በአዲሱ ውህድ ፓርቲ መቀላቀል የማይፈልግ የኢህአዴግ አባልም ሆነ አጋር ፓርቲ ይቀራል እንጂ በአብላጫ ድምጽ አይወሰንም

በአዲሱ ውህድ ፓርቲ መቀላቀል የማይፈልግ የኢህአዴግ አባልም ሆነ አጋር ፓርቲ ይቀራል እንጂ በአብላጫ ድምጽ እንደማይወሰን የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ሕወሃት ላለፉት ሶስት ዓመታት ጥናቱ ሲያደረግ ተቃውሞ አለማቀርቡን፤ ይልቁንስ ጥናቱን ሲመራና ሲደግፍ መቆየቱን ገልጿል።

በኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል የጥናትና ምርምር ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በሌሎች ፌዴራሊዝም ስርዓት ባላቸው እንደ ህንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ቤልጅየም፣ ናይጀሪያ ባሉ አገሮች የሚገኙ ፓርቲዎች አገር አቀፍ ናቸው።

በግንባርነት የቆየው ኢህአዴግ በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ራዕይ ለማሳካት ተቸግሮ መቆየቱን ገልጸዋል።

”በዚህም በተቀናጀ አስተሳስብ አገር ለመምራት ኢህአዴግ ሕብረ ብሔራዊ ውህድ ፓርቲ ለመሆን ወደመጨረሻው ተቃርቧል” ብለዋል።

ውህደቱ በአራት የግንባሩ እህት ድርጅቶችና በሌሎች አጋር ፓርቲዎች በድምሩ ዘጠኝ ብሄራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከታችኛው አባል ድረስ በግልጽ ተነጋግረው የሚወስኑት መሆኑን ገልጸዋል።

የትኛውም ፓርቲም ሆነ የፓርቲ አባል በውህዱ ፓርቲ ውስጥ እንደማይቀጥል ከወሰነ ይቀራል እንጂ በሌሎች ድርጅቶች አብላጫ ድምጽ እንደማይወሰን ተናግረዋል።

የውህደቱ ጉዳይ የአገር ጉዳይ ቢሆን በድምጽ ብልጫ ይወሰናል እንጂ በፓርቲ አስተሳስብ ለመደራጀት በአብላጫ እንደማይወሰን ገልጸዋል።

እስካሁንም ዘጠኙ ብሔራዊ ፓርቲዎች ወደ አገራዊ ፓርቲ ለመሸጋገር ውይይት እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ በጥናቱ መሰረት በሁሉም ብሔራዊ ድርጅቶች እስከ ማዕከላዊ ኮሚቴ ድረስ ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቁመዋል።

በኢህዴግ አባል ፓርቲዎች ሽኩቻ በውህደቱ ሂደት ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም ወይ ለሚለው ጥያቄም፤ ኢህአዴግ ተራማጅ ፓርቲ በመሆኑ ሁሌም ክርክርና ሽኩቻ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ሕወሃት ውህደቱን እንደሚቃወም በይፋ ሙሉ መግለጫ አለማውጣቱን ገልጸው፤ ላለፉት ሶስት ዓመታት የኢህአዴግ ውህደት ጥናት ሲደረግ ተቃውሞ አለማቅረቡን፤ ይልቁንስ ጥናቱን ሲመራና ሲደግፍ መቆየቱን ገልጸዋል።

የሕወሃት አባል በሆኑ ግለሰቦች ደረጃ ውህደቱን የሚቃወሙ ሃሳቦች ሲንጸባረቁ እንደሚስተዋል ገልጸው፤ ”ውህደቱ የራሱ ሂደት ያለው እንደሆነ በመግለጽ የመጨረሻው ሕወሃት ውሳኔ ወደፊት የሚታይ ነው” ብለዋል።

ኢዜአ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.