ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ጃዋርን ለሕግ ማቅረብ ሲገባቸው አብረውት እንደሚሰሩ፣ ጥበቃ እንደሚያጠናክሩለት ተናግረዋል – ጌታቸው ሽፈራው

ለእነ ዐቢይ ከጃዋርና ከኢኮኖሚው ማን ይጠቅማቸዋል?

ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የአማራና የኦሮሞ ባለሀብቶችን እንዳነጋገሩ ሰምተናል። ቀደም ሲልም በዘረፋና በአካባቢው አመራር ፅንፈኝነት የተማረረው ባለ ሀብት ጃዋር ሞሃመድ የተባለው አረመኔ በቀሰቀሰው የመንጋ ሁከት ምክንያት ጭራሽ ተስፋ ቆርጦ ከኦሮሚያ ወደተለያዩ አካባቢዎች መፍለስ ጀምሯል።

የኦዴፓ ሰዎች ሰው ሲገደልና ሲፈናቀል አይደርሱም፣ ተጎጅዎችን አያነጋግሩም እንጅ ከኦሮሚያ እየኮበለለ ያለውን ባለ ሀብት እንኳ ሮጠው ነው ያነጋገሩት። ሆኖም አሁንም ሌላ የባሰ ነገር መጥቷል። ጃዋር ሞሃመድ ምርጫ እወዳደራለሁ ብሏል። ጃዋር ምርጫ ሳይደርስ ይህን ሁሉ ጭካኔ የፈፀመ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ባለሀብቱ አይጠፋውም። ለማንም ግልፅ ነው። በመሆኑም ጃዋር ምርጫ እወዳደራለሁ በማለቱ ብቻ ባለሀብቱ ሙልጭ ብሎ ከኦሮሚያ መውጣቱ የማይቀር ነው። ምንም ባልሆነበት ወቅት ሁከት እየፈጠረ ፋብሪካ እያቃጠለ ያለው መንጋ ነገ ጃዋር “ምርጫው ተጭበርብሯል” ቢለው የሚያተርፈው ፋብሪካ አይኖርም።

እነ ዐቢይ አህመድ ጃዋርን ለሕግ ማቅረብ ሲገባቸው አብረውት እንደሚሰሩ፣ ጥበቃ እንደሚያጠናክሩለት ተናግረዋል። ለፋብሪካ ጥበቃ የማይደረግለት ባለሀብት ያ እነ ጃዋር ምክንያት ፈልገው እሳት የሚጭሩበት ጊዜ ሳይደርስ መውጣታቸው የግድ ነው። እነ ዐቢይ ባለሀብቱን ሲያረጋጉ ኢኮኖሚውን የፈለጉት ይመስላሉ። በደንብ ይፈልጉታልም። ለጃዋር ከለላ ሲሰጡ ደግሞ ጃዋርን እንደመረጡ እየታወቀባቸው ነው። ጃዋርና ፋብሪካ እሳትና ጭድ ናቸው። ኦዴፓ መምረጥ የሚቻለው አንዱን ነው። ኦዴፓ፣ እነ ዐቢይ ፋብሪካን (ኢኮኖሚውን) ከመረጡ ጃዋርን አስሮ ለሕግ ማቅረብ ነው። ጃዋርን ከፈለጉ ደግሞ ፋብሪካዎቹ ከመንደዳቸው በፊት ባለ ሀብቶች ከኦሮሚያ ሙልጭ ብለው ይወጡላቸዋል!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.