በምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዋጁ አንቀፅ 92 መሠረት ብልጽግና ፓርቲ የተዋሃዱት ፓርቲዎች ወራሽ ይሆናል የተዋሃዱት ፓርቲዎች መብትና ግዴታ ይተላለፍለታል‼

ስዩም ተሾመ

አቶ ጌታቸው ረዳ ውህደቱ ስህተት መሆኑን ለማሳየት ከጠቀሳቸው ምክንያቶች ምክንያቶች አንዱ “’በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አባላት ያቋቋሙት የሚሳሱለትን ድርጅት ዘጠኝ ሰዎች ሄደን ልናፈርስ ወስነናል’ ለማለት የሚያስችል ሞራልና ብቃት የለንም” የሚል ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የአንድ ውሳኔ አግባብነት የሚመዘነው በሞራልና ብቃት ሳይሆን በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ እና በኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ አንፃር ነው።

አዲስ በወጣው የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ አዋጅ አንቀፅ 93 መሰረት የራሳቸው ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ እና አባላት ያላቸው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ግንባር መፍጠር እንደሚችሉ ይደነግጋል። በዚህ መሰረት እንደ አንድ ግንባር የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አንድ ዓይነት ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ እና አባላት ሊኖራቸው አይገባም። ምክንያቱም የግንባሩ አባላት “የራሳቸው የሆነ ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ እና አባላት” እንዳላቸው በአዋጁ በግልፅ አስቀምጧል።

ህወሓት ከኦዴፓ፣ አዴፓና ደህዴን እና ህወሓት “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የተባለ እንድ ዓይነት የፖለቲካ ፕሮግራም እንደነበራቸው ይታወሳል። የተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እስካሁን ድረስ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተባለውን የህወሓት ፕሮግራም ሲያራምዱ የነበረው የህወሓት የበላይነት ስለነበር ነው። በህጉ መሰረት ግንባሩ ሳይፈርስ አራቱ አባል ድርጅቶች የራሳቸው የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም ሊኖራቸው ይችላል። አዴፓ፣ ኦዴፓና ደህዴን የራሳቸውን የፖለቲካ ፕሮራም ሲቀርፁ ከህወሓት የሚጠበቀው ዝም ማለት ነው። ምክንያቱም የእኔ ፕሮግራም ተግባራዊ ይሁን ማለት የበላይነቴን አስከብሩልኝ ብሎ እንደመጠየቅ ነው።

ኦዴፓ፣ አዴፓና ደህዴን ህወሓትን ትተው የራሳቸው የሆነ የፖለቲካ ፕሮግራም እና የመተዳደሪያ ደንብ ማርቀቅ ቢጀምሩ በአዋጁ መሰረት መብታቸው ነው። እንደ አዲስ ባረቀቁት የፖለቲካ ፕሮግራምና የመተዳደሪያ ደንብ መሰረት ውህደት ለመፈፀም ከፈለጉ መብታቸው ነው። በኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ አዋጅ አንቀፅ 93 በተደነገገው መሰረት ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት መፈፀም እንደሚችሉ ይገልፃል።

ፓርቲዎቹ ውህደት ለመፈፀም የሚያቀርቡት ማመልከቻ የሚከተሉትን መስፈርቶች ሟሟላት አለበት፤
1ኛ) እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የፓርቲው ጉባኤ ውህደቱን የተቀበለ ስለመሆኑ የሚገልፅ ውሳኔ፣
2ኛ) ፓርቲዎቹ ስለ ውህደቱ ዝርዝር ጉዮች ያደረጉት የፅሁፍ ስምምነት እና
3ኛ ፓርቲዎቹ ሲዋሃዱ የሚኖራቸው አዲስ ስምና በአዋጁ አንቀፅ 67 የተዘረዘሩ ሰነዶች ናቸው።

ከላይ በተገለፀው መሰረት የህወሓትን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም ሲያስፈፅሙ የነበሩት ሦስቱ የኢህአዴግ አባል ድርቶች የራሳቸው ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ መቅረፃቸው ትክክልና አግባብ ነው። ህወሓት ከተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶ ጋር መዋሃድ ከፈለገ አሮጌውን የፖለቲካ ፕሮራም እና የመተዳደሪያ ደንብ መጣል አዲስን ፕሮግራምና ደንብ በማርቀቅ ሂደት ውስጥ መሳተፍ አለበት። በመቀጠል በፕሮግራሙና ደንቡ ላይ ተወያያቱ በአብላጭ ድምፅ የፀደቀውን መቀበል ይኖርበታል። ይህን ማድረግ ከተሳነው ደግሞ ሦስቱ ውህደት ሲፈፅሙ ህወሓት ደግሞ የራሱን ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ እና አባላት ይዞ ከግንባሩ ይወጣል።

ውህደቱን ያልተቀበለው ህወሓት ከግንባሩ ከወጣ በኋላ ሲፈልግ ለብቻው ወይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጥምረት፣ ግንባር አሊያም ውህደት መፈፀም ይችላል። በአንፃሩ የተዋሃዱት ሦስቱ ፓርቲዎች ቀድሞ የነበራቸውን የምዝገባ የምስክር ወረቀት ለምርጫ ቦርድ በመመለስ አንድ ስምና አርማ ይኖራቸዋል። ቀድሞ የነበራቸውን የመተዳደሪያ ደንብ በመተው በአዲሱ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ ይመራሉ፣ የፓርቲዎቹ አባላትም የአዲሱ ፓርቲ ይቀላቀላሉ። ከዚህ በተጨማሪ በአዋጁ አንቀፅ 92 መሰረት የውህደቱ ውጤት የሆነው አዲሱ ፓርቲ የተዋሃዱት ፓርቲዎች ወራሽ ይሆናል፣ የተዋሃዱት ፓርቲዎች መብትና ግዴታ ይተላለፍለታል።

በአዋጁ አንቀፅ 92 ንዕስ አንቀፅ 3 መሰረት ውህደት የፈጠሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባል የነበረና በማናቸውም ደረጃ ያሉ ምክር ቤቶች ተመራጭ ሆኖ በማገልገል ላይ የነበረ ሰው በውህደቱ በተፈጠረው የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ መቀጠል የማይፈልግ ከሆነ የግል ተመራጭ እንደሆነ ተቆጥሮ የቀረውን የምርጫ ዘመን ያጠናቅቃል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.