“በአጉራ ዘለል መንግስት ነን እያሉ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ መንግስት የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል፡፡” አቶ ንጉሱ ጥላሁን

መንግስት በጥፋተኞች ላይ የማያወላዳ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ፤ ከሰሞኑ ሁከት ጋር በተያያዘ እሳከሁን 409 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ነው ብሏል መንግስት።

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች፣በሀረሪ ክልልና በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በተፈጠረው አለመረጋጋት በርካታ ዜጎች ሞተዋል፤ አካላቸው ጎድሏል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ለመገናኛ ብዙኃን ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ንጉሱ በተፈጠረው ችግር ለሞቱ፣ ለተጎዱና ሀብትና ንብረታቸውን ላጡ ዜጎች መንግስት የተሰማውን ሀዘን ገልጸዋል፡፡ በመግለጫቸው እንዳስታወቁት ችግሩ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች 78 ንጹህኃን ዜጎች ሞተዋል፡፡

መንግስት ጥቃቱ እንዳይስፋፋና እንዳይባባስ እየሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ ንጉሱ በጉዳዩ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ስር የማድረጉ ስራ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ እሳከሁንም 409 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ነው ብለዋል አቶ ንጉሱ፡፡

ግጭቱ እንዳይባባስ የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡ የፀጥታ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና የሀይማኖት አባቶችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ጉዳት ለደረሳባቸው አካላትም ደራሽ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ድርጊቱ ተመልሶ እንዳይከሰትና ሰላም እንዲሰፍን በጥብቅ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ንጉሱ ችግሩ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ውይይት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ሀገሪቱ እስካሁን የመጣችበት የማንነት ፖለቲካ አሁን ለመጣው ችግር ዋነኛ ምክንያት እንደሆነም አቶ ንጉስ ተናግረዋል፡፡ ከአንድነት ይልቅ መለያየትን የሚሰብኩ የፖለቲካ ሰዎችም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም ጠይቀዋል፡፡ መንግስት ለሚፈጠሩት ጉዳዮች በሆደ ሰፊነት ሲከታተል ቆይቷል ያሉት አቶ ንጉስ ከዚህ በኋላ ሕግ የማስከበር ስራውን በአግባቡ ይሰራል ነው ያሉት፡፡ በንጹሃን ዜጎች ደም ላይ የሚቀልዱትን ሰዎች እንደማይታገስና ህግ የማስከበር ስራው ጠንካራ እንደሚሆንም ነው ያረጋገጡት፡፡

የኢህአዴግን ውህደት በተመለከተም ያነሱት አቶ ንጉሱ ከእህትና አጋር ድርጅቶች ጋር መግባባት ላይ እንደተደረሰ ገልጸው የሚቃወሙት ቢኖሩም ውህደቱ የማይቀር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለውህደት የሚሆን ምክክርና ጥናት እንደተደረገም ነው አቶ ንጉሱ የገለጹት፡፡ ከዚህ በኋላ በሞግዚትና በጡት አባት መተዳደር በኢትዮጵያ ውስጥ የማይተገበር ነው ብለዋል፡፡ አለመዋሃድ መብት ነው፤ መዋሃዱ ግን የማይቀር ነው ብለዋል፡፡ ጥቅምት 11/2012 የተደረገው ጥሪ ለግጭት መዳረግ እንደማይገባው ያነሱት ኃላፊው የተጠያቂነት ስራው ማንም ይሁን ማን የማይቀር ነውም ብለዋል፡፡ በመሆኑም በድርጊቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ሁሉ ተጠያቂ ይሆናሉ ነው ያሉት፡፡

ባለፉት 18 ወራትም 3 ሺህ 221 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች እንደተያዙና ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑት ለህግ እንደቀረቡ አቶ ንጉሱ ገልፀዋል፡፡ መንግስት ህግን እያስከበረ አይደለም የሚባለው ተገቢ አይደለም ያሉት አቶ ንጉሱ፣ በሀገሪቱ ሁለት መንግስት አለ የሚባለውም ደባል መንግስት የለም፤ በአጉራ ዘለል መንግስት ነን እያሉ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ መንግስት የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት፡፡

ኃላፊነት የጎደለው ዜና የሚያሰራጩ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶችና የማህበረሰብ አንቂዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት አቶ ንጉሱ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አቅጣጫ ተሰጥቶታልም ብለዋል፡፡

ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችን ለማስተካከል እየተሰራ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ ከሰሞኑ በተፈጠረው ችግር እጃቸው ያለበትን የፀጥታ አካላት የማጣራት ስራ እየተሰራ እደሆነም ገልጸዋል፤ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የተወጡትን ደግሞ አመስግነዋል፡፡ አቶ ንጉሱ በችግሩ ወቅት የተፈጠረው የመግለጫ አለመናበብ ዋጋ እንዳስከፈለም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡-ጋሻው ፋንታሁን – ከአዲስ አበባ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.