ጃዋር መሃመድ “አጋችና ታጋች” የሆነበት ድራማ! በያሬድ ሃይለማርያም (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

+ ማነው የዋሸው? ጃዋር? የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ወይስ የኦዴፓ ም/ሊ/መንበር?

+ መንግስት በሕዝብ ገንዘብ ጥበቃ የሚያደርግለትን ጃዋርን በሌሊት የሚከብበት ምን ክምንያት አለ? ማለቴ ተከቦ የተቀመጠው በመንግስት ጠባቂዎች አይደለም ወይ?

+ ለምን ጃዋርስ ተፈጠረ የተባለውን ነገር ሆን ተብሎ በመንግስት የተቀነባበረ እና እኔን ለማጥቃት የተፈጸመ ድርጊት ነው አለ? ማለቴ ይህ አይነት ጥርጣሬ ካለው እንዴት በመንግስት ታጣቂዎች እየተጠበቀ እንቅልፍ ወስዶት ያድራል? እንዴት እንዲህስ ሊያስብ ይችላል? ወይስ ጠባቂዎቹን የራሱ አድርጓቸዋል?

+ ከመቼ ወዲህ ነው የመንግስት ታጣቂዎች በመንግስት ተመድበው ሳለ እራሱ መንግስት፤ ሊያውም እንደ ጃዋር አገላለጽ ዋናው ኮማንደር ለቃችው ውጡ ሲላቸው እንቢ ሊሉ የቻሉት? ከመንግስት ይልቅ ታዛዥነታቸው ለጃዋር ያደላ ነው ማለት ነው?በዚህ አይነት መንግስት በሌሎች ሥፍራዎች ያሉትንስ ወታደሮች ማዘዝ ተስኖታል? ከመቼ ወዲህ ነው መንግስት የመደበው ፖሊስ እና ወታደር ትዕዛዝ የሚቀበልበትን ሰዓት የሚመርጠው? ምነው ስንቱን በእኩለ ሌሊት ቤቱን ሰብረው እያዳፉ ይወስዱ የለም ወይ?

+ ይሄ ትእዛዝ ሰጠ የተባለው ዋና ኮማንደር ማን እንደሆነስ አይታወቅም ወይ? ከታወቀስ መንግስት እንዴት አላውቅም አለ?

+ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የግል ጥበቃዎችን ስናነሳ ቆይተናል በልው ቀድሞም የተወሰነ ነገር መሆኑን ገልጸዋል፤ በጅዋር ላይ ግን ይህ ትዕዛዝ አልተሰጠም ካሉ ታዲያ ማን አዘዘ? ለምንስ ከተወሰነ በጃዋር ላይ ቀድሞ ሳይፈጸም ቀረ? ወይስ ትዕዛዝ ተላልፎለት ጭለማን ተገን ለማድረግ አድፍጦ ይጠብቅ የነበረ የመንግስት አካል ነበር?

+ አንድ ስማቸው ንዳይገለጽ የጠየቁ የመንግስት የደህንነት ባለሥልጣን ድርጊቱ በሌሊት መፈጸሙ ልክ ባይሆንም ትእዛዙ ግን ቀድሞ መሰጠቱን ከተናገሩ ክፍተቱን የሚጠቀም ድብቅ ኃይል በመንግስት ውስጥ መኖሩን አያሳይም ወይ?

+ የአቶ ሽመልስ ይቅርታስ መነሻው በመንግስት የተወሰደው እርጃ ስህተት ነው ከሚል ነው ወይ? ወይስ በሌሊት መፈጸሙ? ጥበቃው ይቀጥልልሃልን ምን አመጣው? እንዲያ ከሆነ ለምን የመንግስት አካላት እርስ በርሱ የሚጋጭ መግለጫ መስጠት አስፈለጋቸው?

+ ጃዋርስ የተፈጠረውን ነገር ለመንግስት ባለሥልጣናት በተለይም ከኦዴፓ ሰዎች ጋር ካለው ቅርበት አንጻር ችግሩን በውስጥ መስመር ከእነሱ ጋር መነጋገር እና መፍታት እየቻለ ለምን በማህበራዊ ድህረ ገጽ ለደጋፊዎቹ የድረሱልኝ ጥሩ አቀረበ? አቅሙን ሊያሳይ? ወይስ በፍርሃት ከመደናበር?

+ ጃዋር ቤት አካባቢ ደረሰ የተባለው ከበባ ምሽቱን ከሆነ የተፈጸመው ለምን ፖሊስ እና የመንግስት አካላት ሌሉቱን ሁኔታውን በማረጋጋት ሕዝቡ ወደ አደባባይ ሳይወጣ በፊት አፋጣኝ ምላሽ አይሰጡም ነበር? የአቶ ሽመልስ ካመሻሸ መግለጫ መስጠት ምን ይሉታል? ከተበጠበጠ በኋላ ማንን ሊያረጋጉ ነው?

+ በሕዝቡ መካከል የእርስ በርስ ግጭት እንዲነሳ፣ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት ማነው ተጠያቄው?

+ መንግስት በምን ምክንያት ነው ኪሱ በዶላር ላበጠ ሰው ከድሃ ሕዝብ በተገኘ የግብር ገንዘብ ደሞዝ እየከፈለ ለጅዋር ለዚህን ያህል ጊዜ ጥበቃ የሚመድበው?

+ ጃዋር በቅርቡ ለህውሃት ያቀረበው የአጋርነት ጥያቄ፣ በLTV ቀርቦ አብይ ላይ ያንጸባረቀው አቋም እና ድንፋታ፣ የጃዋር የድረሱልኝ ጩኸት እንዳሰማ ህውሃት በመግለጫ አለሁልህ ማለቷ ብዙዎች እንደሚሉት የተጠነሰሰ ነገር ይኖር ይሆን? ክስተቱ ከአብይ የውጭ ጉዞ ጋርስ ይገናኙ ይሆን? ተደጋግሞ እንደተስተዋለው በአገሪቱ የተከሰቱ ዋና ዋና ሰበር ዜናዎች አብይ እግሩ ወጣ ማለቱን ተከትለው የሚመጡ ስለነበሩ ነው።

እንግዲህ የእኔ አዕምሮ ውስጥ እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ እየተንገዋለሉ አብረውኝ ያድራሉ። ለተጎዱት ሰዎች ከማዘን ባለፈ ምን ለማለት ይቻላል።

ከላይ የተዘረዘሩት ጥያቄዎች ምላሻቸው ምንም ይሁን ምን መንግስት ግን በአገሪቱ ውስጥ የሕግ የበላይነት ለማስፈን የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባል። ሕዝቡም ለመብቱ ብቻ ሳይሆን ለሕግ አክባሪነትም አብሮ ሊቆም ይገባል።

መልስ ያላችው ወዲህ በሉ፤ እንደ እኔ በጥያቄ የተዋጣችው አብረን እንጠይቅ።

1 COMMENT

 1. ጽፉን በጥሞና ተመልክቼዋለሁ።በህዝብ እንዲሁም በግለሰብ ሲስተዋል ያለዉ ጉዳይ አገር ያወቀዉ ጸሐይ የሞቀዉ ከሆነ የከረመ ቢሆንም ከዛሬ ነገ የተሻለ ቀን ይመጣል ብለን ተስፋ ስናደርግ ቆይተናል ።
  አሁን የምን ድብብቆሽ ጨዋታ ነዉ? የፌደራል ፖሊስ ከሰጠዉ መግለጫ ጋር ፈጽሞ የሚጣረስ ሀሳብ ነዉ።
  እስከ መቼ ነዉ እንዲ አይነት የወረዱ ባለስልጣናት ህዝብ እያጫረሱ የሚኖሩት? ለዚህ ሁሉ ሁከት እና ትርምር ቁጥር አንድ ጉዳይ አስፈጻሚ አቶ ሽመልስ አብዲሳ መሆኑ ግልጽ እየሆነ ነዉ።
  ይሁንና አሁን መንግስትም ሆነ ሕዝብ በጥንቃቄ መንቀሳቀስ ያለበት ጊዜ ነዉ።
  1.ለዉጥ ማነዉ ያመጣዉ የሚል ንትርክ
  ግልጽ አቋሞ መያዝ አለበት ።ለኢትዮጵያ ነጻነት ይብዛም ይነስም ሁሉም ኢትዮጵያዉያን የድርሻቸዉን ተወጥተዋል እየተወጡም ነዉ ያሉት ።ስለሆነም “እኔ ነኝ ለዉጥ ያመጣዉት” እና “እኛ ነን ባለተራ” የሚል እብሪት አገርን ለልቂት የሚዳርግ የረከሰ አስተሳሰብ ስለሆነ እርምት ይደረግ ።በአድዋ;በካራማራ;በማይጨዉ እንዲሁም በተለያዪ የጦር አዉዶች ላይ ደማቸዉን ያፈሰሱት አጥንታቸዉን የከሰከሱ አባቶቻችን ለብሔራቸዉ ብለዉ ሳይሆን ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማቆም ብለዉ ነዉ ።ስለዚህም እኔ አዉቅልሐለዉ ጥበት እና ንትርክ በአስቸኳይ ይቁም ።
  2.ወገንተናዊ አደረጃጀትና መዋቅር በአስቸኳይ መፍረስ አለበት ።አሁን በአለንበት ሰአት በክልል አና በሰፈር የተደራጁ የክልል ፖሊስና ሚሊሻዎች መዋቅራቸዉ ፈርሶ በአዲስ አደረጃጀት ቢዋቀር የተሻለ ይመስለኛል ።ለምሳሌ “የኢትዮጵያ ፖሊስ “ወይም “የኢዮጵያ ጸጥታ አስከባሪ” በሚል ለማንም ያልወገነ አደረጃጀት ቢሆን ጥሩ ነዉ ።
  3.በአክቲቪስትም ሆነ በጋዜጠጭነት ስም ተሰማርተዉ ህዝብን ሚዛናዊ ባልሆነ እንዲሁም እዉነተኛ መረጃ በሌለበት በዉሸት ትርክት ህዝብን ለሁከት;ለዘረፋ እና ለግድያ ሲማግዱ የነበሩትን ግለሰቦችን እና ድርጅቶችን ከህግ በታች እንዲሆኑ በቂ የሰዉና የሰነድ መረጃ በማጠናከር ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ ።
  4.በዜግነት አሜሪካዊዉ በትዉልድ የመናዊ የሆነዉን ጃዋር መሐመድ ላለፉት አንድ አመት አገሪቷን “በማን አለብኝነት” በማተራመስ ነገ እኛ ወደ ማያበራ የእርስ በርስ ጦርነት ዉስጥ ስንገባ እና ኢትዮጵያ “ምድራዊ ሲኦል” ስትሆን አገር ለቆ ወደ አገሩ የሚሔደዉን ጃዋር መሐመድን ለሕግ ተገዢ እና ከህግ በታች እንዳሆን ለማረጋገጥ በቂ መረጃ በማሰባሰብ በአስቸኳይ ለህግ እንዲቀርብ ማድረግ ።
  5.ሕዝብን ባልተጨበጠ መረጃ ለሁከትና
  ለጦርነት የሚቀሰቅሱ ሚዲያዎች በአስቸኳይ ይዘጉ ። በጥቂቱ OMN,DW(ድምጸ ወያኔ),LTV,SMN,ASRAT እና ሌሎችም ደግሞ ማስጠንቀቂያ መስጠት እና የእርምት እርምጃ መዉሰድ ይገባል ።ትኩረት መደረግ ያለበት ጉዳይ “የሚዲያ ነጻነት” ማለት መንኛዉም የሚዲያ ተቋም የሚያስተላልፈዉ ዘገባ በመረጃ የተደገፈ እና ሚዛናዊ የሆነ ጉዳዮችን ማቅረብ ነዉ እንጂ ሚዲያን “ለጦርነት ነጋሪት መጎሰሚያ” መሆን የለበትም ።
  6.ከዚህ ቀደብ ብዙ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የፈለጉ ማህብረሰብ ተጨባጭ ባልሆነ ምክንያት ተከልክለዋል ።አሁን ግን ማንም ወንበዴ ለዘረፋ ;ለግድያ እና አገር ለማፍረስ በመንጋ አደባባይ ሲወጣ ዝም ተብሏል ።ስለሆነም ማንኛዉ ሰልፍ ለመዉጣት ቢፈለግ እንኳ ሕዝብ እና መንግስ አዉቆ እንዱሁም የሚዘጉት መንገዶች ቀድመዉ ታዉቀዉ መሆን አለበት ።
  ባጠቃላይ በኢትዮጵያ የመጣዉን ለዉጥ እናደናቅፋለን ብላችሁ በመንግስት መዋቅር እና ከዳር ቆማችሁ ነዳጅና ቤንዚል የምታቃብሉ ግለሰቦችም ሆናችሁ ድርጅቶች ብዙ አትልፉ ኢትዮጵያ መድረስ ከምትፈልገዉ የእድገትና የብልጽግና ማማ ማንም ሊያቆማት አይችልም ።
  ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.