የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዋናው ትኩረት ቀሪ ስራዎች ላይ መሆኑ ተገለፀ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ትኩረት ቀሪ ስራዎች ላይ እንደሚሆን ተገለፀ።

የግድቡ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 69 ነጥብ 37 በመቶ፤ የሲቪል ምህንድስና ስራው ደግሞ አጠቃላይ 85 በመቶ ያህል መድረሱም ታውቋል።

ኢዜአ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደትን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

በዚሁ ወቅት በምክትል ፕሮጀክት ማናጀር ማዕረግ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሳይት አስተባባሪ ኢንጂነር በላቸው ካሳ እንደገለጹት፥ የግድቡ ስራ በዋነኛነት የዋናው ግድብ፣ የሀይል ማመንጫ ቤቶች እና የሀይል ማከፋፈያ ስራዎችን ያካተተ ነው።

ለዋናው ግድብ ስራ ከሚያስፈልገው 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሌት 8 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ሙሌት ተከናውኖ የግድቡ አጠቃላይ አፈጻጸም ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን ገልጸዋል።

ዋናው ግድብ ከሚይዘው የውሃ መጠን በላይ ይዞ በሚፈስበት ወቅት የሚቀረውን ውሃ ለማስተናገድ በር የሌለውና በር ያላቸው የውሃ ማስተንፈሻዎች ግንባታ ስራ እየተከተናወነም መሆኑን ተናግረዋል።

የውሃ ማስተንፈሻዎቹ ከሚይዙት አቅም በላይ ውሃ ቢመጣ ይህን ማስተናገድ የሚችል የአደጋ ጊዜ የውሃ ማስተንፈሻ እየተሰራ እንደሆነም ነው ኢንጂነር በላቸው ካሳ ያብራሩት፡፡

13 ዩኒቶች ያሉት የሃይል ማመንጫ ቤቶች ግንባታ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም ከ72 በመቶ በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

የሃይል ማከፋፈያ የግንባታ ስራው ከ67 በመቶ በላይ እንደጠተጠናቀቀና አጠቃላይ የሲቪል ምህንድስናው ስራው 85 በመቶ ያህል መጠናቀቁን ገልጸዋል።

የግድቡ አካል የሆነው የኮርቻ ቅርፅ ግድብ ሙሌት ስራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
በቅርቡ ማስታወቁም ይታወሳል።

የፕሮጀክቱ ዋነኛ ትኩረት በቀሪ ስራዎች ላይ እንደሆነ የገለጹት የሳይት አስተባባሪው፥ “ትኩረታችን ካለቀው ላይ ሳይሆን ቀሪዎቹ ላይ ነው” ብለዋል።

የሲቪል ምህንድስና ስራ አፈጻጸሙ ላቅ ያለ ቢሆንም የብረታ ብረት ስራ 15 በመቶ እና የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው 29 በመቶ ያህል ብቻ መከናወኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ለቀሪ ስራዎች ትኩረት በመስጠት በተቀመጠው የተቀናጀ የስራ ማጠናቀቂያ ዕቅድ መሰረት ሁሉንም ስራ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቆሟል የሚባለው ነገር ትክክለኛ መረጃ ካለማግኘት እንደሆነና የግድቡ ስራ ዕለት ተዕለት በሙሉ አቅም እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜም የችግር አፈታት እርከኖች ተቀምጠዋል ያሉት ኢንጂነር በላቸው ካሳ፥ ከሳይት የዘለለ ችግር ሲያጋጥም በፕሮጀክት ቢሮው እንዲፈቱ እንደሚደረግም ጠቅሰዋል።

”ችግሮቹ ከሳይትና ከፕሮጀክት ቢሮው በላይ ሲሆኑም ለከፍተኛ አመራሮች ቀርበው ውሳኔ እንዲሰጥባቸው የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው” ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ2015 ዓ.ም ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

(ኢ.ፕ.ድ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.