እረፍት የነሳኝ ጉዳይ – በአቶ ታዬ ደንደአ በኩል ይድረስ ለዖሮሞ ልጆች (ከአባዊርቱ)

ቦሶኑን በቅፈቴ ራንዳ ጉባ ባቴ
ቁፍኒሺ ባያቴቱ ቢኔንቲ ቱፋቴ
“ጫማ ቃቃማና ”  ጄቴ ሌንጫን ያምቴ!!
ሌንጪስ ዱቢን dhiቤ ያማሺን ኮልፌቶ
አታም ናቱፋናን ቡኬdhaን ላሌቶ
ኢራጋሹ ዴሜ ባካሺን ጂርቱቲ
ዮሚዩ ቦሶኑን  ሲላስ ሌንጫ ሚቲ
ታዬ ያባቀልቢ  ቱን ዱቢን ሲጋልቲ?!!
ለተቀራችሁ ወገኖቼ ዖሮሚፋን ለማትረዱ ፣ ምንም እንኩዋ መልክቱ በአቶ ታዬ በኩል ቢሆንም፣ ሃሜት ያስመስላልና (ዘመኑም ክፉ ነውና) በግርድፉ እንዲህ ልተርጉምላችሁ። በዖሮሚፋ ያደረኩት ጅምሩን የልቤን ስለሚገልጽልኝ ነበር።
እነሆም!
አሽቃባጭ ድኩላ አፋፍ ተስፈንጥራ
ደንደሱዋን ተማምና ትእቢት ተወጥራ
አንበሶን ጠራችው ልታቁዋደስ ጮራ።
አንበሶም ተገርሞ ባሽቃባጭዋ ጥሪ
እንዴት ብትንቀኝ ነው የሌላት መካሪ
እመር ብሎ ዘሎ ወጥቶ ባለችበት
አንበሶ ድኩላን አደረጋት ዱቄት
ታዬም  ይገባሃል የዚህ ስንኝ ትውፊት።!!!
ይህን ካልኩ በሁዋላ ፣ ላንተና ለመላው ኢትዮጵያን ለምትሉ ሁሉ ትውልደ ዖሮሞ ለሆናችሁ የሚከተለውን አስተላልፋለሁ።
አገራችን በብዙ መልኩ እድል ሆነና ከአብራኩዋ በወጡ ልጆችዋ አልታደለችም። በተለይም ከ 50 አመታት በሁዋላ በተፈጠሩ ልጆቹዋ። ዝርዝሩ ውስጥ አልገባም፣ ለእውነትነቱ ግን ዛሬ ያለንበት ሁኔታ ፍንትው ያደርገዋል። ስለሆነም ለምን ይህ ሆነ ብዬም አላደክማችሁም፣ በቀጥታ ወደሚታየኝ መፍትሄ እገባለሁ።
፩) በየቤታችሁ እንደኔ የምትቃጠሉ የዖሮሞ ልጆች ድምጻችሁን አሰሙ። በተለይም ጥንትም ዛሬም የኢትዮጽያ ስም ሲነሳ የሚያብከነክናችሁ የሸዋ ዖሮሞ ልጆች። ለመሆኑ በባሌ ክርስትያን ዖሮሞ ወገኖቻችን እንደሞቱ አልሰማችሁም? ጁዋር የተባለ ሜርሲነሪ እውን የሚሰራው የአክራሪ ኢስላሚክ የአይሲስ አይነት  ዖሮምያ ምኞት ካልሆነ የጤና ይመስላችሁዋል?
፪) ይህ ጁዋር የተባለውን ሰውዬ ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ አውግዙ። በመክሰስም ሂደት ተባበሩ። ይህ ሰው ለአገራችንና ለህዝባችን በጭራሽ የማይበጅ ጥቅመኛ ነውና። ሰውዬው ያበቃልኝ በተለይ እሱ በቆሰቆሰው እሳት የሞቱት አስከሬኖች ጉድጉዋድ ሳይገቡ ቅልቦቹን ስጋ ያበላ እለት ነው። የማውቀው አስተዳደግ  እንኩዋንስ ወገን  ወገን ሞቶ ስጋ ሊበላ ያውም አስከሬን  አፈር ሳይለብስ ይቅርና ስጋ ባለበት መቆም ትልቅ “ሰፉ ” ነበረው። ይህን ሰውዬ በአፍ ማውገዝ ብቻ ሳይሆን በህግም የሚቀፈደድበትን መንገድ በጋራ መምከር የግድ ይላል።
፫) መጠላለፍና መናናቅ ይቁም። ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ በየግሉና መሰሎቹን እያፈላለገ በህብረት ዘብ ይቁም። ስንቱ አቅመደካማና ህጻናት ፍርሃት ውስጥ እንዳሉ መገንዘብ አያዳግትም። በህብረት ሰላማችሁን አስከብሩ። አንድነት ኃይልም ነውና።
፬) እንደ ኢትዮጵያ መስሊምና ክርስትያን የተገመደበት ሀገር ጨርሶ የለም። የጁዋርን ክርስትያን ወገኖቻችንን ትንኮሳ ሙስሊም ወገኖቻችን ፉርሽ እንደሚያደርጉት በሂደት ባልጠራጠርም፣ በጊዜያዊነት እንኩዋ ለአፍታም ቢሆን  በባሌ የሆነው የሺህ አመታት መጋመዳችንን እንዲፈተን አልሻም። ስለሆነም እንጠንቀቅ። እንደ ሙፍቲ ኡመር አይነት አንደበተ ወርቅ አባትም ያብዛልን። ይህ ድልብ ጁዋር ከቶ ሙስሊምም ሊሆን የማይችል ብቃቱም የሌለው ሰው ነው። እየሩሳሌምን መሳለም ጻድቅ እንደማየደርግ ሁሉ መካ ሄዶ ሀጅ መባልም የብቃት መለኪያ አይደለም። የብቃት ቢሆን ዲያብሎስን የመሰለ አዋቂ አልነበረም ከንቱ ሆነና ጸጋው ተገፈፈ እንጂ ይሉኝ ነበር መምሬ ለቺሳ (የልጅነት መምህሬ)
የተከበርክ ታዬ ደንደአ!
አንተን ለይቼ ለምን ባንተ በኩል ጻፍኩ? እንዲህ ነው። ባሁን ጊዜ እንኩዋንስ ሃጢያቱን ባደባባይ በማጀትም  ጁዋርን መቃወም ፋሽን ባልሆነበት በዚች ፈታኝ ጊዜ እውነት ከንክናህ ወንጀሉን ባደባባይ በግልህ የተናገርክና የኮነንክ ሰው በመሆንህ ነው። እኔ እንኩዋ ስህተት ብዬ አንተን የወቀስኩበት ጊዜ ባለፈው አላስፈላጊ እልክ ገብተህ ከአማሮቹ ጋር እሰጥ አገባውን ነበር ያልወደድኩልህ። ስህተትም ነበር። ዖሮሞ ብቻውን አለቀሪ ወገኖቹ ዬትም ኢትዮጵያን አያደርሳትም። የዖሮሞ ብቸኛ አገር እንፈጥራለን ብለው ሌት ተቀን የሚባዝኑ ዖነጎች በቀር። የዖሮሞን መብት እናስከብራለን ቀረና ዖሮምያ አገር እንፈጥራለን የሚሉት ቅዠት ስለ እውነት ከልባቸው አይመስለኝም ነበር እስከ ቅርብ ጊዜ። ይህ የጤንነት አለመሆኑን እንዳንተ አይነቱ ኩሩ ዖሮሞ ድምጹን ከፍ አርጎ ማሰማት አለበት። በአገር ይሉኝታ ያውም የፖለቲካ እርባና ቢስ ነውና። አስተዋዩ መረራ ጉዲና እንዳደረገው ሁሉ። ከሁሉ ሳልጠቅስ የማላልፈው አሳፋሪው ምሁር ተብዬው ገመቹ፣ መስቀል ያሰርነውን ትውልደ ዖሮሞዎች አማሮች ናቸው ብሎ ያሳለቀብንን ሰውዬ እስከ ህልፈት አልረሳውም። ያገራችን ትምህርት ምን ቢወርድ እንዲህ መዝቀጡን በጭራሽ አስቤውም አላውቅም ነበር። ልጆች ካሉት እንዴት ይፈሩበት። እናንተስ ክርስትያን ወገኖቼ ምን ተሰማችሁ? ለዚህም ይሆናል የባሌ ዖሮሞ ወገኖቼ ለእርድ የቀረቡት። ለገመቹና ጁዋር ቢጤ ገልቱዎች አማሮች መሆናቸው ነውና። ይህ ወገኔን ካላቃጠለ ውሎ ሲያድር በየቤቱ የሚመጣበትን ያየዋል። ከመሆኑ በፊት ኢትዮጵያ ሁሌም የምትመካብህ የሸዋ ዖሮሞ ሆይ አይንህን በትልቁ ክፈት። ጫን ያለው ተሰንቆልሃልና!!!
በመጨረሻም!
ይቺን መልክት ለክቡር ለማና አቢይ አድርስልኝ።
በጁዋር በተባለው ሰውዬ ላይ በአስቸኩዋይ ሲሆን በግዳጅ ከአገር እንዲያስወጡልን፣ ከወጣና መውጣቱ ከተረጋገጠ በሁዋላ በአገሩ በአሜሪካ ፍርድቤት እንዲያቆሙልን እንዲያደርጉልን። ይህን ካላረጉ ግን ምንም ለጊዜው ቢረግብ በኢትዮጵያ ምድር ሰላም ይመጣል ማለት ዘበት ይሆናል። ሌላው የፈለገው መስዋት ተከፍሎ ባለፉት አመታት ግፍ የሰሩብን ዜጎች በተለይም በአደባባይ አቃቤህግ ክስ የመሰረተባቸው ቀድሞ ባለስልጣናትን ካላሰሩና ወደህግ ካላቀረቡ በአስቸኩዋይ ፣ የጨለማ ጉዞ ይሆናል። ይህው ነው። ክስ የተመሰረተባቸው ግፈኞች እያሉም  ፈረንጁን ጁዋርን ማሰሩ ትርጉም አልባ ይሆናል። ባይሆን የጁዋር የሚለየው ፈረንጅ ስለሆነ በ  24 ሰአታት ውስጥ ከአገር ይባረርልን። ፍትሃዊ ጥያቄም ነው።
የመጨረሻው ማሳሰቢያዬ፣ በምንም ተአምር መጪውን ምርጫ እንኩዋንስ ሊያስፈጽሙ ቀርቶ እንዳያስቡት ተማጸንልኝ። ለምን? እንኩውንስ ለኢትዮጵያ ለራሳቸውም የማይበጅ፣ የጠላቶቻችን እኛን ማጥፍያ ፈንጂ  የታቀደልን በመሆኑ። የመደመር ምስጢር እንኩዋንስ በወራት በአመታትም ቦዘኔና ምድረሜርስነሪ አይምሮ ውስጥ ከቶ ሊሰረጽ አይችልምና። ሌላው ማሳሰቢያ የቀድሞ ሰራዊት በአማካሪነት የሚያገለግሉ ብዙ አሉና ይታሰብበት። በአገራችን ጦርነት ታውጆ እነሞአ ዘጥበባትን ቀነስ አርጎ ጦር አክሻፊ አማካሪዎች ቢበዙ ወቅቱ ነው። ዳንኤል ክብረት መልካም ሰው ነው። ወቅቱ የመንግስትን ልክ የምናይበትና ህዝቡ፣ አዎ፣ እንዳመጣጡ የተቃጣበትን አምካኝ እንጂ የሀይማኖት አማካሪዋች አያስፈልጉንም። ቀሳውስትና አንድ ሙፍቲ ኡመር ኡመር ብሎም አባገዳዎችና ምእመን በየቤታቸው ከበቂ በላይ ናቸው። እባካችሁ እንደኔ አንጀታችሁ ያረረ ሁሉ ድምጻችሁን አሰሙ። ያየናት የብርሃን ጭላንጭል ጽልመት ልትለብስብን ነውና። አስጨናቂ ዘመን!!
አባዊርቱ ነኝ
የአገሬ ሁኔታ ጤና የነሳኝ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.