‹‹የተፈጠረውን ችግር ሌላ መልክ እና ከከተማው ማኅበረሰብ ጋር ለማስተሳሰር የሚሞክሩ አካላት ከእውነታው መራቅ የለባቸውም፡፡›› የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ

ትናንት ምሽት በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የተማሪዎች ሕይዎት አልፏል፤ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳትም ደርሷል፡፡ ጉዳዩን አስመለክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን ለዞኑ አመራር እና ለፀጥታ ኃይሉ ችግር መፈጠሩ የተነገራቸው ምሽት 5፡00 ላይ መሆኑን ገልፀው 5፡15 ገደማ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ የፀጥታ ኃይል ይዘው መድረሳቸውን ነግረውናል፡፡
‹‹ግጭቱ በተፈጠረ 15 ደቂቃዎች ውስጥ የሁለት ተማሪዎች ሕልፈት እና የአካል ጉዳት ደርሶ ጠብቆናል፤ ከደረስን በኋላ ግን የፀጥታ ኃይሉ እስከ ንጋት ድረስ ችግሩን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ተቆጣጥሮ አድሯል፡፡ ጠዋት ላይም ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር በመሆን የተማሪ ተወካዮችን አነጋግረናል›› ያሉት ዋና አስተዳዳሪው አጥፊዎች ለሕግ እስኪቀርቡ ድረስም በተቀናጀ መልኩ እንሠራለን ነው ያሉት፡፡

ችግሩ ሌሊት ላይ ከመፈጠሩ እና ዩኒቨርሲቲው ከከተማው ወጣ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ‹‹የከተማው ነዋሪ ስለተፈጠረው ችግር ዕውቅና አልነበረውም›› ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ‹‹የተፈጠረውን ችግር ሌላ መልክ ለማስያዝ እና ከከተማው ማኅበረሰብ ጋር ለማስተሳሰር የሚሞክሩ አካላት ከእውነታው መራቅ የለባቸውም›› ብለዋል፡፡
ድርጊቱ ኅብር የኑሮ ዘይቤ በሚስተዋልበት የወሎ ምድር መከሰት ያልነበረበት መሆኑን ያመለከቱት አቶ ወልደትንሳኤ ‹‹የአካባቢው ማኅበረሰብ ተማሪዎቹን የተቀበለበት መንገድ ፍፁም ፍቅር የተሞላበት እና እንግዳ ተቀባይነትን የሚሳይ ነበር›› ብለዋል፡፡ ‹‹አሁንም ድርጊቱን የፈጠሩትን አካላት ለሕግ እስክናቀርብ ድረስ የተፈጠረውን ችግር እንደ መልካም አጋጣሚ ወስደው የሚያራግቡ አካላት ሊታገሡ ይገባል›› ብለዋል፡፡

አብመድ በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ነዋሪዎችን ለማነጋገር እንደሞከረው የአካባቢው ማኅበረሰብ ስለተፈጠረው ችግር ሚዲያ ላይ እስኪሰማ ድረስ ዕውቅና እንዳልነበረው ታዝቧል፡፡ አብመድ ተማሪዎቹ ከዞኑ አመራር፣ ከፀጥታ ኃይሉ እና ከዩኒቨርሲቲው አመራር አካላት ጋር የሚያደርጉት ውይይት እንደተጠናቀቀ መረጃውን ለማድረስ ጥረት ፡፡

አብመድ
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.