ ብሏል።

ብርጋዴር ጄነራል አህመድ ሀምዛ፥ ሜቴክ ህንፃውን እንዲለቅ ከሀምሌ የአራት ወር ጊዜ እንደተሰጠው አስታውቀው፤ ጥቅምት ላይ ህንፃውን ለገቢዎች ሚኒስቴር ያስረክባል ብለዋል።

ሜቴክም ህንጻውን ቢለቅም 37 ሚሊየን ብር ለእድሳት፣68 ሚሊየን ብር ለግዢ ያውጣውን ገንዘብ በህግ እጠይቃለሁ ብሏል።

በሀይለኢየሱስ ስዩም/ ኤፍ.ቢ.ሲ

1 COMMENT

  1. በሌብነት የተሰበሰበ ገንዘብ ከሾለከ በሗላ ልንሰበሰብ ነው እያላችሁን ነው? እስቲ ይሁና እንዲህ ያለ ቀልድ። ለማንኛውም ተረኛ ሌቦች ትምህርት ውሰዱ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.