ዶክተሮቹ (አረጋዊና ዐብይ) ሳይቀሩ “ባልደራስን ማጥቃት ይብቃ!” ማለት ይገባል! – ፈተናው በዛብህ

በኢትዮጵያ ላይ ያለው የዶ/ር ዐብይ አገዛዝ ኦሮሞና ኦሮሞ ያልሆኑ ማሕበረሰቦችን የሚገዛበት አካሄድ በዘረኝነት ፍልስፍና የተቃኘ መሆኑን ለመረዳት በአሁን ሰዐት በሀገሪቱ ላይ የሚደረገውን ክንውን ማየት ብቻ በቂ ነው። እንደምሳሌ ያህል የአማራ የፖለቲካ ድርጅትን በመደገፍዋ ብቻ ቂም ተይዞባት፣ ወልዳ አራስ ቤት በተኛች በአንድ የኦሮምያ የገጠር ከተማ ነዋሪ ላይ በሀሰት የሽብርተኛ ክስ ተመስርቶባት፣ በሀሰት ተመስክሮባት፣ ፈጣን በሆነ መንገድ “ፍርድ” ተፈርዶባት ወህኒ የተላከችበትን ዜና ታዝበናል። ይህ ድርጊት ግፍ ነው ብለን ሳናበቃ፣ ጃዋር መሐመድ የሚባል የኦሮሞ ፅንፈኛ፣ በኢንተርኔት መንጋዎቹን ለአድማ የሚያነሳሳ ጥሪ አቅርቦ ከሰማንያ በላይ ሰዎች ላይ አሰቃቂ የሆነ የሞት፣ ከሶስት መቶ በላይ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት የሆነና የሃይማኖት ተቋሞችና ሌሎች የመኖርያና የንግድ ንብረቶች እንዲወድሙ አቅዶ ላስተባበረ ፅንፈኛ ግን የመንግስት የበላይ አካሎች፣ ጃዋር የእኛ የ”ወርቆቹ” ወገን ነው ተብሎ ጥብቅና ሲቆምለት እናያለን። ይህ ብቻውን እንኳን የዐብይ አስተዳደር ዘረኛ መሆኑን ይጠቁማል። ከዚህ በላይ ደግሞ ዐብይ አህመድንና ለማ መገርሳን ያንገበገባቸው ነገር በጃዋር መንጋዎች ስለሞቱትና ስለተጎዱት ኦሮሞ ስላልሆኑ ወገኖች ሳይሆን፣ ይህ ፅንፈኛ ግለሰብ ሌሊት ከሞቀ እንቅልፉ ላይ በመቀስቀሱ ስለደረሰበት “በደል” መሆኑን መስማት ያስደነግጣል። ይባስ ብሎም እነዚሁ የመንግሥት የበላይ ኃላፊዎች ከዚህ ፅንፈኛ ጋር ትናንትም ዛሬም እንዲሁም ነገም አብረው እንደሚሰሩ በንቀትና በድፍረት ይነግሩናል። ይህ አባባላቸው እንደሚያሳየው የዐብይ መንግሥት ከዚህ ፅንፈኛ ጋር የትናንቱን ዕቅድ አብረው ማቀዳቸውን፣ ጭፍጨፋውን አብረው ማከናወናቸውንና ነገም ሌላ ቀጣይ ዕቅድ በጋራ እንደሚተገብሩ ነው።

እንግዲህ የአዲስ አበባው ባለአደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) ከልደቱ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በጭፍን ዘረኞች የሚካሄድበት ማዋከብና ጥቃት ምክንያቱ የዐብይ አስተዳደር ዘረኛ የሆነና “ኦሮሞ” እና “ኦሮሞ ያልሆኑ” ማሕበረሰቦችን የሚያስተናግድበት መንገድ በሰፊው የተለያየ መሆኑ ነው። የዚህ ዘረኛ አስተዳደር ኅሊና-የለሽ አጫፋሪዎች እንኳን ሰሞኑን የተከሰተውን ይህን የገጠጠ አድልዎ ለማስተባበል እየተቸገሩ መሆኑን እናያለን። ዋናዎቹ የባልደራስ ምክር ቤት አባላት (ስንታየሁ ቸኮልና ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ) እንዲሁም በርካታ የባልደራስ ደጋፊዎችና አባላት (መርከቡ ኃይሌ፣ በኃይሉ ማሞና አዳም ውጅራን ጨምሮ) የዚሁ ጥቃት ሰለባ ሆነው ያለምክንያት እስከ አራት ወራት ድረስ በስቃይና እንግልት ውስጥ ከርመው ከጥቂት ቀናት በፊት ከእስር ወጥተዋል። ይሁን እንጂ ትናንት ደግሞ በባልደራሱ ምክር ቤት አባላት ላይ የኃይል ርምጃ ለመውሰድ አስር ያህል የሚደርሱ ከተራ ወሮበሎች እስከ ሰለጠኑ ግፈኞች ተደራጅተው የሽብር ድርጊት ለመፈፀም ሞክረዋል። ምንም እንኳን በምክርቤቱ አባላት ንቃትና ጥንቃቄ የተነሳ መንጋዎቹ የአካል ጥቃት ሳያደርሱ ይጠብቃቸው በነበረና የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 35 በተመዘገብ መኪና ውስጥ ገብተው ቢሸሹም ከመሐከላቸው ሲቪል ለብሶ የነበረው የፖሊስ ባልደረባ በባልደራስ ምክር ቤት አባላት ተይዞ ለፖሊስ ቀርቦአል። እንደሚጠበቀው የፖሊስ ጣቢያው ኮማንደር ይህ ግለሰብ ለምርመራ ክፍል ቃሉን እንዲሰጥ ለመፍቀድ በጣም ብዙ አንገራግሯል። ምናልባትም ይህ ዳተኝነት የሚያሳየው ኮማንደሩ ስለ ሽብር ተልዕኮው አሰቀድሞ ያውቅ እንደነበር፣ አለበለዚያም የሽብሩን መሳካት ይደግፍ እንደሆነ ነው። ዳሩ ግን በወቅቱ የታየው የተጠናከረ የአዲስ አበባ ወጣቶች ግፊት ለላንቲካም ቢሆን የተከሳሽ ቃል በመዝገብ እንዲሰፍር ማድረግ አስችሏል።

ኅሊና ላለው ሰው ግር የሚለው ጉዳይ ቢኖር ፅንፈኛ ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች ባላደራውን ሲቃወሙ ማየት ነው። ምክንያቱም የባላደራው ዓላማ ያነጣጠረው ዕኩይ በሆነ ስሌት በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በሕወሓትና ኦነግ ሽርክና በተደነቀረው “ኦሮምያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም ይኖራታል።” በሚል አንቀፅ ላይ ነው። ይህ አንቀፅ በዜጎች መካከል አድልዎ በማንበር ልዩነት ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል። የባላደራው ተልዕኮም አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያውያን እንጂ ለአንድ ብሔር አባሎች ብቻ ተለይታ የምትሰጥ መሆን የለባትም የሚለውን የአዲስ አበባ ሕዝብ ፍላጎት ማስፈፀም ነው። ስለዚህም የባለደራው ዓላማ ቢሳካ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ውስጥ እኩል መብት ይኖራቸዋል። የከተማዋ የእስካሁኑ ታሪኳ የሚያሳየውም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በባለቤትነት መብት ላይ እኩል ድርሻ የነበራቸው መሆኑን ነው። አዲስ አበቤ ሰፈር እንጂ ብሔር እንደማይጠይቅ ከተማውን የሚያውቅ ሁሉ ያውቀዋል። አሁን በከተማው ውስጥ ለሚታየው ፖለቲካዊ ችግር መነሻው በተለይ ይህ ጠንቀኛ የሕግ አንቀፅ፤ በጥቅሉ ደግሞ ሕገ-መንግስት ተብዬው ነው። ተደጋግሞ እንደሚነገረው ሕገ-መንግስቱ የሕወሓት ማኒፌስቶ ግልባጭ እንደሆነና የማኒፌስቶው ግንባር ቀደም ደራሲ ደግሞ ዶ/ር አረጋዊ በርሔ ነበሩ። ዶ/ሩ በዚህ ዘረኛ ድርሰታቸው ላይ በተለይ አማራው ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ከማራመድ በተጨማሪ ትግራይ ራስዋን ችላ ለትግራይ ሕዝቦች ብቻ የተከለለች ሀገር እንድትሆን የሚተጋ ቋሚ ዶኩመንት አዘጋጅ ነበሩ። ይህ ማኒፌስቶ በግልፅ የሚያሳየው በወቅቱ እነ አረጋዊ በርሔ፣ በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻና የበቀል ተነሳሽነት ከፍ ያለ የመሆኑን ያህል፣ ልባቸውን እኩል ያማልላቸው የነበረው የትግራይ ነፃ መንግሥት መፈጠርና የትግራይ ሕዝብ “ከአማራ ጭቆና” ነፃ ወጥቶ ፍስሓና ደስታውን ለሚያጣጥምበት ቀን ለመድረስ ቆርጠው የሚታገሉ መሆኑን ነው። ዳሩ ግን ብዙም ሳይቆዩ የትግል አንድነቱ ተናግቶ፣ ሕልማቸውን ሳያዩ በወጣትነት ዘመናቸው ከድርጅቱ ተባረሩ። አሁን ከመሸ ደግሞ በአረጋዊ ዕድሜያቸው ዶ/ር አረጋዊ ያ ሕልም የመሰላቸው ቅዠት ሆኖባቸው ይገኛል።

ዶ/ር አረጋዊ “ትግራይ ለትግራውያን” ብለው የታገሉለት ትግል ያፈራው ፍሬ ያሳየን ሐቅ የዶ/ሩ የወጣትነት ሕልማቸው ቅዠት መሆኑን የተረዱበት አጋጣሚ ነበር ማለት ይቻላል። በጄነራል ሰዐረ ሞት ምክንያት ለቀብር ወደ ትግራይ የሄዱት አዛውንቱ ዶ/ር አረጋዊ፣ ከቀባሪ መሐከል እንደ ወንጀለኛ ተመርጠው፣ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው ከምርመራ በኋላ በእስር ቤት ተቆልፎባቸው (ለአጭር ጊዜ ቢሆንም)፣ ትግራይ አፈር ላይ ልትቆም የማይገባህ ከሐዲ ነህ ተብለው፣ በአጃቢ አየር ማረፊያ ድረስ ተወስደው እንዳይመለሱ ማስጠንቀቅያ ተሰጥቷቸው፣ ከትግራይ deport ሲደረጉ የመጡት ከዚህችው አዲስ አበባ ነበር። ድንጋጤና ፍርሃታቸውን ካሳለፉ ከጥቂት ቀናት በኋላም እሮሯቸውን ለጋዜጠኞች ሊያሰሙባት የቻሉት ከዚህችው የማንነት ልዩነት ከማታራግበው ከአዲስ አበባ ነው። ሀገሪቱ ውስጥ ባለው ሁኔታ ከዚህች አዲስ አበባ ውጭ ለዶ/ር አረጋዊ የተሻለ መብት የሚሰጥ ክልል አይኖርም ነበር። ምንም እንኳን ሕገ መንግሥቱ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ክልል ተዟዙሮ የመኖርና የመስራት መብት አለው የሚል አንቀፅ ቢኖረውም፣ በተጨባጭ ያለው ሁኔታ የሚያሳየው ግን ይህ የሕግ አንቀፅ ከቧልት የማያልፍ መሆኑን ነው። ስለዚህም የዚህን አንቀፅ ፋይዳ ለማስረዳት ጊዜ ማጥፋት ሳይኖርብኝ ክሬዲቱን ለአዲስ አበባ ብቻ ሰጥቼ ልቀጥል።

ይህ ከራስ “ክልል” ተባሮ የመውጣት ሌላው ሰለባ ደግሞ ራሳቸው ዶ/ር ዐብይ ናቸው። ከጥቂት ቀናት በፊት ከገዳይ ወገኖች ጋር ብቻ ለመወያየት ወደ አምቦ ያቀኑት ጠ/ሚንስትርት፣ ስብሰባውን ልንሳተፍ ይገባናል በሚል የክልሉ ተወላጆች ተባረው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል (በነገራችን ላይ ዶ/ር ዐብይ አዲስ አበባን በሚመለከት አቋማቸው ከጃዋር እንደማይለይ ይታወቃል።)። ይህ ማለት በጃዋር ደጋፊዎች ዶ/ር ዐብይ ከኦሮምያ ሲባረሩ የሸሹበት ወደ እዚህችው የሁሉም ዜጎች ወደሆነችው አዲስ አበባ ነው። ከዚህ ሊማሩ ይገባል። እንደ ዛቻው ከሆነ ጃዋር አዲስ አበባን በኦሮምያ ውስጥ ከጠቀለለ ሌላ መሸሽያ ቦታ እንደሌላቸው አስቀድመው ሊረዱ ይገባል። የጃዋርን ጉልበት ደግሞ እንደእርሳቸው የሚፈራ ያለ አይመስለኝም። ስለዚህም ሰለባዎቹን ዶ/ር ዐብይ አሕመድና ዶ/ር አረጋዊ በርሄን ጨምሮ ሌሎችም በቀሪዎቹ ክልሎች ውስጥ ነዋሪዎች የሆናችሁ፣ መቸም በአምባገነንና ዘረኛ አገዛዝ ስር የሚፈጠረው ነገር ስለማይታወቅ አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን እኩል መናኸርያ ሆና እንድትቀጥል ይቻል ዘንድ፣ የባልደራሱ ብቸኛ የትግል ዓላማ የሆነውን አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያኖች ነው የሚለውን ሃሳብ መደገፍ ይኖርባቸኋል!

በተለይ ግን የአዲስ አበባ ነዋሪ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ ቢኖር አዲስ አበቤን ያጋጠመው ችግር በቀጥታ ከኅልውናና የዜግነት መብት ጋር በፅኑ የተቆራኘ መሆኑን ነው። በተለይ ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ በስፋት የምናየው ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነው። ፉከራውን እንኳን ከቁብ ባንቆጥረው፣ ቢያንስ በኤሬቻ ዋዜማና የዕለቱ ዕለት የአዲስ አበባ ሕዝብ ያጋጠመው የመብት መጣስ እጅግ አሳፋሪ ነው። ከተማውን ለመውረር በመጡ መንጋዎች አማካይነት የከተማው ነዋሪ መብቱን ለሚነካ ፍተሻና ዘረፋ ተዳርጓል።  ይህ የተቀነባበረው በከተማው አስተዳደርና በዶ/ር ዐብይ የፌደራል መንግስት ብቻ ሳይሆን በኦሮምያ ክልል መንግስትም ጭምር ነው። እንዴት ማንነታቸው ባልታወቁና በሕግ የተወሰነ መብት ባልተሰጣቸው ቄሮና ፎሌ በሚባሉ ለከተማው ነዋሪ ባዕድ በሆኑ አካሎች አዲስ አበቤ ይፈተናል? ይህ የመንጋ ቡድን በከተማው ዳርቻ ብቻ ሳይሆን ቦሌ ቡልቡላ ድረስ ዘልቆ በመግባት በነዋሪው ላይ ያደረሰው ጥቃትም የሚታወስና የሚያንገበግብ ነው። አሁን ደግሞ የአዲስ አበቤን መብት ለማስጠበቅ ተልዕኮውን የተሸከሙትን ብርቅ የባልደራስ ምክር ቤት አባላትን በወረበሎች በማስጠቃት የተጀመረውን የአዲስ አበቤን መብት ለማስጠበቅ የሚደረገውን ሰላማዊ ጥያቄ ለማኮላሸት የሚደረገውን ዕኩይ ሴራ በንቃት መጠበቅ የእያንዳንዱ ነዋሪ ግዴታ ነው። የአዲስ አበቤ የመቻቻል ባህርይ የፍርሃትና ስንፍና ምልክት ሳይሆን፣ የተለያየ ማሕበረሰብ አብሮ የመኖር የስልጣኔ የፈጠረው ስነልቦና መሆኑን ሊረዱ ለማይችሉ ሰገጤዎች የሚረዱበትን መንገድ መዘየድ ይገባል። ነገር ግን በፍፁም ሊዘነጋ የማይገባው ነጥብ ቢኖር አዲስ አበቤ መብቱን የሚያገኘው በመንቃት፣ በመደራጀትና በመታገል ብቻ እንደሆነ ነው!

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ውስጥ በተለያዩ ዕርከኖች ላይ የሚገኙት የመንግሥት ኃላፊዎች ዋና ግብ የኦሮምያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ልዩ ጥቅም ማስፈፀም እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። እንደ እኔ አተያይ ይህ ማለት ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንን እንደ አልባሌና ዝቅተኛ ዜጋ ለመግዛት የሚፈቅድ የሕግ ከለላ ለማግኘት መሥራት እንደ ማለት ነው። እንደ አንድ ተራ፣ ነገር ግን እንደሚያስተውል ሰው የምረዳው ነገር ቢኖር “ፊንፊኔ ኬኛ” የሚለው አካሄድ ምህረት የለሽ መሆኑን ነው። ማሽሞንሞን የማያስፈልገው እውነታ ነው። ባለፉት ሳምንታት በሀገሪቱ በየቦታው የተደረገው የጭካኔና የአራዊት ስራ መሐከል አዲስ አበባ ውስጥ አይፈፀምም ብሎ አለማሰብ አይቻልም። ተነጋግሮ መፍታት ይቻላል እንዳይባል፣ እንኳን ቄሮና ፎሌ ከሚባሉት (ባለፉት ሳምንታት ሲፈፅሙት የነበረውን የእንሰሳ ሥራ እናስታውሳለን) ቀርቶ በየደረጃው ካሉ ከከተማው አስተዳዳሪዎች ጋር እንኳን መነጋገር አይቻልም። ምክንያቱም እነዚህ ክፍሎች የከተማውን አስተሳሰብና ባህል በቅጡ ባለማወቃቸው ሳቢያ የተፈጠረ ትልቅ ክፍተት ስላለ ነው። ለምሳሌ ያህል ምክትል ከንቲባውን ብንወስድ የአዲስ አበባን ሕይወት በትንሹም ቢሆን እንደማያውቁት በድፍረት መናገር ይቻላል። ከህዝብ ጋር ምን መስራት እንደሚያቀራርባቸው፣ ምን መስራት እንደሚያራርቃቸው በፍፁም አያውቁም። እንደ ከንቲባው ዕሳቤ ማዘጋጃ ቢሮ ውስጥ ጅራፍ ማጮህ ሕዝባዊ ያደርጋል ብለው ይህን ድርጊት በሥራ ሰዐት ቢሯቸው ግቢ ሲከውኑ ማየት ይገርማል። ም/ከንቲባ ታከለ ዑማ “ሕዝባዊ” ያደርገኛል ብለው ይሁን ልጅነታቸው ትዝ ብሏቸው ባላውቅም፣ ቢሯቸው ድረስ ጅራፍ አስመጥተው፣ ካሜራ አሰልፈው በሥራ ሰዐት ፒያሳ ፟- አራዳ ጊዮርጊስ ማዘጋጃ ግቢ ውስጥ በኩራት ጅራፍ ሲያጮሁ እንደማየት ለአዲስ አበቤ እንግዳ ነገር አይኖርም። ይህ ታዲያ የአዲስ አበባን ቅኝት የሳቱ መሆናቸውን ያመላክታል። በአንፃሩ ዘረኛ የሆኑ ሕገ ወጥ የሸፍጥ ሥራ ከመስራት በተጨማሪ የባልደራሱ የሕዝብ ጥያቄ እንዳይሳካ መንጋዎችን በስውር አደራጅተው ሕገ ወጥ የሆነ ሥራን በገሃድ እንዲያከናውኑ ሲያሰማሩና ሲፈቅዱ እናያለን። ለማስታወስ ያህል እነዚህ ሰገጤ መንጋዎች ከአምስት ያላነሱ የባልደራሱን የአደባባይ፣ የአዳራሽና የቢሮ ስብሰባዎችን አደናቅፈዋል። አስተዳደሩ ደግሞ በባልደራሱ አባላትና ደጋፊዎች ላይ የከፋ የጭካኔ በትር ሲሰነዝር ቆይቷል። ይህንና መሰል ድርጊቶች የሚቆሙት አዲስ አበቤ በስፋት ተደራጅቶ ሲጋፈጣቸው ብቻ ነው። “ካፈጠጠ ኋላ የቀረው ምት ነው” ከሚለው ሀገራዊ ብሂል መማር አለብን። አርቀው የሚያዩ ሁሉ ከሰለባዎቹ ከዶ/ሮቹ አረጋዊ በርሄና ዐብይ አህመድ ጀምሮ በባላደራ ላይ የሚደርሰው ጥቃት ይቁም ማለት ይገባቸዋል! ባላደራው ማለት ደግሞ አባላትና ደጋፊዎቹን ይጨምራል። አዲስ አበቤ ግን ንቃት፣ጥንቃቄና ድፍረት የተሞላበት ድርጅታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት! የድርጅት እንቅስቃሴ ደግሞ በብስለትና ጥንቃቄ የተቃኘ ዕቅድ ሊኖረው ይገባል። ይህን ዕቅድ ደግሞ በኃላፊነትና በብቃት የማዘጋጀት አቅም ያለው ባልደራስ ብቻ ነው! ሁላችንም የሕዝብ አደራ ከተቀበለው፤ በፈተናና በወከባ ወቅት መስዋዕትነት እየከፈለ ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጎን በፅናት የቆመው ባላደራስ ላይ የሚደርስ ጥቃት ይቁም እንበል! ባልደራስን መታደግ በኅልውና ላይ የተቃጣን ኢፍትሐዊነትን መታገል ነው!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.