የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የገዳ ሥርዓት ትምህርትን በማስተርስ ደረጃ መስጠት ጀመረ

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የገዳ ሥርዓት ትምህርትን በማስተርስ ደረጃ መስጠት መጀመሩን በዩኒቨርሲቲው የገዳ እና የባህል ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሮባ ደምቢ በተለይ ለኢቲቪ ገልጸዋል፡፡

የትምህርቱ መጀመር ዋና ዓለማ ለአዲሱ ትውልድ እና ሥርዓቱን እንደ ቅርሱ የሚቆጥረው ሕዝብ በጥልቀት እንዲያውቀው መሆኑን አቶ ሮባ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በተሰሩ ጥናቶች በብዛት ሲሰጡ የነበሩት ምክረ ሀሳቦች ገዳ ወደ ትምህርት ካሪኩለም ገብቶ ትውልዱ እንዲማረው ሀሰቦች ሲቀርቡ ነበርም ብለዋል አቶ ሮባ፡፡

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚያጠና ቡድን አቋቁሞ በጥልቀት ጥናት ማካሄዱን እና ቡድኑም አሁን ያለው የገዳ ሥርዓት በተጨባጭ ወደ ትምህርት መግባት አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የገዳ ሥርዓትን በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ለማካተት ከጅማ፣ ሐረማያ እና ወለጋ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ምክክር መደረጉንና በገዳ ሥርዓት ዙሪያ ጥናት ያካሄዱ ሰዎችንም አስተያየት እንደ ግብዓት መወሰዱን ዳይሬክተሩ አክለዋል።

በዚህም መሠረት በገዳ ሥርዓት ውስጥ ያሉ እሴቶችን እና መልካም አስተምህሮዎችን እንዲሁም የሥርዓቱን ዴሞክራሲያዊ ሂደት በትምህርት መልክ ለአዲሱ እና ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል ዳይሬክተሩ።

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የገዳ ሥርዓትን ማጥናት የጀመረው ከ2009 ጀምሮ መሆኑን እና በሥርዓቱ ላይ ጥናት የሚያደርግ ኢንስቲትዩት በ2011 ዓ.ም በይፋ አስመርቆ ወደ ሥራ መግባቱንም አቶ ሮባ ተናግረዋል።

የገዳ ሥርዓት ትምህርቱን በማስተርስ ደረጃ ለመስጠት ካሪኩለም ከመቅረፅ በፊት ለመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች በሙሉ እንደ ‘ኮመን ኮርስ’ እንዲሰጥ ተሠርቷል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሮባ፣ ሁሉም የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ኮርሱን ሳይወስዱ መመረቅ እንደማይችሉ ዩኒቨርሲቲው ውሳኔ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
ከ2012 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ሁሉም የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ኮርሱን እንዲወስዱ ለማድረግ በካሪኩለም ተካትቷል ነው ያሉት።

የገዳ ሥርዓት እና የሰላም ትምህርት ላይ ለመሳትፍ ፍላጎቱ ያላቸው የማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ተማሪዎች በሙሉ ትምህርቱን በማስተርስ ደረጃ መውሰድ ይችላሉ ተብሏል።

በ2012 የትምህርት ዘመን 10 ተማሪዎች ትምህርቱን ለመውሰድ የተመዘገቡ መሆኑን የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰር ሮባ፣ ወደ ፊት ትምህርቱን የሚሰጡ መምህራንን ቁጥር በመጨመር የዩኒቨርሲቲውን የቅበላ አቅም ለማሳደግ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ትምህርቱን ለመስጠት ጅማሮ ላይ ያለ በመሆኑ አብረው ለመሥራት ፍላጎቱ ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት እገዛ ማድረግ እንደሚችሉም አቶ ሮባ ጠቁመዋል።

በዮናስ በድሉ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.