ሌላ ፈታኝ ጊዜ መጥቷል! – ጌታቸው ሽፈራው

ገና ክርክር ላይ እያሉ በርካቶች ታርደዋል። ለስልጣን ሲባል በሀሰት ተፈፀመብን ያሉ ፅንፈኞች ሌላው ላይ ጭካኔ ሲፈፅሙ፣ ከስልጣን የሸሹት ሽብር ሲያስፋፉ፣ በንፁሃን ደም ለመመለስ ሲጥሩ ዝም ተብለዋል። ከአያያዛቸው የወፊቱ የከፋ እንጅ የተሻለ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። በዚህ ወቅት፣ “ውህደት” ይጠቅማል አይጠቅምም የቅንጦት ጥያቄ ነው። ውህደቱ ፍትሕ ከሚጠይቁት ቀርቶ ኢህአዴግን ጠፍጥፎ ከሰራው ትህነግ/ሕወሓት እጅ ውጭ ሆኗል። የለውጥ ኃይል ነኝ የሚለው አንደኛው አካል በሙሉ ልቡ ሳይሆን እየሻከረውም ቢሆን የገባበት መሆኑን እያየን ነው። ውህደቱ ከፍትሕ ጠያቂው እጅ ውጭ ነው።

ፍትሕ ጠያቂው በተለይም በዚህም በዛም የሚጎሸመው አማራው ማተኮር ያለበት እጁ ላይ ያለው አማራጭ ላይ ብቻ ነው።
ውህደት የሚባለው ደኢህዴን፣ ኦዴፓንና አዴፓን ከገጠማቸው የውስጥ ፈተና ይታደግ ይሆናል። አጋር የሚባሉት ፓርቲዎች ለማስጠበቅ የሚጥሩትና የተገባላቸው ቃል እንደሚኖር እሙን ነው። በሌላ በኩል ትህነግ/ሕወሓት እና የኦሮሞ ፅንፈኛ ቡድን ውህደቱን ተቃውሞ እየተፋለመ ነው። ሲፋለሙ የሚረግጡት፣ ሲጓተቱ የሚቀነጥሱት አማራ፣ አዲስ አበባ፣ ቤተ ክርስትያን እና ደቡብ ውስጥ የሚገኘው የተለያየ “ብሔር ብሔረሰብ” ህልውና ህይወት ነው። ውህደቱን ለሕዝብ ሳይሆን ለስልጣናቸው ሲሉ የሚቃወሙት ኃይሎች ሕዝብን ሲያስፈጁ፣ ውህደቱን ለሕዝብ ሳይሆን ለስልጣናቸው የሚፈልጉት ኃይሎች ድምፃቸውን አጥፍተው ሰንብተዋል። ውህደቱን የማይፈልጉት አካላት የሚጠለፍበት ቦታ ላይ ሁሉ እግራቸውን እየሰደዱ ለማደናቀፍ መስራታቸውን ይቀጥላሉ። ውህደቱን የሚፈልጉት ኃይሎች ላለመውደቅ ሲሉ የተቸከሉበት ላይ ሆነው የሞተው ሲሞት፣ የቆሰለው ሲቆስል፣ የወደመው ሲወድም እያዩ ሚዛናቸውን ለማስጠበቅ ይጥራሉ። እነዚህ ኃይሎች አላማቸው ምንም ያህል የእኩይ ይሁን ጠንቅቀው ያውቁታል። ለሕዝብ ቆመናል ቢሉ እንኳ አላማቸው ተለይቶ ያደረ፣ የሕዝብ ደም የዝናብ ውሃ የሚመስላቸው ኃይሎች ናቸው። አማራው እነዚህ ኃይሎች በዜጎች ሕይወት እንደሚነግዱ፣ ሀገር እንደሚያፈርሱ በትንሹ ለ28 አመት ጩኸት አሰምቷል፣ ተጨንቋል። የእነሱ ተግባር ያልተጠበቀ አይደለም። ይህን ፈታኝ ወቅት አሁንም በጥንቃቄ ማየት ያለበት ለፍትሕ እታገላለሁ የሚለው በተለይም አማራው ነው!

1) በዚህ ወቅት የፖለቲካ አሰላለፉን ተረድቶ የጥያቄ ደረጃ ከማውጣት ይልቅ ከዚህም ከዛም የሚራኮት ኃይል የሚመጣውን መከራ ለመመከት የሚጥረውን ኃይልም ይሁን ሕዝብ ከመጥለፍና ከማደናገር ውጭ ፋይዳው እምብዛም ነው። የሰው ልጅ ቀርቶ የዱር እንሰሳት የውስጥ ሕግ አላቸው። ድንጋይ እየፈነቀለ፣ ተራራ ለተራራ ሲዘልል፣ እርስ በእርስ ሲቧጨቅ የሚውል የዝንጀሮ መንጋ ከጠላት ለመዳን ወይንም ጠላት ሳይሰማ የፈለገውን ለማግኘት፣ ሰውን ያህል ፍጡር አታልሎ ማሳ ለመውረር የእርስ በእርሱን ጉዳይ ይተዋል። መጯጯሁን ለተወሰነ ጊዜ ይተዋል። ህይወትን በቅጡ ያለመዱት ጨቅላዎቹ ሳይቀር ተኮርኩመው ለጋራ ደሕንነት ፀጥ ይላሉ። ተልዕኳቸውን ከጨረሱ በኋላ እንደለመዱት የናዳ መዓት ያወርዳሉ፣ ጋራና ሸለቆውን በጩኸት ያደነቁራሉ፣ እርስ በእርስ ይቧጨራሉ። ስርዓት የሌለው የዱር እንሰሳ እንኳን ለአንድ አላማ ሲል ስርዓት ይዞ፣ ጎራ አውቆና ለይቶ ይሰለፋል።

2) በዚህ ወቅት ውህደት የሚባለውን “ለማደናቀፍ” ከዚህም ከዛም እግሩን እየላከ ለመጥለፍ የሚሞክረው፣ በብጥብጥና ሁከት ወደ ስልጣን ለመምጣት የፈለገውን የትህነግ/ሕወሓት እና የኦሮሞ ፅንፈኞች እንዲሁም ይህን በጥባጭ ኃይል ከመምታት ይልቅ ስልጣኑን ለማስጠበቅ የሕዝብ ደም እየረገጠ ጉዞውን የሚቀጥለውን ኃይል ሳይረዳ ከንቱ ጩኸት የሚጮህ ካለ አላማውን ለማሳካት፣ ለመኖር እንኳ ከዝንጀሮ አንሷል ማለት ነው። በዚህ ወቅት አላማቸውን አውቀው፣ አላማቸውንም ታውቆባቸው ሕዝብ ከሚያሳርዱትም ሲታረድ ዝም ብለው ከሚያዩትም በላይ ከዋለው ውሎ ለመጓተት ምክንያት ፈልጎ የሚመጣው ነው ይበልጡን የሚጎዳው። በዚህ ወቅት ፈታኙን ወቅት የከፋ የሚያደርገው የወገንንም ለስልጣን ብለው ሕዝብን ለእርድ ያቀረቡትን ኃይሎች አሰላለፍ በቅጡ ሳይረዳ ከዚህም ከዛም የሚዘልል፣ ራሱ አጋንኖ መስማት የሚፈልገውን ጩኸት ብቻ መጮህ ላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው። ይህን ወቅት የከፋ የሚያደርገው የራሱ ሕዝብ፣ ተቋም፣ ወንድም ላይ የያዘውን ሁሉ ወርውሮ ሌላው ሲመጣ ባዶ እጁን እንደሚያዝ ያልተገነዘበው ነው።

3) በአንድ ሕዝብ ቀርቶ በአንድ አደረጃጀት ውስጥ የተለያዩ ፅንፎች ይኖራሉ። ከዋናው አላማ ግን የሚበልጥ ጉዳይ የለም። ለሕዝብ እሰራለሁ የሚለው ቀርቶ ለስልጣን የሚሮጡት ጊዜያዊ ጉዳያቸውን፣ መቆየት የሚችለውን አቆይተው፣ ደረጃ ለሚሰጡት ደረጃ ሰጥተው አንድ ጠረጴዛ ላይ መግለጫ ሲሰጡ፣ ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን እየነገሩን ነው። ሕዝብን እያረዱ ወደ ስልጣን መምጣት የሚፈልጉትም ሆነ የሕዝብ ደም ምንም ሳይመስላቸው እየረገጡት ስልጣን ለማጠናከር እየገሰገሱ ያሉት ተፅዕኖና ግብ የሚታወቀው በራሳችን ብርታት ብቻ ነው። ሁለቱም እርስ በእርስ የሚጯጯህ፣ ዕዝ አልባ፣ የሚያቆጠቁጡ ተቋማቱን ከመንከናከብ ይልቅ እየቀነጠበ የሚያጫጫን ኃይል እንደፈለጉ ለማድረግ ያካበቱት ልምድ፣ ያነገቡት አላማ አላቸው። አንድ አላማ ላይ ያለ አካል ተግባብቶም የተለያየ ፅንፍ መያዝ ይችላል። ሌሎቹ የጥያቄ ደረጃ አውጥተው አንደኛው ምድር ላይ ያለ፣ ሌላኛው የጣራ፣ ቀሪው የሰማይ ጩኸት እንዲጮሁ ተስማምተው፣ ተደጋግፈው ሲሰሩ በዚህም በዛም የመከራ ድግስ ለሚመጣበት ሕዝብ እቆማለሁ የሚል ከዛም በላይ ይጠበቅበታል። ባይመዳደብ እንኳ አለመሰዳደብ፣ እርስ በእርስ አለመጯጯህ ከዚህ ፈታኝ ወቅት የከፋው እንዳይደርስ ለመከላከል ይረዳል!

4) ይህ ሌላ ፈታኝ ወቅት ነው። ግለሰቦች ብቻቸውን ለውጥ አያመጡም። ስለተደበቁ፣ ስላፈገፈጉ አያመልጡም። በዚህ ወቅት ተቋማቶቻችን ያስፈልጉናል። አደረጃጀቶቻችን ከእነ ድክመታቸው ይጠቅማሉ። ከፋም በጀም ስሜትን በሚፈታተንና በሚያስጨንቅ ወቅት በስምምነት፣ በውይይት፣ በመናበብ የሚደረግ ነገር የተሻለ ነው። የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ሚዲያን አጠናክሮ የሚመጣውን እልቂትና ትርምስ ከማስቆም፣ የራስን አላማ ወደፊት ከመግፋት የተሻለ አማራጭ የለም። ዛሬ ተማሪዎቹ ጥቃት ሲፈፀምባቸው ዝም ያለ ምሁር በዝምታው ራሱን አያድንም። ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ማኅበራትን፣ ሚዲያዎችን እያገዘ ራሱንም ሕዝብንም ማዳን ይቻለዋል። ሌላ ክልል ስላለው ወይንም ፖለቲከኛ ስለሚጎዳበት ጥቅሙ እየተጨነቀ “ጆሮ ዳባ ልበስ” የሚል ባለሀብት ስለ ቤተሰቦቹና ራሱ ሀብት እርግጠኛ መሆን አይቻለውም። ኢንተርኔት ስላገኘን ብቻ “ይዋጣልን”፣ ፊት ለፊት የሕዝብ ሜሴንጀር ግሩም እንደ ምሽግ ቆጥረን ደግሞ የጎጥ መዶለት፣ ፖለቲካን በፊት ገፁ መጨቃጨቂያ በማድረግ መቀጠል በዚህም በዛም ለሚመጣው ጨካኝ ኃይል ራስን አስሮ እንደማስረከብ ይቆጠራል።

5) ውህደቱን ለማስቀረትና ውህደቱን ለመፈፀም የሚላፉት ሲላፉም ሲያሸንፉም የጋራ የሆነ የሚረግጡት ሕዝብ አላቸው። ውህደቱን በሚፈልጉትም ውህደቱን በማይፈልጉትም ኃይሎች የማይፈለግ ሕዝብ ውህደቱ ላይ ቀጥታ ከመጨነቅ ይልቅ ይህ መደባደቢያ አጀንዳ በራሱ ላይ የሚያመጣውን ጦስና ጦሱን እንዴት ማለፍ እንዳለበት አብልጦ መጨነቅና መስራት አለበት! በጥንቃቄና በብልሃት ከተሰራበት እነዚህ ኃይሎች ሲውተረተሩ ላለመጨፍለቅ ከመከላከል ባለፈ ያለ አግባብ አጋብሰውት የነበረውን ጥቅምና ኃይል ለማስመለስም መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.