የቻለ ፓርላማ ያልቻለ ፓልቶክ ይግባ (ሄኖክ የሺጥላ)

የሆነው ይህ ነው
ወያኔ-ትግሬ ( የትግራይ ሰው የሆኑ የሀገረ ኢትዮጵያ ብሔር ሽፍቶች ) ፣ ስልጣን ላይ ወጡ ፣ ህዝቡ አጨበጨበ ፣ ሙህራኖች ከሚኖሩበት ሃገረ አማሪካን ፣ እንግሊዝ ፣ ጀርመን ወዘተ፣ ወዘ-ተርፈ ተጏዙ ፣ የተማሩት ሀገራቸውን ሊያገለግሉ ፣ እውቀታቸውን ሊያካፍሉ በየ ትምህርት ተቋማቱ ገቡ ፣ የቻሉት ቤተ- መንግስት ድረስ ዘለቁ ፣ ከያኔው ጠቅላይ ሚንስትር ጋ ተጨባበጡ ፣ ብርጭቆ አጋጩ ፣ አብረው ለመስራት ተስማሙ ፣ እንደውም አንዳንዶች እንደ ቀብድ አማራን የሚኮንን መጽሐፍ ጻፉ ።
ጊዜው ነጎደ ፣ ህውሃት ከተማ ሲገባ ፣ በሰላምና መረጋጋት ስም ሌባ በአደባባይ በመረሸን ፣ በአንቀጽ 39 ስር ፣ በሽግግር መንግስት እና ወዘተ ስር ደብቆት የነበረው ቀንዱ ወጣ ። ከሀገረ አማሪካ ከህውሃት ጋ ለመስራት የሄዱትን ሙህራኖች አሰረ ፣ ውዳሴ ህውሃት ወይም እርግማነ አማራ መጽሐፍ እንደበረከት ያቀረቡለትን አባረረ ፣ ከዚያ ድብድቡ ተጀመረ ።

ቀጠለ ። ታላላቅ የዩንቨርስቲ መምህራንን አባረረ ፣ እነ ዶክተር ታዬ ወ/ሰማ’ትን እና እነ ፕሮፌስር አስራት አሰረ ፣ በላዩ ላይ እኔ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋንና እነ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን ጨመረበት ። ጥሉ ከረረ ። አሁንም ቀጠለ ። እነ አንዳርጋቸው ጽጌን ተፋታ ፣ እነ ብርሃነ መዋ እና እነ ክቡር ገናን አብጠለጠለ ። በዚህ ውሃ ውስጥ ሌሎች የኢሰመጉ አመራር አካሎች ፣ የመኢአድ ባለስልጣናት ፣ የሃይማኖት ሰዎች ተበሉ ። ሁኔታው ቀጠለ ፣ ሌባ በአደባባይ ከግንቦት 22 1983 እስከ ዛሬ እየገደለ ያለው ስርዓት ፣ ራሱ የወጣለት ሌባ ሆነ ።

ሲጀመር አብረው ለመስራት ከዚህ ከአማሪካ ተሳፍረው የሄዱት እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ማርሽ ቀየሩ ፣ ፊታቸውን እስከ ምርጫ 97 በከፊል አዙረው የምርጫ 97 ለት ጎራ ለዩ ። ባንድ ወቅት እጁን የጨበጡትን ጠቅላይ ሚንስቴር ስልጣኑን እንዲለቅ ሞገቱት ፣ ሞግተውትም አልቀረም ዘረሩት ። የዘረሩት ህውሃት ግን ከካርቶን ፌንቱ ተነስቶ የቅንጅት አመራሮችን አሰረ ። እነሱም ባጋጣሚ ባገኙት ድል እንደ ባቢሎን ሰዎች ልሳናቸው ተዘበራርቆ ስለነበር ተቦጫጨቁ ። ኃይሉ ነው ፣ ብርቱካን ናት ፣ ብርሃኑ ነው ፣ ወዘተ ወዘተ ተባባሉ ። ( በነገራችን ላይ ስለዚህ ሁኔታ ሳስብ ዛሬም ድረስ ያሳፍሩኛል ፣ ሀፍረቴ የሚመጣው ደሞ በጥቅምት 22እና 23 1998 በአደባባይ የተገደሉት ልጆች ሰልስት ሳይወጣ እነሱ ንትርክ በመጀመራቸው ነው ) ። በነገራችን ላይ ቀኑን ጠብቀን ” ቅንጅትን ማን አፈረሰው !” የሚል ጽሑፍ እናወጣለን ። በይበልጥ የኔ ብርሃነ መዋ እና የሌሎች የዛሬ ጀግኖቻችን አስተዋጾ ምን እንደነበር እናትታለን ። ምክንያቱም የስራ ልምድ () ማንነትን በደንብ ስለሚገልጥ ። አሁን አላማችን እሱ ስላልሆነ ወደ ዋናው ሃሳብ እንገስግስ ።
ከፈርሱት የቅንጅት አመራሮች ውስጥ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደ አማሪካን በመምጣት ፣ በሃሳብ፣ በራእይ፣ ርዮት እና በወዳጅነት አብረው ከዘለቋቸው ሰዎች ጋ በመሆን ግንቦት ሰባትን መሰረቱ ። የግንቦት ሰባት እውቅና በሚድህበት ሰሞናት ፣ ህውሃት ግንቦት ሰባትን ማስተዋወቅ ጀመረ ። አሸባሪ ብሎ ሰየመው። ሊቀመንበሩን እና ሌሎች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሎቹን በአሸባሪነት ከሰሰ ። አሁን ላይ ሆኘ ሳስበው ህውሃት ይህንን ያደረገው የሚመስለኝ ለአንድ ነገር ሲል ነበር ። እንደምናቀው “አሸባሪ እዚህ አገር ታየ!” ብለው ያለ ምንም እውነት የሰው ሀገር እንደሚደበድቡት ምዕራባውያን ፣ ወያኔም ግንቦት ሰባትን የሚፈልገውን ለማሰር እና ለማጥፋት ማሳበቢያ ለማድረግ ነበር ። በዚህም የተንሳ ብዙ የብሔረ አማራ የጦር አዛዦች ከስልጣን ተባረዋል ፣ በየ መአከላዊው ታስረዋል ፣ ተገለዋል ። ብዙ ነጻ ጋዜጠኞች ( ምሳሌ እስክንድር ነጋና እና አንዷለም አራጌ ) ፣ እንደ ዞን 9 ያሉ የድህረገጽ ሞገደኞች ፣ እና ወዘተን ። ( በነገራችን ላይ ህውሃት አሸባሪነትን የማይፈልገውን ትግሬ ያልሆነ ብሔር ከስልጣን ማባረሪያ ምክንያት አድርጎ ሲጠቀም ግንቦት ሰባት የመጀመሪያው ድርጅት አይደለም ፣ እንደውም ከግንቦት ሰባት ቀደም ብሎ ብዙ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ባለስልጣናትን በኦነግ ስምነት አስሯል ፣ ገሏል ፣ ወዘተ )።

ታዲያ በዚህ ሁናቴ ላይ እያለ ነው ህውሃትን የማይመጥን ስህተት የተሰራው ። ግንቦት ሰባትን ከመንግስት ግልበጣ ጋ ያያያዘ ዜና አፈትልኮ ወጣ ። ያቺ ቀን ለግንቦት ሰባት ከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ሥራ ሰርታ አለፈች ። በዛ ውለታው ውስጥ ግን ብዙ የጦር መኮንኖችን መአከላዊ አስገብታ ማሰቃየት ጀመረች ። እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ሰሞን ላይ ነው ኢሳት የተመሰረተው ። ( ምን ያህል እውነት እንደሆነ ባላውቅም ፣ ይህንን ኢሳት የሚባለውን ነገር በሃሳብነት ካፈለቁት ሰዎች መሃከል አንዱ አቶ ክንፉ አሰፋ ( የኢትዮጵያ ሚዲያ ፎረም ድህረ ገጽ ዋና አዘጋጅ ) እንደሆነ ሰምቻለሁ ። ምስጋና ሃሳቡን ላፈለቁት ። ሌላ ምስጋና ያንን ሃሳብ ላላባከኑት ! ( ለሰረቁት አላልኩም !) የግንቦት ሰባት ምናባዊ ጥንካሬ ወደ ቁሳዊ ህልውና ቀስ እያለ መቀየር ጀመረ ። በተለይም ትኩስ ሁኔታዎችን ለማብራራት በኢሳት መስኮት ላይ በተደጋጋሚ ብቅ እያሉ አስተያየታቸውን የሚሰጡት ዶ/ ር ብርሃኑ ነጋ ፣ ስለ አስመራ ጉዟቸው እና ቆይታቸው የነገሩን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ፣ የራሱ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መታሰር ፣ የነ-መሳይ መኮንንና ፋሲል የኔ ዓለም የአስመራ ቆይታ ፣ ጦሩ ፣ ሳንጃው ፣ የግራር ክላሹ እና ወዘተ ነገሩን አሟሟቀው ። ግንቦት ሰባት ከአርበኞች ጋ ተዋሐደ ፣ ኢሳት እያንዳንዷን ነገር አስተላለፈ ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ይህንን መጀመሪያ መስማት ከዚያ ማዳመጥ ጀመሩ ። አንዳንድ ወዳጆቼ (የማቃቸው እና የማላውቃቸው ሰዎች ) ፣ በየት በኩል ጫካ ልግባ የሚል ጥያቄ ያጎርፉልኝ ጀመር ። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን ፣ ከዚህም ሁኔታ ቀደም ብሎ ፣ ምርጫ 2007 ድሆ ድሆ ከተፍ አለ ፣ ወያኔ-ትግሬ የለመደውን ውንብድና ጀመረ ። በቀን ጆሯቸው ምርጫውን በግራ ጆሯቸው ኢሳትን ሲያዳምጡ የከረሙት የአንድነት እና መኢአድ አባሎች ፍትህን ሲነፈጉ ፣ ፍትህ ልናገኝበት እንችላለን ወዳሉት ወደ ኤርትራ ጫካ ገቡ ። እንደኔ እምነት ( ከሚደርሰኝ መልእክት እና መረጃ ኢሳት ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ጋ ያደረገውን ቃለ ምልልስ ጥበብ በተሞላበት መንገድ አድርጎት ቢሆን ምናልባት ዛሬ አሁን ካየነው በተሻለ “የሰው ጎርፍ ” አርበኞች ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል በሄደ ነበር )። አሁንም ቢሆን የምወደው እና የማከብረው ኢሳት እዚህ ጉዳይ ላይ በጥንቃቄ ይሄድ ዘንድ እንመክራለን ።

ምርጫው ቀጠለ ፣ መድረክ እንደለመደው ዛሬም ፓርላማ ገብቶ መሰዳደቡ እንደናፈቀው እገምታለሁ ( መድረክ ስል በተከታዮቹ እና መሪዎቹ መሃል ያለ የነጻነት አስተሳሰብ ልዩነት እንዳለ እጅግ ስለሚገባኝ ነው )። አንቦ ላይ መድረክን ደግፎ የወጣውን ሕዝብ አዲስ አበባ ላይ ቅንጅትን ደግፎ ከወጣው የ 1997 ሕዝብ በምንም ለይቼ አላየውም ። ሁለቱም ስርዓቱን ከመጥላት እና በስርዓቱ ተስፋ ከመቁረጥ የታየ እና አጋጣሚውን በመግለጽ ንዴቱን ለመግለጽ የወጣ ሕዝብ ስለመሆኑ ዶ/ር መራራ ጉድና በደንብ ያወቀዋል ። ብልጥ ፖለቲከኛ ስለሆነ እንደለመደው ያንን ኃይል ወደ ወንበር ለመቀየር እየትጋ ነው እንጂ !

ሰማያውዊም እስሩን ፣ እንግልቱን ፣ ስቃዩን እና መከራውን ተቋሙሞ ዛሬ ላይ ደረሰ ። ምርጫው ደረሰ ሰማያዊ ም አለሁ አለ ። እስከሚገባኝ ታዲያ የሰማያዊ ሃሳብ ኢፍትሃዊ በሆነ ምርጫ ተሳትፎ የተሰጠውን ድምጽ ይዞ ፓላማ መግባት እና የመንግስት ደሞዝተኛ መሆን ፣ ከዚያም በቴሌቪዥን በሳምንት ወይም በወር አንዴ እየቀረቡ ወያኔ ወስኖ ለጨረሰው ጉዳዮች ድምጽ አለመስጠት አይመስለኝም ። እሱ ከሆነ እኔም እንደ ብርሃኑ ነጋ የምርጫ ካርዳቹን ቅደዱት በሚለው ሃሳብ ላይ እስማማለሁ ። እኔ እማስበው ሰማያዊ ከዚያ የተለየ ማንነት አለው ብዬ ነው ። ጫካ መግባት አማራጩ የማይሆን የሚሆነው ፓርላማ ለምግባት ሰለወሰ ነው ብዬ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ አላስብም ። ምክንያቱ ግን ያ ከሆነ አሁንም የምርጫ ካርዱን ቅደዱት በሚለው ሃሳብ እስማማለሁ ። ባንጻሩ ግን በአሁኑ ሰዓት እንደ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ በጭንቅላታችሁ የያዛችሁት ሃሳብ ” የሆነለት ፓርላማ ፣ ያልሆነለት ፓልቶክ ይግባ ” የሚል እንዳልሆነ ስለማምን የምርጫ ካርዱን ቅደዱት በሚለው ሃሳብ ብዙም አልስማማም ።

እስከ መጨረሻው መጀመሪያ ድረስ በመታገል አምናለሁ ። የናንተ መንገድ ዛሬ የናንተ ብቻ ነው ፣ ነገ በምትወሱነት አካሄድ ወይ የናንተ ብቻ ሆኖ ይቀራል ወይም ደሞ ወደ ሕዝብ የኛነት ይቀየራል ።

ሄኖክ የሺጥላ

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.