መንግሥት ለጃዋር የተመደቡ ጠባቂዎች እንዲነሱ ወሰነ- ህብር ራዲኦ

ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ በፓርላማ ማክሰኞ ጥቅምት 11/2012 ተገኝተው የዓመቱን የአስፈጻሚውን አካል እቅድ እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ማብራሪያ ላይ የውጭ ዜግነት እያላቸው ሚዲያ ከፍተው የሚንቀሳቀሱ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል በትዕግስት ጉዳዩን ማየት የሚቻለው ለአገር አስጊ እስካልሆነ ድረስ ብቻ መሆኑን መግለጻቸውን ተከትሎ ጃዋር መሐመድ ፈጥኖ ምላሽ ከሰጠ በሁዋላ መንግስት ያቆመለት ጠባቂዎቹ እንዲነሱ መደረጋቸውን የመረጃ ምንጮች ይገልጻሉ።ጃዋር ጠባቂዎቹ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ የተጠየቀው ከመንግስት ወገን መሆኑን የአንድ ጠባቂውን እና ትዕዛዝ ያስተላለፉ ኮሚሽነር የስልክ ልውውጥ ይፋ አድርጎ አሰምቷል።

ትዕዛዙ ከመንግስት መጥቱዋል ወይም የጃዋርን ምላሽ ተከትሎ በጸጥታ ውስጥ የሚሰሩ ባለስልጣናት ያስተላለፉት ትዕዛዝ ነው የሚለውን ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም።

ጃዋር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያ በቀጥታ ለራሱ ወስዶ በሰጠው እኛም አውቀናል ጉድጉዋድ ምሰናል አለች አይጥ ከዚህ በሁዋላ ኑራችንም ሞታችንም ኦሮሚያ ውስጥ ነው የሚል መስጠቱ አነጋጋሪ ሆኖ ውሉዋል።በዚህ ምላሽ ሳቢያ አላስፈላጊ ግጭት እንዳይነሳ በሚል አንዳንድ ወገኖች ሰከን በል የሚል ምክር በቀጥታ ቀርበው ለጃዋር እንደ ሰጡት እና ምክራቸውን እንዳልተቀበለ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይገልጻሉ።

የአባገዳ ልጆች ዛሬም አንድ ላይ ናቸው ጃዋርም ሆነ ጠቅላይ ሚ/ር አብይ ለአንድ ዓላማ ቆመዋል ብለው የሚያምኑ ወገኖች በቅርቡ ጃዋር ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርቦ በሰጠው ምላሽ “አሁን ያለነው የኦሮሞ አመራሮች ሶስት ነን አብይ አለ ለማ አለ እኔ አለሁ” እኛ አንድ ነን ሲል መግለጹን በማስታወስ ምንም የፖለቲካ ልዩነት የለም ብለው የሚገልጹም አሉ።መከራከሪያቸው ነገ በአዳባባይ አንድ ላይ ታዩዋቸዋላችሁ የሚል ጭምር ሲሆን የጃዋርን ምላሽ አግባብ ነው ብለው ያልተቀበሉም አሉ።

ሁኔታውን እንደ ፍጥጫ የቆጠሩት ግጭት እንዳይነሳ ስጋታቸውን በልዩ ልዩ መንገድ በመግለጽ የፖለቲካ ልሂቃኑም ሆኑ ተከታዮች ከብሽሽቅ እና ግጭት ቀስቃሽ መንገድ እንዲወጡ በማበራዊ ሚዲያ የጠየቁ ወገኖችም ነበሩ።

ጠቅላይ ሚ/ሩ በፓርላማ ያደረጉት ንግግር ውስጥ ጃዋር እኔን ይመለከታል ያለው የሚከተለው ነው።

<<በተለይ የዉጭ ሀገር ዜግነት ያለችሁ እና የኢትዮጵያ ፓስፖርት የሌላችሁ እዚህ ሚዲያ ከፍታችሁ የምትንቀሳቀሱ ተጠንቀቁ። ነገ ችግር ቢፈጠር እናንተ ትሄዳላችሁ እኛ ግን መሄጃ የለንም፣ የምንታገሳችሁ ምህዳሩን ለማስፋት ብለን ነዉ። በሀገር ሕልዉና ከመጣችሁ ግን ኦሮሚኛም ይሁን አማርኛ ብትናገሩ እርምጃ እንደምንወስድ ማወቅ አለባችሁ።>> ጠሚ ዓቢይ አህመድ
***
ምንጭ፦ #Hiber_Radio

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.