የፖለቲካና የሕሊና እስረኞች “ፍትህ እንፈልጋለን “በሚል መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት የጀመሩት የ3 ቀናት የርሀብ አድማ እንደቀጠለ ተነገረ

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን)የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ካሡ ኃይሉ ለአማራ ሚዲያ ማዕከል እንደገለፁት አላግባብ በእስር ላይ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት አመራሮችና አባላት ተቃውሞ ላይ ናቸው።

አቶ ካሡ እንዳሉት የረሀብ አድማው የተጀመረው አርብ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም ሲሆን ዛሬ 3ኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

ያለአግባብ የታሰሩት ፍትህ እንዲሰጣቸው ከመጠየቅ ባሻገር ባልደራሱ የጠራውንና በመንግስት ክልከላ እንዲቀር የተደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ የሚደግፉት መሆናቸውን የሚገልፅ፣ የርሀብ አድማ ያደረጉትም በእስር ላይ የሚገኙ 28 የአማራ ብሔራው ንቅናቄ(አብን) አመራሮችና አባላት፣በሸዋ የደራ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አመራርና አባላት እንዲሁም የአዲስ አበባ የባለአደራ ም/ቤት አመራሮች እንደሆኑ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በረሀብ አድማው ላይ የሚገኙት እስረኞች ከባለፈው አርብ ጀምሮ ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ እንዳይጎበኛቸው ያሳወቁ ሲሆን፣ ለሦስት ቀን እናደርገዋለን ያሉት የረሀብ አድማም ነገ ጠዋት እንደሚጠናቀቅ ተነግሯል።

በርሀብ አድማውም የአብን አመራሮች መካከል የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣የአብን የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ በለጠ ካሳና ሌሎችም ይገኙበታል ተብሏል።

በጠ/ሚ አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ሰኔ 15 በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና በጄኔራሎች ላይ የተፈፀመውን የግድያ ወንጀል መፈንቅለ መንግስት የሚል ስያሜ በመስጠት ለአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል ላይ ከፍ ያለ ሚና እየተጫወቱ ያሉ አመራሮች ላይ በማነጣጠር አላግባብ በማሰር ትግሉን ለማዳከም እየሞከረ ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።

የረሀብ አድማ ያደረጉት የተለያዩ ተቋማት አመራሮችና አባላት በአዲስ አበባ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ይታወቃል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.