‘ህዝቤ ሆይ – የት አለህ?’ (ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ)

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ
(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡2009 እና
የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

በዓለም ላይ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከገዢ እስከ ተገዢ፣ ከመሪ እስከ ተመሪ፣ ከአዋቂ እስከ አላዋቂ፣ ከጥበብ ሰው እስከ የጥበብ ጠላት እስከኾነው ድረስ ያለ ልዩነት ያነሣውና የሚያነሣው ዐቢይ የጋራ ጉዳይ ቢኖር ስለህዝብ ስለመኾኑ በማህበራዊ የጥናት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ህዝብ ማነው? ምንድነው? በማን ይመራል? እንዴት ይመራል? ኹለንተናዊ ግንኙነቶቹ ምን ይመስላሉ? ዋና ዐምዶቹስ እንደምን ያሉ ናቸው? ከወዴትስ ይገኛሉ? በማን ተጽዕኖ ስር ይወድቃሉ? በምን? ለምን? ስለምን? የሚሉ ኹለንተናዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶችንና ጉዳዮችን የሚያጠኑ ባለሙያዎች ስለህዝብ ሰፊነት፣ ውስብስብነትና ኃያልነት አብዝተው ይተነትናሉ፡፡

በሀገራችንም ቢኾን በየመድረኩ፣ በየመግለጫው፣ በየሥነ – ጽሑፋዊ ጥበቦች (ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ የኾኑ ማንነቶቹ በሚገለጹባቸው ድርሰቶች (ልብ ወለዶችና ኢ – ልቦለዶች)፣ ግጥሞች፣ ተውኔቶች፣ ሥነ – ቃሎች፣ መነባንቦች – – – ወዘተ)፤ በእይታዊ ጥበቦች (የሥዕል፣ የፎቶግራፍ፣ የምልክት ሥራዎች፣ የፊልም፣ የድራማ፣ የጭውውት፣ የኪነ – ህንጻ ሥራዎች፣ የዲዛይን፣ – – –  ወዘተ)፤ በትዕይንታዊ ጥበቦች (የሙዚቃ፣ የትያትር፣ የውዝዋዜ፣ የጭፈራ፣ ባሕላዊ የሐዘንና የደስታ መገለጫዎች የኾኑ ተግባራት፣ ለመንፈሳዊ አገልግሎት በሚውሉ የሃይማኖት በዓላት መገለጫ – ስብከቶች)፤ – – – ወዘተ) ውስጥ ህዝብ ኃያል ተደርጎ ይቀርባል፡፡

በየትኛውም ህዝባዊ መድረኮች ላይ የፖለቲከኛና ፖለቲከኛ ተብዮዎች አፍ ማሟሻ ስለህዝብ ኃያልነት መናገር ስለመኾኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በዚህም በርካታ የመግለጫ ጋጋታዎች – በዚህ ዲስኩር ላይ የሚያጠነጥኑ ኾኖ እናገኛቸዋለን፡፡

ብዙዎች እጅግ ደጋግመው ህዝቡን ‘ጀግና’፣ ‘ልዩ’፣ ‘ተወዳዳሪ የሌለው’፣ ‘ሥልጡን’፣ ‘ቀዳሚ’፣ ‘አሸናፊ’፣ ‘ልዕለ ኩሉ የኾነ’፣ ‘ትዕግስተኛ’፣ ‘ጨዋ’፣ ‘ለፍትህ ቋሚ የኾነ’፣ ‘ለእውነት አንገቱን የሚሰጥ’፣ ‘ሃይማኖተኛ’፣ ‘የመቻቻል ተምሳሌት’፣ ‘የምሁር አብነት’፣ ‘የጥበብ ጫፍ’፣ ‘የዕውቀት ጥግ’፣ ‘ተፈሪ’፣ ‘አዋቂ’፣ ‘ትዕግስተኛ’፣ ‘ቀናኢ’፣ ‘የዋህ’፣ ‘ሰው አክባሪ’፣ ‘ነጻነት ጠባቂ’፣ ‘የማንም ባሪያ ኾኖ የማያውቅ’፣ ‘ዲሞክራሲያዊ’፣ ‘ጥበበኛ’፣ ‘ብልሃተኛ’፣ ‘የኹሉ ነገር ምንጭ’፣ ‘ራስ ወዳድ ያልኾነ’፣ ‘ስለወዳጆቹ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ’፣ ‘ኹሉን አዋቂ’፣ ‘ቀጪ’፣ ‘ኃይለኛ’፣ ‘ደፋር’፣ ‘አቻ የሌለው’፣ ‘ማንንም የማይፈራ’፣ ‘ለማንም ተንበርክኮ የማያውቅና የማይንበረከክ’፣ ‘አርቆ አሳቢ’፣ ‘ባለርዕይ’፣ ‘የኹሉ ነገር ባለቤት’፣ ‘ከኹሉ የቀደመ’ – ‘ቀዳሚ እንጂ ተከታይ ያልኾነ’ – – –  ወዘተ (የማይባለው ምን አለ – እንዲያው ከብዙ በጥቂቱ!) ሲባል መስማት የተለመደ ነው፡፡ ዕውን ህዝብ እንደዛ ነውን? ዕውን እንዲህ ያለ ህዝብ ከወዴት አለ?

ኢትዮጵያ ውስጥ በየመግለጫውና በየመድረኩ የተደሰኮሩ – ስለህዝብ የተባሉ ነገሮችን ቆጥረንና ሰፍረን በዕውነት ሚዛን ላይ ብናስቀምጣቸው ምን ይኾን የምናገኘው? ዕውን የተባለው ህዝብ የነበረ ነው? ወይስ ያለ ነው? ወይስ ገና እንዲኖር የምንሻው?

መጠይቃችንን ሰፋ ብናደርገው – የመጠይቁን አድማስ እጅግ ብናረቀው ዕውን የሃሰተኞች መጫወቻ የኾነ ህዝብ ዕውነተኛ ነውን? የሴረኞች ሰበዝ የኾነስ ሥልጡን ነውን? የኢ – አማንያን ጀርባ የኾነስ አማኝ ነውን? የሰየጠኑ መራቢያ የኾነ የራሱ ጌታ ነውን? የፈሪዎች መደበቂያ ዋሻ የኾነ ጀግና ነውን? ዕውን ኃያል የተባለ የድኩማን መጫወቻ ሊኾን ይገባልን? በስሜት የሚነዳ ምክንያታዊ – የማይጠይቅ አስተዋይ ነውን? በአላዋቂዎች የሚጠበቅ አዋቂ ነውን?

ዕውን ህዝቤ ከተባለው ይልቅ የኾነውን ካስተዋልነው – በልሳን አልባ ልሳን ባለቤቶች እየተመራ አይደለምን? ሥልጣን፣ ገንዘብና ዝና ህዝቤ ከሚባለው አንጻር በተቃራኒ የቆሙ አይደሉምን?

እነዚህ ሶስት ዐቢይ መሣሪያዎች መኾን ካለበት ይልቅ መኾን የሌለበት ነገር በህዝብ ላይ እንዲሠለጥን አላደረጉምን? ሥልጣን፣ ገንዘብና ዝና ያለው ሲዋሽ ውሸቱ እንደእውነት፤ ቢንሾካሾክ ድምጹ ጎልቶ የሚሰማ፣ ቢያስመስል ጥበብ – ቢሰየጥን ሥልጡን፣ ቢቀልድ – እንደቁም ነገር ፣ ቢሰርቅ – እንደቆጣቢ፣ ሴሰኛ ቢኾን የመጡበት እንጂ የሄዱበት ተደርጎ የማይታሰብ፣ የአደባባይ ለራሱ እንኳ ደግሞ ሊለው የማይችል ውሸት ቢዋሽ – እውነት ነው ብሎ የሚሟገትለት መንጋ፤ ቆሻሻ ማንነት ቢኖረው – እንደንጹህ ፕሮፕጋንዳ የሚሰሩለት ወዶ ገቦች፤ – – –  እንዲኖሩት የሚያስደርግ አይደለምን? እንዲህስ የሚቀበለው ህዝቤ አይደለምን?

ሥልጣንና ገንዘብ ያለው እጅግ የወረደ ትርኪ ሚርኪ ቢያወራ  – እንደቁም ነገር ተወስዶ እከሌ እንዳለው የሚባልለት በህዝቤ አይደል? እነዚህን የያዘ ነውር ቢሰራ እንደነውር ማይቆጠርበት፤ ሴረኛ ቢኾን እንደታታሪ፤ ባሪያና አሽከር ቢኾን እንደነጻና ጀግና የሚታይ በህዝቤ አይደልን?

ልሳን አልባዎች ድምጽ አውጥተው ሳይናገሩ የሚሰሙ – አለፍ ሲልም የሚደመጡ፤ አካል ኖሯቸው ውብ ባይኾኑ ከኹሉ ልቀው ውብ የኾኑ ተደርገው በህዝቤ የተሳሉ አይደሉምን? መመለክ የለባቸውም ቢባልም በተግባር ግን እየተመለኩ አይደሉምን? አይሰልጡንብን ቢባልም የሠለጠኑብን አይደሉምን?

ህዝቤ እውነተኛ ተብሎ የሃሰተኞች መጫወቻ፤ ጀግና ተብሎ የጀብደኞች መጫወቻ፤ አዋቂ ተብሎ የአላዋቂዎች መጫወቻ፤ ሥልጡን ተብሎ የስይጡኖች መደበሪያ፤ ተወዳዳሪ የሌለው ተብሎ ኃላ ቀር፤ ጥበበኛ ተብሎ ከማሰተዋል እጅጉን የራቀ፤ አርቆ አሳቢ ተብሎ ከአፍንጫቸው አርቀው በማያስቡ የሚነዳ፤ ምክንያታዊ ተብሎ በስሜት የሚሸነፍ፤ ባለርዕይ ተብሎ ርዕይ በሌላቸውና ሊኖራቸው በማይችል የሚታለል፤ አሸናፊ ተብሎ በተሸናፊዎች እንደበሶ የሚበጠበጥ፤ ኃያል ተብሎ በድኩማን የሚገዛ – – – አይደለምን?

ዕውን ህዝቤ ከአሜሪካ፣ ከእስራኤል፣ ከጃፓን፣ ከሩስያ፣ ከኩባ፣  – – – ወዘተ ህዝብ በላይ በየመድረኩ የሚደነቀው – ለምን ይኾን? ለመሸወድ ራሱን ስላዘጋጀ? ወይስ ሸዋጆች ከዚህ ውጪ አማራጭ ስለሌላቸው? ተፈልጎ ወይስ አስፈላጊነቱ ጎልቶ ታይቶ? ምን ስለኾነ ይኾን?

ዕውን ህዝብ እንደተባለው ቢኾን ፈጽመው እሱን የማይመስሉትን ከወዴት አፈራቸው? ስለምንስ ይሸከማቸዋል? እንደምንስ በነሱ ሊገዛና ሊመራ ይችላል?

አንድ ገበሬ ስንዴ ዘርቶ ቦቆሎ ቢጠብቅ – እርሱ እንጂ ማንም ተጠያቂ አይኾንም፡፡ ተመልካቾችም ብንኾን በሱ ሞኝነት እንስቅና የሞኝነት ጥግ አብነት እናደርገው ይኾናል እንጂ በምንም ተአምር ዘሩን አንወቅስም፣ የዘሩን መፍሪያ ቦታ አናማርርም – ጠባቂና መጋቢ የኾነውን ልዕለ ኃያል ስም ፈጽሞ በከንቱ አናነሳም፡፡ ያነሳን እንደኾነ ግን በዕውነት ከሱ የላቅን ግንባር ቀደም ተወዳዳሪ የሌለውና ሊኖረው የማይችል የጅል አብነት ኾነናል ማለት ነው፡፡

ህዝብ የሰው ስብስብ መጠሪያ አይደለምን? የነጠላዎችስ ብዜት ውጤት አይደለምን? ስብስቡ ንጹህ ኾኖ እንደምን ነጠላው ተቃራኒ ይኾናል? ስብስቡ ሥልጡን ኾኖ ነጠላው በምን ተአምር ስይጡን ይኾናል? ስብስቡ ባለርዕይ ኾኖ ነጠላው ርዕይ አልባ ፈጽሞ እንዴት ሊኾን ይችላል? ዕውን ያ ህዝብ ከወዴት አለ? ሳይኾን ነህ በተባለ ህዝብ ኹለንተናዊ መሠረታዊ ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ የቀን ቅዠት አይደለምን? ያልኾነውን ነህ – የሚል ሃሰተኛ! እሱንስ የሚቀበል አላዋቂ! አይደለምን? ህዝቤ ሆይ! – የት አለህ? ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.