ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር የአለም ሰላም ሎሬት ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ (ዶ/ር)

ከመሰረት ተስፉ

በመጀመሪያ የከበረ ሰላምታየ ይድረስዎ እላለሁ። በመቀጠል ይህን ግልፅ ደብዳቤ ስፅፍለዎ ምንም እንኳ እርሰዎ የኢህአዴግ ሊቀመንበርነቱንና የጠቅላይ ሚ/ርነቱን ቦታ ከያዙ ጀምሮ ከምራብውያን፣ ከአንዳንድ አረብና ጎረቤት ሃገራት ጋ መስርቻቸዋለሁ ከሚሏቸው መተክላዊ ያልሆኑ ግንኙነቶች ጀምሮ በርከት ባሉ አገራዊ ውሳኔዎችዎና ተግባራተዎ ላይ ልዩነቶች ቢኖሩኝም ከሚያደርጓቸው ንግግሮችዎና ከአንዳንድ ስራዎችዎ ተነስቸ ኢትዮጵያ አድጋና በልፅጋ እንድትታይ ፅኑ ፍላጎት እንዳለዎ ተረድቻለሁ። ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ ኢትዮጵያ በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ ከተፈፀሙ ስህተቶቿ ተምራ በጎ በጎውን እያጎላች እንድትሄድ እንጅ ፈርሳ እንደ አዲስ እንድትሰራ ወይም ደግሞ እንድትበታተን ከሚሰሩት “ታሪክ አሳባቂ ልጆቿ” ውስጥ አንዱ አይደሉም ብየ አስባለሁ። ።

በነገራችን ላይ በአለም ላይ ከዛሬ መቶና ሁለት መቶ አመታት በፊት የተደረጉት አገረ-መንግስታት ምስረታዎች በግጭት የተሞሉና ፀረ ዴሞክራሲያዊ እንደነበሩ እንዲሁም በወቅቱ ነባራዊ ሁኔታም ከዚህ ውጭ ሊሆኑ እንደማይችሉ “እነዚህ የታሪክ አሳባቂ ልጆች” በሚገባ አይረዱትም ብየ ለማሰብ ምንም ምክንያት የለኝም። ይሁንና እነዚህ የታሪክ አሳባቂዎች ከሂደቱ ትምህርት ወስደን የወደፊት አብሮነታችን እናጠናክር ከማለት ይልቅ የሃያ አንደኛውን ክፍለዘመን አስተሳሰብ ወደኋላ ወስደው በነዚያ ዘመናት የተፈፀሙ ህፀፆችን ለማጦዝ ሲጠቀሙበትና አንድነታችን ሲገዳደሩት ማየት የተለመደ ሆኗል።

ያም ሆነ ይህ ሁኔታዎችን በንፅፅር ስመለከት ያሉበዎ እጥረቶች እንደተጠበቁ ሆነው እርሰዎ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ተስፋ ይሰንቁ ዘንድ ፍላጎት እንዳለዎ ማመን ጀምሪያለሁ።  ይህ የተሰፋ ፍላጎት እውን እንዲሆን፣ ጉልህና ብሩህ ሆኖ እንዲቀጥል ግን የካፊያ አንድ ጠብታ ያህል ውሃ የሚቋጥሩ መሆናቸውን እርግጠኛ ባልሆንም በውስጤ የሚመላለሱትን ችግሮችና መፍትሄ ይሆናሉ ብየ የማስባቸውን ነጥቦች በዚህ ፅሁፍ ላሳውቀዎ ተገድጃለሁ።

በዚህም መሰረት ላሳስበዎ የምፈልገው የመጀመሪያውና እጅግ ፈታኝ የሆነው ሃገራዊ ችግር ራሱ እርሰዎ የሚመሩት ኢህአዴግ ነው ብየ የማስብ መሆኔን ነው። እርሰዎም እንደሚያውቁት ይህ ግንባር ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት የሰብአዊ መብቶችን ሲጥስ፣ ሙስና ውስጥ ሲዋኝ፣ በአድሎና ፍትሃዊ ባልሆኑ ተግባራት ሲናኝ እና ሌሎችንም ፀረ ህዝብ የሆኑ ተግባራት ሲፈፅም በነበረበት ወቅት እንኳ አካሄዱ ሽክፍ ያለና ወጥነት ያለው ነበር። ያሁኑ ኢህአዴግ ግን፣ ዝርክርክና ውጥንቅጡ የወጣ ብቻ ሳይሆን አጥንቱ፣ ቆዳው፣ ስጋውና ጅማቶቹ ሁሉ ርቀውት ስሙ ብቻ የሚጠቀስ ግንባር ሆኖ ቀርቷል። ሌላው ቢቀር ተስማሙም ተለያዩ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ስርዓት ባለውና በሰለጠነ መንገድ መወያየት እንኳ አልቻሉም። ጭራሽ ማዶ ለማዶ ሆነው እንካ ስላንቲያ ሲገጥሙ እየተመለከትን ነው።

አንዲያውም አንዳንዱ የኢህአዴግ አካል የራሱ የሆነ አገራዊ መንግስት የመሰረተ ያህል እየተሰማው ከፌዴራሉ መንግስት እዝ ውጭ የሆነ ይመስላል። ሌላው መርሁ ሁሉ ተሳክሮበት ሲዋዥቅ ይታያል። ከፅንፈኞች ጋ የወገነ የሚመስል ሃይልም አለ። ባጠቃላይ ግንባሩ ውስጥ የሃይል አሰላለፍ መደበላለቅ ጎልቶ ይታያል። በሌላ አነጋገር ኢህአዴግን ኢህአዴግ ሊያሰኘው የሚችለው የአመለካከትም ሆነ የተግባር አንድነት ከነበረበት ብሶ ጭራሽ ድራሹ ጠፍቷል።  በዚህ ምክንያትም አሁን ላይ አገር እየመራ ያለው የፖለቲካ ድርጅት ማን እንደሆነ ለማወቅ ፈታኝ ሆኗል።

 

ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር፡

አገሪቱን እየመራ ያለው እርሰዎ የሚመሩት ኦዲፒ ነው እንዳንል እርሰዎ እከተላቸዋለሁ ከሚሏቸው መንገዶች ያፈነገጡ ወይም የሚቃረኑ ድርጊቶች ሲፈፀሙ እያስተዋልን ነው። ለምሳሌ የኦዲፒ አመራሮች በአዲስ አበባ “ባላደራ ም/ቤት” አባላት ላይ እየወሰዷቸው ያሉ ፈር የለቀቁ የመብት ጥሰቶች እርሰዎ አለኝ ከሚሉት ዴሞክራሲያዊ ራዕይ ጋ አብረው የሚሄዱ ናቸው ብየ አላምንም። ሌላው አሁንም ኦዲፒ በሚመራው ክልል ውስጥ በመንግስት ባላስልጣናት ይሁንታ ጭምር መንገዶች ሲዘጉና ሰላማዊ ሰልፎች ሲከለከሉ ማየት እየተለመደ መጥቷል።

በተለያየ መንገድ እንደሚገለፀው አገሪቱ እየተመራች ያለችው በአዴፓና በኦዲፒ ጥምረት ነው ብለን እንዳናምን እንኳ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ስምምነት መጥፋቱን የሚያመላክቱ መናቆሮችንና ተግባራትን እያስተዋልን ነው። በዚህ ረገድ አንዳንድ የአዴፓ አካላት የሚያወጧቸው የቅሬታ መግለጫዎች ተጠቃሽ ናቸው። በተወሰኑ የኦዲፒና የአዴፓ አመራሮች መካከል የሚደረጉ የቃላት መወራወሮችም በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ያለውን ጤና ያጣ ግንኙነት ያመላክታል።

በሌላ በኩል አገር እየመሩ ያሉት እርሰዎ ብቻወን ሆነው ነው ብለን እንዳናስብ ደግሞ የእርሰዎ “የመደመርና” ኢህአዴግን የማዋሃድ ፍላጎቶች እርሰዎ በፈለጉት ጊዜና ፍጥነት ተግባራዊ መሆን ተስኗቸው ሲንደፋደፉ አያየን ነው።

እነዚህን ከላይ የጠቀስኳቸውን ነጥቦች አጠቃልየ ስመዝናቸው ነው እንግዲህ የሃገሪቱ ቁጥር አንድ ችግር እርሰዎ የሚመሩት ኢህአዴግ እንደሆነ ልጠቁመዎ የተገደድኩት።

 

ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር፡

ላሳስበዎ የፈለኩት ሁለተኛው ችግር ስርዓት አልበኝነት ነው። በእርግጥ ይህ ችግር በቀጥታም ሆነ በተዘዋሪ መንገድ ከኢህአዴግ መዝረክረክና መወነቃቀጥ ብሎም ከስም ውጭ በገቢር አለመኖር ጋ የተገናኘ እንደሆነ እገነዘባለሁ። ይሁን እንጅ ከክብደቱ አንፃር ራሱን አስችየ እንደችግር አስቀምጨዋለሁ። እውነት ለመናገር ኢትዮጵያ ውስጥ ስርዓት መጥፋት የጀመረው አቶ ሃይለማሪያም ጠቅላይ ሚ/ር ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ እረዳለሁ። እጅግ እየባሰና አሳሳቢነቱ ጎልቶ እየወጣ ያለው ግን እርሰዎ አመራር ላይ ከወጡ ጀምሮ እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው። ለምሳሌ ያህል ሰው ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ በአደባባይ የተሰቀለው፣ ቤተክርስቲያን ውስጥ በደንጋይና በዱላ የተቀጠቀጠው፣ መንገድ እየተዘጋ ያለው፣ አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ ዜጎች ለአመታት ከኖሩበት ቦታ በማንነታቸው እየተፈናቀሉ የሚገኙት፣ በቡድኖች ማስፈራሪያ ምክንያት ፍርድ ቤቶች ነፃነታቸውን እየተነፈጉ ያሉት በርሰዎ ዘመን እንደሆነ ለርሰዎም የሚጠፋዎት አይመስለኝም።

ህግ የማስከበር ስራ ተሰራ በተባለበት ሁኔታ እንኳ ወጥነት የጎደለውና አድሎ የተሞላበት የሚመስልበት ሁኔታ ሰፊ መሆኑን መታዘቤን ልደብቀዎ አልሻም። በዚህ ረገድ አንድ አገር ውስጥ እየኖሩ አንዱ በጣም የከፋ የሙስናም ሆነ ሌላ የወንጀል ድርጊት እንደፈፀመ እየታወቀ በክብር የሚኖርበት፤ ሌላው ደግሞ በስራ ግድፈት ወይም እንዲሁ ሰበብ ተፈልጎለት በእስርና በክስ የሚማቅቅበት ሁኔታ ይስተዋላል።

ከዚህ አልፎም በአንድ በኩል እንቅስቃሴው ህገወጥ ነው ቢባል እንኳ በጠጨባጭ ማስረጃ አስደግፎ ወደፍትህ ስርዓቱ ከማቅረብ ይልቅ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እታገላለሁ የሚልን ሃይል ሰበብ አስባብ በመፈለግ ለማጥፋት ጥረት ሲደርገ ይታያል። በሌላ በኩል ደግሞ ህገመንግስቱንና የፌዴራላዊ ስርዓቱን መሰረታዊ ችካሎች በሚቃረን መልኩ ከዴሞክራሲያዊ ምርጫ ውጭ እራሱን እንደ “ሁለተኛ መንግስት” የቆጠረና የመሰለውን የመንግስት አካል እጅ ጠምዝዞ የፈለገውን የሚያስፈፅም፣ ሌላውን እንደፈለገ የሚዘልፍ፣ ያሻውን መልዕክት በማስተላለፍ ጉዳዩን የሚከውን፣ በፈለገው ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያስደርግ፤ አመፅና ሁከት የሚቀሰቅስ፣ ሲፈልግ ደግሞ ሌላው ሰልፍና ስብሰባ እንዳያደርግ የሚከለክል ሃይ ባይ የሌለው ከህግ በላይ የሆነ ግለሰብና ቡድን ተፈጥሯል።

ከዚሁ ከስርዓት አልበኝነት ጋ በተያያዘ ስርቆት፣ ዝርፊያና ሌሎች መሰል ወንጀሎችም እየተበራከቱ እንደሆነም አፅንዖት ሰጥቸ ላስገነዝበዎ እወዳለሁ። በተለያየ መንገድ እንደሚገለፀው ከሆነ   በስርዓት አልበኝነት ምክንያት አዲስ አበባም ሆነ ሌሎች አከባቢዎች ሰው በሰላም ወጥቶ ለመመለስ የደህንነት ስጋት እየተሰማው ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ከደህንነት ስጋት ጋ ተያይዞ በአለም ላይ ብዙም ስማቸው ሲጠቀስ ያልነበሩት ኢትዮጵያ በአጠቃላይና አዲስ አበባ ደግሞ በተለይ የማፍያ መሰል እንቅስቃሴዎች ማእከል ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላካቾች ናቸው።

በእርግጥ ሽግግር በሚመስል በእንደዚህ አይነት ወቅት የተጠቀሱት ችግሮች መፈጠር አልነበረባቸውም ብሎ መናገር ከእውነታዎች ጋ መጋጨት ይሆናል። በኛ አገር እየሆነ ያለው የስርዓት አልበኝነት ደረጃ ግን መረን ለቆ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሷል። ሁኔታዎች በአጭሩ ካልተቀጩ ከደህንነትና ከፀጥታ አካላቱ ቁጥጥር ውጭ ይሆኑና ከተለያዩ የወንጀልና የማፍያ መሰል ተግባራት አልፈው የስርዓት አልበኝነቱ የመጨረሻ ደረጃ ወደሆነው መጠፋፋት ሊያደርሱ እንደሚችሉ ላፍታም ቢሆን መዘንጋት ያለበዎ አይመስለኝም።

 

ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር፡

እንደ ችግር ላስገነዝበዎ የወደድኩት ሶስተኛው ነጥብ ደግሞ በጋራ ማንነት ላይ ያሉ የሰሉ ልዩነቶችን ይመለከታል። በዚህ ረገድ በጋራ ታሪካችን ላይ ስምምነት የለንም። ላንዱ ጀግና የሆነው ለሌላው ወራሪ ነው። ላንዱ የመብት ተሟጋች የሆነ ሰው ለሌላው ከፋፋይ ነው። ከዚህ አልፎም በሰንደቅ አላም ላይ እንኳ መግባባት አልተቻለም። በዚህ ረገድ አንዳንዱ ሰንደቅ አላማየ ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ሆኖ መሃሉ ላይ ኮከብ ያለበት ነው ይላል። ሌላው አይ የኔ ሰንደቅ አላማ ኮከብ የሌለው ምን አልባትም የአንበሳ አርማ ያለበት ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ነው ሲል ይሞግታል። ከኒዚህ ውጭ ያለ የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ሰንደቅ አላማየ የፖለቲክ ድርጅት እንደ አርማ እየተጠቀመበት ያለ ምስል ነው ይላል። በዚህ ምክንያትም የተለያዩ ግጭቶች እየተከሰቱ የሰው ህይወት ሲቀጠፍና ንብረት ሲወድም ይታያል። በፌዴራል የስራ ቋንቋ ላይም ውጥ የሆነ አመለካከት የለም።

በሌላ በኩል ደግሞ የቀድሞ “ገዥ መደቦችንና” የተለያዩ ሌሎች “ቡድኖችን” የሚመለከቱ ናቸው እየተባሉ ጥቅም ላይ የሚዉሉ የወል ስሞች ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ እንደሆነ በደንብ ሊረዱት ይገባል የሚል እምነት አለኝ። እኔ እንደታዘብኩት እነዚህ ስሞች እየፈረጁ ያሉት ነበሩ የተባሉትን ገዥ መደቦች ወይም ቡድኖች ብቻ ሳይሆን እነሱ የወጡባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በሙሉ ነው ብየ አስባለሁ። ከዚህ ውጭ ያለው ማስተባበያ መሸዋወድ ካልሆነ ሌላ ጥቅም አለው ብየ አላምንም። ለምሳሌ የሱንም ሆነ የቤተሰቡን ኑሮ ለማሸነፍ እላይ እታች ሲራወጥ የሚውል እንጅ ስለሰዎች የብሄር ልዩነት ትኩረት የማይሰጥ አርሶ አደር አማራ ስለሆነ ብቻ ትምክህተኛ ወይም ነፍጠኛ ሲባል፤ ኦሮሞ ወይም ትግራዋይ ከሆነ ደግሞ ጠባብና ከፋፋይ የሚል ስም ሲለጠፍበት መስማት የተለመደ ነው። እነዚህን የመሳሰሉ ለመናገር ቀላል የሆኑ ግን አደገኛ ትርጉም ያላቸው ቃላቶች አሁንም ጥቅም ላይ እየዋሉ ልዩነቶችን እያሰፉ እንደሆነ በአንክሮ ሊገነዘቡ ይገባል። ይህን ስል ግን ሰዎች ወይም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት አይገለፁባቸው ለማለት እንጅ አመለካከቶቹና አስተሳሰቦቹ ጭራሽ አልነበሩም ወይም የሉም እንዲሁም አይወገዙ  እያልኩ እንዳልሆነ እንዲገነዘቡልኝ እፈልጋእሁ።

ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር፡

በዚህ ፅሁፍ ከፍ ብየ የገለፅኳቸው ችግሮች አሁን ባለኝ መረጃ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸውና መፍትሄ ሊቀመጥላቸው ይገባል ብየ ያመንኩባቸው እንጅ አገራችን ውስጥ ያሉ ችግሮች እነዚህ ብቻ ናቸው እያልኩ እንዳልሆነ እንዲረዱልኝ እፈልጋለሁ። ሁሉንም ያገራችን ችግሮች ልጥቀስ ብልማ ሊወስድ የሚችለውን ጊዜ፣ ሊያልቅ የሚችለውን ወረቀትና በዕር መገመት አዳጋች ይሆናል። ለማንኛውም ችግሮቹን ካስገነዘብኩዎ ዘንዳ እግረመንገዴን ደግሞ መፍትሄውችንም ብጠቃቅስ ምን አይነት ደፋር ነው እንደማይሉኝ እገምታለሁ።

የመጀመሪያ አድርጌ ልጠቁመዎ የምፈልገው ቁልፍ መፍትሄ ኢህአዴግን ተቋማዊ አድርገው በመርህና በስርዓት መምራት ያለበዎ መሆኑን ነው። እርሰዎም እንደሚያውቁት ኢህአዴግ የራሱ ፕሮግራምና ህገደንብ አለው። ፕሮግራሙና ህገደንቡ በጉባኤ እስካልተቀየሩ ድረስ ግንባሩ ሊገለገልባቸው ይገባል ብየ አምናለሁ። ፕሮግራሙም ሆነ ህገደንቡ እንዲሁም ሌሎች የግንባሩ መሰረታዊ አቋሞች እንዲቀየሩ ወይም እንዲሻሻሉ ከፈለጉ የግንባሩን አሰራር በመከተል ሃሳበዎን አራምደው ተቀብይነት ሲያገኙ ብቻ እንዲፈፀሙ ቢያደርጉ በዴሞክራሲያዊ ሂደት እና በተቋማዊ አሰራር ላይ ያለዎትን ቁርጠኝነት ማስመሰከር ብቻ ሳይሆን ውጤታማም ይሆናሉ ብየ አስባለሁ። ምናልባት በተለያየ ደርጃ ያሉ የግንባሩ መዋቅሮችና የግንባሩ ጉባኤ ሃሳበዎን ውድቅ ቢያደርጉት ውጤቱን በፀጋ ተቀብለው ቀጣይ ትግል ውስጥ ለመግባት በመዘጋጀት ግንባሩ ተዋሃደም አልተዋሃደ ሃሳብ የሚንሸራሸርበት መዕከል እንዲሆን ቢያስችሉት ለሃገሪቱና ለህዝቦቿ የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ይሆናል። ከዚህ ውጭ ያሉ መንገዶች አምባገናዊ ስለሚሆኑ ባይመርጧቸው የሚል ሃሳብ አለኝ።

በዚህም መሰረት “መደመር” አብዮታዊ ዴሞክራሲን እንዲተካና ኢህአዴግም ኢንዲዋሃድ ከፈለጉ የግንባሩን ሀገደንብና አሁን በስራ ላይ ያለውን አሰራር ተከትለው መሆኑን መዘንጋት አይገባዎትም። በዚህ መንገድ መሄዱ የብልህነተዎንና በተቋማዊ አሰራር ያለዎን ቁርጠኝነት ያሳይ እንደሆነ እንጅ ተሸናፊ ወይም ደካማ ሊያደርገዎ አይችልም። ይህ ሲሆን ኢህአዴግ የግለሰብ መሪዎች መፈንጫ መሆኑ ቀርቶ በመርህና በስርዓት የሚመራ ድርጅት ወደመሆን ይሸጋገራል። ኢህአዴግን በዚህ መልክ ተቋማዊ በሆነ መንገድ እየመሩ ያስወሰኗቸውን የፕሮግራምና የህገደንብ አጀንዳዎች አልቀበልም ብሎ ከግንባሩ የሚወጣ አካል ወይም ግለሰብ ቢኖር እንኳ ይህን ወይም ያንን ባደርግ ኖሮ ብለው የሚፀፀቱበት ሁኔታ አይኖርም።

ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር፡

ሁለተኛው የመፍትሄ መንገድ ነው ብየ የምጠቁመዎ ደግሞ የህግ የበላይነትን ከንግግር አልፎ በገቢርም ማስከበር ያለበዎ መሆኑን ነው። በእኔ እምነት ስርዓት አልበኞች እንደፈለጉ እንዲፈነጩ መፍቀድ ዴሞክራሲያዊ መሆነንን አያሳይም። እንዲያውም በተቃራኒው ስርዓት አልበኝነትን ለመግታት ጠንክሮ አለመስራት ፀረ-ዴሞክራሲያዊነትን ያጎለብታል ባይ ነኝ። በዚህ ረገድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር መስከረም 2012 የወጣው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ መግለጫ “…the rule of law and democracy are interlinked and mutually reinforcing…” በሚል ግልፅ የሆነ ቋንቋ አስፍሮታል። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ዴሞክራሲና የህግ የበላይነት እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩና የሚመጋገቡ እንጅ የማይቃረኑ መሆናቸውን ነው።  ለምሳሌ ምርጫ በሰላም የሚካሄደውና ህዝቡ ወኪሎቹን በፍላጎቱ የመምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብቱ የሚከበርለት የህግ የበላይነት ሲኖር ብቻ ነው።  ምርጫ በህግ ካልተመራ ህዝቡ ወኪሎቹን በስርዓት መምረጥ አይችልም። ይህ ሲሆን ደግሞ ህዝቡ በነፃ ፍላጎቱ በመረጣቸው ወኪሎቹ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተነፈገው ማለት ነው። ከዚህ በመነሳት የህግ የበላይነት መከበር ዴሞክራሲን እንዲፋፋ እንጅ እንዲቀጭጭ አያደርገውም ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል።

በተጨማሪም የህግ የበላይነት ይንገስ እያልኩ ያለሁት የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥበቃ እንዲደርግላቸውና የወንጀል ተግባራትን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን የራሰዎ መንግስታዊ አስተዳደር የሚከበረውም በዚህ መንገድ እንደሆነ ላሳስበዎ ስለወደድኩ ነው። የህግ የበላይነት ካልተከበረ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ጉልበት አለኝ የሚል ሃይል እየተነሳ መንግስትን አሳንሶ የሚያይበት ወይም የሚገዳደርበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም። አሁን እያየናቸው ያሉ አንዳንድ ክስተቶች የሚያመላክቱትም እሱን ነው።

በሌላ በኩል የህግ የበላይነት እንዲከበር ሲያደርጉ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበዎ አይዘንጉ። ለርሰዎም ግልፅ እንደሚሆነው ህግ ፍትሃዊ የሚሆነው ሁሉንም ዜጎች በተመሳሳይ አይን ማየት ሲችል ነው። ከዚህ አልፎ ግን አሁን እንደሚታየው ዜጎች የሚጠየቁትም ሆነ ነፃ የሚወጡት ብሄራዊ ማንነት፣ የፖለቲካ አመለካከት፣ የግል ጥላቻና ሌሎችም መስፈርቶች ግምት ውስጥ ገብተው ከሆነ የህጉ አፈፃፀም ፍፁም ኢፍትሃዊ ይሆናል። በዚህ መንገድ ደግሞ ዴሞክራሲን መገንባትም ሆነ የህግ የበላይነትን ማስፈን አይቻልም።

ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር፡

ኢህአዴግን ተቋማዊ ከማድረጉና የህግ የበላይነትን ከማስከበሩ ጎን ለጎን እንደሶስተኛ አድርጌ ልጠቁመዎ የወደድኩት መፍትሄ ሃገራዊ የሆኑ ውይይቶችና ድርድሮች እንዲጀመሩ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ ነው። እነዚህ ውይይቶች በማዕከል የሚመሩ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያካተቱ፣ ቀጣይነት ያላቸው፣ ህዝብ በሚመርጣቸው ዜጎች አወያይነት የሚካሄዱ፣ ነፃና ከመሸዋወድ የፀዱ ቢሆኑ  እስካሁን በነበረው ታሪካችን በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የሻከሩ ግንኙነቶችን ለማስተካከል ይጠቅማሉ ብየ አስባለሁ።

የውይይት አጀንዳዎቹ ደግሞ በታሪካችን፣ በሰንደቅ አላማ፣ በፌዴራል መንግስቱ የስራ ቋንቋዎች፣ በፌዴራል ስርዓቱ፣ ህብረተሰብን ይወክላሉ በሚባሉ የወል ስሞች፣ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠልና በሌሎች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሚነሱ የልዩነት ነጥቦች ዙሪያ ያተኮሩ ቢሆን ይመረጣል የሚል ግንዛቤ አድሮብኛል።

በውይይቶቹ ላይ የተደረሱ ስምምነቶች ሲኖሩ እነሱን ለይቶ በማውጣት እንዲጎለብቱ በማድረግ በሌሎቹ የልዩነት ነጥቦች ዙሪያ ተጨማሪ ውይይቶችን ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል። አንዳንድ ልዩነቶችን ማጥበብ ባይቻል እንኳ ልዩነትን በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ማራመድ እንደሚገባ የጋራ ስምምነት መድረስ የሚያስችል ጥረት ማድረግ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው የሚል ፅኑ እምነት አለኝ። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ከልዩነቶቹ ውስጥ መሰረታዊ የሆኑትን በመለየት ህዝበ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው በማድረግ ሚዛናዊነትን ለማጎልበት መሞከር በጎ ተግባር ነው እላለሁ።

ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር፡

ለማጠቃለል ያህል በዚህ ፅሁፍ ላሳስበዎ የፈለኩት አብይ ጉዳይ ቢኖር ከላይ የተገለፁትን ችግሮች በሚገባ አጢነው መፍትሄዎቻቸው ላይ ቢሰሩ አገሪቱና ህዝቦቿ ካሉበት ውጥረት ተንፈስ ሊሉ ይችላሉ የሚለው ነው። ይህ መሆኑ ለእርሰዎም ጊዜ ስለሚሰጠዎ የሃገሪቱንና የህዝቦቿን የተስፋ ችካል ለመቸከል አለዎት ብየ የማስበውን ፍላጎት እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ሃሳቦችን ለማፍለቅ እድል ይሰጠወታል የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ።

 

መልካም የስራና የስኬት ዘመን እመኛለሁ!!!

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.