የጃዋር መንግሥት የሲዳማን ሕዝበ ውሳኔ አስፈጻሚ ነው!? የሚመለከተው አካል ምን ይሰራል!?

ከቀናት በፊት የጃዋር ተከበብኩን ተከትሎ የተፈጠረውን ሀይማኖት እና ብሄር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንዲፈጸም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የሚባሉ ሲጠቀሱ የዚህ ሰው ስም አብሮ ይነሳል።ጃዋር ያለው ሁለተኛ መንግሥት ጡንቻውን ከሚያሳይባቸው እና የኦዴፓ ባለስልጣናት፣በደህንነት እና በልዩ ልዩ የጸጥታ መዋቅር ያሉ አንዳንድ ጽንፈኞች ብቻ ሳይሆን ጊዜያችን ነው የሚሉ ባለሀብቶች ጭምር ይሄን ቡድን ይደግፉታል።ስለዚህም በነውጡም መንግስታዊ ውንብድና ውስጥም እጁ አለበት።

የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን ተከትሎ በነጻ ምርጫ ሕዝቡ የፈለገውን እንዲመርጥ ከምንም በላይ ይህን ሰበብ አድርጎ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ የብዙሃኑ ፍላጎት ነው። ከዚህ ቀደም የሲዳማ ክልልነት ሐምሌ 11/2011ይታወጃል በሚል ለብዙ ሰው ህይወት መጥፋት እና የዕምነት ተቋማት እና የዜጎች ውድመት ተከስቷል። እርግጥ ከንፈር ለመምጠጥ ካልሆነ የአብይ አህመድ(ዶ/ር) አንደኛው መንግስት የዜጎች ጉዳይ ሳይሆን የእነ ጃዋር ምቾት መነካት እንደሚያሳስበው ከ86 ንጹሃን ታርደው፣በድንጋይ እና በዱላ ተቀጥቅጠው፣በስለት ተወግተው ፣በጥይት ተመትተው መሞት ግድ እንዳልሰጠው በወንጀሉ የሚጠረጠረውን ዋነኛ ለህግ ለማቅረብ አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን በሐረሩ ስብሰባ ለዚህ ህገወጥ ቡድን መሪ ያለው አጋርነት ተጋልጡዋል።

አሁን የጃዋር መንግሥት ሲዳማ ገብቶ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረገ ነው እንዳይባል በምርጫ አያምንም። እስክንድር በሕዝብ ድምጽ አዲስ አበባን የተቆጣጠሩትን (አዲስ አበባን የሚያስተዳድረው የኦዴፓ የበላይነት ያለበት ኢህአዴግ መሆኑ ሳይዘነጋ) ምርጫው ይምጣ እንሸኛቸዋለን ማለት በቀጥታ ከኦሮሞ ጋር በማገናኘት ይሄው ግለሰብ በይፋ እስከማስፈራራት ደርሱዋል። ለእነሱ ከምርጫ ቅስቀሳም በላይ አልፎ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ ወንጀል መፈጸም ይቻላል።ማን ይጠይቃል።ከዚህ ቀደም ሲዳማ ዞን ላይ ላስፈጸሙት ወንጀል ሌሎች ሲጠየቁ በጉልበት የሲዳማን ክልል ነህ አውጁ ያለው ጃዋር ጫፉን የነካው የለም።

የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ የሲዳማ ዞን መላው ነዋሪዎች ቀዳሚ ጉዳይ ነው።በነጻ የሰጡት ድምጻቸው በአግባቡ ተቆጥሮ የሚመጣው ውጤት ለቀጣዩ ሂደት ስኬት ነው ይህ ደግሞ የምንንም ጣልቃ ገብነት አይጠይቅም።የሀዋሳ ጉዳይ ከውጥረቱ ውስጥ ቀደም ሲል የክልሉ ምክር ቤት በሰጠው ውሳኔ እልባት አግኝቷል ።አሁን የዚህ ቡድን ድብቅ ፍላጎት ምንድነው? ማሸበር? የሕዝብ ድምጽ መስረቅ? የሲዳማ ሕዝብን ፍትሃዊ ጥያቄ እና ማንኛውንም ህጋዊ መስመር ተከትሎ የሚሄድ ሂደት ሁሉንም ወገን ሊያስደስት ይገባል።ከዚው ውጭ የጊዜው የግጭት ነጋዴዎች ጣልቃ ገብነትም አያስፈልገውም። ሕዝበ ውሳኔው ያለ አንዳች ጫና መደረጉን ሁሉም ወገኖች እርግጠኛ ሆነው መስረት አስከትሎም በየትኛውም ደረጃ ግጭት እንዳይፈጠር ማድረግ አለባቸው።በተለይ ወግድ መባል የሚገባውን ሀይል ከወዲሁ ወግድ ማለት አለባቸው።

ምርጫ ቦርድ ምርጫ አስፈጽማለሁ ብሉዋል። የጃዋር መንግሥት ደግሞ አስቀድሞ ይረዳኛል ያለውን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ትላንት ለሐምሌ 11 ግጭት ቆምሮ አልተጠየቀም።በቀደም በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች፣በድሬዳዋ ፣ በሐረር እና በአዲስ አበባ ለጠፋው ህይወት እና ንብረት የሚጠይቀው የለም።ስለዚህ ዛሬም ሕዝበ ውሳኔውን ተከትሎ ሊያስነሳ በሚችለው ነውጥ የሚጎዳው ሕዝቡ እንጂ በመግለጫ ስለ ህግ የበላይነት የሚፎክረው የእነ አብይ አስተዳደር አይደለም።

የዜጎች ተጨማሪ ሕይወት ሳይጠፋ ይህ ለአመጽ የሚንቀሳቀስ ቡድን ከአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤትን መግለጫ ከመከልከል ጀምሮ በጃዋር ቤት ዙሪያ መሳሪያ ታጥቆ እስከ መንቀሳቀስ የደረሰ ህገ ወጥ ታጣቂ መንግስት ውስጥ ባሉ ማጅራት መቺዎች እየተረዳ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ምርጫ ቦርድ ፣የሲዳማ ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች ከወዲሁ እጅህን በማለት ሕዝብ የፈለገውን በነጻነት እንዲመርጥ አንድ ሊሉት ይገባል።አስቀድሞ ላለቀ ሕዝበ ውሳኔ በምንም ምክንያት የንጹሃን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ስጋት ሊኖር አይገባም እንላለን።

ህብር ራዲኦ

1 COMMENT

  1. የሚመለከተው አካልማ፣ በነፍጠኞች ስለተሞላ፣ ሪፈረንደሙን ለማሰናከል ባለው ጉልበቱ ሁሉ ሴራ ስሸርብ ይውላል። ይህቺ ጽሁፍም የሴራው አካል ሳትሆን አትቀርም፣ አመጽ ይነሳል ብሎ ለመተንበይ ለድርጊቱ ከተዘጋጀው ይበልጥ ማን እርግጠኛ ይሆናል?!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.