ሳይቃጠል በቅጠል – ነአምን ዘለቀ

ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፦

ታሪክ (ኮች)፣ ትርክቶች፣ የታሪክ፣ የማህበራዊ ሳይንስ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ የእወቀት ውሱንነት። ፦ የልዩ ልዩ ትርኮቶችና ታሪኮች ለማጣጣም ፣ ታሪካችን (ታሪኮቻችህን) የእሁኑን ህይወትና የነገን ተስፋ እንዳያጨልሙ ከሁሉም የተውጣጣ ኮሚሽን ስለማቋቋም።

የኢትዮጵያ ምድር ከጥንት ከሺ አመታት በፊት ዛሬ የሚገኙ ሕዝቦች ያልነበሩበት፣ አንዱ በአንድ ዘመን ከደቡብ ተነስቶ ሌሎችን ማህበረሰቦች አስገብሮ መሬት ሲይዝ፣ በሌላ ዘመን ሌላው ይህኑ አጸፋ ሲያደርግ፣ ሲስፋፋ፣ በአመዛኙ ደግሞ የየብሔሩ ገዢዎች ፣ በአለም ላይ እንደነበሩ ገዥዎች ሁሉ የተደረጉ ሂደቶች ናቸው፡፡ ሌሎች የአለም ሃገሮች ከተመሰረቱበት የሀገሮች ምስረታ ሂደት ምንም የሚለየው የለም። ባርያ ፈንጋዩና አስገባሪው ደግሞ የአንድ ብሔር አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ብቻም አልነበሩም። በልዩ ልዩ የታሪክ ምእራፎች የልዩ ልዩ የየማህበረስቦች/ብሄር ንጉሶችና ገዢዎች፣ አስገባሪዎች ፣ ተስፋፊዎች በመሆን ተፈራርቀዋል።

የልዩ ልዩ ብሔሮች/ማህበሰቦች ገዢዎች ከመሃል ወደ ደቡብ ፣ከደቡባዊ ከምስራቃዊ ኢትዮጵያ ተነስቶ እስከ መሃላዊ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እስከ ሲሜናዊና ሰሜን ምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍሎች በመዝመት በመስፋፋት ሲፈራረቁበት የቆዪበት የረጅም ዘመናት ሂደት ነው። የረጅም ዘመናት ታሪካችን እያንዳንዱ ማህበረሰብና በየዘመኑ፣ በሰፊው የታሪካችን ምእራፎች የነበሩ የብሔርም የሕብረ ብሔርም ገዥዎች በቀደሙት ዘመናት አጣሁዋቸው ያላቸውን መሬቶች ለማስመለስ ዳግም በሃይል ሲስፋፋ የነበረበት ውጥንቅጥና አባይን በጭልፋ እንደሚባለው ረጅምና ተጽፎ ያላለቀ፣ ተጽፎም ሊያልቅ የማይችል ፣ የብዙ ዘመናት የመጥበብ ፣ የመስፋት ሂደቶችና ተደጋጋሚ ኡደቶች ብቻም አልነበሩም፡፡ የንግድ ልውውጥ፣ የማህበራዊ ግንኙነቶች፣ የቋንቋና ባህል መወራርስና መዳቀል የነበሩበትም ሂደት ነበር። ለዳር ድንበርና ለሕዝብ ክብር ለኢትዮጵያ አገራዊ ግንባታ በኦሮሞም ፣ በአማራም ፣ በአፋር ፣ በትግሬ፣ በወላይታ ፣ጉራጌ በሌሎችም የቋንቋና የባህል ማህበረሰቦች ባፈሯቻቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሀገራዊ እርበኞች ፣ አንጸባራቂ ጀብድ በፈጸሙ ፣ታላላቅ ጀግኖችና የጦር መሪዎች መስዋዕትነት የተገነባ ሕብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያ ማንነትና ሃገራዊነት የታሪክ ሂደትም ነው። ይህ ውስብስብ የታሪክ ሂደት በ150 አመት ታሪክ ትንሽ አጭር መነጽር ሊታጠር ፣ሊገደብ የማይችል ሰፊ የዘመናት የታሪክ ባህርን በጭልፋ በሰፈረ ፣ እጅግ ቁንጽ የሆነ የነፍጠኛ የሰባሪ የገባር/የአስገባሪ ትርክትና እንድምታ የማያይወክለው፣ የማይገልጸው ሰፊና ጥልቅ የሆኑ የታሪኮቻችን ገመዶችና ክሮች የልዩ ልዩ ማህበረስቦች መስተጋብሮች፣ ግንኙነቶችና ፣ የሂደቶች ውጤት ነው።

ዋናው፣ ትልቁ ሃቅ ግን ከዚህም ከዚያም ወገን ማንም የታሪካችን ሙሉ እውቀት፣ ሙሉ መረጃ እንኳን በዚህኛው በወዲያኛውም ሕይወቱ ሊኖረው አይችልም። ታላላቆቹና በአለም ደረጃ የሚታወቁት የታሪክ ጸሐፊዎች እነ አርኖልድ ቶዬንቢ፣ ኤድዋርድ ጊበን፣ ዘመናዊና ትላልቅ ስም ያላቸው ኒያል ፊርግሰን ፣ ፈርናንድ ብራውዴል ፣ ሌሎችም ታዋቂ የታሪክ አጥኚዎች የሀገራቸውንም ሆነ የአለምን ታሪክ በሚመለክት የጻፉዋቸው ሁሉንም የታሪክ ምዕራፎች፣ ሁሉንም ታሪካዊ ክንውኖች፣ ሁሉንም ታሪካዊ መረጃዎች፣ ሁሉንም ታሪካዊ ሂደቶች አጣርተው በሙሉ ፣ ፍጹም በሆነ እውቀት/ዩኒቨርሳል የታሪክ ዘይቤም የታሪክ ሙሉ እይታ ሊኖራቸው እንደማይችል የታወቀ ሃቅ ነው። የብዙ አገሮች ታላላቅ የታሪክ ጸሐፊዎች በእያንዳንዱ የታሪክ ምዕራፍ አስከ ዛሬ የሚወዛገቡባቸው በርካታ የታሪክ ኩነቶች ፣ የታሪክ ትርጓሜዎች፣ የታሪክ ዘይቤዎች እንዳሉ ራሱ የኢትዮጵያን ታሪክ በራሳቸው ልክ ለሚፈልጉት የፓለቲካ አጀንዳ ቀንጭበውና ቆንጽለው የሚያቀርቡ የየብሔሩ ልሂቃን የሚያጡት ሓቅም አይደለም።

እነዚህ አጨቃጫቂ ፣ አወዛጋቢ የሆኑት በሁሉም ወገን ቁንጽል የሆኑና ማንም በምንም መልኩ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ እንደበርክታ የታሪክም የማህበራዊ ሳይንስ የመነጩ ጥናትችና ትርክቶች ሙሉ እይታ፣ ሙሉ እውቀት፣ ሙሉ ግንዛቤ፣ እንደሌላቸው ይታወቃል። የተፈጥሮ ሳይንስ በተለይም አልበርት አንስታይን የሬላቲቪትይ የፊዚክስ ቲዎሪ ግኝት በኋላ ሁሉን አዋቂና ሁሉን ተንባይ ነኝ የሚለው ፊዚክስ ማንነቱ ላይ በደረሰብት ቀውስ ሳቢያ የሳይንሱ ማህበረሰብ የሚቀበለው በአመዛኙ ፍጹም የሆነ፣ ሙሉ የሆነ እውቀት፣ ዩኒቨርሳል የሆነ እርግጠኝነት፣ የትንበያ አቅምም እንደሌለ ነው። ሌሎች ታላላቅ የሳይንስ ፈላስፎች ኢ-እርግጠኝነት (Uncertainty principle) የሚል ስያሜ የሰጡት የተፈጥሮ ሳይንስ ንጉስ የሆነው ፊዚክስ ተፈጥሮን ሙሉ በሙሉ ፣ ሁሉን ለማወቅና የሚሆነውንም ለመተንበይ የማይችል፣ በእጅጉ ያለውን ውሱንነት ያጠናከሩ ፣ ልዩ ልዩ የእውቀት ዘርፎችም ከኢኮኖሚክስ እስከ የፓለቲካ ሳይንስ የእውቀት ዘርፎች ጠቅላይ ሊሆኑ፣ ሙሉና የወድፊቱንም በፍጹም እርግጠኝነት ሊተነብዩ እንደማይችሉ፣ ልዩ ልዩ የእውቀት ዘርፎች በተወስነ አውድ፣ በተወሰነ ካባቢ ውሱን ለሆነ ግንዛቤና እውቀት፣ ለውሱን ችግሮች መፍቻ ዘይቤዎች/መሳሪያዎች ብቻ እንደሆኑ፣ የወደፊቱም የመተንብይም ሆነ ያልፈውን የታሪክም የማህበረሰብን ውጥንቅጦች በሁለንተዊና ጠቅላይ/ዩኒቨርሳል በሆነ መልኩ ለማወቅ እንደማይቻል እንዱ ሌላውን ሲገለብጡ፣ የኖሩ ንደፈ ሃሳቦች ፣ ጽንሰ ሃሳቦች ፣ ቲዎሪዎች፣ የአለም እይታዎች/ፓራዳይሞች፣ ልዩ ልዩ የማሀበረስባዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ፍልስፍናዎች ፣ እንዲሁም የዘይቤዎች/ሜተድስ።ሞዴልስ የትየለሌ መሆናቸው የሚያረጋግጡት ይህንንኑ ነው። በብዙች ዘንድ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ግንዛቤና መግባባት የተደረሰ ይመስለኛል።
ስለዚህ የኢትዮጵያ ልሂቃን በተለይ በፓለቲካው ትልቅ ሚና ያላችሁ የታሪክና የህብረተሰቡን ችግሮች ሁሉ በሚመለከት አለን የምትሉት ግንዛቤ ውሱንነት መቀበል። ትህትና ብትህውትነት (humbleness and humility) እኛ ሁሉን እናውቅለታለን ብለው ለሚገምቱት ህዝብና ማህበረሰብም የተሻለው ምልከታ ይመስለኛል ።

ምክንያቱም ፍጹም እወቀት፣ ፍጹማዊ እውነት አለኝ ለማለት በማይቻልበት እጅግ ሰፊና ጥልቅ የተፈጥሮ ፣ የታሪክ፣ የማህብረሰብም ሂደቶች፣ ጉራማይሌዎች፣ ጓዳ ጎድጓዳዎች፣ ጉራንጉሮች፣ ዥጉርጉር ሁኔታዎችና ሂደቶች የነበርን ህዝቦች በመሆናችን። የሰው ልጆች ህይወትም ሆነ የአለም ህዝቦች ታሪክ አካል የሆነ የኢትዮጵያ ታሪክ(ታሪኮች) ግራጫ ቀለም ያላቸውእንጂ ነጭና ጥቁር ባለመሆናቸው የኋላ ታሪኮቻችን፣ የሚጋጩ ትርክቶች ያን ወይንም ይህን ቁንጽል የታሪክ ጠብታ ይዞ ሙሉ እውቀት ባለቤት ነኝ ፣በሞኖፖል እውቀት እኔ ጋር ብቻ የሚል ስሜት ያላቸው የየብሄሩ ልሂቃን ቁንጽ የታሪክ ትርጉሞች/ትርክትን መሰረት አድርገው የሚሰነዘሩ ሽኩቻዎች የህዝብ፣ የማህበረሰብ ቅራኔዎች ፣ ጥላቻና ፣ ግጭቶች፣ ጥቃቶች መንሴም እየሆነ የመጣበት ይህ እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ እሁን ላይ መቆም ይገበዋል። ለአገርና ለሕዝብ የተሻለው፣ የሚበጀው መንገድም ይህ ይመስለኛል።

የኦሮሞም የአማራም ከዚያም የደቡባዊና የምስራቃዊ ኢትዮጵያን ፣ እንድሁም የኦሮሞን ታሪክ በአግባቡ አላካተተም ወይንም አይወክልም የሚባለው የግዕዝ ስልጣኔ ታሪክ ፣ ሌላም ካለ ሁሉም ወገን የኔ የሚላቸው ትርክቶች፣ ልዩ ልዩ ታሪኮች ወይንም የሚጣጣሙበት ወይንም የሚቀራረቡበት መንገዶችና ዘዴዎች መፈለግ። ወይንም ደግሞ ተመሳሳይ የታሪክ አረዳድ ያልነበራቸው አገሮች ፣ የሚጋጩ ትርክቶች አገራዊ ትርምስ የፈጠሩባቸው የሌሎች ሀገሮችን ሕዝቦች ልምድ ቀስሞ ከሁሉም የተውጣጣ፣ ይህንኑ የሚያጠና ባለሙያዎች የሚገኙበት ኮሚሽን የሚቋቋምበት ሁኔታ ቢመከር ምናልባት አንዱ የመፍትሄ አካል ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ቀደም ሲል እንደተነሳው የአገራችን ትላልቅ የፓለቲካ ቅራኔዎች አንዱ ከአለፉ ታሪኮቻችን የታሪክ አረዳድና አተረጓጎም ልዩነቶች፣ የሚጋጩ ትርክቶች ላይ የሚመነጩ በመሆናቸው ከፍተኛ ትኩረትና ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል እላለሁ። ይቀጥላል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.