ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የአዲስ አበባ ከንቲባ ይሁኑ!

የግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ውሣኔና ትዝታዎቻችን!

ቅዳሜ መጋቢት 7 ቀን 1997 ዓ.ም ነበር:: ወያኔ-ኢህእዴግ ዜጎችን ካናቴራ አልብሶ፣ ዐበል ከፍሎና ትራንስፓርት አቅርቦ “የምረጡኝ ድጋፍ” ሠልፍን ጠርቶ መስቀል አደባባይን በሕዝብ ጭንቅንቅ የሞላው::

“ባለራዕዩ የወያኔዎቹ የቀኝ መሪ” መለስ ዜናዊ የሠልፉ ታዳሚዎችን ብዛት ካስተዋለ በሁዋላ “እኛ ምርጫውን ለማሸነፍ ድምፅ ማጭበርበር አያስፈልገንም” በማለት ድምፅ ለማጭብርብር ተዘጋጅቶ እንደነበር በራሱ አንደበት እራሱን ያጋለጠበት ታሪካዊ ዕለት ነበር::

በማግስቱ እሁድ የዳግማ-ትንሣኤ ዕለት ማለትም መጋቢት 8 ቀን 1997 ዓ.ም ቅንጅት በጠራው የድጋፍ ሠልፍ ላይ ቅዳሜ የኢህእዴግ ድጋፍ ተገዶ የወጣውን ሕዝብ ጨምሮ የወጣው ሚሊዮኖች የአዲስ አበባ ሕዝብ ‘ትላንት ለገንዘብ ዛሬ ለፍቅር’ እያለ አደባባዩንና ድፍን ከተማዋን ቀወጠው:: ወያኔ-ኢህእዴግን “ወኔና የይመርጡኛል ተስፋን” ሆዱ ውስጥ ከተተው:: ጥቁር ቱቢት አለበሠው:: የወያኔን ጠመንጃ ሕዝቡ በድምፁ ቀጣው::

ምርጫውም ተካሄደ:: ቅንጅት ከ25ቱ የምርጫ ወረዳዎች 24ቱን አሸነፈ:: ወያኔ-ኢህእዴግ 1 ወረዳ በመመረጥ በምርጫው ተዘረረ:: የአዲስ አበባም ሕዝብ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሱን ከንቲባ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን በማድረግ መረጠ::

ከሕዝብ ፣ በሕዝብና ለሕዝብ የተመረጡ ምሪዎችን ታሪክ መዘገበ:: እኛም የታሪክ ምስክር ሆንን::

ብዙም እልቆየ ወያኔ የምርጫ ውጤቱን ቀልብሶና የሕዝብ ተመራጭ የሆኑትን የቅንጅት መሪዎችንና ደጋፊዎችን ለእስር ዳረገ:: አምባገነንንቱን አስመሰከረ:: የነአየለ ጫሚሶን የመሰለ እራሳቸውን የሸጡ አገልጋዮችን ከቅንጅቶች ውስጥ በፈቃደኝነት ማረከ::

አዎን! ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የአዲስ አበባ ከንቲባ ይሁኑ እላለሁ!
ግን ለምን?

ይህን የወያኔ-ኢህአዴግ የምርጫ ውጤት ቅልበሣን ለማስታወስ ሲባል በሕዝብ ተመርጠው ነገር ግን በከንቲባነት ሳያገለግሉ ዘብጥያ የወረዱት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው በዶ/ር አቢይ አህመድ ቢሰየሙ እወዳለሁ:: በጎሣ ፓለቲካ ገመድ ታንቆ የሚንገላታውን የሐገራችንን ፓለቲካና የፓለቲከኞቻችንን ጎሣዊ ነቆራና ፉክክር በማርገብ ፓለቲካዊ መረጋጋትን ያመጣል ብዬ አስባለሁ:: ትልቅ ዴሞክራሲያዊ ተመክሮ የምናገኝበትና በራሱ ግዙፍ ፓለቲካዊ አንደምታ እንደሚኖረውም እረዳለሁ::

የግል አስተያየቴ የመነጨው ከግል ሐሳቤና አመለካከት ነው:: እኔ የምወክለው እራሴን፣ የምሰጠውም የግል አስትያየት ለሐገሬ ሕዝብና ሠላም ይበጃል የምለውን እንጂ ድርጅታዊ ውክልና ወይም ዝንባሌ ይዤ አይደለም::

በነፃነት ጎሣና ሐይማኖት ወይም ፆታን ሳልወግን ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ መብትና ነፃነት የቆምኩና በነፃነት የማስብ አንድ ኢትዮጵያዊ ተራ ዜጋ ብቻ ነኝ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.