ይድረስ ለእግዚአብሔር ልጆች (መ/ር አበባው አሰፋ)

ይድረስ ለእግዚአብሔር ልጆች (A Message to the children of God)
ከሐዋርያው ቅዱስ አርዮስ (መ/ር አበባው አሰፋ) መስከረም 2012 ዓ.ም

ከገጽ 14-26 እንደሚከተለው ይቀርባል። ለማንኛውም አስተያየት- abebawacc3368@gmail.com

Tadesse Abebaw Assefa
Ph.D. in Physics

ይህ መጽሐፍ ለማን ተፃፈ?
I am against religion because it teaches us to be satisfied with not understanding the world. —Richard Dawkins
ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በዋናነት ለአማኞች ነው፡፡ በተጨማሪም ኢ-አማኞች፣ ያልወሰኑ ሰዎች፣ ተማሪዎች እና ተመራማሪዎችም ሊጠቀሙበት ይችላሉ።

1ኛ. አማኞች፡-መጽሃፉ ለሁሉም አማኞች የተዘጋጀ ቢሆንም በተለይ ግን ቀጥሎ ለተዘረዘሩት እንዲደርስ እፈልጋለሁ።

  1. ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ ለካቶሊክ፣ ለፕሮቴስታንትና ለሙስሊም ሊቃውንት
  2. ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ አጥማቂዎች እና ለፕሮቴስታንት ነብያት፣ ሀዋርያትና ቴሌቫንጋሊስቶች
  3. ለዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣ መ/ር ዘበነ ለማ፣ ለመ/ር ሮዳስና ለመጋቤ ሃዲስ እሸቱ አለማየሁ
  4. ለንቡረ ዕድ ኤርሚያስ ከበደና ለተክለ ኪዳን
  5. ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምርያ ማህበረ ቅዱሳን
  6. ታሪክን በተለይ የኢትዮጵያን ታሪክ በመስኮትተምረው ለሚሰብኩን ሙህራን

አማኞች ሆይ እንደ አማኝ ከመፅሀፉ ሀሳቦች ከአብዛኛዎቹ ጋር አትስማሙም ይሆናል ሲጀምር ስለኢ-አማኛን አመለካከቶች እንድታውቁ እንጅ እንድትስማሙ አልጠብቅም፡፡ ይህንን መጽሐፍ ማንበቡ ኢ-አማኞች ምን እንደሚያምኑ፣እንዴት እንደሚኖሩ እና ስለ ተፈጥሮ ያላቸውን ግንዛቤ ምን እንደሚመስል እንድትመለከቱ ያስችላችኃል፡፡ እነዚህ ሰዎች የእናንተን እምነቶች እንዴት እንደሚጠራጠሩ ትረዳላችሁ፡፡ ስለእምነታችሁ ለመሟገት እቅድ ካላችሁ ይህ መጽሐፍ የተቃዋሚዎች ያለማመን ምክንያቱን በመረዳት ምክንያታዊ ክርክር እንድታደርጉ ሊረዳችሁ ይችላል፡፡ ስለ አምላክ እና ስለ ሃይማኖት በጠንካራ ማስረጃዎች ላይ የተመሰረተ ፍሬያማ ውይይት ማድረግ ትችላላችሁ፡፡

የሂስ መፅሀፍ እንደመሆኑ እምነታችሁን እስከቻልኩት ድረስ ለመተቸት ሞክሬአለሁ ከጥቂት ሙገሳ ጋር፡፡ ለምን ወደ ትችቱ አደላህ ብትሉ ሀይማኖታችሁ በእየ ቀኑ ሳይወደስ አይዉልም የጎደለው ሊያስተካክል የሚችል ትችት ነው፡፡ መፅሀፉን አንባችሁ ልማርበት የሚችል የማስተባበያ ፅሁፍ እንደምትልኩልኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ወገኖቸ ብትችሉ ውደዱኝ ፍቅር ነው የራበኝ፣ ባትችሉ ግንሽህ ጊዜ ጻፉብኝ፣ አምራችሁ እርገሙኝ፣ አስደግሙብኝ፣ እንደሰይጣን ጥሉኝ፣ ስደቡኝ፣ መሳለቂያ አድርጉኝ ይህ ሁሉ ለኔ ፀጋ ነው። ነገር ግን ድንጋይ ለመወርወር፣ ቡጢ ለመሰንዘር፣ ለማሰር እና ለማሳደድ ለምታስቡበምታምኑት አምላክ፣ በምትወዷት ሀገር በተለይም በወላጅ እናታችሁ ልለምናችሁ ተውኝ። ይህን የምላችሁ ስለምፈራ ብቻ አይደለም የተለየ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች በህዝብ ፊት ሲደበደቡ፣ ሲሰቀሉ፣ ሲዘረፉ፣ ሲታሰሩ እና ሲሳደዱ ስላየሁ ነው። እኔም ብዙ ጊዜ <ሰው የሚያስብ ፍጡር ነው> የሚለውን እስክጠራጠር ድረስ በአሳዳጆቸ ቀለበት ውስጥ ገብቸ አውቃለሁ።  አንዳንዴ ስንተኛው ክፍለ ዘመን እንዳለን ግራ ይገባኛል። በኦሪት ዘመን ይሆን እላለሁ። ስንተኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነን እባካችሁ???

ብዙ እቅድ አለብኝ ብዙ መመራመር፣ ብዙ መፈላሰፍ፣ ብዙ መጎብኘት፣ ብዙ ማንበብ እና መጻፍ፣ ብዙ መማር እና ማስተማር አለብኝ። እንዴ! የአፍሪካን መዲና አዲስ አበባን፣ ውቧ ባህር ዳርን፣ ንግስቷ ጎንደርን፣ ጥንታዊቷ አክሱምን፣ ባለድሏ አድዋን፣ ድንቋ ላሊበላን፣ ሞቃቷ አፋርን፣ ጠበብቷ ሀረርን፣ ስብጥር ደቡብን፣ አርባምንጭ ሀዋሳን፣ የገዳ ስርአትን ሌሎች ሌሎችንም የማየት ህልም አለኝ። ኢትዮጵያ እኮ የሚስጢር መፅሃፍ (መጽሃፈ ሚስጢር) ናት። እንዴ! በማይክሮስኮፕ ህዋሳትን ሳላይ፣ በቴሌስኮፕ ህዋውን ሳላየው፣ በጥንት ግሪኮች የተተከለውን የእውቀት ዛፍ ፍሬን ሳልበላው ማለፍ አልፈልግም። ብዙ ያላነበብኩት መፅሃፍ፣ ያላሳትምኩት ረቂቅ ጹህፍ፣ ያላጣጣምኩት ሙዚቃ፣ ያልጎበኘሁት ቦታ፣ ማየት የሚገባይ ያላየሁት አለም አለ። ይህን ሁሉ ከምትለማማጥ ለምን አርፈህ አትቀመጥም ልትሉኝ ትችላላችሁ እኔ ግን ከአባቶቼ አልበልጥም እላችኋለሁ፣ ድግሜም ህልም ፈርቸ ሳልተኛ አላድርም እላችኋለሁ። ለማንኛውም የሰለጠነ ሰው ይግጠምህ፣ የተማረ ይግደልህ በሉኝ።

እንደ ተወዳጁ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት የሰለጠኑት አማኞች የእኔን መሰሎችን ሃሳብ እንደ መልካም ተግዳሮት እና ግብዐት ይጠቀሙባታል። ያም ብቻ ሳይሆን አማኞች ልበ ሙሉ እንዲሆኑ ያስተምራሉ፣ ምሳሌ ይሆናሉ። ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በዕውቀቱ ስዩም ‘እግር አልባ ባለ ክንፍ’ ብሎ ለጻፈው ‘እግር ያለው ባለ ክንፍ’ ሲል የመልስ ምት በሰጠበት የዳንኤል ክብረት ዕይታዎች ከተሰኘው ድረ ገጹ እንዲህ ያስደምመናል፦“ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍቷን በቀኖና እንድትወስን፣ ሥርዓቷን እንድትወስን፣ የሃይማኖት መግለጫዋን ወስና እንድታወጣ፣ ሕግ እና ደንብ እንድትሠራ፣ መጻሕፍትን እንድትጽፍ፣ ያደረጓት ተግዳሮቶች በየዘመናቱ መኖራቸው ነው፡፡ ሄሊቪዲየስ ተነሥቶ በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የተለየ ትምህርት ባያመጣ ኖሮ አባ ጄሮም እና አባ ኤጲፋንዮስ የጻፏቸውን መጻሕፍት ባላገኘን ነበር፡፡”ይላል ምሳሌውን ይቀጥልና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ክብር የሚሰጣቸው አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ስላደረጉት ነገር ይነግረናል። “ቴዎድሮስ የተባለ የጦር አዛዥ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫን ስለ ሃይማኖት ባይገዳደረው ኖሮ አስደናቂውን ርቱዐ ሃይማኖት የተሰኘ መጽሐፍ ባላገኘን ነበር፡፡ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዜና መዋዕል እንደሚነግረንም በንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በሃይማኖት ምክንያት ክርክር ሆነ፡፡ አባ ጊዮርጊስም ከአንድ ፈረንጅ ጋር ተከራክሮ ረታው፡፡ መጽሐፈ ምሥጢርንም ደረሰ።” ዲ/ን ዳንኤል ክብረት የምናምነውን የማያምኑ መኖራቸው እምነታችንን እንደሚያጠነክሩልን ሲግልፅ እንዲህ ይላል፦ “መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬ (የሞተ ልጃቸውን በጸሎት ያስነሱ ብርቱ አማኝም ነበሩ ይባላል) ያንን የመሰለ ኮኩሐ ሃይማኖት የተሰኘ መጽሐፍ እንዲጽፉ ምክንያት የሆናቸው አባ አየለ ተክለ ሃይማኖት የሚባል ካቶሊካዊ ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጻፈው ጽሑፍ ነው፡፡ እነ አስረስ የኔሰው ያንን የመሰለ ትቤ አኩስም መኑ አንተ የተሰኘ የታሪክ፣ የእምነት፣ የቅርስ እና የሥነ ልሳን መጽሐፍ የጻፉት በወቅቱ ለተነሡት የታሪክ፣ የቋንቋ እና የእምነት ተግዳሮቶች መልስ ለመስጠት ነው፡፡”(በቅንፉ የተጨመረውን ያገኘሁት ከካሳሁን አለሙ ተጠየቅ ድህረ ገጽ ነው)

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ‘እግር አልባ ባለ ክንፍ’ ሳይሆኑ ‘ክንፍ ያለው ባለ እግር’ መሆናቸውን ለማስረዳት ታሪክን እና እምነትን መሰረት አድርጎ አብራርቶ መልሶታል፣ በአንድ ወር ደሞወዝ የሚገዛ ዳጎስ ያለ መፅሃፍም ለአቡኑ ጽፎላቸዋል። (በነገራችን ላይ እኒህ አወዛጋቢ ቅዱስ ሰይጣንን ወንጌል ሰብከው ገርዘው ስሙን ክርስቶስ ሀረዮ በማለት ሰይመውና አመንኩሰው በዘመኑ ሁሉ መነኮሳቱን በቅንነት አገልግሎ ሲሞት መንግስተ ሰማይያት እንዳስገቡት በገድላቸው ይተርካል። ይገርማል!) ዳንኤል ወቅታው እይታወቹን በሚዳስስበት ድህረ ገጹም የበዕውቀቱን ጥርጣሬ እንደጠቀሳቸው አባቶቹ በግብዐትነት ተጠቅሞበታል።ከዳንኤል ክብረት ጋር የማያግባቡን ብዙ ልዩነቶች ቢኖሩኝም እንደሱ የማደንቀው አማኝ ፈልጌ አጥቻለሁ። እንደ ብዞዎቹ ተቆርቋሪ ነን ባዮች ማጥላላት አይታይበትም፣ ጠላቴ ከማለት ይልቅ ወንድሜ ማለትን አስቀድሟል። ብዙዎች ግን አይነኬ ሀይማኖታቸውን በዕውቀቱ ስዩም ስለነካባቸው አይናቸው ቀልቷል፣ እስከ መደባደብም የደረሱ አሉ።እነዚህ የሂትለር ርዝራዦች ለቡጣ ቡጢ እንጅ ለውይይት ስላልታደሉ ያስፈራሉ፣ ያሳፍራሉም።

የተማሩት የተመራመሩት እነዲ/ን ዳንኤል ክብረት ግን የሰጡን የመጻፍ ነጻነት ብቻ ሳይሆን በመሃይሞች ለሚደርስብን ጥቃት ጥብቅና እስከመቆም ነው። በምንም መንገድ ይላል ዲ/ን ዳንኤል ክብረት “በምንም መንገድ ይሁን በምንም እንደ በዕውቀቱ ያሉ ጸሐፍት የመጻፍ ነጻነታቸው መከበር አለበት፡፡ ጥያቄ ያለው ወይንም በሃሳባቸው የማይስማማ ሰው እስከ ሕግ አግባብ ድረስ በመሄድ ጤናማውን እና የሠለጠነውን መንገድ ተከትሎ መሞገት ይቻላል፡፡ አንድ ጸሐፊ በመጻፉ ምክንያት ብቻ አካላዊም፣ ሃሳባዊም ጥቃት እንዳይደርስበት የምንከላከለው በሚጽፈው ሃሳብ ስለምንስማማ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ለማንስማማበትም ሃሳብ ነጻነት መሟገት አለብን፡፡ ሃሳቡን እየተከራከርነውም፤ መብታችን ተደፍሯል ብለን በፍርድ ቤት እየከሰስነውም ቢሆን ለሃሳብ ነጻነቱ ግን መሟገት ግድ ይለናል፡፡እናም በዕወቀቱ ይጻፍ፣ የማልስማማበትንም ነገር ይጻፍ፣ እኔም የምስማማበትን እይዛለሁ፣ የማልስማማበትን እሞግታለሁ፡፡ ለበዕውቀቱ የመጻፍ ነጻነት ግን ጥብቅና እቆማሁ፡፡” (የዳንኤል ክብረት ዕይታዎች ድህረ ገጽ)

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ይህን ተስፋ ሰጭ ፅሁፍ በመጻፉ እኔን ጨምሮ ብዙ አድናቂዎቹ ቢደሰቱም አንዳንዶቹ የዘራፍ ዘመን አስተሳሰብ አራማጆች ግን ከበዉቀቱ ይልቅ ዳንኤል ያናደዳቸው ይመስላል። እነዚህን ሰዎች ለማስደሰት ሲል ዳንኤል በዕውቀቱን መሳደብ ነበረበት፣ መናፍቅ ምናምን ማለት ነበረበት ግን አላደረግውም ይልቅስ በዕውቀቱ ሥዩም ነገሮችን በአዲስ መልክ ከሚያዩ ጥቂት የሀገራችን ጸሐፍት አንዱ ነው ሲል አወደሰው፡፡ ገና ብዙ ሥራ የሚጠበቅበት ወጣት ጸሐፊም እና ሕይወቱን ለጽሑፍ የቀየደ ሰውም ነው በማለት የቤት ስራ ሲሰጠው ይታያል። መታደል ካመኑም ከተማሩም እንዲህ ነው። ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በርታ ተበራታ እላለሁ፣ ምን አለ ያለ ስጋት በነጻነት የምንኖርበት ዘመን በሆነልን ወይም ቢያንስ ሲናገሩ እንጅ ሲናገሯቸው የማይወዱ ባይኖሩ።

በስጋቴ ዙርያ አንድ ኤቲስት የማህበራዊ ሚድያ ጓደኛየ በሚድያው ገጽ ያሰፈረውን ላካፍላችሁ እኔም እጅግ በጣም እስማማበታለሁ።

‘‘የምፅፈዉ እኔ የተሰማኝን እንጅ እናንተ የተሰማችሁን አይደለም። የተሰማችሁን ፅፌዉ ካገኛችሁ መልካም ነዉ። ካልፃፍኩትም አትበሳጩ። ምክንያቱም እኔ እናንተ አይደለሁም። ሰወች ይጠሉኛል ብየ የማምንበትን ነገር ከመፃፍ ወደ ኋላ አልልም። ሰወች እንዲወዱኝ ብየም የማላምንበትን ነገር አልፅፍም። ስለዚ እኔ እንድትወዱኝም ሆነ እንድትጠሉኝ ሆን ብየ የምፅፈዉ ነገር አይኖርም። እኔ የምፅፈዉ የራሴን ሀሳቦች ነዉ። ሀሳቦቸ ሁሌም ትክክል ሊሆኑ አይችሉም፣ የተሳሳተ ሀሳብ ልፅፍም እችላለሁ። እኔ ለእናንተ አስቤ አልፅፍም እናንተም ለኔ ብላችሁ አታነቡም። ስለዚ እኔም የተመቸኝን የመፃፍ እናንተም የተመቻችሁን አብባችሁ ያልተመቻችሁን የማለፍ መብት አላችሁ። የናንተና የኔ ግንኙነት የሻጭና የገዥ ግንኙነት ነዉ። ሻጩም እቃዉን የሚሸጠዉ ለገዡ አስቦ አይደለም። ገዡም እቃዉን የሚገዛዉ ለሻጩ አስቦ አይደለም። በመሀል ግን ሁለቱም ተጠቃሚ ይሆናሉ።’’<ከማመን መጠራጠር ይሻላል>

በጣም የሚገርመኝ አይቶ ማለፍ፣ ማስተባበል፣ አለማንበብ፣ አለመግዛት፣ ዲሌት፣ አንፍሬንድ፣ ብሎክ እና የማሳሰሉት የማንፈልጋቸውን የመከልከያ መንገዶች እያሉን ይህ ሚድያ ይዘጋ፣ ያ መጽሀፍ ይቃጠል ወዘተ እያልን መንግስትን የምንወተውት አለን። ወገኖች እናንተ ስለ ሌላ ሰው እያወራችሁ ስለእናንተ የሚያወራውን አትከልክሉት። ከኢ-አማኒ ወደአማኒ የሚሰነዘር ማንኛውም ሃይማኖት ነክ ጉንተላ ምክንያታዊ አይደለም የምትሉ እናንተ ስለ ኢ-አማኝ በህዝብ ሚድያ ሳይቀር ስትደነፉ ቅር አይላችሁም? ተስፋ አደርጋለሁ እናንተ የሰው ስጋ ካልበላችሁ የእናንተን ስጋ የሚበላ የለም። መውገር ያለበት ንጹህ የሆነ ብቻ ነው። ማን ነው ንጽህና እውነተኛ ማንም የለም። ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ደረጃ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ረቂቅ ሕገ ቤተክርስቲያን፣ አንቀጽ 3 ቁጥር 7-8 “ቤተክርስቲያን ያሏትን ጥንታውያት መጻሕፍት እየተረጎመችና እያሳተመች ለምእመናን አገልግሎት የማዋልና የማሰራጨት እንዲሁም የጥናትና የምርምር ተቋማትን የማቋቋም መብት አላት። ቤተክርስቲያን ማሠልጠኛዎችንና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶችን የማቋቋም፤ ለተቋቋሙትም እስከ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ዕውቅና የመስጠት፤ በትምህርት ቤቶቿም አማካይነት ሃይማኖቷንና ቀኖናዋን የማስተማርና የማስፋፋት፤ በየገዳማቱና በየአድባራቱ የሚገኙትን ጥንታውያን የአብነት ትምህርት ቤቶች የማጠናከርና ከየትምህርት ቤቱ ለሚመረቁ መምህራንና ደቀመዛሙርት የሙያ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የመስጠት መብት አላት. . .”  እያለች ከኔ ውጭ ወደ ውጭ የምትል ከሆነና ልጆቿን አብሮ መኖርን እንዲላመዱና ልበ ሙሉ የማታደርግ ከሆነ እኛስ የት ሂደን ሀሳብችንን እናሰማ።

ቀና አስተሳሰብ ያላችሁ ውድ አማኞች ክህደቴን በማሰብ እኔ ስለምቃጠልበት ሲኦል አንዳች እንዳታስቡ በወላጆቸ በኩል ከ10 ትወልድ በላይ ዋስትና ተሰጥቶኛል። ከፈለጋችሁ ከእልፍ ቅዱሳን ውስጥ ለአንዱ ቅዱስ አገልጋይ ክርስቶስ የገባለትን ቃል ኪዳን አንቡ፡፡ ለነገሩ በወላጆቸም በኩል ብቻም ሳይሆን እኔ እራሴ ከበላየ ሰብ የተሻለ በብዙ ቅዱሳን ስም እመፀውታለሁ በተለይ በድንግል ማርያም ስም፣ ገዳማት እጎበኛለሁ፣ በክበረ ብአላት ቤተ ክርስቲያን እሳለማለሁ ወዘተ፡፡ይህም እንኳ ባይሆን ቅዱሳን ሲኦልን ሲበረብሩ በክንፋቸው ተጥልየ ገነት እገባለሁ። ስለዚህ ጌታ እኔን በተመለከተ ልዩ የህግ ማስተካከያ እስካላደረገ ድረስ ከእናንተ ጋር መንግስቱን እወርሳለሁ አትጠራጠሩ፡፡ ለማንኛውም የሚያደርገውን አያውቅምና ሀዋርያው ቅዱስ አርዮስን ማረው እያላችሁ አንቡት፡፡

2ኛ. ኢ-አማኞች፡-ይህ መጽሐፍ አምላክ የለሾቹ እራሳችሁን በደንብ እንድትገልጹ ይረዳችኃል፡፡ በእርግጥ ማስረጃን ማቅረብ ያለበት ፈጣሪ አለ የሚሉት ናቸው፡፡ እግዚአብሄርን በተመለከት አማኞች መኖሩን ማረጋገጥ ካልቻሉ ለእናንተ በቂ ነው፡፡ ግን ከዚህም አልፎ አለመኖሩን ማስረዳት ባይጠበቀባችሁም ለውይይት ሲባል ከመፅሀፋቸው እና ከተፈጠሮ እያመሳከራቸሁ ላመናችሁበት እውነት ተጨማሪ ዘዴዎችን ማወቅ ይኖርባችኃል፡፡ የዚህን መፅሀፍ ክርክሮች በመረዳት እና ሌሎች እንዴት እንደሚረዱ በመመልከት ሎጂካዊ በሆነ መንገድ ውይይቶች እንድታደርጉ ሊያግዛችሁ ይችላል፡፡ከአማኞች ወይም ከህሊናችሁ ጋር ለመከራከር በመጀመርያ እግዚአብሄር ሊኖር ይችላል ብላችሁ ተነሱ፡፡ ቀጥሎ መመራመር ይቻላል፡፡ ሲጀመር አለ ወይም የለም ብላችሁ ከዘጋችሁት ግን መመራመር፣ መፈላሰፍ አያሰፈልግም፡፡

እኔ አርዮስ በዚህ መጽሐፍ የእኔና የሌሎች ኤቲስቶችን ተፈጥሮአዊ አረዳድ ለሃይማኖታዊ ክርክር በሚያስኬድ እና የሀሳብ ለውውጥን በሚያመጣ መልኩ ለመማዘጋጀት ሞክሬየለሁ፡፡ የእኔን አሰተሳሰብ ወደ ለየለት ሂሰኛ ያደረሱኝይህን መሰለ መፅሀፍት እና የኢንተርኔት መጣጥፎችናቸው፡፡ “The Internet is the modern-day World Book Encyclopedia. Everyone should have access to the Internet in their home, school, or public library” የሚለውን የአክቲቪስት Margaret Downey ምክር የተገበርኩት ይመስለኛል። ብዙ ደፋር ኤቲስቶች ህይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል ለምክንያታዊነት እየታገሉ ይገኛል፡፡ ተግሉም ህንፃ በማፈራረስ፣ በማሸበር፣ እና ነፃ አስተሳሰብን በመንፈግ አይደለም፡፡ ይልቁንስ አማኞች አይተው የሚፈሩት የእውነትን ማጅክ የሚያስረዱ መፅሀፈትን በመፃፍ እና ጹሁፎችን በእንተርኔት በማሰራጨት አንጅ፡፡ በግሌ የግሪክ ፍላስፎች፣ የአበው ሊቃውንት፣ የማርክስ፣ የፍሬድሪክ ኒቸ፣ (የአርዮስ?፣ የንስጥሮስ?፣ የሉተር?፣)የዘረዐ ያዕቆብ፣ የወልድ ህይወት፣ የዙምራ፣ (የበውቀቱ ስዩም፣ የዋለልኝ እምሩ፣ የብሩህ አለምነህ፣ የሃይለ ጊዮርጊስ ማሞ፣ የወርቁ ፈቀደ፣ የደረጀ ፀጋዬ) የኦሾ፣ የክሪስቶፈር ሂችን፣ የሳም ሃሪስ፣ የሪቻርድ ዶውኪንስ፣ የካርል ሳጋን፣ የማርሻል ብሬን፣የአያና አርሲ አሊ፣ የማይክል ሸርመር፣ የዳርዊን፣ የፍሮይድ፣ የጋሊሊዮ፣ የአንስታየን፣ የሀውክንግ ኧረ ስንቱን ሙህር ልጥራበቃ የነዚህ እና የሌሎች የሳይንስ እና የምክንያታዊነት አቀንቃኞችአደናቂ ነኝ፡፡ሞት ይርሳይ በፍቃዱ ሃይሉን ረሳሁት ምን ነበር ያለው፦ “የዓለም ሕዝቦች የቀለም እውቀት እና ከተሜነት እየተስፋፋ እና እየተመነደገ እየመጣ እንደመሆኑ መጠን፣ ከጥቂት መቶ ዓመታት በኋላ፣ አሁን ኢ-አማኒነት እብድነት እንደሆነው ሁሉ አማኒነት እብድነት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡”

አንተ ኢ-አማኝ ከሆንክ በቻልከው መጠን የቱንም መፅሀፍ ማንም ይፃፈው መቸም ይፃፍ ያለፍርሃት አንብብ እውነትን ካገኘህበት ተቀበል ካልመሰለህ ተወዉ፡፡ ብዙ ሰወች ከራሳቸው እምነት ውጭ ማንበብ ይፈራሉ፡፡ የሚገርመው እነዚ ሰወች የራሳቸውን ቀኖና እንኳ ቄሶቹ እንዲያውቁት እንጅ እነሱ እንዲገባቸው አይፈልጉም፡፡ ከተኙበት የሰመመን እቅልፍ ለመንቃት አያስቡም፣ ቀስቃሽም አይሹም፡፡ በአጭሩ ይህን መፅሀፍ በጃቸው ከነኩት ሰይጣን የሚያዛቸው የሚመስላቸው፣በመንጋ አስተሳሰብ የሚነዱ፣ ከእዉቀት ዛፍ እንዳይበሉ የተከለከሉ፣ ለራሳቸው ሀላፊነት የማይወስዱና ከጦር ይልቅ አስተሳሰብ የሚያስፈራቸው ናቸው፡፡ ስለ እምነታቸው እንዲሁም ስለ ፍልስፍን እና ሳይንስን ላለማወቅ ራሳቸውን ከጥበብ ያወሩ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ህይወታቸውን በአደራ ያስቀመጡ አስከሬኖች ናቸው፡፡ አስከሬን የት እንደተነሳ፣ በዙርያው ምን እየተፈፀመ እነደሆነ እና የት እነደሚሄድ አያውቅም፡፡ ሰው የትላንት ማንነቱን፣ የዛሬ ውሎ እና አዳሩን፣ እና የነገ ተስፋውን ከራሱ አሳልፎ ለ3ኛ ወገን ከሰጠ የቀረው ስጋ ብቻ ስለሆነ አስከሬን ማለቴ ቢከፋም አማራጭ የለኝም፡፡ ወይስ እንደ ደረጀ ፀጋየ “የስሜት የሹፌርነታቸውን ቦታ ለቀውለሸክም የተመቻቹ ጋሪዎች” ልበል። ለነገሩ እነዚህ ወቀሳዎች ደንበር ጥሰው ኢ-አማኝነትን ‘ሰነፎች’ ‘የገሃነብ ድጆች’ ‘የሰይጣን ልጆች’ ‘አረምውኔ ከሃዲዎች’ ‘አርዮሳዊያን’ ‘ለሶኦል የተጠበቁ’ ‘እራሳቸውን አምላኪዎች’ ‘666ቶች’ ‘እሪያዎች’ ‘አህዛብ’ እያሉ ለሚሳደቡ ሰባኪዎች ሲያንስ እንጅ አይበዛም።

ኢ-አማኞችን በተመለከተም ፍርሀት አለኝ። አንዳንድ የፀረ ሀይማኖት አስተሳሰብ አራማጆች በአንድ ጀንበር አማልዕክት ሙተው፣ ሀይመኖት ተወግዶ፤ቤተ-እምነቶች ሙዝየም ሁነው፤እና ዝግመታዊ ለውጥ ብቸኛው የተፈጥሮ አተረጓጎም ሁኖ ማየት የሚፈልጉ ጠባብ አተያይ ያላቸውን አሉ፡፡ ለምሳሌ ኮሚኒስት መንግስታት ሀይማኖት ካልጠፋ እድገት አይመጣምብለው በማሰባቸው በእምነቶች ላይ ዘመቻ ከፍተው ነበር፡፡ለእኔ ይህ አለማመንን ማምለክ ነው፡፡ ከማምለክ ስላልወጡ መሬት ገነት ሳትሆን ቀረች፡፡ ህልመቸውም ከሸፈ፡፡ መፍትሄዉ ይላል <ከማመን መጠራጠር ይሻላል>

‘‘መፍትሄዉ በተለያየ አጋጣሚ የሀይማኖቶችን አላስፈላጊነት የተረዱና ሐይማኖቶችም ለሀገር እድገት ፀር መሆናቸዉን የተገነዘቡ ምክንያታዊ አሳቢወችን አደራጅቶ ህዝቡን የማስተማር ስራ እንዲሰሩ እድል መስጠት ነዉ። ታድያ እነኝህ ምክኒያታዊ አሳቢያን ማህበራዊ ሚድያ ላይ የምንፅፈዉን አይነት ሐይማኖትን የማዉገዝና የማንቁዋሸሽ ስራ እየሰሩ ህዝቡን የሚያስቆጡ መሆን የለባቸዉም።ምክንያቱም ህዝቡ ሐይማኖቱን ከጥንት ጀምሮ ጠብቆ ያቆየዉና ከህልዉናዉም ለይቶ ስለማያየዉ በህዝቡ ሊፈረድበት አይገባም። ሌላዉ ቢቀር የኛ ህዝብ አለም ላይ ከእስልምናና ከክርስትና ዉጭ ሌላ ሐይማኖቶች መኖራቸዉን እን የማያዉቅ አሳዛኝ ህዝብ ነዉ። ታድያ ይሄ ህዝብ ሳይንስንና ፍልስፍናን ቢፀየፍ ምን ይፈረድበታል? የሌላዉ አለም ህዝቦች እኮ ለሐይማኖታቸዉ ብዙም ቦታ የማይሰጡት በሐይማኖት ፋንታ ሳይንሳዊ እዉቀቶችን በደንብ በመማራቸዉና በማወቃቸዉ ነዉ። ስለዚህ የኛንም ህዝብ በባዶዉ ሀይማኖትህን ተዉ ማለት ሳይሆን ሳይንሳዊ እዉቀቶችን እያስጨበጡ በሐይማኖቱ ላይ ጥርጣሬን መፍጠርና ሀይማኖቱንም የሚተዉበትን መንገድ ማመቻቸት ነዉ የሚያዋጣዉ።’’

ይህ የ<ከማመን መጠራጠር ይሻላል> ሀሳብ በ21ኛው ክ/ዘመን ላለን የድሀ ሀገራት ቦርን አጌን (Born Again) ኤቲስቶች ጠቃሚ ምክር ይመስለኛል። እንደ ኢ-አማኝ ልናስበው የሚገባን ነገር ቢኖር የእውቀትን ዛፍ ፍሬ ወደ አለም መዝራት ነው፡፡ ከዚ ሌላ ሀይል መጠቀም ጅልነት ነው፡፡ በአራቱም የምድር ማዕዘኖች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ መረጃን መስጠትና መቀበል እንችላለን፡፡ ቀደም ሲል ኤቲስት ብትሆኑ ኖሮ የራችሁን ድምጽ ከመስማት በቀር አማራጭ አልነበርም፡፡ አሁን ግን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ በነፃነት በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ በድብቅ የሰውን ልጅ ጠፍንጎ ካሰረው አሉባልታ ነፃ መውጣታቸውን ልታውቁ ይገባል፡፡ ሳይንቲስት፣ፈላስፋ ወይም የስነ መለኮት ተመራማሪ መሆን ሳይጠበቅብን የሙህራኑን ምርምር በመረዳት ለዚህ ሰላማዊ ትግል የሚጠበቅብንን ማድረግ እንችላለን፡፡ በዚህ አብዮት የሚሳተፍ ከሰውነት የዘለለ ማዕረግ አይሰጠውም፡፡ ታምራት፣ ገድላት እና ድርሳናት አይፃፉለትም፡፡ ሽልማቱ በአደባባይ የሚሰጥ የኖበል ሽልማት አይደለም በጨለማ ለሚኖሩ ብርሃን በማካፈል የሚገኝ ደስታ እንጅ፡፡

ለብዙ አማኞች ኢ-አማኝ የሆናችሁት ባለማወቅ፣ በማይረባ ሳይንስ እና ፍልስፍና በመሸወድ፣ በሰይጣን በመታለል፣ አሊያም በድፍረት ይመስላቸዋል። አማኝ አለመሆናችሁ ሲታውቅ ከሀድ አርዮስ እና ጭራቅ ትባላላችሁ። ይልቁንም መፅሐፋቸዉም የማያምኑ ወዮላቸዉ የገሃነብ ደጆች የሰይጣን ልጆች ናቸውና ይላሉ። የሚያሳዝነው አማኞች እንደሰው እንኳላይቆጥሯችሁ ይችላሉ። ራሳቸዉን ቅዱስ የፈጣሪ ልጆች ለማለት እናንተን ርኩስ የሰይጣን መልዕክተኛ ያደረጋሉ። እናንት ግን ነፃ ሰው እንደመሆናችሁ መጠን በትርፍ ጊዛአችሁ ማነሰላሰል፣ መፈላሰፍ እና መመራመር ትችላላችሁ፡፡ ስለራሳችሁ ብቻ ሳይሆን ስለ አማኞች መሰረታዊ ዶግማዎች እውቀት ይኑራችሁ።እኔ ስለ ሀይማኖት ለማንበብ እና ለመፃፍየምጠቀመው የእርፍት ጊዜየንነው፡፡ በማንኛው መደበኛ ስራየ ውስጥ ስለ ጉዳዩ አላስብም፤ ሀይማኖትን የማሰካድ የስብክት አጀንዳም የለኝም፤ ማንም እኔን እንዲመስል አልጠይቅም፡፡ እንዲያውም ለቅርብ ጓደኞቼ ሳይቀር ክርስቲያን እመስላቸዋልሁ። ይህን የተማርኩት ከመምህሬ ከፈላስፋው ዘረ-ያዕቆብ ነው <ለሰዎች አማኝ (ክርስቲያን) እመስላቸው ነበር፡፡> ነው ያልው። አላማየ በህይወት ዘመኔ ይህ ማህበረሰብ ማንነቱን መልሶ እንዲፈትሽ ማሳሰብ ነው በተለይም ስለ ኢ-አማኝነት የተዛባ እሳቤ ላላቸው ሰባኪዎች አፀፋ ከመመለስ ወደኋላ አልልም። ይህ ለእኔ በቂ ነው ፈረስ ያደርሳል እንጅ አይዋጋም፡፡

3ኛ. ለወላዋዮች፡-መወላወል መጠራጠር አይደለም ግራ መጋባት ነው። ‘ፅድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም፡፡’ በዚህ አባባል ህዝባችን ያለውን ጥርጥሬ በግልጽ ነግሮናልይህን የነገረን ማህበረሰብ አብዛኛው ፍፁም አማኝ ነው ወላዋይ አይደለም፡፡ ብዙ ሰወች ፈጣሪ ቢኖር ይኑር ባይኖርም አይመለከተኝም ብለው ተከናንበው ተኝተዋል፡፡ መላዋዮች የሃልወተ እግዚአብሔር ጥያቄ የማይሞቃቸውና የማይበርዳቸው ለዘብተኞች ናቸው፡፡ ህሊናቸውን እንዳያስብ አስረውት ካልሆነ ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን የፈጣሪን መኖር ወይም አለመኖር ማወቅ አይቻልም ብለው ደምድመው ከሆነ ከሞት ባልተናነሰ ስንፍና ውስጥ ናቸው፡፡ ሳያስቡ ከመኖር እያሰቡ መሞት እጅግ ይሻላል። እናም በእግዚአብሔር ህልውና ጉዳይ ገና ያልወሰናችሁ ሰዎች እውነት ከሁለቱም ጫፍ በአንዱ አንጅ በማዕከል አትገኝም፡፡ እኔ ለ6 ወር ያህል ወላዋይ ነበርኩ ያ የሽግግር ጊዜ ወሳኝ እና ከባድ ነበር፡፡ ከጭንቀቴ ብዛት የተማንፀንኳቸው አዳኞች፣ የተሳልኩት ስለት እና የጸለይኩት ጸሎት ዛሬ ድረስ ይገርመኛል፡፡ ሁሉም ከእንባየ ጋር ደረቀ፡፡ ከአንዱም ሳትሆኑ ራሳችሁን ከነፃ አሰተሳሰብ በማራቅ የምትኖሩ እየተሸወዳችሁ መሆኑን አውቃችሁ ጥጋችሁን ለመያዝ ሞክሩ እላለሁ፡፡ እናም ይህን መፅሀፍ እና ሌሎች የሀይማኖት ነክ መፅሀፍትን በማንበብ ከሁለቱ የተሻለውን ምረጡ፡፡ በእርግጥ በዚህ መፃሀፉ እግዚአብሔር እንደለለ ለማሰረዳት እሞክራለሁ ቢሆንም እኔ ፍንጭ እንጅ እግዚአብሔርን ካመናችሁ ሲኦል ትገባላችሁ፤እግዚአብሄርን ከካዳችሁ ግን ገነትን ትወርሳላችሁ አልልም፡፡

4ኛ. ለተማሪዎች እና ተመራማሪዎች፦ወድ ተማሪዎች እና ተመራማሪዎች ታሪክን፣ ባህልን፣ ሀይማኖትን፣ ፍልስፍናን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጅን ስታስተውሉ ትደነቃላችሁ፣ ሁሉንም ግን ታሪክ ይጠቀልላቸዋል። ታሪክን ሙት ወቃሽ ነው የሚሉ አሉ፣ እነዙህ ሰዎች ራሳቸው የሞቱ ናቸው እንጅ ታሪክ አይሞትም። በታሪክ ውስጥ ስነ ፍጥረትን፣ ባህልን፣ ሀይማኖትን፣ ተቃርኖን፣ ለውጥን፣ ፍቅርን፣ ጥላቻን፣ ፍልስፍናን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጅን ታገኛላችሁ። ብንችል የሁለንታን ታሪክ፣ ካልሆነም የስርዓተ ፀሀይን ታሪክ፣ ቢያንስ ቢያንስ ግን የመሬትን ታሪክ እስከቻልነው ርቀት ማውቅ አለብን። ለነገሩ የኢትዮጵያን ታሪክስ ስንት ኢትዮጵያዊ ያውቀዋል፣ በተለይ የተማረው ለብዙ ጥንታው ክስተቶች እንግዳ ነው። ታሪክ ለታሪክ ተመራማሪወች የተተወ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ የቤት ስራ ነው። አለማወቅ ሀጢአት አይደለም የሚባለው ትረት እዚ ላይ አይሰራም። የሀገሩን ታሪክ አለማወቅ ከሴቶች መሃል እናትን እንዳለማወቅ ይቆጠራል የሚባለው ግን እውነት ነው። ማንም ተነስቶ (እኔን ጨምሮ) ኢትዮጵያን ያለስሟ ስም ሰጥቶ፣ ያለግብሯ ግብር ሰቶ፣ ያልሆነውን ሆነ የሆነውን ሀቅ አልሆነም ብሎ ሲቀባጥር መሞገት የምንችለው ስንማርና ስንመራመር ብቻ ነው። እውነትን በመደባበቅ የትም አይደረስም፣ የሚሻለው እውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ማደር እንጅ ለፖለቲካ አበል ሲባል መዋሸት ያስተዛዝባል።የሆነስ ቢሆን ከሩዋንዳ እልቂት የባሰ ተፈፅሟልን? ሩዋንዳዊያን በግሃድ የተፈፀመውን ያውቃሉ፣ አላስተባበሉም፣ ይቅር ለመባባልም ልባቸው አልደነደነም። እውነት ለመናገር የኢትዮጵያን ታሪክ እንፈራዋለን እንጅ የሚፈራውን ያህል የሚጎዳን አይመስለኝም። በማንምና የትም የተፈፀመ መጥፎ ታሪካችንን በአመድ በመሸፈን የትም አንደርስም። የሞተ ሙቷል የገደለ ግድሏል አበቃ። ታሪኩን ማስታወስ መብት ነው መድገም ግን ወንጀል ነው። አሜሪካ በጃፓን፣ በጀርመንና በቬትናም ምድር ያደረገችውን አለም ያውቃል፣ እኛም ተምረናል። አሁን ግን ሮማንቲክ በሚመስል ፍቅር ውስጥ ናቸው፣ ደም የማይመልስ ትውልድ አፍርተዋልና። እኛስ?

ችግራችን አባቶቻችን ፍጹም፣ ሀይማኖታችን ፍጹም፣ ብሔራችን ፍጹም፣ ነገስታቶቻችንና ጳጳሳቶቻችን ፍጹም ነበሩ ብለን ስለምናምን ከታሪክ ጋር ሆድና ጀርባ ሆንን። እንደ ፍጹምነት ነቀርሳ የሆነ በሽታ በአለም የለም።  በዚህ በተዳፈነው ታሪካችን ጉዳይ የበዛ ቅሬታ አለኝ ቢሆንም ብዙ ሰው ለታሪኩ ባዳ በመሆኑ ሊረዳኝ ስለማይችል ዝም ብል ደስ ይለኝ ነበር፣ ቢሆንም ይህንም አልችልምና በጹህፌ ውስጥ ሊንጸባረቅ ይችላል። ብዙ ሰው ለታሪኩ ባዳ ነው ስል የማንንም ጥናት መሰረት አድርጌ ሳይሆን የራሴን ምልከታና ለታሪካችን ያለንን አናሳ ግንዛቤ መሰረት አድርጌ ነው፣ (እርግጠኛ ነኝ ለዚህ አባባሌ መቸም አይቆጨኝም)። በነገራችን ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ለሞሙላት ጥረት የሚያደርጉትን የታሪክ ጽሃፍትን፣ የሬድዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች (በተለይ የebsን አርአያ ሰብ ዝግጅት) ሳላመሰግን አላልፍም።

ዜጎች ላብራቶሪ ውስጥ ገብተው ኬሚስት መሆን አይጠበቅባቸውም፣ መፅሀፍትን አንበው መሰረታዊ ታሪካቸውንና አመጣጣቸውን ማወቅ ግን የሰብአዊነት ግዴታቸው ነው። የሩቁን ተውትና በኢትዮጵያ ምድር ለ5000 አመታት በቤተ መንግስቱ፣ በቤተ ህዝቡና በቤተ እምነቱ የተከናወነውን ሲያውቅ በመደነቅ አፉን በእጁ የማይጨብጥ፣ ራሱን የማያወዛውዝ አለ ብየ አላስብም። ምን አለ በሉኝ ትገረማላችሁ። ታሪክን ማንበብ የተዋጣለት ፊልም እንደማየት ቅርብ ነው። ልዩነቱ ፊሊም የሚተወነው በተምሳሌት ሲሆን ታሪክ ግን መቸቱና ተዋናዮቹ አማናዊ ናቸው።ምስጋና ለተክለ ፃዲቅ መኩርያ፣ ለፍስሐ ያዜ፣ ለመራሪስ አማን በላይ፣ ለካሳሁን ደምሴ በላይ፣ ለፕ/ር ባህሩ ዘውዴ፣ ለፕ/ር ላጲሶ ድሌቦ፣ ለአለቃ ታየና የብራና መፅሀፍትን ከትበው ላቆዩን አባቶቻችን በሙሉ ይሁንና ታሪካችንን አብስለው እንድንበላው ሰተውናል። ከትውልዱ የሚጠበቀው ማንበብ ነው፣ አንብቦም ማወቅ፣ አውቆም ማስተዋል፣ አስተውሎም በጎውን መውሰድ መጥፎውን መተው፣በስማ በለው መነዳት ግን የከብት እንጅ የሰው ባህሪ አይመስለኝም።ተወዳጁ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት “የታሪክ ሂደት ያመጣቸውን የትናንት ነገሮች ዛሬ አንቀይራቸውም። ሆነዋልና። ነገር ግን እንማርባቸዋለን፤ ከትናንት ወስደንም ለዛሬ እንጠቀምባቸዋለን። የዛሬ ማንነታችን መገንቢያም እናደርጋቸዋለን። በታሪክ መስክ ላይ የተሠማራ ትውልድም ጊዜውን ማጥፋት፣ ጉልበቱን መሠዋት፣ ጥበቡን ማፍሰስ፣ ዕውቀቱን መከስከስ፣ ያለበት ለአረሙ አይደለም ለእህሉ እንጅ። ጥላቻው፣ ቂም በቀሉ፣ መቆራቆሱ፣ መናከሱ፣ መለያየቱ፣ መጠፋፋቱ፣ ይኼ የትውልድ አረም ነው። በስንፍና ብቻ ሊበቅል የሚችል ነውና። ትኩረታችንን እህሉ ላይ ካደረግነው አረሙን እንቋቋመዋለን፣ እናጠፋዋለንም። አረሙን ማጥፋት ያለብን አረም ስላልነበረ አይደለም፣ አረምን ለመሸፋፈን ሲባልም አይደለም። አረም ስለማይጠቅመን ነው።” ነበር ያለው (ዳንኤል ክብረት፣ የቀለም ቀንድ ቅፅ 3 ቁጥር 11)። የጥቅጥቅ ደኖች፣ የብርቅየ ዱር እንስሳት፣ የአዕዋፍት፣ የታላላቅ ወንዞችና ሃይቆች፣ የትናንሽ ደሴቶች፣ የአስደማሚ ስምጥ ሸለቆዎች፣ ጋራዎችና ሸንተረሮች እንዲሁም ረዥም ታሪክ ያላቸው ቅርሶች ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን እንድታውቋት የምመክራችሁ በፍቅር እየለመንኩ እንጅ እንደ ንቡረ እድ ኤርሚይስ ከበደ እያስፈራራሁ አይደለም።

ንቡረ እድ ኤርሚይስ ከበደ ኢትዮጵያ የአለሙ መፍረጃ በሚለው ሀይማኖታዊ መጻፋቸው ሦስተኛ እትም ገፅ 32 እና 40 እንዲህ ይላሉ፦“(መጽሃፌ) ስለ ኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያዊነታችሁ የእግዚአብሔር እውነት የሰጠችውን የምስክርነት ቃል የያዘ ስለሆነ እርሱን አንስታችሁና ገላልጣችሁ ለማንበብ አትፍሩ! ካልወደዳችኋት አትፈልጓትም! ካልፈለጋችኋት የእሷን ልጆች አይደላችሁም እርሷ በእግዚአብሔር እውነትነቷ ኢየሱስ መሲህና ድንግል ማርያም ኾና ስለተገለጸች የእርሷ ወገን፣ የእርሷ አገልጋይ አይደላችሁም ማለት ነው! እንዲህ ካልኾናችሁ ደግሞ ይህ አቋማችሁ የሀሰት ያውም የዲያብሎስ ወገኖችና አገልጋዮች ያደርጋችኋል፡፡ይህን መጽሀፍ (የአለሙ መፍረጃን) ከዳር እስከ ዳር በንባብ ለመውጣት ቀርቶ ወደውስጥ ገላልጦ ለመመልከት እንኳ አንባቢዎች መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸው፣ የእግዚአብሔር ወገኖች ብቻ መኾናቸውን የምታረጋግጠው እውነት ናት፡፡” እኔ ግን እላችኋለሁ የቱንም መፅሀፍ፣ ማንም ይጻፈው ተጠራጠሩ፣ አለመቀበልም ትችላላችሁ፣ ከቻላችሁም መተቸት ትችላላችሁ ከዜግነታችሁ ቅንጣት አይቀንስባችሁም። እኔ ካልኩት ውጭ ሙቸ እገኛለሁ፣ እኔ ከሞትክ ሰርዶ አይብቀል የሚሉት ኤርሚይስ ከበደና ተክለ ኪዳን ወጣቱን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በሚሸት ርዕስ ግን ለምርምር በር በማይከፍት አሳሪ ትንታኔ እያጃጃሉት ይመስለኛል። ተክለ ኪዳን የጨለማው ገዥ ተግባርና ንግግር የሚለውን ሀይማኖታዊ መጽሃፍ ገፅ 1 ላይ መጽሃፉን ሲያስተዋውቁን እንዲህ ነበር ያሉት “ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በስጋና ደም ስሜት መነሻነት ሳሆን፣ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ፣ የማይኖርበት ጊዜ የማይኖር፣ ረቂቁንና ግዙፋን ፍጥረት በመለኮታዊ ሀይሉ የፈጠረ፣ ሁሉ በእርሱ የእርሱ የሆነ፣ ከእርሱ ዕይታና ቁጥጥር ውጭ የሀነ አንዳች ነገር የሌለ፣ ከለእርሱ ፈቃድ አንዳች ሊሆን ሆነ ሊኮን የማይቻል፣ ፈተኛውና መጨረሻው፣ አልፋና ኦሜጋ የሆነው ፈጣሪ አምላክ ከመስከረም አጋማሽ እስከ ታኅሣሥ መጀመሪያ (2004 ዓ.ም) ድረስ በተለያዩ ቀናትና ስዓት ወደ ኅሊናዬ በሚያሳስበኝና በሚናገረኝ ድምፅ ብቻ ተመርቼ ነው የጻፍኩት፡፡”በቃ መጠራጠር አይቻልም፣ የመፅሀፉን እውነታ በተለይም ሰይጣንና እግዚአብሔር ጋዜጠኛ ሁኖ ለቀረበው ተክለ ኪዳን የሰጡትን ቃለ ምልልስ አሜን ብሎ አለመቀብል እንደ ትልቅ ክህደት ተቆጥሯል። ቅን ልብና አስተዋይ አዕምሮ ላላቸው ተመራማሪዎች ግን መፅሃፍቱ ከምፈተሽ አይድኑም፣ በምንም አጥር ይታጠሩ። የሁለቱም ግለሰቦች መፅሃፍቶቻቸው ብዙ መልካም ነገር ቢኖራቸውም ውስጥ ውስጡን ግን በአድሎ የታጨቁና ኢ-ፍትሀዊነት የሰፈነባቸው ናቸው።

ተማሪና ተመራማሪ የተጻፈን በመረጃ በማመሳከር እንጅ እንደወረደ መቀበልን የምርምር ስነ-ምግባር አይፈቅድለትም።በሀገራችን ወግ ውስጥ የልቡን የነገሩት የኮለኮሉት ያህል ይስቃል ይባላል፡፡ የተማሪዎች እና የተመራማሪዎች ስራ ግን የልብን ከመናገር የበለጠ ነው፡፡ ተመራማሪ ማለት ከማህበረሰባዊና ከግል ፍላጎት ነፃ በሆነ መልኩ የማህበረሰቡን መልካምና መጥፎ ልምዶች፣ አኗኗሮች እና ስርዓቶች ማንኛውም ሰው ሊረዳው ከሚችለው በላይ ወደ ውስጥ ጠልቆ ወይም ወደ ላይ ተመስጦ የሚያሳስ የእውነት አፍቃሪ ማለት ነው፡፡ ለመማር እና ለመመራመር ከውጫዊ ተፅዕኖ እና ከውስጣዊ ተፅዕኖ ነፃ መሆን አለብን፡፡ ተፅዕኖ ወደ እውነት የሚደረገውን ጉዞ የሚያደናቅፍ ታላቅ መሰናክል ነው፡፡ በሀይማኖት፣ በፍልስፍና እና በሳይንስ ላይ ተፅዕኖ ከባድ አሉታዊ ጫና አለው፡፡ አንድ ሰው በእግዚአብሔር ካመነ በኋላ ስለእግዚአብሔር መኖር መመራመር አይጠቅመውም፣ ከጥያቄው መልሱ ስለቀደመ፡፡ የማያምንም እግዚአብሔር የለም ብሎ ከተነሳ ድካም ነው፡፡

ለአንድ ተመራማሪ ሊኖረው የሚገባ ትልቅ ሀብት “መጠራጠር” ነው፡፡ እራሳችሁን እኔ ግን በህይወት አለሁ፣ እስከ ሚለው ድረስ መጠራጠር፡፡ ፈላስፎቹ እኮ ከመጠራጠራቸው ብዛት የምናየው ነገር ሁሉ illusion ነው ይላሉ፡፡ በመጠራጠር ዉሰጥ ድምደሜ የሚባል የለም፡፡ በመጠራጠር ፈልስፍና ማር ጥፈጭ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ ማርን የሚመገቡት ሰዉእና ጥቂት እንሰሳት ናቸዉ፡፡ ማር ፈጹም ጣፈጭ  ቢሆን ሁሉም በወደዱት ነበር፡፡ ከሌሎች እንሰሳት ጋር መወዳደሩ ይቅርና  የእባብ ጥብስ እና የአይጥቋንጣ ፍርፍር ምንምን እንደሚል ታዉቃላችሁ? ካወቃችሁ ምሰክር ትሆናላችሁ ካልሆነ ግን እኛ የማንበላዉ ሰለማይጣፈጥ ሳይሆን ሰላልለመድነው እና ሰለማናዉቀዉ ነዉ ሰለዚህ እባብ አይበላም፣ ይባላል (አሳ በጾም ወቅት ይበላል አይበላም እንደማለት ነው) ብላችሁ ከመከራከር በፊት መመራመር ያሰፈልጋል፡፡ ምርምሩ በላብራቶሪ ወይም በተግባር በመቅመስ ወይም የቀመሱትን እና ያልቀመሱትን ሰለጉዳዪ ያላቸዉ ግንዛቤ በመጠየቅ ሊሆን ይችላል፡፡ የምርምሩ ዉጤት እንዳይበላሸ የምርምሩ መንገድ ከአድሎ ነፃ መሆን አለበት፡፡ ስለእግዚአብሄር መኖር ቤተ-ክርሰትያን ሂደህቃለ መጠይቅ ከምታደርግ ምንሊሉ እደሚችሉ አዉቀህ ፈጣሪ አለ ብለህ ብትደመድም ይሻላል፡፡

ምርምር ፍርድነዉ፡፡ ከሳሻ እና ተከሳሸ ሀሳቦች መነሳት አለባቸዉ፡፡ የሁለቱም ወገን ምስክሮችም መጠራት አለባቸዉ፡፡ ያካልሆነ ግን ፈርዱ ይዛባል፡፡ሠዎች ያለጥፋታቸዉ በእሰር ይማቅቃሉ፣ እዉነትስ በዉሸት ተወንጅላ በእሰር እተሰቃየች እንደሆነ በምን እናዉቃለን? እንደ ተመራማሪ ይህ የቅንብር መጽሀፍ በአለማዊ እና መንፈሳዊ ኮሌጆች ለሚማሩ እና ለሚመራመሩ እንደማጣቀሻ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ በነገራችን ላይ እኔ በዚህ መጽሀፍ የቀረብኩት ተመራማሪ ሁኜ ሳይሆን እንደ ሰባኪ ሀዋርያ ነዉ፡፡ በይበልጥ እናንተ ገምግሙት። የመጽሀፉ አለማ ከማመራመር ይልቅ ከመንገድ ዳር ሰባኪዎች እስከጳጳሳት ድረስ በአለማመን አስተሳሰብ ላይ ለሚሰነዝሩት ወቀሳ የመልስ ምት መስጠት ነው፡፡

ይቀጥላል—-

Tadesse Abebaw Assefa

  • Ph.D. in Physics-European XFEL facility GmbH and University of Hamburg, Germany

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.