ከሰኔ 15ቱ ጥቃት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በአዲስ አበባ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ከታሰሩት ከ100 በላይ ሰዎች የቀሩት 59 ናቸው

ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ
“ካለነው መካከል ጌታቸው አምባየ ህመሙ በርትቶበታል።”
አቶ ስንታየሁ ቸኮል/የባልደራስ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ

የአማራ ሚዲያ ማዕከል ልዑክ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ በመገኘት ከሰኔ 15ቱ ጥቃት ጋር በተያያዘ ፖሊስ ጠርጥሪያቸዋለሁ በሚል ያሰራቸውን ተጠርጣሪዎች ጠይቋል።

በዚህም የአብን ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የንቅናቄው የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ አቶ በለጠ ካሳ፣ የብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አሰፋ፣ ኤሊያስ ገብሩ/ጋዜጠኛና የባልደራስ አባል፣ የአ.አ ባላደራ ምክር ቤት/ባልደራስ ህዝብ ግንኙነት አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ጌታቸው አምባየ እና አስጠራው ከበደን አግኝተናል።

ወይዘሮ ደስታ አሰፋን በመስታወት በመተያየት በስልክ አውርተናታል፤ ስለጤንነቷ ጠይቀናት ከሞላ ጎደል ደናነኝ ብላለች።

ክርስቲያን ታደለ ደህና ስለመሆኑ ቢነግረንም ከፊቱ ገጽታ ከህመሙ ጨርሶ እንዳላገገመ ተረድተናል፤ ግን መንፈሰ ጠንካራ እንደሆነ እናንተ በርቱ አይዟችሁ በቅርቡ እንወጣለን ሲል ተስፋውን ገልጾልናል።

ወጣት ስንታየሁ ቸኮል ብርቱ ነው፤ እኛ ደናነን ሲል ስለውጩ የከተማው እንቅስቃሴ ጠይቆናል። ጌታቸው አምባየ በጠና ታሟልና ድምጽ ሁኑት፤ መውጣት ይኖርበታል፤ አደራችሁን ሲል ጠይቆናል።

እርግጥ ነው ጌታቸው አምባየ ፈገግ ብሎ እየተሻለኝ ነው ቢለንም ደረቅ ሳሉ አሸንፎት ፈነቀለ፤ ምነው አልነው፤ ከደረት እስከአንገቱ እየዳበሰ አለርጅክ ነገር ነው አለን።

ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ ቁጥብ በሆነ አንደበቱ እንዲሰማን ጮህ ለማለት እየሞከረ “ከ100 በላይ ሰዎች ከሰኔ 15ቱ ጋር አገናኝተው እዚህ አስረውናል፤ በዋስም በምንም እየወጡ የቀረነው 59 ነን” አለ። እናም እንድንበረታ ነገረን።

ወጣት አስጠራው ከበደ እንደልጅነቱ ወዲያ ወዲህ እያለ አዋርቶናል። በአርአያ ሰው ሽልማት ታሪክን በመዘከር ዘርፍ እሱ የሚያስተባብረው የጊዮን ነፍጠኞች የኪነጥበብ በድን ማሸነፉን ቀድሞ ቢሰማም እኛም ነግረነው ደስታውን ተጋርተናል።

ሁላቸውም መንፈሰ ጠንካራ እንደሆኑ፤ ነገን ተስፋ እንደሚያደርጉና ከራሳቸው በላይ ውጭ ስላለው ሰው እንደሚጨነቁ ተረድተናል። እኛንም በርቱ ብለውናልና በርትተን ሙያዊ ትግላችንን እንቀጥላለን።

የአማራ ሚዲያ ማዕከል
ጥቅምት 5 ቀን 2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.