ታላቁ ተቃርኖ በኢትዮጵያ “የስለት እና የእንጀራ ልጆች”!

የህግ የበላይነት እንደአሁኑ የሀገራችን ሁኔታ አቅም አጥቶና ተሽመድምዶ ሲታይ የህግ አዋቂዎችን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ያሳዝናል።
በአንድ አገር ውስጥ ሁለት መንግስት ሲንቀሳቀስ የማየትን ያህል ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር የለም። ግን ግን ከዚህ ሁሉ የሚልቀው ሚስት የገዛ ባሏን ፊቷ ላይ በድንጋይ ተቀጥቅጦ ሲገደል ማየትና እሬሳውን ለማንሳት እንኳን የሚደርስላት ወገን ማጣት ነው።
አሁንም ከዚህ በላይ የሚያመው 78 ንጹሃን በማንነታቸው የተነሳ እንዲጨፈጨፉ ያደረገ አካል እንደማይጠየቅና ለሌላ ጭፍጨፋ እራሱን እንድያዘጋጅ የሚያበረታታው መንግስት መኖሩን ማየት ነው!

በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ኢትዮጵያ የስለት እና የእንጀራ ልጆቼ ብላ አቅፋ የምታኖራቸው ሁለት ክልሎች አሏት።
በአንደኛው ክልሏ ያለ የስለት ልጇ ከሌላ አካባቢ የመጣ ወንድሙን ውጣልኝ ብሎ ግፍ ሲፈጽምበት “ያልከው ይሁን” ተብሎ ይታለፋል። የእንጀራ ልጇ በሚኖርበት ክልል እራሴን በራሴ ላስተዳድር ብሎ ህገመንግስታዊ ጥያቄ ሲያነሳ “የለውጡ እንቅፋት” የሚል ተቀጽላ ተሰቶት እንዲኮረኮም ይደረጋል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለደቡብ ወይስ ለኦሮሚያ?

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ቅርጫት ውስጥ ለ56 መታፈን ይብቃኝ፤ ህገመንግስታዊ መብቴን ተጠቅሜ የራሴን ክልል ላቋቁም ብሎ ጥያቄ ባነሳ ማግስት ራሱን “የለውጥ ሀይል” በማለት የሚጠራው መንግስት የህዝቡን ድምጽ ለማፈን እንድያመቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነጋሪት አስጎሰመ።

በአንጻሩ በገሃድ የሚታይ ህብረተሰብዓዊ ቀውስ በተቀሰቀሰበት፤ 78 ነብሶች 48 ሰዓት ባልሟላ ጊዜ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ በተጨፈጨፈበት፤ ጋሞ እና አማራ የሚባል ህዝብ ጋር እንዳትኖሩ ተብሎ በአደባባይ አዋጅ በተነገረባት የኦዲፒዋ ኦሮሚያ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አያስፈልግም ተብሏል።

የኤጄቶ መሪዎች እስር Vs  የቄሮ መሪ ክብር

ሐምሌ 11 በሲዳማ በተቀሰቀሰው ሁከት የኤጄቶ መሪዎች ናቸው የተባሉ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የሚዲያ ሰዎች እና የህግ ባለሞያዎች ተለቃቅመው ከያሉበት እንዲታሰሩ ተደረገ። ያውም የቄሮ መሪ በቄሮዎች ላይ ያለውን ያክል ተፅኖ በኤጄቶዎች ላይ የሌላቸው ግለሰቦች!

የዶሮ ነብስ እንኳን ክብር እንዳለው ለመግለጽ ”በስመአብ“ ወይም “ቢስሚላሂ” ተብሎ በሚታረድባት ሀገር ቄሮ ነኝ እያለ የሰው ልጅን በጠራራ ፀሃይ ያረደ ቡድን መሪ ግን እንኳንስ ሊጠየቅ “እግሩ ላይ ተወድቆ“ ይቅርታ እየተጠየቀ ይገኛል።

የኦነግ ባንዲራ የተፈቀደባት ኦሮሚያ Vs  ባንዲራ መያዝ የተከለከለባት ደቡብ

ኦሮሚያ ውስጥ የህዝብ ተቋማት ላይ እንኳን ሳይቀር የሪፓብሊኩን ሠንደቅ ዓላማ አውርዶ የኦነግን ባንዲራ መስቀል የተፈቀደ ነው። አስፓልት እና የስልክ ፖልን በኦነግ ባንዲራ መቀባት ቀቢውን እስካልደከመው እና ቀለም እስካላለቀበት ድረስ ሁሉ በእጁ ነው።

ደቡብ ላይ ብሄር ብሄረሰቦች ይገልጸኛል ያሉትን ምልክት እና ባንዲራ መያዝ በህግ ያስጠይቃል፤ ዕድሜ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይግባውና!

ዶ/ር ዐቢይ ተወዳጅ የፖለቲካ ሰው ነው። ያውም ሀገርን የመምራት ተመራጭ ግለሰብዓዊ ስብዕና ያለው። ይሄንን መልካም ስብዕናቸውን ግን ህዝባቸውን በእኩልነት በማገልገል ሊደግፉት ይገባል። በእንጀራ እና የስለት ልጆች መካከል ያለውን ልዩነት ሊያጠፉ ይገባል።

የዶክተሩ እና የእኛ ፍቅር ዓመት 2 ዓመት ከዝያም አልፎ እንዲዘልቅ ከተፈለገ ግን በሰበታ ለተጨፈጨፉ ጥበብ ሠሪ የጋሞ ልጆች ፍትህ ይስጡ! በዶዶላ ለተጨፈጨፉ አማራዎች ፍትህን ያምጡ! ሀረር ላይ እሬሳ በገመድ አስረው መንገድ ለመንገድ ሲጎትቱ የነበሩ ሰው መሳይ አውሬዎችን ለፍርድ ያቅርቡ! ነገም ሌላ ግፍ ከመፈጸም ወደኋላ የማይሉትን ቦዘኔዎች ልክ ያስገቡልን! መንጋውን ለጥፋት ያዘጋጀውን፤ የኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ ጠላትን፤ ከኔ ውጪ ሌላው አይኑር በሚል እብሪት የብሄር ብሄረሰቦች ልጆችን ርህራሄ ባልፈጠረበት መንገድ ያስጨፈጨፈውን ያንን ”ሉሲፈር“ በህግ አደባባይ ያቁሙልን!

#ጋሞ
የቱንም ያህል እንግልቱ ቢበዛ፣ የቱንም ያህል ሰው ወደ አውሬነት ተለውጦ ሊገለን ቢጥር፣ የቱንም ያልህ ብንሳደድም ጋሞነት እና ኢትዮጵያዊነት ተጋጭተው አያውቁም።

Gamo Media Network

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.