ኢሰመኮ በሲዳማ የሕዝበ ውሳኔ ምርጫ ቅስቀሳ የሻፌታ ቡድን የበላይነት ነበር አለ

የሲዳማ ክልል የሕዝበ ውሳኔ የምርጫ ቅስቀሳ፤ የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት እንዲቋቋም በሚጠይቀው የሻፌታ ቡድን ከፍተኛ የበላይነት የተሞላ ነበር ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ትናንት የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን አስመልክቶ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶች ብሎ ባወጣው መግለጫ፤ የሻፌታ ቡድን በሰላማዊ ሠልፍ፣ በስብሰባዎች፣ በጎዳናዎች፣ ቤት ለቤት በመዘዋወር፣ በመንገዶች እና በአደባባዮች ልዩ ልዩ የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቶችን በመስቀልም ሰፊ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረጉ ተጠቅሷል።

የሲዳማ ዞን የደቡብ ክልላዊ መንግሥት አካል ሆኖ እንዲቀጥል የቀረበው የጎጆ ቡድን ግን፤ የምርጫ መረጃው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት በቴሌቭዥንና ሬዲዮ በተመደበለት ሰዓቶች ከመደመጡ በስተቀር፤ የምርጫ ቅስቀሳ አልነበረውም ማለት ይቻላል ሲል መግለጫው ያትታል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የክትትል ቡድን አባላት በጎበኙት አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ የተወሰኑ የወጣት ቡድኖች ድምፅ ለመስጠት ለተሰለፉ ሰዎች የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መስተዋላቸውም ተገልጿል።

በመግለጫው፤ “ለአማራጩ የጎጆ ቡድን የምርጫ ቅስቀሳ በይፋ የተከለከለ ነገር ባይኖርም፣ በርካታ አስተያየት ሰጭዎች ለኢሰመኮ ታዛቢዎች እንደገለጹት፤ በሲዳማ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ አማራጩን ሐሳብ በይፋ ለመቀስቀስ ስጋት እና ፍራቻ ነበር” ተብሏል።

2.3 ሚሊየን መራጮች በተመዘገቡበት የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ በመራጮች ምዝገባ ወቅት፤ የኢሰማኮ የክትትል ቡድን ለመራጭነት ዕድሜያቸው ያልደረሰ የሚመስሉ ነገር ግን ለአካለ መጠን የደረሱ መሆኑን የሚያመለክት መታወቂያ ካርድ ያላቸው የተወሰኑ መራጮች መመልከቱን በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

በመራጮች ምዝገባ ወቅትም ሆነ በሕዝበ ውሳኔው መስጫ ዕለት ይህ ነው የሚባል የጸጥታ፣ የደህንነት ችግር እንዳልነበር ተገልጿል።

መግለጫው አክሎም፤ አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተጨናነቀ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ሰላማዊ ምርጫን ለማደራጀት እና ለማስፈጸም የተቀናጀ ጥረት ማድረጉን ጠቅሶ፤ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች አነስተኛ የሥነ ሥርዓት ችግሮች መታየታቸውን ዘርዝሮ አስቀምጧል።

በመግለጫው፤ ኢሰመኮ በዋና ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የተመራ 20 አባላት ያሉት የሰብዓዊ መብት ክትትል ቡድን ማሰማራቱ ተገልጾ፤ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ. ም. በተካሄደው ምርጫ ላይ የተከሰተ ይህ ነው የሚባል ችግር እንደሌለ ተገልጿል።

ይህ የክትትል ቡድን በምርጫው ቀን በአምስት የከተማ አስተዳደሮች እና 15 የገጠር ወረዳዎች ውስጥ ከ100 በላይ የምርጫ ጣቢያዎችን መመልከቱም ይፋ ተደርጓል። የኮሚሽኑ የምርጫ ክትትል ቡድን በቅድመ ምርጫው ወቅትም ተጨማሪ የምርጫ ጣቢያዎችን መመልከቱንም በመግለጫው ተካቷል።

የኢሰመኮ የክትትል ቡድን በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ከ2000 የሚበልጡ መራጮች መመዝገባቸውን ማስተዋሉን ጠቅሶ፤ ይህም ለምርጫ ጣቢያዎች ሥራ አፈጻጻም አስቸጋሪ መሆኑን ገልጿል።

እንደ የድምፅ መስጫ ሳጥን፣ የምርጫ ወረቀቶች እና ቀለም ያሉ የምርጫ ቁሳቁሶች አቅርቦት እጥረት ያስተዋለባቸው የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸውንም በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች መግባት፣ ድምጽ በሚስጥራዊነት ለመስጠት በበቂ ሁኔታ የተከለለ ሚስጢራዊ ቦታ አለመኖር፣ የድምፅ አሰጣጥን በሚመለከት ለመራጮች ተገቢውን መመሪያ ወይም መረጃ አለመስጠት፣ የምርጫ ታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያው ውጭ መሆን፣ የተወሰኑ የምርጫ አስፈፃሚዎች የፌደራሉን የሥራ ቋንቋ [አማርኛ] የማይናገሩ እንደነበሩ በመጥቀስም ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን አለመቻላቸውን መታዘቡንም በመግለጫው ላይ አስቀምጧል።

መግለጫው፤ ኮሚሽኑ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ብቻ በመመርኮዝ ስለ ሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ እና አንዳንድ ቁልፍ የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቶችን የሚገልጽ መሆኑን በመጥቀስ፤ አጠቃላይ የምርጫው ግምገማ አለመሆኑንም ተገልጿል።

የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ውጤት በዛሬው ዕለት ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ፡ የሐዋሳ ነዋሪዎች ምን ይላሉ
BBC Amharic

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.