ለመሆኑ ሰባሪው ማን ይሆን? ተሰባሪውስ? – ከመርሀጽድቅ መኮንን አባይነህ

መንደርደሪያ

“Power makes man mad” ይሉ ነበር በሁለተኛው የአለም ጦርነት የታላቋ ብሪታንያ መሪ የነበሩት እውቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርቺል፡፡

በግርድፍ አማርኛችን “ስልጣን የሰውን አእምሮ ያዛባል” ማለታቸው ይመስለኛል፡፡ ጨርሶ ‘ያሳብዳል’ ማለቱ ስላስጸየፈኝ እኮ ነው ጎበዝ፡፡

በአንዲት አገርና በብዙኃኑ ዜጎቿ ላይ ታይቶ የማይታወቅ ገደብ-የለሽ አበሳና በደል የሚደርሰው ቀድሞ ነገር መንግሥታዊ ስልጣን ምን እንደሆነና ለየትኛው አላማ ሊገለገሉበት እንደሚገባ እንኳ መሰረታዊ ግንዛቤው ሳይኖራቸው በአቅምም ሆነ በስነ-ምግባር የወረዱ ግለሰቦች በሀላፊነት ማማ ላይ የሚወጡበትንና ያለችሎታቸው የፖለቲካ ዙፋኑን የሚቆናጠጡበትን እድል ያገኙ እንደሆነ ነው፡፡

የምክትሎች ሀሰተኛ ትራንስፎርሜሽን: ብልሹ ወይስ ጠቃሚ ልምድ?

ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትመራው በፓርላማ ስርአት እንደሆነ የሕገ-መንግሥቷ አንቀጽ 45 ድንጋጌ ለወጉ ያህልም ቢሆን ይደነግጋል፡፡ የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ ማለትም የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ማቋቋሚያ ቻርተሮችም ሆኑ የየክልሎቻችን ህግጋተ-መንግስታት ይህንኑ በቀጥታ እየኮረጁ የተቀረጹ በመሆናቸው እንደፌደራሉ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ሁሉ ርእሳነ-መስተዳድሮቻቸውም ሆኑ ከንቲባዎቻቸው በምርጫ ወቅት የየህዝብ ምክር ቤቶቻቸውን አብላጫ መቀመጫ ባገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች አቅራቢነት ሊሰየሙ የሚችሉት በምክር ቤቶቻቸው አማካኝነት ብቻ መሆን አለበት፡፡

የፌደራሉን ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 56ና አንቀጽ 73 ንኡስ አንቀጽ (2)፣ እንዲሁም  የየክልሉን ሕገ-መንግሥት አቻ ድንጋጌዎች በጥሞና ይመለከቷል፡፡

ነገር ግን ከፍ ብሎ የተጠቀሰው የአመራር መሰየሚያ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ የፌደራሉ መንግሥት የኔ ናቸው በሚላቸው በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች ይቅርና በአመዛኞቹ ክልሎች በህያውነት መስራት ወይም በጥቅም ላይ መዋል ካቆመ ብዙ ቆይቷል፡፡

ለምሳሌ የዛሬን አያድርገውና የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ክልሎች ነን እያሉ ከሚመጻደቁት ክልሎች መካከል በሶስቱ፣ ማለትም በትግራይ፣ በኦሮምያና በደቡብ ክልሎች ውስጥ የምናገኛቸው መሪዎች የፖለቲካ ተሿሚዎች እንጂ ሕገ-መንግሥቱ በሚጠይቀው መሰረት የተመረጡ የህዝብ ምክር ቤቶች ስዩማን አይደሉም፡፡ በሌላ አነጋገር የየምክር ቤቱ አባላት ካለመሆናቸው የተነሳ ‘ምክትል’ የሚል መአረግ ያለአግባብ እየተለጠፈላቸው ክልሎቻቸውን ወይም የከተማ አስተዳደሮቻቸውን እንደሁኔታው በርእሰ-መስተዳድርነት፣ በፕሬዚደንትነት ወይም በከንቲባነት እንዲገዙ የተሾሙ ባለስልጣናት ናቸው፡፡

ምናልባት ይህ አጓጉል ቧልት ቢያንስ በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ እስካሁን ሲፈጸም ያልታየው በአማራ ክልል ብቻ መሆን አለበት፡፡ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ከተከሰተው አሰቃቂ አደጋ በኋላ እንኳ ርእሰ-መስተዳድሩን ሳይቀር በሞት የተነጠቀው ይኸው ክልል ህዝብ ባልመረጠው ምክትል ርእሰ-መስተዳድር በተጠባባቂነት ሲመራ የቆየው ለአንድ ወር ያህል ብቻ ነበር፡፡ እርሱም ቢሆን ታዲያ እንደጎንደርና ደሴ በመሳሰሉትና በስሩ በታቀፉት ዋና ዋና ከተሞች የምክር ቤት አባላት ያልሆኑ የፖለቲካ ምልምሎችን ከህግ ውጭ በምክትል ከንቲባነት የመመደብ ወይም የመሾም በሽታ አልተጋባበትም ማለት አይደለም፡፡

ለመሆኑ የምክትል መአረግ ይዞ በዋናነት እንደምን ማገልገል ይቻላል?

ቀድሞ ነገር ዋና ሳይኖር ምክትል ይኖራል እንዴ?

ዋናው ከሌለ ምክትሉ የሚከተለው ማንን ይሆን?

እውነቱን እንነጋገር የተባለ እንደሆነ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” ካልሆነ በስተቀር በሁለተኛ መአረግ ተሹሞ የአንደኝነትን ሙሉ ስልጣንና ሀላፊነት በቆረጣ መቀዳጀት ሕጋዊነት አይኖረውም፡፡

በርግጥ በአንድ ተቋም ዋናና ምክትል ወይም ምክትሎች ያሉ እንደሆነ ዋናው መሪ በተለያዩ ምክንያቶች በስፍራው የሌለ ወይም ስራውን ለጊዜው ማከናወን የማይችል በሚሆንበት ጊዜና ሁኔታ ምክትሉ ወይም ከምክትሎቹ መካከል በሹመት ቀደምትነት ያለው ምክትል እርሱን ተክቶ ሊሰራ ይችል ይሆናል፡፡ ዋናው ጨርሶ ከሌለ ግን ምክትል የሚባል ነገር የሚታሰብ አይደለም፡፡

ይልቁንም በስራ ላይ ያለው የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት በዚህ ረገድ የጎላ ህጸጽ ይታይበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ አለም በሞት ቢለይ ለጊዜው ምክትሉ እንደሚተካው እንኳ ደፈር ብሎ አይናገርም፡፡

የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ ፸፶73ና አንቀጽ 75ድንጋጌዎች በዋቢነት ይመለከቷል፡፡

እንዲያውም በሀገራችን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስያሜና ስልጣን የሞት መድሀኒት ያህል ተቆጥሮ ያለአማራጭ የተደነገገ ነው የሚመስለው፡፡ ይህንን ስልጣን የሚጨብጠው ሰው ዘልአለማዊነቱ እንጂ መዋቲነቱ ጨርሶ አልታሰበም፡፡ በቁጥር ላልተገደበ የአገልግሎት ዘመን በየአምስት ዓመቱ በሚካሄድ ምርጫ አሸናፊነቱ በሚታወጅለት የፖለቲካ ድርጅት አማካኝነት እጩ ሆኖ እየቀረበ በፓርላማው ፊት በርእሰ-መንግሥትነት የመሰየምና ቃለ-መሀላ የመፈጸም ልዩ መብት ተቀዳጅቷል፡፡

መሬቱ ይቅለላቸውና ታላቁን መሪያችንን አቶ መለስ ዜናዊን ‘በሞት የተቀማን’ ሰሞን አቶ ሀይለ-ማርያም ደሳለኝን በይፋ ለመተካት ፓርላማውን በአስቸኳይ ጠርቶ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እስኪያሰይማቸው ድረስ ምን ብሎ እንደሚጠራቸው እንኳ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ራሱ ግራ ተጋብቶ አደናጋሪና እርስበርስ የሚጣረሱ መግለጫዎችን በየእለቱ እየሰጠ እኛንም ሲያደናግረን የሰነበተው ከዚሁ የተነሳ ነበር፡፡

የየክልሉና የከተማ አስተዳደሮቻችን ሁኔታም ከዚህ የተለየ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡

እንግዲህ በአሁኑ ወቅት በምክትል ፕሬዚደንት መአረግ የኦሮምያ ክልል ፕሬዚደንት ተብለው የሚያገለግሉት መሪ የዚሁ የተዥጎረጎረና ግልጽነት የጎደለው አሰራር ውጤት መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡

ምክትል በመሆን ተሹመው ሳለ የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን በዋና ከንቲባነት የሚገዙት ሌላው የኦ..ዴ.ፓ አጋራቸውም እንዲሁ፡፡

የመጀመሪያዎቹ ባይሆኑም እነዚህ ሁለት ለእግዜር የከበዱ መንትያ ሹማምንት እንደእውነቱ ከሆነ የስልጣኑን ማማ የተቆናጠጡበት መንገድ ያን ያህል አስተማማኝነት ያለው ህገ-መንግስታዊ መሰረት የለውም፡፡ ቀድሞውኑ በህዝብ ያልተመረጡ እንደመሆናቸው መጠን ቴክኒካዊ ብቃትና ክህሎቱ አላቸው ብለን ብናምን እንኳ በቀላል ቋንቋ የፖለቲካ ሹመኞች እንጂ በእንደራሴዎች ድምጽ የተደገፉ ስዩማን እንዳይደሉ ልቦናችን ያውቀዋል፡፡

እዚህ ላይ ኦ ሮምያም ሆነች አዲስ አበባ በምክር ቤት የተመረጡና ህዝባዊ ተቀባይነት ያላቸውን እጩ የክልል ፕሬዚደንትና የከተማ ከንቲባ በማፈላለግ አቅርበው ለማሾም እንዴትና ለምን እንደተሳናቸው በውል የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

መስበርና መሰበር

ቀደም ሲል የርእሰ-መንግስቱ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ሆነው ሲያገለግሉ ከመቆየታቸው የተነሳ በተለይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅርበት ያላቸው የወቅቱ የኦሮምያ ምክትል ፕሬዚደንት አሁን ለያዙት ሀላፊነት ከበቁበት ጊዜ አንስቶ ቅድመ-ጥንቃቄ በጎደለው አኳኋን አወዛጋቢ ዲስኩሮችን በመሰንዘር ወይም በማሰማትና ደንበኞቼ ናቸው ያሏቸውን አድማጭ-ተመልካቾች ያለአግባብ በማስፈንጠዝ አብዝቶ መታወቅን የመረጡ ይመስላሉ፡፡ በርግጥ ይህንን አይነቱን ያልታረመና እንደነውር ሊቆጠር የሚችል ልቀተ-ልሳን ሆነ ብለው ይፈጽሙት ወይም ድንገት የምላስ እንሽርት እያጋጠማቸው ይጋለጡበት ለመገመት ሳያስቸግር አይቀርም፡፡

ያም ሆኖ ይህ አይነቱ ልምምዳቸው ፍጹም አደገኛና እንደአገር መቆጠር ያለበት ያህል በብዙ የኦሮሞ ወንድምና እህቶቻችን አማካኝነት ከሚቀነቀንለት ከኦሮምያ ክልል ቁንጮነታቸው ባሻገር የሰብእና ደረጃቸውን እንጦርጦስ የሚያወርድ ክብረ–ነክ አድራጎት ነው፡፡

ምክትል ፕሬዚደንቱ መሪነታቸው አዲስ ቢሆንም ንግግሮቻቸው ግን ተንኳሽ ከመሆናቸው የተነሳ መረጃው ለምልአተ-ህዝቡ አይንና ጀሮ እንግዳ ባይሆንም ጥቂት ማሳያዎችን እዚህ ላይ መጥቀሱ ሳይበጅ አይቀርም፡-

ሀ. ትዝ ይለን ከሆነ ባሳለፍነው ዓመት መገባደጃ ላይ የትምህርት ፍኖተ-ካርታው ረቂቅ ሰነድ በሀገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር ባለስልጣናት አማካኝነት ለህዝብ ይፋ በተደረገበት ወቅት ግለሰቡ ከመሬት ተነስተው ተከታዮቻቸውን ለማስደሰት ብቻ “በአፋን ኦሮሞ አንደራደርም” በማለት አስደንግጠውን ነበር፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ትንሽ ሸብረክ ባይልና የቀደመው አቋሙ ባይወዛወዝ ኖሮ የሰውየው አነጋገር ከመስመር የወጣና ይፋዊ የሆነ የአጸፋ ምላሽ የሚያስፈልገውና የሚገባውም ነበር፡፡

ሰውየው ይህንኑ ዲስኩር እስከማሰማት የደረሱትና በሚዲያ ቅብብሎሽ እየተጠቀሙ ሲያስጮሁት የሰነበቱት ለኦሮምያ ህጻናት መደበኛ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ከአፍ መፍቻ ቋንቋቼው ጎን ለጎን የፌደራሉ መንግሥት የስራ ቋንቋ በሆነው በአፋን አማራ እንዲሰጥ መታቀዱን በመስማታቸው ብቻ ነው፡፡

 

“ገረመኝ ደርሶ ቢስመኝ” ነበር ያለቺው እታታ ታገኝ?

ለ. በዚያ ሰሞን ምክትል ፕሬዚደንቱ የኦሮምያን ቤተ-ክህነት በተናጠል ለማቋቋም ተወጥኖ ከነበረው የውሁዳን ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የመንግሥታቸውን አቋም እንዲገልጹ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት ተጠርተው በነበረበት ወቅት የሰጡት ሃሳብ ከውስጥ የተናገሩትን ከመሰብሰቢያ አዳራሹ እንደወጡ ወደሚዲያ ቀርበውና አይናቸውን በጨው አጥበው በይፋ እስከማስተባበል ድረስ የተጋለጡበትና ጨርሶ የተምታታ እንደነበር ሁላችንም እናስታውሳለን፡፡

ሐ. ይበልጡን የሚያስገርመው ግን በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ በመስቀል አደባባይ የተከበረውን የኢሬቻ በአል መነሻ በማድረግ በእለተ-አርብ፣ መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም ያሰሙት የጠብ አጫሪነት ንግግር ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክትል ፕሬዚደንቱ ባሰሙት በዚህ ዲስኩር ከ150 ዓመት በፊት መከበር አቁሟል የሚሉትን ባህላዊ በአል ነፍጠኛውን በሰበሩበት አደባባይ እነሆ በነጻነት ለማክበር መቻላቸውን በስፍራው ለተሰበሰቡት ታዳምያን ያለአንዳች ይሉኝታና ያለመሸማቀቅ ነግረዋቸዋል

በርግጥ መስቀል አደባባይ ላይ ያስተጋቡትን ይህንኑ የሰባሪ/ተሰባሪ ትርክት እንዲያብራሩ የBBC ጋዜጠኛ የተሰባሪውን ማንነት በስም እንዲገልጹ ያቀረበላቸውን ቁልፍ ጥያቄ አድበስብሰዉት አልፈዋል፡፡፡ እንዲያውም ለጀሮ በሚቀፍ ሁኔታ በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖሩትን ዋና ዋና ብሄር/ብሄረ-ሰቦች በስም እየጠሩ እነርሱ ሊሆኑ እንደማይችሉ አስቀድመው ካረጋገጡ በኋላ አማራ ብሄር ላይ ሲደርሱ መዘርዘሩን በማቆማቸውና ሸውደው ለማለፍ በመሞከራቸው የነፍጠኛውን ስርአት ከተጠቀሰው መከረኛ ብሄር ጋር ብቻ ለማስተሳሰር ወይም ለማቆራኘት የፈለጉ ያህል በብርቱ አሳብቆባቸዋል፡፡

“ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” ይላል የአገሬ ሰው፡፡

ለነገሩ “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር” እንደሚባለው ሆኖ እንጂ ኢሬቻ እኮ እንዲህ የመዘባበቻ መድረክ አልነበረም፡፡ የዛሬ ሶስት ዓመት አማሮች ሳይቀሩ ከወሎና ከጎንደር በጥሩምባ ተጠራርተው ወደብሾፍቱ በመጉረፍና ከኦሮሞ ወንድምና እህቶቻቸው ጋር በመቀላቀል ባከበሩትና በርካታ ወገኖቻችንን ባጣንበት በአል ላይ ያ መብረቅ የኦሮምያ ብላቴና “Down down WeYane; Down down TPLF” በማለት አየረ-አየራትን ሰንጥቆ ያሰማውንና ለመላው አለም ያስተጋባውን ነጎድጓዳማ ድምጽ ማን ሊረሳው ይችላል?

ስም አይጠሬውና የተሳከረው የኦ.ዴ.ፓ መግለጫ

ይህ በዚህ እንዳለ አዲስ አበባ ላይ የኢሬቻ በአል በወቅቱ የብሄር ፖለቲካ ተጠልፎም ቢሆን በድምቀት ከተከበረ አራት ቀናት ያህል ዘግይቶ መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦ.ዴ.ፓ) እንደተለመደው አንድ አደናጋሪ የአቋም መግለጫ በማውጣት ለምልአተ-ህዝቡ አሰራጭቷል፡፡

ለነገሩ የዚህ አደናጋሪ መግለጫ ትክክለኛ አላማው ምን እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ አይመስልም፡፡ በአንድ በኩል ዘመናትን በተሻገረውና በተወሳሰበው ታሪካችን ከተፈጸሙ ስህተቶች ይልቅ ለወደፊቱ አንድ የሚያደርጉንና እርስበርስ የሚያጋምዱን በጎ እሴቶች ያመዝናሉና ንግግሮቻችንም ሆኑ ተግባሮቻችን ጨቋኞችንና ጭቁን ህዝቦችን በአንድ አይነት መነጽር የሚመለከቱና አንደኛውን ህዝብ ከሌላው ጋር ጨርሶ የሚያራርቁ መሆን አይኖርባቸውም ሲል በደምሳሳው ያውጃል፡፡ ከዚያም አለፍ በማለት በተለይ በአማራና በኦሮሞ ማህበረ-ሰቦች መካከል ለውጡን ተከትሎ እየጎለበተ መጥቷል ያለውን ወዳጃዊ ግንኙነት የሚያሻክር አንዳች ነፋስ እንዳይገባበት ጨምሮ ያስጠነቅቃል፡፡

በሌላ በኩል ግን በተከላካይነት ይሁን በአጥቂነት የተሰጠ ስለመሆኑ የማይታወቀው ይኸው የኦ.ዴ.ፓ ዥንጉርጉር መግለጫ ማን መቸና ምን ስላጠፋ ወይም ስላጎደለ በሁለቱ ብሄሮች የሰመረ ግንኙነት ላይ የተባለው አይነት የስጋት ደመና እንዳንዣበበበት ስም፣ ቦታና ጊዜ በውል ጠቅሶ ለመናገር አልደፈረም፡፡ ይልቁንም የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሰረት ስጋቱን በፈጠሩትና የነጃዋር መሀመድን ሳንባ ተውሰው እምብዛም ሳይጠነቀቁና አፋቸውን በመሀረብ መጋረድ ሳያስፈልጋቸው በብዙ አስር ሺዎች የሚቆጠሩ የክብረ-በአሉ ታዳምያን በከተሙበት በዚያ ደማቅ ትእይንት ላይ ከወትሮው የተሻሻለ ትምክህት የተቀላቀለበትን የሰባሪ/ተሰባሪ ድራማ ለመተወን በአዲስ የብሄረተኝነት ሞቅታ ከወዲያ ወዲህ ሲወራጩ በታዘብናቸው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉ ላይ ተገቢውን የስነ-ስርአት እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቦ ዙሪያ ጥምጥም መንከላወስን እንደመረጠ ልብ ብለናል፡፡

ታዲያማላችሁ፣ ስንፍና የተጫጫነው ይህ የኦ.ዴ.ፓ መግለጫ ስለሰነፉ መምህር የተገጠመውን አስታወሰኝ፡፡

እንዲህ ይል ነበር፡-

ሰነፍ አስተማሪ ያለበት አባዜ፤

አስተዋይ ተማሪ የጠየቀው ጊዜ፡፡

ቃለ-ምእዳን

የዚህች አነስተኛ መጣጥፍ ባለቤት በሀገሩ ጉዳይ እንደሚያገባው እንደአንድ ዜጋ በምክትል መአረግ ተሹመው ሳለ በዋና መሪነት ለሚያገለግሉት ጉንቱ ፖለቲከኛ አንድ አቢይ መልእክት አለኝ፡-

ትርፉ ትዝብት ሆነብዎ እንጂ እርስዎ በሰባሪነትና በተሰባሪነት የመደቧቸው ማህበረ-ሰቦች እኮ በሁሉም የህይወት መስኮች የተዋሃዱና ጨርሶ ላይለያዩ የተዛመዱ፣ የተጋመዱ ናቸው፡፡ ስለሆነም ያለማስተዋል በተሰነዘረው በዚህ ሀኬተኛ ዲስኩር እንደታሰበው ሳይከፋፈሉና እርስበርሳቸው ሳይበጣበጡ እስከወዲያኛው አብረውና አንደኛው ከሌላው ጋር ተደጋግፈው እንደሚዘልቁ አጽንኦት ሰጥቼ ላስታውስዎ እፈልጋለሁ፡፡

ተወደደም ተጠላ የግንባሩ አባል የሆነውን ድርጅትዎን ኦ.ዴ.ፓን ጨምሮ ለሕገ-መንግሥቱ ቆሜያለሁ የሚለው ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ እርሱ ከፈለገ በባለስልጣናት ሹመት አሰጣጥ ረገድ ምን ያህል ከቁብ እንደማይቆጥረው ለተደራስያን ለማስታወስ እንጂ እኔ  በበኩሌ ምክትልም ተባሉ ዋና እምብዛም አያሳስበኝም፡፡ ይሁን እንጂ በያዙት መንበረ-ስልጣን ላይ የመቆየትዎ ጉዳይ ካላጠያየቀ ፈጣሪ ለቀሪው የስራና የአገልግሎት ዘመን የታረመውንና ለመልካም እረኛ የሚመጥነውን ተለዋጭ አንደበት እንዲያላብስዎ ከወዲሁ እመኛለሁ፣ እጸልያለሁም፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.